Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 14:23

“የሚታመን ውሸት ለመዋሸት ከፈለግህ፤ የማይታመን እውነት አትናገር” - የጃፓኖች አባባል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“እያንዳንዷ ሩዝ ላይ የሚበላት ሰው ስም ተፅፏል!” - የህንዶች አባባል

በአንድ ወቅት እንደዋዛ ያለፍናቸው ታሪካዊ ክስተቶች ሲቆዩ ተረት ወይም አፈ-ታሪክ ይመስላሉ፡፡

አንድ ጊዜ በሀገራችን እንዲህ ሆነ፡-

በዱሮ ዘመን ነው፡፡ አንድ እውቅና ትልቅ ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ ሌሎች ባለሥልጣኖች፣ ካድሬዎች፣ ምሁራንና አብዮታዊ ምሁራን አሉ፡፡ (ያኔ “ማህል ሰፋሪዎች”) የሚባሉት ሳይቆጠሩ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ንግግር አደረጉ፤ የምናስታውሰውን ያህል ባጭሩ ስናቀርበው የሚከተለውን ይመስላል፡-

“ጊዜው የጭንቅ ጊዜ ነው! የሱማሌ ጦር እስከ አዋሽ ድረስ የመስፋፋትን ያለውን “የታላቋ ሶማሊያን ህልም” አሳካለሁ ብሎ ጦር በመስበቅ ላይ ይገኛል፡፡ የሁሉም ህዝብ ተሳትፎ የሚጠበቅበት ጊዜ ነው፡፡ አንዱ የዚህ ስብሰባ ዓላማም በዚሁ ዙሪያ ለመወያየት ሲሆን፤ በተለይ የምሁሩ ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለው ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር የሚጠየቁ ማናቸውም ጥያቄዎች ካሉ እቀበላለሁ…” አሉ፡፡

ይሄኔ፤ በዚያን ጊዜ አንቱ የተባሉ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር እጃቸውን ያወጣሉ፡፡

ባለሥለጣኑ፤ “ቀጥል፤ ሃሳብህን አቅርብ!” ይሏቸዋል፡፡

ምሁሩ ተነሱና፤

“አራት ጥያቄዎች ናቸው ያሉኝ” አሉ፡፡

“ተራ በተራ አቅርባቸው”

“የመጀመሪያው ጥያቄዬ፤” አሉና ጀመሩ ምሁሩ፤ “የመጀመሪያው ጥያቄዬ፤ እናንተ መንግሥትን የምትመሩ ሰዎች ማናቸውንም እንቅስቃሴ የምታደርጉት ያለምሁሩ ምክር፣ ያለምሁሩ ተሳትፎ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሀገራችን፤ በዘፈቀደ የሚመራ፣ በጉልበት የሚጠነሰስ የአንድ አካል እዝ ውስጥ ወድቃለች፡፡ ይሄንን እንዴት እንፍታው? ነው ዋናው ፈተና…

ሁለተኛው ጥያቄዬ፤ በየምክንያቱ ወደ ዐረብ አገርና ወደሌላ ውጪ ሀገር እየሄዱ ስለሚቀሩ ሰዎች ነው፡፡ ወጣቱን ወክለው ይሄዳሉ - ይቀራሉ፡፡ የፖለቲካ ልዑክ መርተው ይሄዳሉ - ይቀራሉ፡፡ የኳስ ቡድን ልዑክ ተብለው ይሄዳሉ - የውኃ ሽታ ይሆናሉ! የቴክኒክ ልምድ ልውውጥ ተብለው ይሄዳሉ - ለወሬ ነጋሪ እንኳ ሳይመለሱ እዚያው ይጠፋሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ምን ያስባል?...

ሦስተኛው ጥያቄ፤ በውጪ አገር በየዐረብ አገሩ እየተሰባሰቡ በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱ ብዙ ኃይሎች አሉ፡፡ በነዚህ ላይ ምን እርምጃ ለመውሰድ ታስቧል? ወይም ምን ዝግጅት ታስቧል?

አራተኛው ጥያቄ እናንተ አመራሮቻችን እርስ በራሳችሁ አትስማሙም አሉ - ያ አደጋ ወይም ሥጋት የለውም? አመሰግናለሁ” ብለው ተቀመጡ፡፡

ሰብሳቢውም፤

“መልካም፤ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ አስቀድሜ ለነዚህ መልስ ልስጥና ፤ ለሌሎቻችሁ እድል እሰጣለሁ፡፡ ከአራተኛው ጥያቄ ልጀምር… ጥያቄው እርስ በርስ አትስማሙም አሉ? ነው፡፡ እንስማማለን! ጠላት ወዮለት ለእኛ የውስጡ አደለም የውጪው ነው ዋናው!

