Saturday, 27 November 2021 14:52

አምባሳደር ጄፌሪ ፌልትማን ምን እያሉ ነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጦርነቱ በሚቆምበት ዙሪያ  ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን የሚገልፁት የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፌሪ ፌልትማን፤ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ በተልዕኳቸው ዙሪያ ለጋዜጠኞች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ይህን አምባሳደሩ የሰጡትን ማብራሪያ አጠር ባለ መልኩ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው ያጠናቀረው ሲሆን በቅድሚያም ወደ ጥያቄና መልስ ከመግባታቸው በፊት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ሁለቱንም በአጭሩ እነሆ፡

        “በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ሳደርግ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ትንሽም ቢሆን ተፋላሚ ሃይሎች ከጦርነት ይልቅ ወደ ድርድር ለመምጣት ቢያንስ ፍላጎት እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም በመሬት ላይ የኢትዮጵያን አንድነትና ሠላም ሊያናጋ የሚችል የአደጋ ስጋት መኖሩ ያሳስበናል፡፡ አሁን አንድ ግልጽ የሆነው ነገር ጦርነቱን ለማስቆምና ውጥረቱን ለማርገብ የሚያስችል ድርድር ለማድረግ መሰረቶች እንዳሉ ተረድቻለሁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመንግስታቸው ቀዳሚ ፍላጎት፣ የትግራይ ሃይል፣ በሃይል ከያዛቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣና ወደ ትግራይ እንዲመለስ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ እኛም ይሄን ሃሳብ ወይም አላማ እንጋራለን፡፡ በሌላ በኩል ያነጋገርናቸው የህወኃት ሰዎች ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ሠብአዊ ድጋፍ የሚቀርብበትን መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲከፍት ለማስገደድ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ይሄንንም አላማ እኛ እንጋራለን፡፡ ይሄንኑ ሃሳባቸውን ሁለቱም ወገኖች ለዲፕሎማቶችና ለማሸማገል ጥረት እያደረጉ ላሉት ለቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ነግረዋቸዋል፡፡
“ትልቁ ነጥብ ሁለቱም ወገኖች ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና አላማዎች በፖለቲካዊ መፍትሔ ሳይሆን በሃይል በወታደራዊ እርምጃዎች ማሳካት እንደሚሹ ብቻ ማመናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ለአንድ ዓመት ውጊያ ከተደረገና በሺዎች ሞተው ተፈናቅለው እንኳ ዛሬም ወታደራዊ አማራጮች ውጤት አላመጡላቸውም፡፡ በኛ በኩል መንግስት የሰብአዊ ድጋፎችን ሊገድቡ የሚችሉ መሠናከሎችን እንዲያስወግድ፣ ህወኃትም ወደ አዲስ አበባ ለመጠጋት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆም ነው ፍላጎታችን። በዚህ በኩል የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይቀጥላል። ከዲፕሎማሲ ውጪ በዚህ ግጭት ላይ ሌላ አማራጭ የመጠቀም ፍላጎት የለንም” ብለዋል- አምባሳደር ጄፌር ፊልትማን ወደ ጥያቄና መልስ ከመግባታቸው በፊት።
ጥያቄ 1- በዲፕሎማሲ ጥረቶች ከዚህ በፊት ከነበረው አስጨናቂ ሁኔታ መሻሻሎች እየታዩ ነው ብለዋል። በዚህ ላይ ትንሽ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እፈልጋለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ህወኃት “ከአዲስ አበባ በ130 ማይል ርቀት ላይ ነኝ” እያለ ነው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ደግሞ አማፂያኑን ለመዋጋት ጦር ሜዳ ዘልቀዋል፡፡ እነዚህ ነገሮችን ስንመለከት ነገሩ በጎ መሻሻል ያለው አይመስልም፡፡ የእርስዎ መረጃ የተፋለሰ ይሆን? አሁን ምንድን ነው በጦር ሜዳ እየተካሄደ ያለው?
