Sunday, 19 December 2021 00:00

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በትግራይ “እንገንጠል” የሚያስብል የተለየ በደል አልተፈፀመም

         የቀድሞው ፖለቲከኛና አንጋፋው ምሁር ፕ/ር አድማሱ ገበየሁ፣ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከንጉሣዊው ስርዓት ማብቂያ ጀምሮ እስካሁኑ ዘመን ድረስ a የፖለቲካ አባጣ ጎርባጣ የፈተሹበትና በቀጣይ ምን አይነት መንገድ ብንከተል ይበጃል ለሚለው አቅጣጫዎችን ያመላከቱበት ሰፊ ቃለ ምልልስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አድርገዋል። የመጀመሪያው ክፍል ባለፈው ሳምንት ለንባብ የበቃ ሲሆን ቀሪው  ደግሞ እንደሚከተለው  ተጠናቅሮ ቀርቧል። መልካም ንባብ።

             በ1966 ተከስቶ በነበረው ለውጥ፣ አጠቃላይ የፖለቲካ ሃይሎችን አሰላለፍ ስንመለከት፤ ለሀገራችን የሶሻሊዝም ስርዓት ያስፈልጋል የሚል እሳቤ ነው በአብዛኛው ዘንድ የነበረው።  “ነገር ግን ይህ እሳቤ እንዴት ወደ ተግባር ይቀየር የሚለው ጥያቄ ሲመጣ፣ የፖለቲካ ተዋንያኑ በአንድ ላይ ለመቆም ፈቃደኛ አልነበሩም። አንዱ ጎራ ከሌላው ጎራ በፀጉር ስንጠቃ ወይም በማይረቡ ጥቃቅን ልዩነቶች እስከ መሳሪያ መማዘዝ ደረሰ። ተወያይተው ሃሳባቸውን በማቀራረብ በሃገር ላይ የተፈለገው ለውጥ እንዲፈጠር አላደረጉም። በዚህም ለውጡን መደገፍ ብቻ ሳይሆን ተሳታፊ የነበረው ህዝብ ሁሉ የሚፈልገውን ሳያገኝ ቀረ። ሁሉም  ተመሳሳይ ጥሩ ሃሳብ  ነበራቸው፤ ነገርግን በስልጣን ሽኩቻ ተላለቁ።
ለምን ሽኩቻን መረጡ?
የፖለቲካ ተዋንያኑን ያሻኮታቸው ስልጣኑ ላይ ማን ይቀመጥ የሚለው ነው። የርዕዮት ዓለም ልዩነት አልነበራቸውም። ሁሉም የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ወይም ከሶሻሊዝም ውጪ የሆነን እሳቤ (ርዕዮተ ዓለም) የሚያወግዙ ነበሩ። አንዱ ሌላውን ወደ ስልጣን ለመውጣት ከሚያደርገው ሩጫ ለመግታት ስምን የማጠልሸት፣ የመፈራረጅ ተግባር ውስጥ ነው የተገባው። ይሄ ነው ያሻኮታቸውና ያጠፋፋቸው እንጂ የተለየ እሳቤ ወይም ርዕዮተ ዓለም አይደለም። ሽኩቻው ስልጣን በመቋመጥ “እኔ እሻላለሁ” በሚል የተፈጠረ ነው። ሁሉም ራሱን ብቸኛ የህዝብ ወኪል አድርጎ፣ ከመሰየም የመጣ ነው። በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ችግር፣ ጥቂቶች ብቻ በብቸኝነት የሚፈቱት ሳይሆን፣ ሁሉም በትብብርና በመናበብ ሊፈቱት የሚገባ ነበር። አሁንም  ቢሆን ይሄንኑ አይነት ትብብር ነው የሚፈልገው።
በዚህ ሂደት የ”ብሔር ብሔረሰቦች” አጀንዳ የነበረው ሚና ምንድን ነው?
