Sunday, 28 November 2021 00:00

የ30 አመቱ አሜሪካዊ በ10 አመታት ሁሉንም የአለማችን አገራትን ጎብኝቶ መጨረሱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አለምን በሙሉ የመጎብኘት ህልም ሰንቆ ለ10 አመታት ያህል አገራትን ሲያስስ የኖረው ድሪው ቢንስኪ የተባለ የ30 አመት አሜሪካዊ ተጓዥ፣ ከሰሞኑ ጉዞውን በስኬት በማጠናቀቅ፣ ሁሉንም የአለማችን አገራትን ጎብኝተው መጨረሳቸው ከሚነገርላቸው 249 ሰዎች ተርታ መሰለፉ ተዘግቧል፡፡
ለአስር አመታት ያህል አለማችንን ሲዞር የኖረው ቢንስኪ፣ ከሰሞኑ የጉዞው የመጨረሻዋ መዳረሻ በሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ጉዞውን አጠናቅቆ ህልሙን ማሳካቱን የዘገበው ሲኤንቢሲ ኒውስ፤ ቢንስኪ መላውን አለም ጎብኝቶ ለመጨረስ 1 ሺህ 458 የአውሮፕላን በረራዎችን ያደረገ ሲሆን፣ በ1 ሺህ 117 አውቶብሶች ተሳፍሮ መጓዙንም አመልክቷል፡፡
ለጉዞው የሚያስፈልገውን ወጪ በስፖንሰሮች ድጋፍና በዩቲዩብና በስናፕቻት አፕሊኬሽን ከሚለቃቸው ቪዲዮዎች በሚያገኘው ገንዘብ መሸፈኑን የተናገረው ቢንስኪ፤ በጉዞው ለ30 ጊዜያት ያህል የምግብ መመረዝ ችግር እንዳጋጠመው አስታውሷል፡፡
በጎበኛቸው አገራት በአማካይ ለአንድ ሳምንት ብቻ እንደሚቆይ የተናገረው ተጓዡ፤ በጉዞው ካጋጠሙት ፈተናዎች መካከል በአንዳንድ አገራት ቪዛ ለማግኘት እጅግ አዳጋች መሆኑና በኮሮና ቫይረስ ክልከላዎች ሳቢያ 6 አገራትን ዘግይቶ ለመጎብኘት መገደዱ እንደሚገኙበትም ገልጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአሁኑ ወቅት ሉአላዊ አገራት ብሎ የመዘገባቸው 193 አገራትን ቢሆንም፣ ተጓዡ ግን 197 አገራትን ጎብኝቻለሁ ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ልዩነት ሊፈጠር የቻለው ጎብኝው ኮሶቮን፣ ፍልስጤምን፣ ታይዋንንና ቫቲካንን እንደ አገር በመቁጠሩ መሆኑንም ገልጧል፡፡


Read 2848 times