Saturday, 27 November 2021 14:23

የእነ‘ኒማ’ ነገር...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...ዘንድሮ እኮ ግርም የሚል ነው፡፡ ስንቱን ጉድ እያየን እኮ ነው! እነኚህ የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉ፣ ያለእኛ እውነት ተናጋሪ ላሳር ሲሉ የነበሩ የዓለም ሚዲያዎችን የሞላው ለካስ ምድረ ቀጣፊ ነውና!  ኧረ ‘ሼም’ ነው!
የበፊት ወሬያችን...
“ስማ፣ ትናንት ማታ ሲ.ኤን.ኤን አየህ?”
“አላየሁም፣ ያመለጠኝ ነገር አለ እንዴ?”
“ያቺ እንትና የሚሏት ያንን እንትና የሚባለውን የእንትን ሀገር ሰውዬ በጥያቄ ድንብርብሩን አታወጣው መሰለህ!”
“እሷን ሴትዮ እኮ ሳደንቃት፡፡ አታፈናፍንህም እኮ!”
አሁን...
“ስማ የሲ.ኤን.ኤንን ጉድ ማታ አየህልኝ አይደል!”
“አየሁ እንጂ፡፡ እነሱ ሰዎች ግን እየገረሙኝ ነው፡፡ ለሚናገሩት ኦሪጂናል የሆነ ውሸት ጥንካሬ የሚሰጥ ‘ኤሚ አዋርድ’ ምናምን የሚባል ነገር አለ እንዴ!”
“ለነገሩ እኛማ ስለነቃንባቸው ምን ቸገረን፡፡ ግን ይብላኝ ለባሏ!”
“ባሏ፣ ያማከረህ ነገር አለ እንዴ! አጅሬ እኮ መግቢያህ አይታወቅም፡፡”
“አይ... ሳስበው እስከዛሬ አድራ እየመጣች ‘የት ነበርሽ’ ሲላት ሰልስት ነው ያደርኩት እያለች ስንት ጊዜ ተጫውታበት ይሆን!”
“ቆይ፣ ቆይማ... ስለ እሷ ባል ነው የምታወራው ወይስ ስለ ራስህ?”
“እየው እንግዲህ ጀመረህ!”
እናላችሁ... የሚገርም ነው፡፡ ለካስ እነሱ ሲያደናብሩ የሚደናበርላቸው ሲገኝ ነው ‘ትንታግ ጋዜጠኛ’ ምናምን ነገር የሚያደርጋቸው!
ስሙኝማ፣ ይቺ ኒማ ኤልባጊር የሚሏት.......ሴትዮ #ይብላኝ ለወለዷት፤ ያገባማ ባዶ ቤት ጥሏት ይሄዳል...” የምትባል አይነት ሆነች እኮ! አስታቅ... (“ወስፌ ነገር” ማለት ይቻል እንደሁ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቄ ክፍት ቦታውን እሞላዋለሁ፡፡ የሚያውቅ ሰው ማለት ‘የሚያውቅ ሰው’ ማለት ነዋ! አሀ... የምን ቤኪ አንደርሰን መሆን ነው! ቂ...ቂ...ቂ... እናላችሁ...ለምሳሌ ቀደም ሲል በአብዛኛዎቹ መንደሮቻችን የታወቁ ማንንም ቢሆን ልክ፣ ልኩን ነግረው አፍ የሚያሲዙ ሰዎች አሉ አይደል...ከእነሱ ምክር ማግኘት ይቻላላ!
“እባክሽ፣ ይሄ ግቢያችን አዲስ የተከራየው ወንደላጤ አላስቀምጥ አለኝ እኮ!”
“የአልጋ ልብስ አጋሪኝ ማለት ጀመረ እንዴ?”
“እስቲ አንዳንድ ጊዜ ከአልጋ ውረጂና ስለ ወንበር አውሪ!”
“አንቺ ስልጠና ስጪኝና ነዋ! ይልቅ ሰውየው ምን አለኝ ነው የምትዪው?”
“ኧረ የሚወራ አይደለም፡፡ እንደዛ ሱፉን አሳምሮ የሚናገረው ነገር...የሆነ ወመኔ ነገር ነው፡፡”
“ለምን ለዛች ለእንትና አትነግሪያትምና እስከ ዶቃ ማሰሪያው አትነግረውም!”