በዚያን ወቅት ከነበሩ ተነባቢ የፖለቲካ መጻሕፍት መካከል በመጠኗ በጣም አነስተኛ የሆነችው የጆሴፍ ስታሊን ትንሽ መፅሐፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነበረች። በወቅቱ በግሌ ንባብን እወድ ነበርና ይህችንና ሌሎች  ዳጎስ ያሉ መፅሐፍት አነብ ነበር። ከእነዚያ ሁሉ መፅሐፍት ግን ይህቺ የጆሴፍ ስታሊን አነስተኛ መፅሐፍ እንዴት ተፅእኖ መፍጠር እንደቻለች አስገራሚ ነው። ይህቺ አነስተኛ መፅሐፍ ካነበብኳቸው ሌሎች ዳጎስ ዳጎስ ያሉ መፅሐፍት አንፃር፣ ለአገራችን ገዥ ሃሳብ ትሆናለች ብዬ አስቤ አላውቅም። በወቅቱ ለዚህች መፅሐፍ ሃሳብ ትኩረት የሚሰጥ አካል ይኖራል የሚል ግምትም አልነበረኝም። በወቅቱ ግን የኤርትራ ነፃነት ብለው የሚንቀሳቀሱ ብሔርተኛ የሚመስሉ ድርጅቶች ነበሩ። ከእነሱ ውጪ ሌላ አልነበረም። ያችን ትንሽ መፅሐፍ በወቅቱ ማያያዝ ብፈልግ  እንኳ ከኤርትራ ጉዳይ ጋር ብቻ ነው ሊሆን  የሚችለው። በኋላ ነው እንግዲህ ወያኔ የተፈጠረው። ወያኔ በ67 ዓመተ ምህረት ሲፈጠር፣ እኔ አክሱም ውስጥ መምህር ነበርኩ። አላማቸውና ግባቸው ምን እንደሆነ በወቅቱ በፍፁም አልገባኝም ነበር። አሁንም ቢሆን ገብቶኝ አያውቅም፣ አይገባኝም። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ኤርትራ ቀደም ብሎ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር የነበረች በመሆኗ፣ በፖለቲካው በኩል የሆነ ነገር ሊፈጥር እንደሚችል እገነዘባለሁ፤ ተጠባቂም ነው። የትግራይ ግን በፍፁም አልገባኝም። ለምን ከተባለ እኔ በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን በምገነዘበው፣ አንድ አካባቢ “አስተዳደሩ በኔ ተወላጆች ይሁን” የሚል ጥያቄ ቢያቀርብ ለመረዳት አዳጋች አይሆንም። በነገራችን ላይ ትግራይ በወቅቱ በአካባቢው ተወላጆች ነበር የምትተዳደረው። የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ራስ መንገሻ ነበሩ። በትግራይ ከሌላው አካባቢ በተሻለ በራሳቸው ተወላጆች ነበር የሚተዳደሩት። መሰረተ ልማትን በተመለከተ፡- ከአስመራ መቀሌ፣ ከመቀሌ አዲስ አበባ- አስመራ፣ ክረምት ከበጋ የሚያገናኝ መንገድ ነበር። በወቅቱ በጠቅላይ ግዛቱ ተንቀሳቅሼ  እንዳየሁት፣ ከተንቤን በስተቀር በትግራይ አውራጃዎች በሙሉ ክረምት ከበጋ የሚያገናኙ መንገዶች ነበሩ። አምስት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ነበሯት- ትግራይ። ይህ ከጎንደርና ጎጃም ወይም ወሎ ጋር ሲነጻጸር፣ የሰማይና ምድር ያህል የሚራራቅ ነው። በጤና ተቋማት  ደረጃ ሶስት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች ነበሯት። ከሌሎቹ ጠቅላይ  ግዛቶች አንጻር የተሻለ የሚባል ነው። ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ  ብዬ  ስጠይቅ ምንም መልስ አላገኘም።
