Saturday, 27 November 2021 14:30

ዓለምን ሁሉ ለማትረፍ፣ ዓለምህን ለማየት! “ሰው” ለመሆን!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በትርምስ መሃል፣ ፀንቶ ለመቆም የቻለ ሰው።
በጭፍን መስማማት ሰላም አይደለም፤ በጭፍን ማፈንገጥም ጀብድ አይሆንም።
ራቀ ዘገየ ብለህ ከውጥንህ ከመንገድህ የማትወጣ፣ ፅኑ አላማ ጠባቂ!
ማሰብ ሌላ፣ መብሰልሰል ሌላ! በሕልም መተለም ሌላ፣ በሕልም መነሁለል ሌላ!
ስኬትን ትሸጋገርበታለህ። እንቅፋትን ትሻገረዋለህ። ሐውልትና መቃብር አይደሉም።
የሰራኸው ሊሰበር ይችላል፤ መንፈስህ ግን ማንሰራራት ይችላል።
“አይዞኝ” የምትል የነፍስህ ድምፅ!
ከፍታም ዝቅታም፣ ወዳጅም ባላንጣም፣ ሁሉንም በልኩ ነው።
ነፍስ ያለህ ሙሉ ሰው ትሆናለህ፣ ዓለምንም ታተርፋለህ።

            የኪነጥበብ ሰዎች፣ ለምንድነው የሰውን ፈተና የሚያከብዱት? ልብወለድ፣ ግጥም አንብቡ። ፊልም፣ ትያትር ተመልከቱ። ሁሉንም የችግር ዓይነት ከምረው፣ እስከ ጥግ ድረስ አክርረው፤ ሕይወትን በውጥረት ያስጨንቋታል። ሰማይ ምድሩን ቀውጢ ያደርጉታል። ዓለም ሁሉ ይተራመሳል፤ የእንጦሮጦስ አፋፍ ላይ ይንጠለጠላል- በድርሰት። ለምን? ሰውን ለማሳነስ ተስፋውንም ለማጨለም ሊሆን ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ፤ የሰውን ድንቅ ብቃትና የመንፈስ ፅናትን አጉልተው ለማሳየት ይጠቀሙበታል- ድንቅ ደራሲዎች። ይህ ግጥም ጥሩ ምሳሌ ነው።ሰው ሁሉ በጭፍን ስሜት የሰከረበት ዓለም ይታያችሁ። በዚያ መሃል፣ ራሱን የገዛ ሰው፤ ሰው ለመሆን የቻለ ሰው! ተመልከቱ።
በትርምስ መሃል፣ ፀንቶ ለመቆም የቻለ ሰው።
If you can keep your head when all about you
Are losing theirs and blaming it on you,
If you can trust yourself when all men doubt               you,
But make allowance for their doubting too;
ራስ በራስ ተሳክረው ልብ እየሳቱ፣ ናላቸው ዞሮ ነገር ዓለሙን ሲያምታቱ፣ “ሰማይ ምድሩ ዞረብን” እያሉ ያማርራሉ። አሳሳተን፤ አዞረብን ብለው፣ አንተ ላይ እያሳበቡ ይወቅሳሉ። ሕሊናቸውን ጥለው በደመነፍስ ሲቅበዘበዙ፣ “ቀልባችንን ገፈፈን” ብለው፣ ባንተ ላይ ያላክካሉ።
አይናቸውን እየጨፈኑ፣ “ፀሐይ ተጋረደብን፣ ብርሃን ጠፋብን፣ ቀኑ ጨለመብን” ይላሉ። አይኖችህን መግለጥህና ብርሃን ማየትህ እየከነከናቸው ይራገማሉ።