“እንኳን አስታወስሽኝ! ምን አለች በዪኝ፣ አይደለም ሰፈር ሀገር ጥላ ባታስኬደው!”
ታዲያላችሁ... ይቺ ኤልባጊር የሚሏት ሴትዮ የጣቢያውን ቁጥር አንድ ቀጣፊነት ‘ማዕረግ’ ለመያዝ እየሮጠች ያለች ይመስላል፡፡ ከወራት በፊት ውጊያ ቀጠና ሄዳ ወታደሮች አካባቢ “ሲ.ኤን.ኤን.” እያለች የጮኸችው ትዝ ይላችኋል? ቆይ እንደዛ የሆነችው...“ቀይ ምንጣፍ አንጥፉልኝ...” ነው! ለነገርዬው እሷ የዛ ጣቢያ ሠራተኛ ስለሆነች ‘ሻኛ’ ምናምን ማሳየቷ ነው፡፡  ደግሞ ባይደንንም፣ አልቡርሀንንም በአንድ ጊዜ ለማስደሰት መከራዋን ከምታይ ተራ በተራ ብታደርገው አያልቅባትም ነበር፡፡ ይቺ......! (እነ እንትና... ‘ፊል ኢን ዘ ብላንክ’ ስለሆነ አግዙኝማ!)  
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንድ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ግን ሁላችንም እውነት ብለን የምንቀበለው ነገር አለላችሁ፡፡ “አፍሪካውያን እኛንም አይወዱንም፣” የሚባል ነገር አለ፡፡ ግን...አለ አይደል... መቼም ቢሆን ራሳችንን እዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰው እንዴት ነው ብለን ጠይቀን አናውቅም፡፡ ‘በቃ፣ አይወዱንም፣ አይወዱንም!’ አፍሪካውያን በአንደበታቸው “ኢትዮጵያውያንን አንወዳቸውም፣” ሲሉ ሰምተናቸው እናውቃለን? “በቃ እነኚህ ሀበሾች ጤፍና በርበሬ ስለሚመገቡ ደረታቸውን የሚነፉት ምን የሆኑ መሰላቸው!” ሲሉ ሰምተን እናውቃለን? (እነ እንትና በርበሬዪቱ ትንሽ ዋጋዋ ወረድ እንደማለት እያለች ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ! ከሆነ ሸጋ!) ለነገሩማ ከዋሽንግተን እስከ ብረስልስ፣ እስከ ናይሮቢ ስንቱ የማረቆን አስር እጅ የሚለበለብ በርበሬ ፈልቶብን የለ!
አሀ፣ እቅጭ እቅጩን መነጋገር አለብና! አሁን ...ከርመን እየነቃን ቢሆንም መለስ ብሎ ነገሮችን ማየት አሪፍ ነው፡፡  
እሺ ስንቶቻችን ነን የአፍሪካ ሙዚቃ የምንሰማው ብቻ ሳይሆን ሰምተን የምናውቀው?
ስንቶቻችን ነን የአፍሪካ ደራስያንን ሥራ ለማንበብ የምንሞክረው?
ስንቶቻችን ነን የአፍሪካውያን ፊልሞች የምናየው?
(እነ እንትና...እንደዚህ እንደምትሉ አውቂያለሁ፡፡ እኔ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ምንም አይነት ቢዙ የለኝም! ደግሞ ኒማ ይህን ትስማና “ሀገሪቱ በገጠማት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ማሽቆልቆል ጋዜጠኞቹ ሥራ ካልሰጣችሁን እያሉ የአፍሪካ ህብረትን ሥራ እንዲሰጣቸው እየለመኑ ነው...”  ትበለና!)
