Sunday, 28 November 2021 00:00

የጎንደር ከተማ ም/ከንቲባ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ለህልውና ዘመቻው ነገ በሸራተን ከ100 ሚ. ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል

     የጎንደር ከተማ አስተዳደር በነገው ዕለት በሸራተን አዲስ ለህልውና ዘመቻው የገንዘብ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ያዘጋጀ ሲሆን በፕሮግራሙ ከ100ሚ. ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል። በአዲሱ መንግስት ምስረታ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና በከተማው የህልውና ዘመቻው የሎጂስቲክ አስተባባሪ ከሆኑት አቶ ባዩህ አቡሃይ ጋር የአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች። እነሆ፡-

          የጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ያሉ አካባቢዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
የከተማችንና የዙሪያዋን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ አሁን ያለንበት የክተት አዋጅና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ጊዜ ላይ እንደመሆኑ፣ በከተማችን መዝመት የሚገባው ወደ ግንባር እንዲዘምት ተደርጓል። የተወሰነው ሀይል በደጀንነት ዘምቷል። ቀሪው ደግሞ በሎጂስቲክ ስራ (ስንቅ ዝግጅትና ማቅረብ) እየተሳተፈ ይገኛል። ከከተማ እስከ ክ/ከተማ፣ እስከ ቀበሌ፣ ከመንግስት ተቋማት እስከ የግል ተቋማት ሁሉም በየድርሻው የደጀንነት ሚናውን እንዲወጣ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል።
በሌላ በኩል፤ የፀጥታና የደህንነት ጉዳይ አለ። የከተማውን ፀጥታና የደህንነት ሁኔታ ለማስከበር የአድማ ብተና ሃይል፣ የከተማችን ሚሊሺያዎች፣ የግል ታጣቂዎችና የከተማው ወጣቶች አሉ። እነዚህ ተቀናጅተው የፀጥታውን ሁኔታ እያስከበሩ ይገኛሉ። ህብረተሰቡም ጭምር በብሎክ ተደራጅቶ፣ በአምሺና አንጊ ተከፋፍሎ፣ አካባቢውን በጥብቅ እየጠበቀ ይገኛል። ስለዚህ የከተማችን የጸጥታ ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቀደም ሲል በከተማዋና ዙሪያዋ ሰዎች ባልታወቁ ሀይሎች እገታ ይፈፀምባቸው እንደነበረ፣ ይህ የዕገታ ተግባር ለነዋሪዎች ከፍተኛ የስጋት ምንጭ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ይህ ችግር በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
ትክክል ነው፤ አንዱና ዋነኛው የከተማችን ችግር የነበረው ያነሳሽው ጉዳይ ነው። በተለይ እኛ ወደ ሃላፊነት ስንመጣ ይህ የሰዎች መታገት ጉዳይ፣ በጣም አንገብጋቢ ችግር ነበር። የትግራይ ወራሪ ሃይል አንዱ ሲጠቀምበት የነበረው  አሻጥር፣ በዚህ መልኩ ህዝቡን ማስመረር ነበር። እኛ ወደ ሃላፊነት እንደመጣን ወዲያውኑ ያደረግነው ምንድነው፤ የፀጥታ መዋቅሩን በጥልቀት ገመገምንና እርምጃ መውሰድ ጀመርን። እርምጃው በፀጥታ መዋቅር፣ በፖሊስ፣ በሚሊሻ በሁሉም የጸጥታ አካላት ላይ ተወስዷል። ምክንያቱም ከምንም በፊት በራሳችን በኩል ያለውን ክፍተትና ችግር ማየት ነበረብን። የሚጠረጠሩና ህዝቡ አመኔታ ያልጣለባቸውን ሰዎችና  ለዚህ እገታ ከውስጥ ሆነው  መረጃ የሚያቀብሉት ላይ እርምጃ ወስደናል።
ከዚያ ቀጥሎ የዚህ ተግባር ዋና አቀናባሪ የሆነውን ቀንደኛ ሰው መያዝ ቻልን። በአጠቃላይ በዚህ ወንንጀል ከከፍተኛ አስተባባሪነት በቀጥታ እጃቸው እስካለበት ድረስ 36 ያህል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል። ምርመራውም እየተጣራ ነው። ነገር ግን ገና ያልተያዙም አሉ። ሴላቸው እስከ አዲስ አበባ ድረስ የዘለቀ ነው። ማስተር ማይንድ ሆነው ይሰሩ ከነበሩት የተያዙ አሉ፤ ነገር ግን ቀሪዎችም አሉ። ክትትል እየተደረገ ነው። በዚህ ሁኔታ እኛ ወደ ሃላፊነት መጥተን ጠበቅ ያለ እርምጃ ከወሰድን ጀምሮ እገታ የሚባል ነገር ሙሉ ለሙሉ ቆሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸው ይታወቃል። ሁኔታው በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ላይ ምን አይነት ስሜት ፈጠረ?