አረፍ ብለህ መተኛትህን፣ ነቅተህ መነሳትህን እየጠሉ፣ በብዥታና በሰመመን እድሜያቸውን ይገፋሉ። በድንዛዜና በውዥንብር፣ ውለው ያድራሉ። በቁም ቅዠት እየተደናበሩ፣ በእንቅልፍ ልብ እየተሰናከሉ ሲላተሙ፣ “ጊዜው ጠመመብን”፣ “ዘመኑ ጨከነብን” ብለው ይጮሃሉ። ለዚህም፣ ጣታቸውን እየቀሰሩ አንተኑን ይወነጅላሉ።
“ሰው የጠፋ እለት” ማለት እንዲህ አይነት ጊዜ ነው። “ሰው ሲጠፋ”፣… የአዳሜን ስካር ተከትሎ መጥፋት መፍትሄ አይሆንም። ጀማው እውኑን ቢክድ፣ ቢያብር በአሉታ፣ የገዛ ራስህ ነው እምነትህ። ራስን መግዛት ነው፣ ያንተ ፋንታ።
ታዲያ፣ አዳሜ ሲሳከር፣ “አይሞቀኝ አይበርደኝ” አትልም። ብርድ ብርድ ይላል። ብርክ ያስይዛል። ግን፣ ወገብህን አጥፈህ አትቀርም።
“ያለህ” አእምሮ ነው፣ ብርቱ “አለኝ-ታህ”። እውኑ አለም ነው መተማመኛህ። እውነት መጨበጥህ ነው፣ መዳኛ ዋስትናህ፣ ጋሻ ከለላህ።
“ይኸው ተመልከቱ፣ ይኸው እውነት ነው” ብትል፣ ሰሚ ተመልካች ቢጠፋ፣ አይን ተጋርዶ በብዥታ፣ ለቅዠት ቢሸነፍ፣ ለውዥንብር ቢረታ፣ ጆሮ ተደፍኖ በሁካታ፣ መንፈስ ቢደነዝዝ በቁም ቢተኛ፣ ወይም እየተነዳ እየተጎተተ ቢንጋጋ- በሆይሆይታ… ምንድነው የሚሻለው?
እውኑ ዓለም ግን ፅኑ ነው፣ ይሄም ነው ላንተ ፅናትህ። ለእውነታ መታምን ነው፣ በራስ መተማመንህ።
በጭፍን መስማማት ሰላም አይደለም፤ በጭፍን ማፈንገጥም ጀብድ አይሆንም።
አዳሜ ሁሉ አሌ ቢል፣ እውነት አይለወጥም። እና ምን ተሻለህ? ከአዳሜ ጋር፣ ከነፋሱ ጋር መንሳፈፍ፣ ከጎርፉ ጋር መንደፋደፍ፣ አይበጅህም። ለጥፋት መጣደፍ ነው። ትርፍ አያመጣልህም።
ግን፣ ከጎርፍ ጋር መጋፋት ፈልገህ አይደለም። ቅራኔና ንትርክ አይጥምህም። በእርግጥ፣ በጭፍን መስማማት ሰላማዊ አይደለም። ግን ደግሞ፣ በጭፍን ማፈንገጥ ጀብድ አይደለም። ከወዳጅ ከዘመድ፣ ከጎረቤት ከባልደረባ ጋር መቃረን ምን ይረባል?
ይልቅስ፣ ጎረቤትህ ብርታት ቢሆንህ፣ እኩያህ መንገድ ቢጠቁምህ በወደድክ። የሚያስተምር ታላቅ፣ የሚመክር አዋቂ ቢበዛልህ ነው ምኞትህ። አጥፍተህ ከሆነ ለመታረም፣ ያጎደልከው ነገር ካለ ለመካስና ለማሟላት፣ ቅንጣትም አታመነታም። ስተህ እንደሆነ የሰው ምክር፣ የምስክርም ቃል ለመስማት፣ አይተህ እርግጡን ለመፈተሽ አይንህን አታሽም። ግን፣ ለመምሰልና በጋርዮሽ ለመመሳሰል አይደለም። በይሉኝታ መቀላቀል መማሰል ጥቅም የለውም። ዞሮ ዞሮ፣ መጣም ቀረ፣ ለራስህ ራስህ ብቻ ነህ አለኝታህ።
ራቀ ዘገየ ብለህ ከውጥንህ ከመንገድህ የማትወጣ፣ ፅኑ አላማ ጠባቂ!