ሦስተኛው ጥያቄ፤ ውጪ አገር ኢትዮጵያ ላይ ይዶለታል የሚል ነው፡፡ መልሱ - አደለም ውጪ አገር፤ እዚህ መርካቶ በኢትዮጵያ ላይ ይዶለታል! - ዋናው ተዘጋጅቶ ጠንቅቆ መጠበቅ ነው!

ሁለተኛው ጥያቄ - ኢትዮጵያን እየከዱ ውጪ ስለሚቀሩ ሰዎች ምን ታስባላችሁ? የሚል ነው፡፡

መልሱ - ኢትዮጵያ፤ የማይፈልጓትን አትፈልጋቸውም! ነው!

አንደኛውና (ዋንኛው ጥያቄ ይመስለኛል) መንግሥት በታላላቅ ውሳኔዎች ላይ የምሁራኑን ምክር አይጠይቅም - የሚል ነው!

መልሱ - መንግሥት ምሁራንን ያልጠየቀበት ጊዜ የለም፡፡ በአስረጅነት የማቀርበው - እርሶ ራስዎን (የፖለቲካ ሣይንስ ምሁሩንና ጥያቄ አቅራቢውን ማለታቸው ነው) “ስለሶማሊያ ጉዳይ ምን እናድርግ?” ብለን ደብዳቤ ልከንልዎ፤ የላኩልን መልስ እኔ ፋይል ውስጥ አለ፡፡ ምንድን ነው ያሉን፤ “የሶማሊያ ጥያቄ ውስብስብ በመሆኑ መታየት ያለበት፤ ከኢኮኖሚ አንፃር፣ ከሶሺዎሎጂ አንፃር፤ ከሳይኮሎጂ አንፃር፣ ከፖለቲካ አንፃር፣ ከጐረቤት አገሮች ግንኙነት አንፃር ችግር እንዳለው ተደርጐ ሲሆን፤ መቸኮል አይገባም የሚል ነው… አንፃር፣ አንፃር፣ አንፃር… ምሁር አንፃር ያበዛል! (የታዳሚው ሳቅና ጭብጨባ አስተጋባ)

እኛ ግን ምን አደረግን? በአጭር ጊዜ 300ሺ ሚሊሺያ መለመልንና ስናበቃ አዘመትን! ሱማሌ ድራሿ ጠፋ! ጦርነቱን ድል መታን! ይሄው ነው ጓዶች!! አንፃር ማብዛት አያስፈልግም!

***

በሀሳብ ካለመግባባት ይሰውረን! ሁሉን፤ “የራሱ ጉዳይ!” ከማለት ያውጣን! “የራሴ ጉዳይ” ከማለትም ያውጣን፡፡ የእኔ መንገድ አንድ ጊዜ ሰርቷል፤ ስለዚህ ምንጊዜም ይሰራል - ከማለት ያድነን! “ውጪ አገር ለሚዶልቱ እዚህም ይዶለታልኮ!” ብሎ መልስ ከመስጠት ይጠብቀን! ስምምነታችን በባላንጣችን ላይ ሳይሆን መጀመሪያ በእኛው መካከል እንዲሆን፣ ለፓርቲም፣ ለተቃዋሚም፣ ለህዝብም በጐ ንፋስ ያምጣልን!

ያልተዘጋጀንበት ጠብ ውስጥ አይክተተን፡፡ የተዘጋጀንበት ጠብ ውስጥ አምባገነንና ጦር - ጠማሽ አያድርገን! ዛሬም ከህዝብ ለመማር እንችል ዘንድ ልቦና ይስጠን!