ትግራይ ከሌሎቹ ጠቅላይ ግዛቶች መጠነኛ የህዝብ ብዛት ኖሯት ግን የተሻለ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ነበራት። እነ ኢሊባቦር፣ ጋሞጎፋ ጋር ሲነጻጸርማ ልዩነታቸው በወቅቱ ትግራይ የተሻለ ተጠቃሚ ሆና ባለችበት እነዚህ ወገኖች እንዴት እንዲህ ያሉ ጥያቄ ውስጥ ገቡ ምን አሳማኝ የሚለው ለኔ እስከዛሬም እንቆቅልሽ ነው። ስታሊን ካነሳነው ጥያቄ ጋር በጭራሽ የሚገናኝ ነገር የለውም። ስታሊን ያነሳነው ጥያቄ በኋላ ከራሽያ በርከት ያሉ ሃገሮች እንዲገነጠሉ በር የከፈተ ጉዳዩም በቀጥታ እነሱን የሚመለከት ነበር። ስለዚህ አላማውን አሳክቷል። ራሺያ ውስጥ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ያመሩና ከተሜነት የተስፋፋባቸው ነበሩ። በእኛ ደግሞ በአብዛኛው የገበሬ ማህበረሰብ ነው ያለን። ታዲያ ለምን ይሄ እሳቤ አስፈለገ? ቢያስፈልግ እንኳን አጠቃላይ የሃገሪቱ እድገትና ልማት ጥያቄ ሆኖ ለምን አልተነሳም? ትግራይ እንደሌሎቹ ጭራሽ ከእነመፈጠራቸው እንደተረሱት አካባቢዎች አልነበረችም። የራሳችን ወይም ነፃ ሃገር ይኑረን የሚያስብል ነገር አልነበረም። ከዚህ በመለስ ያለ የጀርባ ሚስጥራዊ ችግር አላውቅም። በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ትግራይ “ከሌላው አካባቢ ተለይቼ ተበድያለሁና መገንጠል አለብኝ” የሚያስብላት ነገር ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም። ጥያቄውም የሕዝቡ አይመስለኝም።
በኢትዮጵያ መንግስታት ውስጥ የትግራይ ተወላጆች የስልጣን ድርሻ ምን ይመስላል?
የትግራይ ተወላጆች በንጉሡ ጊዜ በተሻለ ደረጃ የስልጣን ተጋሪ ነበሩ። የህዝቡን ቁጥር አስልተን የስልጣን መጋራቱን ሁኔታ ብንመለከት፣ ሁልጊዜ ትግራይ የተሻለ ድርሻ አላት። ሃቁ ይሄ ነው። በንጉሡም ይሁን በደርግ ጊዜ የትግራይ ተወላጆች ጠቅላላ በሃገሪቱ የሥልጣንና የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ  የነበራቸው ድርሻ እስከ መገንጠል የሚያደርስ መከፋትን የሚፈጥር አልነበረም። እንደውም በሃገሪቱ ባለው የህዝብ ብዛት ስልጣን ይከፋፈል ቢባል፣ በወቅቱ የትግራይ ተወላጆች የነበራቸውን ስልጣን ያህል አይኖራቸውም ነበር። ይሁን እንጂ በኋላም  የሃገሪቱን ሃብትና ስልጣን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው አቅማቸውን አፈርጥመው ሲያንቀጠቅጡን የኖሩት፣ በየትኛው የፍትሃዊነት መለኪያ ነበር? ከውጭ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነበር ያንሰራፉብን። እየዋለእያደር ፍንትው ብሎ የወጣው ነገር እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን በተለያየ መንገድ ለመቆጣጠር ላሰቡ አካላት የተዘጋጁና ፈቃደኛ አሽከር ሆነው ለማገልገል የተፈጠሩ ጉዶች አድርጌ ነው የምቆጥራቸው።