If you can wait and not be tired by waiting,
Or being lied about, don’t deal in lies,
Or being hated, don’t give way to hating,
And yet don’t look too good, nor talk too wise:
ከቁም ነገር ሳይጥፉ ቢዘነጉህ? ለጥዋት በተሰጠ ቃል መሽቶ እስኪነጋ በይደር ቢያጉላሉህስ? አሰንብተው ለከርሞ ቢያስጠብቁህ? አለመታደል ነው። ነገር ግን፤ አይታክቴ የማትዘናጋ፣ ፅኑ አላማ ጠባቂ መሆንህ ነው - ሰውነትህ። ጥበቃ አይሰለችህም።
መድረሻህ በአንድ ዝላይ የማይደረስ፣ ሃሳብህ የአንድ ጀምበር አዝመራው የማይሰበሰብ፣ ቢሆንም ጥበቃ አይታክትህም። መንገዱ ቢርቅ፣ ወቅቱ ቢረዝም ቢፈራረቅ፣ አቀበት ቁልቁለቱ ቢበዛ፣ … ዘገየ ብለህ ከመንገድህ አትዛነፍም። አላማህ በፀሐይ በዝናብ አይደበዝዝም፣ ትእግስትህ ለዝለት አያሸበርክም፣ በጊዜ ብዛት ዝገት አይበላውም።
ዶፉ መዓቱን ሲያወርድ፣ ውሽንፍር ሰማይ ምድሩን ሲንጥ፣ መብረቁ ጥቁር ደመናውን እየሸረከተ ጽልመቱን ሲሰነጥቅ፣ ተራራው በነጎድጓድ ሲናወጥ ሲንገጫገጭ፣ ተጠልለህ ትጠብቃለህ። ግን ዋሻው ውስጥ እስከ ዘላለም በጨለማ አትጠብቅም። ጎርፍ እስኪያልፍ መጠበቅህ፣ ውጥን አላማህ ተሸርሽሮ እስኪያልቅ አይደለም።
ቢያብሉ ቢዋሹህ፣ የማትፋለም በአፀፋ፣ ውሸትን በውሸት ሸፍጥን በሸፍጥ የማትላፋ። በክፋት በጥላቻ ሲመጡም፣ አትሆንም የጥላቻ ወዶገቢ። እጅህን አትሰጥም ለጭፍን ስሜት። …ይሄ ሁሉ የምርህ የውስጥህ ስለሆነ እንጂ፤ ለይምሰል ለትወና አይደለም።
ውሸትን ለመመከት እውነትን ይዘህ መፅናትህ፣ የገራገርነት አይደለም። ግን፣ ለይስሙላም አይደለም። “ቃሉ መሬት ጠብ አይልም” እንዲሉህ፣ ጆሮ በሚያሞቅ “የአዋቂ ልሳን” የምትናገር ወገኛ አልሆንክም።
ጥላቻን ለማጥፋት ቅንነትን እንጂ ጥላቻን አለመታጠቅህ፣ በየዋህነት አይደለም። ግን፣ ለታይታም አይደለም። በበጎነት በልጠህ ለመታየት፣ “ደጉ የፍቅር ሰው” እንዲሉህ የምትጓጓ፤ አስመሳይ ብልጣብልጥ አልሆንክም።
ማሰብ ሌላ፣ መብሰልሰል ሌላ! በሕልም መተለም ሌላ፣ በሕልም መነሁለል ሌላ!
If you can dream – and not make dreams          your master;
If you can think – and not make thoughts          your aim;
If you can meet with Triumph and Disaster
And treat those two imposters just the          same.