እኔ ሁሉም ነገር የተቃና ነው የሚል ነገር አልተናገርኩም፡፡ እኛን በእጅጉ የሚያስጨንቀን በሁለቱም ወገን የወታደራዊ አማራጮች በበዙ ቁጥር ሊፈጥር የሚችለው ቀውስ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ በተመላለስኩበት እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን በስልክ አግኝተው በተወያዩበት ወቅት እና በጉዳዩ ላይ በመከርንባቸው ጊዜያት ሁሉ የተገነዘብኩት፣ እንዴት ጦርነቱን ማስቆምና የተኩስ አቁም ማድረግ እንደሚቻል በቀናነት ሃሳብ የመለዋወጥ ፍላጎት መኖሩን ነው፡፡
ሁለቱን ወገኖች አግኝተን  በምናናግርበት ወቅት በሁለቱም በኩል ጦርነቱን ለማስቆም ፍላጎትና ፍቃደኝነት መኖሩን ተገንዝበናል፡፡ የተኩስ አቁም ስለሚደረግበት ሁኔታ፣ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ስለ መግታት፣ያለ ገደብ የሰብአዊ ድጋፍ በሚቀርብበት፣ ህወኃት ወደ ትግራይ ድንበር ስለሚመለስበት ሁኔታ  ሁሉ ለመነጋገር ሁለቱም ወገኖች ፍቃደኛ ናቸው። ነገር ግን ፍቃደኛ ናቸው  ማለት ለዚሁ  የሚረዳ ነገር አሁን ላይ እያደረጉ ነው ማለት አይደለም፡፡ ጉዳዩን በትኩረት  ይዘው ለማሸማገል ጥረት እያደረጉ ያሉት ኦባሳንጆ፤ እነዚህን ነገሮች ከግምት አስገብተው በአለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ የሚል እምነት ነው ያለን፡፡
ነገር ግን በመሬት ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እየተጠናከሩ መሆናቸውና ወታደራዊ እርምጃዎቹም ፈጣን የመሆናቸው ጉዳይ እኔንም ያሳስበኛል፡፡ ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቶቹ በበለጠ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ፈጣን ናቸው፡፡
ጥያቄ 2- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ብዛት ምን ያህል እንደሆነ  ግምት እንኳን ቢነግሩን? በአፋርና አማራ ያሉ የጦር ግንባር ሁኔታ ላይ መረጃ አለዎት? ህወኃት የጅቡቲ መንገድን የሚቆጣጠር ከሆነ በመስመሩ እርዳታ የሚጓጓዝበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል?
በታሰሩ ሰዎች ጉዳይ ያለን መረጃ የተሟላ አይደለም፡፡ ምን ያህል እንደታሰሩ ግልጽ መረጃ የለንም፡፡ ነገር ግን ሰዎች እየታሰሩ ስለመሆኑ ለኮቪድ አጋላጭ በሆነ ሁኔታ እንደታሰሩ፣ ያለ ህግ ሂደት ተይዘው እንደሚገኙ መረጃዎች ደርሰውናል፡፡ ነገር ግን ብዛታቸውን በውል አላወቅንም፡፡
ከጦር ግንባር ጋር በተያያዘ ለቀረበው ጥያቄ፣ በህወኃት በኩል ወደ ጅቡቲ የሚሄደውን መንገድ ለመያዝ ወደ ሚሌ የማጥቃት እንቅስቃሴ አለ፤ ነገር ግን የፈለጉትን ያህል አልተሳካላቸውም፡፡ የመከላከያ ሠራዊትና አጋሮቹ የክልል ፖሊስና ሚሊሺያዎች አሁንም መንገዱን በሚገባ እንደተቆጣጠሩት ነው ያለው፡፡ ሌላኛው የጦር ግንባር ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን መስመር ተከትሎ ያለ ነው፡፡ አጣዬ ሸዋ ሮቢት ፣ ደብረ ሲና ያለው መስመር ነው፡፡ ህወኃት መጠነ ሰፊ የማጥቃት እንቅስቃሴ አድርጎ በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ መጓዙና መቃረቡ ለኛ አሳሳቢ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ የወታደራዊ ግጭት የሚሸፍናቸው ቦታዎች በበዙ ቁጥር በርካታ ሠላማዊ ሰው መጎዳቱ አይቀርም፡፡ ይሄ ነው እኛን ያሳሰበን። በዚህም እኛ ህወኃት ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን ግፊት ተቃውመናል እንዲሁም የጅቡቲን መስመር ለመቁረጥ የሚደረገውን ጥረትም ተቃውመናል፡፡
ጥያቄ 3- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይን ባገኟቸው ወቅት ወደ ጦር ግንባር እንደሚሄዱ ነግረዎት ነበር? እርስዎ ይሄን እንዲያደርጉ መክረዋቸው ነበር? ይሔ ግጭት የሚቀጥል ከሆነ አሜሪካ ከማዕቀብ በተጨማሪ ሌላ የምትወስደው እርምጃ ይኖር ይሆን?