መልካም! የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመትና ውጊያውን መምራት ለጎንደር ህዝብ ይበልጥ መነቃቃትን ፈጥሯል። እንግዲህ የጎንደር ህዝብ የወራሪውን ሀይል ክፋትና ሴራ ጠንቅቆ ከሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። ምክንያቱም አሸባሪው ህወሃት ብዙ ደባና በደል ሲፈፅም የነበረው ጎንደርና አካባቢውን ኢላማ አድርጎ ነው። ይህን የሚያውቀው አጠቃላይ የጎንደር ህዝብ፣ ወራሪው ሊያጠቃው ሲመጣ ተቆጥቶ ሙከራውን አክሽፎበታል። እንደምታውቂው ወራሪው ሀይል ጎንደርን ለመውረር ያለ የሌለ ሀይሉን ተጠቅሞ ነበር። ነገር  ግን ህዝቡ ተቆጥቶ ከመከላከያ ሰራዊቱ፣ ከልዩ ሀይሉ፣ ከሚሊሻውና ከፋኖው ጋር ሆኖ ከጦር ሀይሉ ጋር ባደረገው ተጋድሎ ጠላት ያሰበው ከሽፎ ተመልሷል። ጭና፣ ማይካድራና ሌሎች ቦታዎች ወራሪው ሀይል ባደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ የተቆጣ ህዝብ ነው። ከዚህም በፊት ህዝቡ ለህልውና ዘመቻ ከአንድ ቤት ሁለት ሶስት ልጆች ከመስጠት ጆሮ እራሱ ዋናው አባወራ እስከመዝመት ድረስ ቆረጠ ነው። ህዝቡም ስንቅ በማዘጋጀት ቀን ከሌት እየተጋ ነው የነበረው። አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ወደ ግንባር ሲዘምቱ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባው እንደቀደሙት መሪዎቻችን ማለቴ ነው፣ በህዝቡ ዘንድ ይበልጥ መነቃቃትና ተስፋ ተፈጥሯል።  አፄ ምንሊክ ወረኢሉ ላይ የክተት አዋጅ አውጀው፣ ጦር ጎራዴያቸውን ይዘው ዘምተው ከህዝባቸው ጋር አድዋ ላይ አሸንፈው እንደተመለሱት ሁሉ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መዝመታቸው በህዝቡ ዘንድ ትልቅ ተስፋን ፈጥሯል። እሳቸው ከዘመቱ ጀምሮ ተደራራቢ ድሎችም እየተመዘገቡ ነው። ይሄ ትልቅ ነገር ነው። በህዝቡ ብቻ ሳይሆን በጦር ሰራዊታችን  ላይም ትልቅ መነቃቃትና ጉልበት የማግኘት ስሜት ፈጥሯል። ሰሞኑን እየሰማናቸው ያሉት ድሎችም የዚህ ስሜት ውጤት ጭምር ናቸው የሚል እምነት አለኝ። አሁን ላይ “ሰራዊታችን አጠቃ፤ ይህን ቦታ አስለቀቀ” ነው እንጂ “ወራሪው ይሄን ከተማ ተቆጣጠረ፤ ይህን ቦታ ያዘ” የሚል ዜና እየቀረ በድል እየታጀብን ነው። አሁንም ለሀገራችን በፅናት ቆመን እናሸንፋለን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ ከመላው የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ከፍተኛ አመራች፣ እንደሆነ አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴና ፈይሳ ሌሊሳ ያሉ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ሰዎችን ጨምሮ በርካታ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ወደ ግንባር ለመዝመት በዝግጅት ላይ ናቸው፤ የዘመቱም አሉ። ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመዝመት ቃል የገባ ወይም የዘመተ አለ?