ህልመ ብሩህ፣ የማለዳ ምንጭ፣ ሩቅ አሳቢ ነህ። ነገን ሰሪ፣ ብርሃን ፈንጣቂ ፋና፣ መንገድ ቀያሽ ብልሃተኛ ባለሙያ- የነገን ሕይወት ፈጣሪ ጥበበኛ። አሻግረህ የልምላሜ ወራትን የምታይ። የእንቁጣጣሽ አደይ አበባን፣ የደመራ ብርሃንን ለከርሞ የምታስተውል ህልም አዋቂ።
ታዲያ፣ ህልም አምላኩ አይደለህም፤ የህልም ዓለም ምርኮኛ። የባዶ ምኞት እስረኛ አትሆንም፤ ሃሳብ ቀለቡ ቅርብ አዳሪ።
ይልቅስ፣ ነገን በተግባር በእውን ለመቅረፅ ነው፣ አፍላቂ መሆንህ የሩቅ ሃሳብ ቀማሪ። እንቶፈንቶ ለመደረት፣ የሃሳብ አቧራ እያቦነኑ ለመታፈን፣ እውኑን ዓለም በሚያስክድ የሃሳብ ጉም ውስጥ ቀልጦ ለመቅረት አይደለም። እውኑን ለመሸወድ ጨለማ ዋሻ ውስጥ ለመወሸቅ፣ በሃሳብ ቁማር እየተራቀቁ ለመድቀቅ፣ በትብታብ መፈናፈኛ ለማጣት አይደለም። ከሆነማ፣ ሃሳብ ማለት በሃሳብ ቀንበር መጠመድ ነው።
ስኬትን ትሸጋገርበታለህ። እንቅፋትን ትሻገረዋለህ። ሐውልትና መቃብር አይደሉም።
ትልቅ ስኬት እና ከባድ ስብራት (Triumph and Disaster)… አንዱን አጣጥሎ፣ ሌላውን አናንቆ ማየት አይቻልም። ቢቻል እንኳ፣ ተገቢ አይሆንም።  ጣፋጩንና መራራውን፣ በእኩል አይን መመልከት፣ እኩል ማስተናገድና መሸኘት፣… ለምን ሲባል? እንዴት ያዋጣል? ጥቅምና ጉዳት፣ ፍሬና ገለባ፣ አረምና አዝመራ፣… ስብራትና ጥገና፣ ምን አገናኛቸው? በጣም ይለያያሉ። በእርግጥ፣ የሕይወትና የሞት ያህል አይሆኑም። ነገር ግን፣ የማግኘትና የማጣት ልዩነት፣ ሊጠፋብን አይገባል። ቢጠፋብን፣ ስተናል፣ ወይም ተሞኝተናል። በእርግጥ፣ ሁሉም ልክ አለው። ማግኘትም ማጣትም፣ ከልኩ አይጎድልም፤ ከልኩ አያልፍም። ማጣጣል ስህተት ነው። ከልኩ በላይ ማጋነንም፣ እንዲሁ።
ማግኘትን አግንኖ ማጣትን አካብዶ እያየ፣ ብዙ ሰው ይሳሳታል።
እለታዊውን ስኬት በማጋነን፣ “ነገ” የሌለው፣ ዘላለማዊ የሕይወት ማሳረጊያ ጉልላት ያስመስሉታል።
ጊዜያዊውን እንቅፋት በማግዘፍ፣ “ነገ” የሌለው፣ የዓለም ፍፃሜ የመጨረሻው መዓት ያስመስሉታል። በእርግጥም ደግሞ፣ ከምር ሊመስሉን ይችላሉ።
ወርቅ ቅብ እንጨት፣ የወርቅ ዙፋን ከመሰለን፤ እንዘናጋለን። አቧራና ጥቀርሻ ሲለብስ፣ “ነደደ፣ ከሰል አመድ፣ ፍርስራሽ አፈር ሆነ” የምንል ከሆነም፤ ልክ ልኩን ስተነዋል። መምሰልና መሆን ሲምታታ፣ ማታለያ (imposter) ይሆንብናል - ያታልለናል።
አንዳንዱ ስኬት፣ በደስታ ብዛት፣ ሕይወትን ለማስረሳት ይቃረባል። አንዳንዱ አደጋም፣ በሃዘን ብዛት፣ “ሰማዩ ተደፈነብኝ” ያሰኛል። ግን፣ ስህተት ነው። ሁሉንም እንደአመጣጡና በልኩ መሆን አለበትና።
እድል ቢደርስህ፣… በቃ? ሩጫህን ጨረስክ? ሕይወትህ እስከዘላለሙ ረጋ? እክል ቢገጥምህ፣… በቃ? ተስፋህ ጨለመ? ታሪክህ ተዘጋ?
