Monday, 27 December 2021 00:00

የሃይማኖት ፍልስፍና

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(2 votes)

  (ክፍል-1 ሃይማኖትና ፍልስፍና)
                     
             እንደምን ሰነበታችሁ የአዲስ አድማስ ቤተሰቦች? ባሳለፍነው ክረምት በዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት ውስጥ ከተለያዩ የፍልስፍና መምህራን ጋር በመሆን የተለያዩ ኮርሶችን ስናስተምር ነበር፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት ከእነዚያ ኮርሶች ውስጥ አንዳንዶቹን ለእናንተ በፅሁፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
በመጀመሪያው ክፍል ላይ የመረጥኩት ኮርስ በአሞን በቀለ የተሰጠውን ‹‹የሃይማኖት ፍልስፍና›› የሚለውን ትምህርት ነው። ከእሱም ውስጥ ለዛሬ በሃይማኖትና በፍልስፍና፣ በእምነትና በአመክንዮ፣ በማመንና በመረዳት መካከል ያለውን ግንኙነት እንመለከታለን፡፡
ሃይማኖት የሰው ልጆች ከየት እንደመጣን፣ የት እንዳለን፣ እንዴት መኖር እንዳለብን፣ በስተመጨረሻም ወዴት እንደምንሄድ ዝርዝር መልሶችንና ማብራሪያዎችን የሚሰጠን ተቋም ነው፡፡ ባጭሩ፣ ሃይማኖት ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ፣ ልደት፣ ህይወት፣ ሥነ ምግባርና ሞት ትርጓሜ የሰጠ እና ስለ ዓለም ያለንን አመለካከት በጥልቀት የቀረፀ ተቋም ነው፡፡ ሃይማኖት በሃዘን ጊዜ መጽናናትን፣ በአደጋ ጊዜ ጥንካሬን፣ በሞት ውስጥ ደግሞ ተስፋን በመስጠት ለህይወታችን ትርጉም እንድናገኝ ያስቻለን ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ሃይማኖት በኪነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሁፍ፣ በኪነ ህንፃ፣ በሥነ ትምህርት፣ በአስተዳደር፣ በፍትህ ሥርዓት፣ በሰላምና ደህንነት…. ዘርፎች ለሰው ልጅ ያበረከተው አስተዋጽዖ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ታሪክ ስንጽፍና ስናወራ ሃይማኖትን ነጥለን ማውጣት እስከማንችልበት ድረስ በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ህይወት ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረ ተቋም ነው፡፡
ምንም እንኳ፣ ሃይማኖት በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ይሄንን ያህል ትልቅ ፋይዳ ያለው ቢሆንም፣ ይሄ ነገር ብቻውን ግን ስለ ሃይማኖቱ እውነትነት እና ስለ እግዚአብሔር ነዋሪነት በራሱ በቂ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባት፣ ሃይማኖት የሰው ልጅ በፍጥረታት መካከል ደካማ ሆኖ ከመገኘቱ፣ ሃይለኞችን ለማንበርከክ ከመፈለግ፣ በዕውቀት ካለማደጉና ተፈጥሮን መቆጣጠር ካለመቻሉ የመጣ አስተምህሮም ሊሆን ይችላል፡፡
በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ እሳቤዎች የተነሳ፣ ፈላስፎች ከሃይማኖት ፋይዳ ባሻገር ሄደው የሃይማኖቱን እውነትነት እና የእግዚአብሔርን ነዋሪነት የሚያረጋግጡበት ሐሳብ ከአመክንዮ ውስጥ ማግኘትን ይፈልጋሉ፡፡ እናም ሃይማኖትን በፍልስፍና መነጽር ስናየው ከአድልዖ በነፃና ገለልተኛ በሆነ እይታ ከእግዚአብሔር ህላዌ ጋር በተያያዘ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን የምንመረምርበት የፍልስፍና ቅርንጫፍ ነው፡፡
ሃይማኖትን በታሪኩ፣ በአስተምህሮዎቹ፣ በፋይዳውና በተፅዕኖው ማጥናት ቢቻልም፣ የሃይማኖት ፍልስፍና ዋነኛ ትኩረት ግን የእነዚህ ሁሉ ነገሮች መሰረት የሆነው የእግዚአብሔር ህላዌ ላይ ነው፤ ዋነኛ ሐሳቡም ‹‹ስለ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችና ፋይዳቸው ከማውራታችን በፊት በመጀመሪያ የእግዚአብሔር መኖር ወይም አለመኖር ይረጋገጥ፤ ሃይማኖቱ የቆመበት መሰረት ይፈተሽ›› የሚል ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ፍልስፍና መሰረታዊ ሐሳቦች ላይ የሚያተኩር የጥናት መስክ ነው›› የሚባለው።
በእግዚአብሔር ህላዌ ላይ ወደ ቀረቡት መከራከሪያ ሐሳቦቹ ከመሄዳችን በፊት ግን አንድ ወሳኝ ነጥብ እናንሳ፡፡ በመካከለኛው ዘመን መጀመሪያ ላይ ‹‹በርግጥ ሃይማኖት በፍልስፍና መጠናት አለበት ወይ?›› የሚለው ጥያቄ ተነስቶ በሃይማኖት ልሂቃን ውስጥ ሁለት ዓይነት የሐሳብ ቤተሰቦች ተፈጥረው ነበር – የተርቱሊያን ቤተሰብ እና የኦገስቲን ቤተሰብ (Tertullian and Augustinian Family) የሚባሉ፡፡
የተርቱሊያን ቤተሰብ ‹‹በሃይማኖትና በፍልስፍና መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት የለም›› የሚል እሳቤ የሚያራምድ ቡድን ነው፡፡ የሐሳቡ ዋነኛ አራማጅ የሆነው ቄስ ተርቱሊያን (155–220 (በቤ/ክ ‹‹ተርቱለስ›› ተብሎ ይጠራል)) አንድ የታወቀ አገላለፅ አለው፣ ‹‹በእየሩሳሌምና በአቴንስ፣ በመፅሐፍ ቅዱስና በሪፐብሊክ፣ በኢየሱስና በሶቅራጠስ መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት የለም፤›› የሚል፡፡ አቴንስ፣ ሪፐብሊክ (የፕሌቶ መፅሐፍ ነው) እና ሶቅራጠስ ፍልስፍናን ሲወክሉ፤ እየሩሳሌም ደግሞ ሃይማኖትን ትወክላለች፡፡ በተርቱለስ አመለካከት እነዚህ ሁለቱ ውክልናዎች እጅግ በጣም ተቃራኒ የሆኑና የርስበርስ ውስጣዊ ተቃርኖ ያለባቸው ሐሳቦች ናቸው፡፡ እንደውም ተርቱሊያን ምን እስከማለት ይሄዳል ‹‹እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ስለገለጠልን፣ እኛ ማሰብ ራሱ አይጠበቅብንም፤ በመሆኑም፣ አይደለም ፍልስፍና ውስጥ ወዳለው የሐሳብ ውጣውረድ መግባት ይቅርና ማሰብ ራሱ አይጠበቅብንም፡፡››
ሁለተኛው የሐሳብ ቤተሰብ ደግሞ በቅዱስ ኦገስቲን (354–430 ዓ.ም) የሚመራው ነው፡፡ በዚህ ቡድን አስተሳሰብ መሰረት ሃይማኖትና ፍልስፍና፣ እምነትና አመክንዮ፣ አቴንስና እየሩሳሌም አብረው መሄድ ይችላሉ፤ የሃይማኖት እውነቶች በፍልስፍናም ሊደረስባቸው ይችላል፤ የሰው ልጅ በፈጣሪው የምክንያታዊነትን ችሎታ የተሰጠው በራሱ መንገድም እውነት ላይ የመድረስ አቅምም እንዲኖረው ነው፡፡ እናም  የሰው ልጅ የራሱን ተፈጥሯዊ የማሰብ አቅም በመጠቀም የእግዚአብሔርን ህልውና ማረጋገጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም፣ በእምነትና በምክንያት መካከል የግድ ጸብ ወይም ቅራኔ የለም፡፡