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ከዚህ በፊት ስለ አፍሪካ ፊልሞች ስትጠየቅ በግና ዶሮ ብቻ ነው የሚያሳዩት አይነት ነገር ያለችው ‘የፊልም ባለሙያ’፤ የሆሊዉድ ሥራዋ ምነው እስከ ዛሬ አልወጣምሳ! አሀ....በግና ዶሮ የሌለበት ፊልም እዛ ነዋ የሚገኘው! ለነገሩ እሷስ ምን ታድርግ... የሰማንያና የመቶ ሺህ ብር ሶፋ ካልተደረደረ፣ ‘ጂ ፕላስ ሥሪ’ ቤት ካልሆነ፣ ሦስት ሰው ላለበት ቤት ምሳ ወይም እራት ሠላሳ ምናምን አይነት ምግብ ጠረዼዛ ላይ ካልተደረደረ ፊልም አይሆንማ፡፡ (እኔ የምለው... ይሄ መአት ምግብ የመደርደር ነገር...ባለሙያዎች በኋላ ‘ኢን’ ታደርጉታላችሁ ወይስ በኪራይ ነው የሚመጣው! ቂ...ቂ...ቂ... አሀ...ልክ ነዋ... መለስተኛ ሰርግ የሚመልስ ምግብ ሦስትና አራት ሆናችሁ አትሸከሙት ነገር!)
እናላችሁ... ይሄ “አፍሪካውያን አይወዱንም፣” የሚለው ነገር በምን ሁኔታ፣ በምን አይነት ክስተቶች እንደተጀመረ እሱው ይወቀው፡፡ አሁን ወደ ኋላ እየተንደረደርን “እንዲህ አድርገውን...” “እንዲህ ጉድ ሠርተውን...” ማለት ሳይሆን ወደ ራሳችን ቀልብ መመለስ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ... ሰሞኑን በተለያዩ የአፍሪካውያን በሆኑ ዩቲዩብ ቻነሎች ላይ የሚለቀቁትን ዘገባዎች ስታዳምጡና እነሱንም ተከትሎ የሚሰጡትን አስተያየቶች ስትሰሙ ምን ያህል የተሳሳተ አስተያየት ተሸክመን እንደከረምን ታያላችሁ፡፡ የሚገርም እኮ ነው...ስለ እኛ ምንም የማያውቁ የሚመስሉን አፍሪካውያን ከምናስበው በላይ ያውቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ ሀገር መሆኗን ከማንም በላይ ጮክ ብለው እየተናገሩ ያሉት እኮ አፍሪካውያን ናቸው!
ኢትዮጵያ የሦስትና የአምስት ሺህ ዓመታት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን እየተናገሩ ያሉት እኮ አፍሪካውያን ናቸው!
“ኢትዮጵያ ኢዝ ዘ ማዘር ኦፍ አፍሪካ!” ወይም ‘ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ነች እያሉ ያሉት እኮ አፍሪካውያን ናቸው!
ስለ ንግሥት ሳባና ስለ ንጉሥ ሰለሞን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለዓለም እየነገሩ ያሉት እኮ አፍሪካውያን ናቸው!
ይህ ጦርነት የኢትዮጵያ ጦርነት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ጦርነት ነው እያሉ ያሉት እኮ አፍሪካውያን ናቸው!
እናላችሁ...ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ደግሞ ምን መሰላችሁ...በአሁኑ ጊዜ ነገሩ ሁሉ እየገባቸው የመጡ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን “በአፍሪካዊነቴ እኮራለሁ!” ሲሉ ከመስማት በላይ ምን ደስ የሚል ነገር ይኖራል!
እኔ የምለው... የእነዚህ የምዕራባውያኑ ጋዜጠኞች ነገር አሁንም ግራ ግብት ነው የሚለው! የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ግዴላችሁም ...ዶላሩ በደንብ ተደርጎ ‘እየተበጠሰላቸው’ ነው፡፡ አሁን እንደው የፈለገው ፖለቲካ ይሁን ምን ይሁን... የእሁድ ዕለት እነኛ ሰልፎች ጭጭ ብለው የሚታለፉ ነበሩ! እኛ እዚህ ያለነው ብቻ ሳይሆን... እዛው ሰልፎቹ በተካሄዱባቸው ከተሞች ለረጅም ጊዜ የኖሩ ወገኖቻችን “እንዲህ አይነት ነገር መቼም አይተን አናውቅም!” እስከ ማለት ያደረሱ ሰልፎች የዜና ሚዛን ሳይደፉ ቀርተው ነው!
ቆዩኝማ፣ እኔ የምለው...ሰልፋችን እነሱ ሚዲያ ላይ እንዲዘገብ የግድ ‘መንከባለል’ አለብን እንዴ! (ቂ...ቂ...ቂ...) እነ ኒማ “ሰከን በሉ” ይባሉልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1610 times