ወድቀህ አፈር ብትበላ፣ በግርማ ሞገስ ዘውድ ብትደፋ፤… ያሰብከው ቢቃና፣ ከምኞትህ በላይ ህልምህ ቢሳካ፣ ወይም ሳታስበው ቢጠፋ፣ የፈራኸው ሁሉ ከላይ ተንዶ ቢመጣ፣
ሲሳይ ሰተት ብሎ ከእጅህ ቢገባ፣ የያዝከው ቢያመልጥ፣ የሚጨበጥ ብታጣ፣ ምን ታደርጋለህ?
ቤትህ ሞልቶ በደጅህ ቢከመር ቢትረፈረፍ፣ ጓዳህ በአፍታ ቢራቆት፣ ግቢህ ኦናው ቢቀር፣
“አለፈልኝ” ብለህ እስከወዲያኛው በደስታ ትተኛህ? “አለቀልኝ” ብለህ ጉድጓድ ትቆፍራለህ? አይሆንም አታደርገውም።
በረከት ከነምርቃቱ ቢጨመርልህ፣ በፌሽታ፣ በምረቃ ድግስ፣ ከሕይወት አለም ትሰናበታለህ?
መከራ ከነብሶቱ ቢያስጨንቅህ፤ በምሬት በዋይታ፣ በግዞት ከሕይወት አለም ትመንናለህ?
አታደርገውም።
አዎ፣ የስኬት በረከት፣ የምትለፋለት ምኞት ነው። የምስራቹ ቶሎ ይምጣ።
አዎ፣ እክልና ውድቀት፣ መራራ ነው። ዓለም የተደፈነ ይመስላል - መከራ ሲበረታ።
ነገር ግን፣ አንድ ስኬት፣ የሕይወት ማሳረጊያ፣ የታሪክ መዝገብ ማጠቃለያ፣ የፍፃሜው መዝጊያና ማህተም ማሳረፊያ አይደለም።
እክል መከራም፣ የሕይወት ማሳጠሪያ፣ የታሪክ ፈትል መቋጫ፣ የክሩ የመጨረሻ ጫፍ ማንጠልጠያ አይደለም። ይመጣል፤ ይሄዳል። እውነት ነው - ይህን ታውቃለህ።
መውደቅና መነሳትን፣ ውጣ ውረዱን፣ ደመናና ፀሐዩን፣… ሁሉንም እንደአመጣጡ፣ ሁሉንም በልኩ ታስተናግዳለህ፤ ታሳልፋለህ፤ ትመልሳለህ።
ሕይወት፣ ከነውጣ ውረዱ፣ ይቀጥላል። ሕልምህ ሕያው ነው። መሽቶ ሲጨልም አይሞትም። ጥዋት ሲነጋ፣ በእለታዊ ችግር፣ ሕልምህ በንኖ አይጠፋም፤ ፀሐይ ሲመታው አይቀልጥም። ሕልምህ፣ “ሕያውም ብሩህም” ነው። ግን፣ የሕልም እስረኛ አይደለህም። በሕልም የታወረ ነሆለል አትሆንም።
ማሰብን የምትችል አዋቂ ነህ። ግን፣  ማሰብና መብሰልሰል ይለያያሉ። በሃሳብ አትሟሟም። ሃሳብ ቀለቡ አይደለህም።
ሃሳብህ፣ ቁም ነገር ነው - በተግባር የሚያፈራ። ሕልህም በእውን ሕይወትን አለምልሞ ለማሳመር የሚበቃ። ግን፣ “እዚያው በዚያ” አይሆንም። “ያኔውኑ ወዲያውኑ” አይከወንም። ጉዞ ነው። መውደቅና መነሳት አያጣውም፤ ውጣ ውረድ አይለየውም። ግን ትጓዛለህ። እድልና እክልን፣ እንደ አመጣጡ ትወጣለህ።  
የስራ ፍሬህ ሲበረክት፣… እንኳንም በረከተልህ፣ አልልታ ነው። ግን፣ እልልታው፣ አለልክ አይጦዝም፤ አናትህ ላይ አይወጣብህም።