የምስራቅ አብያተ ክርስትያናት በአብዛኛው የተርቱሊያንን አቋም የሚከተሉ ሲሆን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ደግሞ የቅዱስ ኦገስቲንን መንገድ ተከትላለች። ይሄ የአቋም ልዩነት ሁለቱ አካባቢዎች በታሪክ ውስጥ የሥልጣኔና የዕድገት ልዩነት እንዲያመጡ አድርጓቸዋል፡፡ እምነትንና አመክንዮን አስታርቀው የሄዱት ህዝቦች በፍልስፍና፣ በሳይንስና በኢኮኖሚያዊ ደረጃ (ባጠቃላይ በህሊናዊ ሥልጣኔ) ከፍ ብለው ሲገኙ፤ ‹‹እምነትና አመክንዮ ፀበኞች ናቸው›› የሚል አቋም ያራመዱት ምስራቃውያን ግን በዓለማዊ ህይወታቸው ጎስቋሎች ሆነዋል፡፡
ሆኖም ግን፣ በቅዱስ ኦገስቲን ቤተሰብም ውስጥ ቢሆን ‹‹በእምነትና በመረዳት መካከል (between Belief and Understanding) የትኛው ይቀድማል?›› በሚለው ጥያቄ ላይ ሁለት የተለያዩ አቋሞች ያላቸው ልሂቃን አሉ፡፡
አንዳንድ የሃይማኖት ፈላስፎች ‹‹ለማመን በመጀመሪያ መረዳት አለብኝ (I must understand first in order to believe)›› በማለት የመረዳትን ቀዳሚነት እና የእምነትን ተከታይነት ሲያራምዱ፤ አብዛኛዎቹ የቅዱስ ኦገስቲን የሐሳብ ቤተሰብ አባላት ግን ይሄንን አቋም በመገልበጥ ‹‹ሃይማኖታዊ እውነታዎችን ለመረዳት በመጀመሪያ ማመን አለብኝ (I must believe first in order to understand)›› በማለት መረዳት ከእምነት በኋላ የሚመጣ እንደሆነ ያስተምራሉ። ይህ ቡድን ሃይማኖታዊ እውነታዎችን ለመረዳት ‹‹ማመንን እንደ ቅድመ ሁኔታ›› ያስቀምጠዋል፡፡
ሆኖም ግን፣ እዚህ ላይ ‹‹ከመረዳት በፊት ማመን ይቀድማል›› የሚለው ቡድን ላይ ‹‹አንድ ሰው ካመነ ለምን በምክንያት ነገሮችን መረዳት ያስፈልገዋል? አምነው የተቀበሉትን ነገር እንደገና በአመክንዮ መረዳት ለምን ያስፈልጋቸዋል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የቅዱስ ኦገስቲን ቤተሰብ ለዚህ ጥያቄ መልስ አለው፤ ከቅዱስ ኦገስቲን እስከ ቅዱስ አኳይነስ ድረስ ያሉ የቡድኑ ልሂቃን ማመንን የሚያስቀድሙበት ዋነኛ ምክንያታቸው ጭንቀታቸው ለራሳቸው ሳይሆን ለማያምኑ (non-believers) ሰዎች በመሆኑ ነው፡፡ በእነሱ አመለካከት ‹‹አንድ ሰው በቅዱሳት መጻሕፍት ካመነ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት.ልናስረዳውና ልናሳምነው እንችላለን፡፡ አንድ ሰው፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ካላመነ ግን፣ እንደዚህ ዓይነቱን ሰው ‹‹እንደፈለገ ይሁን›› ብለን ከምንተወው ይልቅ፣ እርሱ በሚያራምደው አመክንዮአዊ አስተሳሰብ ቀርበን ልናስረዳው ይገባል፡፡
በመሆኑም፣ የምናምነውን ነገር በአመክንዮም መረዳት ያለብን ለራሳችን ሳይሆን የማያምኑ ሰዎች ሲያጋጥሙን በራሳቸው ሜዳ ለመግጠም እንዲያስችለን ነው›› በማለት ይከራከራሉ፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት የእግዚአብሔርን ህልውና በተመለከት በፍልስፍና ውስጥ የሚነሱትን መከራከሪያዎች ይዤ እቀርባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4903 times