ስለ ህወሃት የጭቆና ተረኮች-
ጭቆና ፈጽሞ ሊፈቀድ የማይገባው ነው። በኢትዮጵያ ማንም ሰው በሰውነቱ ሊጨቆን አይገባም። የተጨቆኑ ሰዎች ሲሰባሰቡና ተመሳሳይ አጀንዳ ሲኖራቸው ደግሞ በቡድን ጭቆናን ለመታገል ይነሳሉ። ተጨቆን የሚሉ ወገኖች ሁሉ ወረድ ብለው በሁሉም ቡድን ውስጥ ያሉ ነገሮችን ቢመለከቱ ደግሞ የበለጠ ለሚይዙት ግንዛቤ ይረዳቸዋል። እኔ እስከተረዳሁት ድረስ ጭቆና መልኩና መጠኑ ይለያይ እንጂ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ነገር ነው። ጨቋኞችም ተጨቋኞችም የሌሉበት የኢትዮጵያ ክፍል የለም።
ስለዚህ ጭቆናን ከሆነ የተጠየፍነው፣ በሁሉም ቦታ ጭቆና ስላለ፣ ጭቆናን የሚፀየፉ ወገኖች አንድ ላይ ቢቆሙ አሸናፊ ይሆናሉ። አንድን ማህረሰብ በጥቀሉ ጨቋኝ ብሎ ፈርጆ በመነሳት ጭቆናን ማጥፋት አይቻልም። በጥቅሉ እኔ እስከምረዳው ድረስ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ማህበረሰብ ጨቋኝ የሆነበት ወይም የሚሆንበት ሁኔታ ፈጽሞ የለም። በዚህ የተጣመመ ተረክ ምክንያት ግን ጭቆናን ከመታገል ይልቅ አንዱ ሌላውን  ጠላት ነው በሚል ግጭት ወያኔ ይህን ማድረግ ችሏል።  አላማውን በሚገባ አሳክቷል። አንዱ አንዱን እየተጠራጠረ ሲፋጠጥ ለወያኔ ስልጣኑን አደላድሎ ኖረ።  ለ27 ዓመት ስልጣን ላይ የቆየበት ሚስጥር ይሄው ነው። የሥልጣን ልደቶቹን እንዲያሸበርቁለት በየመሃሉ ብዙ ተረኮችን መፍጠርም ችሏል።
አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጠላቱ ድህነት ነው። ከድህነት ጋር ተፋልሞ ራሱን ነፃ ማውጣት የሚችለው ደግሞ እንደ ጎጥ ሳይሆን አንድ ላይ በማበር ነው። ምክንያቱም ድህነት በአንድ አጥር ውስጥ ራስህን በጎጥ አደራጅተህ ስለአጠርክ የሚሸነፍ አይደለም። አንዱ ከሌላው ጋር ተባብሮ በሃሳብም በጉልበትም በመደጋገፍ ነው ከድህነት መውጣት የሚቻለው።  ይሄ አይነቱ ሁኔታ ለጥቂቶች ያላለሙትን ስልጣንና ሃብት አስገኝቶላቸው ሊሆን ይችላል፤ ለሃገራችን ግን ትልቅ የማይገባ ጠባሳ ነው የተወልን።
ይህን ስርዓት የተከለው ህውኃት አሁን ደግሞ ጦርነት ከፍቷል…
እኔ እስካሁን መመለስ ያልቻልኩት ጥያቄ  ወያኔ ይሄን  ሁሉ ጦርነት ሲያደርግ ይዞት የተነሳው ዓላማ ወይም ይሄን እንዲያደርግ ገፊ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው የሚለው ነው። የወያኔን ድርጊት ስመለከት ምንም አይነት አመክንዮ (ሎጂክ) ማግኘት አልቻልኩም። “ምክንያቱ ይሄ ነው?መነሻው ይህ ነው፤  ወደዚህ አቅጣጫ ለመሄድ ፈልጎ ነው፤? እልኩ ለመመራመር ሙከራ ባደርግም ምንም ማግኘት አልቻልኩም። ይሄን ለማወቅ ሞክሮም አሳማኝ ምላሽ ያገኘ ሰውም አላውቅም። ይህ ነው ለማለት ያስቸግራል። በጥቅሉ ወያኔ የከፈተው ጦርነት ግልፅ መነሻ ምክንያትና፣ መድረሻ ግብ የሌለው ነው- ውል አልባ ጦርነት። ሂደቱም የወያኔን የእውር ድንብር ጉዞ እያሳየን ነው።

Read 1054 times