እክል ተደንቅሮ ሲያደናቅፍህ፣ የነበረው ሁሉ እንዳልነበረ ሲሆንብህ፣… ያሳምምሃል። ግን፣ እንዳልነበርክ አድርጎ አይጥልህም።
እውነት ነው፤… እንቅፋቱ፣ የዓለም ፍፃሜ፣… እርምጃህም፣ የሕይወት ጫፍ ጉልላት ይመስላሉ። ነገር ግን፣ imposters ናቸው - ከመምሰል አያልፉም።
አዎ፣ እርምጃህ ፋይዳ አላት። ግን፣ እርምጃህ በአጭር አይቋረጥም። የምታገኛትን ስኬት ተጠቅመህ፣ በሕይወት መንገድ፣ ጉዞህን ትቀጥላለህ።
አዎ፣ እንቅፋት ይጎዳል። ግን ከወደቅክበት ትነሳለህ። የእንቅፋትን ነገር አስተውለህ፣ ወደ ተቃና የሕይወት መንገድ ታመራለህ።
እክልም እድልም፣ እንቅፋትም ስኬትም፣ የከፍታ ማብቂያና የተስፋ መጨረሻ አይደሉም - ቢመስሉም እንኳ።
እድልና ስኬትን ትሸጋገርበታለህ። እክልና እንቅፋትን ትሻገረዋለህ። እንዲህ ነው ሕይወት።
ስኬት፣ ሐውልት አይደለም - ተገትሮ የሚቆም። እንቅፋት መቃብር አይደለም - አጋድሞ የሚያስቀር።
የሰራኸው ሊሰበር ይችላል፤ መንፈስህ ግን ማንሰራራት ይችላል።
If you can bear to hear the truth you’ve spoken
Twisted by knaves to make a trap for fools,
Or watch the things you gave your life to, broken,
And stoop and build ’em up with worn-out tools:
በቀና አንደበትህ፣ የተናገርከው የእውነት ቃልህ፣ በዋዘኛ ሲበረዝ፣ በሸረኛ ሲጠመዘዝ፣ የዋሆችን ለማንሸዋረር፣ ሞኞችን ለማታለል፣ ቃልህ እየተቆረጠ እየቀጠለ ሲሸረብ ብትሰማ ምን ትላለህ? ምንስ ታደርጋለህ? “ምን ልሁነው!”፤ “ምን ይዋጠኝ!” አትልም።
“እርም የሰው ነገር!”፤ “ከእንግዲህ ቅንጣት እውነት ብተነፍስ፣ ግዑዝ አለት ያድርገኝ!” ብለህ፣ ሰውን እየተራገምክ፣ ምለህ አትገዘትም። ለተሳሳተው ታስረዳለህ - በቻልከውና ባወቅከው መጠን። ለባሰበት ምላሽ መስጠት ትችላለህ። ጆሮውን የደፈነውስ፣ ምን ታደርገዋለህ! ካልደረሰብህ፣ ትተወዋለህ።
የገነባኸው ሁሉ ሲፈርስ ያየህ ጊዜ፣ አብረህ አትፈርስም። እድሜህን የገበርክለት፣ ሁሉመናህን የሰጠህለት፣ በሙሉ ሃሳብህና ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና ሃይልህ የደከምክለት ስራ፣ እንደራስህ የምትሳሳለት የምታከብረው የጥረትህ ውጥንና ውጤት ነው። የተሰባበረ እንደሆነ ግን፣ መንፈስህ አብሮ አይሰበርም። ታንሰራራለህ። ዝቅ ጎንበስ ብለህ፣ በባዶ ኪስ ያለ ሽራፊ ሳንቲም፣ ሰባራ ጎባጣ መሳሪያህን ጨብጠህ፣ ዳግም ለመገንባት ትቆፍራለህ።