ሀገራችን በመንግሥትም፣ በፓርቲዎችም፣ በህዝብም አኳያ ዝግጅትና ድርጅት የሚያስፈልጋት አገር ናት፡፡ “ሃይ” የሚል ሽማግሌ ያሻታል፡፡ “ግዴለም ከኔ ይለፍ!” የሚል ያስፈልጋታል፡፡ “ህዝብ ሸርተቴ ነው!” ከሚል የማን-ያህሎኝ አስተሳሰብ የሚወጣና ትልቁ ዳቦ የህዝቡ ነው - ሳሊለኩና የተቆራረሰው ዳቦ ለየፓርቲው፣ ለየድርጅቱና ለየሰንበቴው ነው የሚል አሳቢ ይፍጠርልን! ጉዳይና ዓላማ ያለው ተፋላሚ (Rebel with a cause) የሚያስፈልገውን ያህል አርአያነት ያለው የፓርቲና የእድር መሪ ያሻናል፡፡ አርአያ የመጥፋቱን ያህል መታገያ መፈክር የጠፋ ስለሚመስልም ድህነታችንን የከፋ የሚያደርገው ጊዜ እንዳይመጣ እናስብ!! አንድ አዛውንት፤ “እንደው አገራችንን የሚመራ ሰው ማን ይሻላል ብንባል ሳይጨንቀን ይቀራል?” ያሉት ጥያቄ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ “ህዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ካልቻለ፣ ፓርቲው የሚፈልገውን ህዝብ ይምረጥ” ይለናል፤ ቤርቶልት ብሬሽት፡፡

ይህን መርህ ከመጠየቅና ከመመርመር ይልቅ “የአምላክ ፍርድ ቀኑን ጠብቆ ይመጣል”፤ “መፍትሄው ፀሎት ነው!”፤ “በሃይማኖትም፣ በብሔር ብሔረሰብም፣ በጦሩም፣ በድርጅቶችም ወዘተ… የሚነሳን ውጥረትና ትርምስ እንደትግል ስልት መማጠን ተገቢ የፖለቲካ አቅጣጫ ነወይ? “የሚቀምሰው ለሌለው ድሀ ይቅርና ቁንጣን ለያዘውስ ካብታምና ዲታ ይጠቅማል ወይ? ከሀገር መዘበራረቅ የምናተርፈው፤ (ግለሰባዊ ካልሆነ) ማህበረሰባዊ ፋይዳ ምንድን ነው?” …ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በተለይ ፊደል-ቀመስ ነን የምንልና ለሁሉ የሀገር ችግር መፍትሄ እንሰጣለን የምንል ወገኖች እዳችንም ጥያቄያችንም ሁልቆ መሳፍርት ነው፡፡

አንድ የዚሁ ጋዜጠኛ አምደኛ ገና በጠዋት፤ “አትንኩኝ የሹም ዶሮ ነኝ ለምንለው ከተነከርንበት ችግር እንወጣ ዘንድ ጠበል ቢረጩን ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶቻችን፣ አንዳንዴም አብዛኞቻችን፣ ራሳችንን ከሆንነው በላይ አድርገን ስለምንወስድ ብዙ ነገር ይበላሻል፡፡ ልባችን ዘውድ ይጭንና አኳኋናችን የንጉሥ አይነት ይሆናል፡፡ ተፈጥሮ በጥበቡዋ ይበቃሃል ብላ የለገሰችንን ፀጋ አውልቀን፤ በፈጠርነው ቅዠት ውስጥ የምንኖር ይመስለኛል”፤ ሲሉ የፃፉት ራሳችንን እንድንመረምር ያግዘናል፡፡

ዕውነታችንን በአሳማኝ መንገድ ካልተናገርን ወይ ማጋነን ይመስላል ወይ ከመዋሸት ይተካከላል፡፡ ዕውነትን በቀላሉ፣ በግልፁና በቀናው መንገድ ብናውቅ ከጥርጣሬ እንወጣለን! “ሸወዱን”/”ቀጠፉን ከሚል ማንገራገርና ግትርነት እንወጣለን፡፡ ጃፓኖች “ውሸት ለመዋሸት ከፈለግህ የማይታመን ዕውነት አትናገር!” የሚሉን ለዚህ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሥልጣንን የሚይዘው ሥልጣን ይይዛል፡፡ በዚህና በዚያ መንገድ ነው የምንመርጠው ቢባልም፤ ዕውነቱ አንድ ነው - የተፃፈለት ሰው የወንበሩ ባለቤት ነው፡፡ ጽሑፉ በዕምነትም ተፃፈ፣ በፖለታካ፤ በችግርም ተከተበ ዘና ተብሎ፤ ተደበቀም አልተደበቀ፣ የተፃፈለት ሰው ተጽፎለታል፡፡ ህንዶች፣ “እያንዳንዱዋ ሩዝ ላይ የሚበላት ሰው ስም ተጽፏል” የሚሉን ይህንኑ ሊያረጋግጡልን ነው!!

 

 

 

Read 7031 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 14:30