እኔ እና ጠ/ሚኒስትሩ በስፋት  የተነጋገርነው እንዴት ግጭቱ በድርድር ሊፈታ ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ  ነው፡፡ ነገር ግን ጠ/ሚኒስትሩ በወታደራዊ እርምጃ ህወኃትን ወደ መጣበት ትግራይ እንደሚመልሱት በሙሉ እርግጠኝነትና በራስ መተማመን ነበር የነገሩኝ፡፡ ነገር ግን እኔ ይሄን በራስ መተማመናቸውን  ጥያቄ ውስጥ አስገባለሁ፡፡ በሰኔ ወር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ከወጣ በኋላ ህወኃት የያዛቸውን ቦታዎች ከካርታው ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ይሄን ካርታ ስመለከት የጠ/ሚኒስትሩን በራስ መተማመን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባ አድርጎኛል፡፡
ነገር ግን እኔ የነገርኳቸው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ሠላም አለመሆን የሚያስከፍለው ዋጋ፣ የሠላማዊ ዜጎች መጎዳት የሚያስከፍለው ዋጋ፣ በዚህም ጦርነት የኢትዮጵያ ክብር መነካቱ---እነዚህ ሁሉ የሚያስከፍሉት ዋጋ ከፍተኛ ነው፣ ስለዚህ ነገሩን በጦርነት ከመፍታት ይልቅ በዲፕሎማሲያዊ ሂደት መፍታቱ ኪሳራውን ይቀንሰዋል የሚለውን ነው፡፡
ጥያቄ 4- በኢትዮጵያ ያሉ አሜሪካዊያን ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ተደጋጋሚ ጥሪዎች እየቀረቡ ነው። ይሔ በሃገሪቱ ያለው ሁኔታ አስጊ መሆኑን ለማሳየት ነው ወይስ በእርግጥም የሃገሪቱ መንግስት ሊፈርስና የእርስ በእርስ ጦርነት ሊጀመር የሚችልበት እድል በመኖሩ ነው?
በመሰረቱ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ተመልክተን ነው ማስጠንቀቂያውን እያወጣን ያለነው፡፡ ጦርነቱ እየተባባሰ ከሄደ ምናልባት የመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦቶች ሊጓደሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለን፣ የግንኙነት አማራጮች ሊዘጉ ይችላሉ፣የጉዞ መረባበሾች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባ አየር ማረፊያ መደበኛ ስራውን እያከናወነ ነው፡፡ ጉዞዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንደ ወትሮው ቀጥለዋል፡፡ በዚህ በተረጋጋ ሁኔታ ዜጎቻችን ቢወጡ በኋላ ከሚፈጠር መተረማመስ ይታደጋቸዋል ከሚል እምነት ነው ቀድመው እንዲወጡ እየጠየቅን ያለነው፡፡ጥያቄ 5- መደበኛ በረራዎች ሳይቋረጡ በተረጋጋ መልኩ ዜጎቻችን እንዲወጡ  በማሰብ ነው ብለዋል፤ በእርስዎ ግምገማ እዚህ ያሉ ዜጎች በተረጋጋ መልኩ ለመውጣት ምን ያህል ጊዜ አላቸው? እስከ መቼ ነው ጊዜ  ያላቸው? ዛሬ ብቻ ነው? አንድ ወር ነው? የሳምንት ያህል ጊዜ ነው?