ደግሞም ትገነባዋለህ። ታቃናዋለህ። ቀና ትላለህ። ቀላል ስለሆነ አይደለም። ከባድ ነው። የአመታት ድካምና ላብን ይጠይቃል። ያጎሳቁላል። የብዙ በጋዎችን ሀሩር፣ የብዙ ክረምቶችን ዶፍ አልፈህ ነው፣ ለፍሬ የምትደርሰው። የወጠንከውን ስራ፣ በሁለት እግሩ የምታቆመው። ዳገቱን አሸንፈህ ነው፣ ከከፍታው ላይ የምትወጣው። በኩራት ከፍ ብለህም፣ በክብር የጥረት ፍሬህን ታጣጥማለህ።
ከጉብታው ለመውረድ አታመነታም፣ ከፍ ወዳለ ኮረብታ ለመሻገር።
If you can make one heap of all your winnings
And risk it on one turn of pitch-and-toss,
And lose, and start again at your beginnings
And never breathe a word about your loss;
ታዲያ፣ ሕይወት፣ “በአንድ የአዝመራ ወቅት” አያበቃም። ጉዞም፣ በአንድ ከፍታ አይገላገሉትም። ጉብታው ቋሚ አድራሻህ፣ የሕይወት ማቀዝቀዣ ስፍራ፣ የከፍታዎች ሁሉ አውራ፣ የጉዞ መጨረሻ እንዳልሆነ ታውቃለህ። ከጉብታው ማዶ፣ ከፍ ያለ ኮረብታ አለ፤ ከጋራው ባሻገርም፣ እጅግ የላቀ ተራራ። የሚታይ ብቻ ሳይሆን የሚጣራ። “በቃኝ፤ ይቅርብኝ” አትልም።
አዎ፣ በጉብታውና በኮረብታው መሃል፣ አስቸጋሪ ሸንተረር ይጠብቅሃል። ከጋራው ወዲያ፣ ወደ ተራራው ለመሻገር፣ የሸለቆ ቁልቁለት ክፉኛ ይፈታተንሃል። ወደ ላይ ወደ ላቀ ከፍታ ከተመኘህ፣ በስንት መከራ የተቀዳጀኸውን ጉብታ ትተህ ትጓዛለህ። ወደ ሸንተረሩ ወደ ሸለቆው ወደ ታች መውረድ የግድ ነው።
ከእጅህ የገባውን ጉብታ ትተህ መጓዝ፣ ከዜሮ እንደመጀመር ቢሆንም፣ አያስፈራህም። ቢያስፈራህም፣ ከጉዞ አያስቀርህም። “ጉብታዬን ትቼ የወረድኩ፣ አግኝቼ ያጣሁ” ብለህ አትተክዝም፣ አታማርርም። ከጉብታ የላቀ ኮረብታን መርጠሃልና።      
“አይዞኝ” የምትል የነፍስህ ድምፅ!
If you can force your heart and nerve and sinew
To serve your turn long after they are gone,
And so hold on when there is nothing in you
Except the Will which says to them: “Hold on!”
አንዳንዱ ፈተና፣ ትእግስትን ያስጨርሳል። ኃይልህ ጠንጠፍጥፎ ሲያልቅ ይሰማሃል። ጉልበትህ ሲብረከረክ ይታይሃል። የዛለ አካል፣ አጥንቶችህ ጭምር፣ ለአፍታ አጠፍ በርከክ ማለት ናፍቋቸዋል። የልብህ አቅም ተጨምቆ የተሟጠጠ ይመስላል። ደምስሮችህ በግለት ተንተክትከዋል። ጅማቶችህ እስከ ጫፍ ተወጣጥረዋል። ቢሆንም፣ “አይዞኝ”፣ “በርታ” ትላለህ።
ማረፊያ መደገፊያ የለህም። ወኔ ብቻ ነው የቀረህ። “አይዞኝ” የምትል የነፍስህ ድምፅ ብቻ ናት፣ ሃይልና ምርኩዝህ፣ የመንፈስህ ፅናት።
ከፍታም ዝቅታም፣ ወዳጅም ባላንጣም፣ ሁሉንም በልኩ ነው።
If you can talk with crowds and keep your virtue,
Or walk with Kings – nor lose the common touch,
If neither foes nor loving friends can hurt you,
If all men count with you, but none too much;
የሚያበረታታ ሰው ቢኖር፣ የአፍታ ድጋፍ ብታገኝ አትጠላም። እያንዳንዱ ሰው፣ ባንተ ዘንድ ዋጋ አለው። ለሰው የሚገባ ክብር፣ ለሁሉም ሰው ትሰጣለህ። ነገር ግን፣ እንደየስራውም ትዳኛለህ። እንደየብቃቱ ታደንቃለህ፣ እንደየመልካምነቱ ሰውን ትቀርባለህ፣ ትወዳለህ። ከአጥፊው ከወራዳውም፣ ትርቃለህ፤ ራስህን ትከላከላህ። ሁሉንም በልኩ ነው።
ከባላንጣህ ቅንጣት አትመኝም። ምንም አይቀርብህም፤ ጉዳት አይደርስብህም።
ወዳጅ ጓደኛ፣ መስተዋት ነው። እንደ አቅሙ ወድዶ ቢደግፍህ፣ እንደቻልከው ብትደግፈው፣ እሰየው ነው። የሃሳብ አስከታይና ተከታይ፣ ገዢና ጥገኛ ለመሆን አይደለም። እንዲያ ብትመኝ፣ ከንቱ ጥፋት ይሆናል። እሺ ብሎ በጭፍን ቢከተልህ ቢታዘዝህ፣ ያ ያደነቅከው የግል ማንነቱ ይመክናል። እምቢ ቢል፣ ቅሬታና ቂም ብቻ ይተርፍሃል።
 የግል ማንነትን በማክበር፣ ልክን በማወቅ ላይ የቆመ ትክክለኛ ጓደኝነትና ወዳጅነት ግን፣ አይመክንም፤ ፅኑ ነው። ከጥፋትና ከቅሬታም ያርቃል።
ነፍስ ያለህ ሙሉ ሰው ትሆናለህ፣ ዓለምንም ታተርፋለህ።
If you can fill the unforgiving minute
With sixty seconds’ worth of distance run,
Yours is the Earth and everything that’s in it,
And – which is more – you’ll be a Man, my son!
ካለፈች የማትመለስ፣ ካመለጠች የማትጨበት እያንዳንዷ የሕይወት ቅፅበት ዋጋ አላት። የልብ ትርታ ብርታትህ፣ የሕይወት ጣዕም ትንፋሽህ ናት - ቅንጣቷ የሕይወት  ቅፅበት። እያንዳንዷ ደቂቃ፣ የ60 ሴኮንድ ሩጫ ናት - ባንተ ሕይወት። የግስጋሴ።ይህን ሁሉ ከቻልክ፣ በሃሳብና በተግባር ከተጓዝክ፣ ኑሮህንና ማንነትህን እንዲህ አቃንተህ ከቀየስክና ከቀረፅክ፣… ዓለምን ሙሉ፣ በውስጧ ያለውንም ሁሉ ታተርፋለህ። ደግሞም፣ ነፍስ ያለህ ሙሉ ሰው ትሆናለህ።

Read 1263 times