እኛ ዛሬውኑ ለቀው እንዲወጡ ነው እያሳሰብን ያለነው፡፡ እንዳልኩት አሁን መደበኛ የትራንስፖርት አማራጮች ክፍት ናቸው፡፡ ይሄን አስመልክቶ ኤምባሲዎች በየቀኑ ለዜጎቻቸው መረጃ ከህዳር መጀመሪያ አንስቶ  እየሠጡ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ በፍጥነት እየተለወጠ የመሆኑ ነፀብራቅ ነው፡፡ በኋላ ችግር ከተከሰተ የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹን በመደበኛ በረራዎች ከኢትዮጵያ ማስወጣት የሚችልበት እድል የለውም። ስለዚህ ሃገሪቱን ለቆ ለመውጣት ጊዜው አሁን  ብቻ ነው፡፡
ጥያቄ 6- በ1983 ሃገሪቱን ጥለው ወጥተው በዚምባቡዌ ተጠልለው የሚገኙት መንግስቱ ሃ/ማርያም ለውድቀታቸው የአብዮቱን መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭን ይቀውሳሉ። በእርስዎ ግምገማ አሁን በኢትዮጵያ ላለው ቀውስ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማንን የሚወቅሱ ይመስልዎታል? በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትሩ ከኬኒያው ፕሬዚዳንት ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዳላቸው የሚያመለክት ምስል በማህበራዊ ሚዲያው ሲዘዋወር ይስተዋላል። እንደው ጠ/ሚኒስትሩ በአህጉሪቱ ካሉ ሃገራት በአንደኛው ጥገኝነት የሚጠይቁ ይመስልዎታል?
በመጀመሪያ ደረጃ የ1983 ጉዳይን በጥያቄህ ስላነሳህ፣ ለትግራይ መሪዎች ልለው የምፈልገው ነገር አለ። አሁን 1983 አይደለም ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡ በ1983 እንደሚታወቀው ህወኃት የመንግስቱ ሃ/ማርያምን መንግስት ውድቀትን ተከትሎ አዲስ አበባ ሊገባ ችሏል፤ ዛሬ ግን ህወኃት በህዝብ እጅግ የተጠላ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ እገባለሁ ብሎ ካሰበ የሚጠብቀው የከፋ ነገር ይሆናል፡፡ አሁን 1983 አይደለም፤ ይሄንንም የትግራይ መሪዎች ይረዳሉ የሚል እምነት አለን፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይን በተመለከተ በተደጋጋሚ ስንነጋገር የተረዳሁት በሰኔ ወር መከላከያው የተናጥል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ መውጣቱ እንዲሁም በጥቅምት 24 ህወኃት የፈፀመው ድርጊት በአሜሪካ መንግስት እውቅና አለማግኘቱ ተገቢ አለመሆኑን ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን አንድ በስፋት የሚነገር የተሳሳተ ነገር አለ። የአሜሪካ መንግስት ህወኃት ድጋሚ ወደ መንግስት እንዲመለስ እየረዳ ነው የሚለው የተሳሳተ ነው፡፡ እኛ እንዲህ ዓይነት አላማ የለንም፡፡ የሚሆንበት እድልም የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ምርጫ በሥልጣን ላይ ያሉ መሆኑንና ሠፊ ድጋፍ እንዳላቸው እንረዳለን፡፡
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታን በተመለከተ፣ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከልባቸው ያሳስባቸዋል፡፡ እንደ ጎረቤት ከኛ በበለጠ ያሳስባቸዋል፡፡ ስለዚህም ነው ከፍ ያለ ሚና እየተጫወቱ ያሉት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይንም በኢትዮጵያ ሠላም ስለሚሰንፍበት ሁኔታ ነው በተደጋጋሚ እያነጋገሩ ያሉት፡፡ ዋናው ነገር፣ የሰላም መፍትሔ ያለው በአሜሪካ በአፍሪካ ህብረት ወይም በሌላ እጅ አይደለም፤ መፍትሔው በሁለቱ ወገኖች እጅ ነው የሚል እምነት ነው ያለን፡፡

Read 1744 times