እኛ ቀድመንም አዝምተናል። እኛ እዚህ የቀረነው ሥራ ተከፋፍለን ነው። ግማሹ ያስተባብራል፤ ግማሹ ዘምቷል። እስከ  ክፍለ ከተማ ደረጃ ባለው ከ40 በላይ አመራሮችን አዝምተናል። እነዚህ አመራሮች ግንባር ነው ያሉት። የተወሰኑ አመራሮች ቅድም እንዳልኩሽ፣ ጎንደር ከተማ ብዙዎች ሊያጠቋት የሚፈልጓት ከተማ ነች። ከነዚህ አንዱ በትግራይ ወራሪ ሀይል ሳንባ የሚተነፍስ የቅማንት ተላላኪ ስላለ  የቀረው አመራር ይህንን ሀይል ለመግታትና ሌሎች ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ስራዎች ለመስራት ተከፋፍለን እንጂ ሁሉም ለመሄድ ልቡ የተነሳ ነበር።
አሁን ላይ በዳባትና በደባርቅ በኩል ያለው አካባቢ ከስጋት ነጻ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው ወይስ ስጋት አለ?
በዚያ አካባቢ ሁሉም በተጠንቀቅ እየተጠበቀ ነው፤ በቂ ዝግጅትም ነው ያለው። ከሁሉም የአካባቢው ወረዳና ዞን ዘምቶ እዚያ ነው ያለው፤ በቂ ሀይል በተጠንቀቅ እየጠበቀ ይገኛል። በዚያ በኩል እመጣለሁ ለሚል ወራሪ እንዳይመለስ አድርጎ የሚቀጣ በቂ ዝግጅትና ቁመና ነው ያለው። አሁን ላይም ፀጥታው በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው።
አሁን ደግሞ ብዙ ገድል እየፈፀሙና እየተዋደቁ ስላሉት ፋኖዎች እንነጋገር። ቀደም ሲል በሌሎች የጦር ሰራዊቶች አደረጃጀት ሥር ባለመሆናቸው ስንቅም፣ ትጥቅም ሳይሰፈርላቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ለሀገራቸው መቆማቸውንና መንግስት እንዲያስታጥቃቸው ሲማጸኑ ይሰማ ነበር። አሁን ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው?
ትክክል ነው! ፋኖ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ያለ ሀይል ነው። አሁን ባለው ውጊያ ላይ የራሳቸውን አሻራ አያሳረፉ ይገኛሉ። እነዚህ ፋኖዎች የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከመከላከያ ሰራዊት ከልዩ ሀይልና ከሚሊሻው ጋር ተቀናጅተው ትልቅ ገድል እየፈጸሙ ያሉ ናቸው። ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም። በዚያው ልክ ደግሞ አንዳንዶቹ በፋኖ ስም የሚነግዱ እንዳሉም ይታወቃል። ነገር ግን በግንባር ከሌሎቹ የጦር ሀይሎች ጋር ሆነው እየተዋጉ ያሉት ፋኖዎች የሎጂስቲክ ችግር የለባቸውም። እሬሽንም ቢሆን እዛ ካለው መከላከያ፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ጋር እኩል ተሰፍሮ እየተሰጣቸው ይገኛሉ። የሎጂስቲክ ችግር አለባቸው የሚባለው የተሳሳተ መረጃ ነው።
በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ከግንባር እየቀረቡ ቅሬታ ሲያሰሙ ስለሚታዩ ነው የጠየቅሁት…
ይሄ ከላይ ያነሳሽው ጥያቄና ቅሬታ ከትክክለኛዎቹ ፋኖዎች ሊነሳ አይችልም። ምናልባት  ቅድም በፋኖ ስም  ከሚነግዱ ፋኖ ነን ባዮች የተገኘ መረጃ ነው ሊሆን የሚችለው። ትክክለኛ ፋኖዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ፣ ሎጅስቲክ ይጎድላቸው እንደሆነ፣ ከሌላው የጦር ሀይል ተለይተው አድልኦ ይደረግባቸው ከሆነ ግንባር ላይ እነሱን ማነጋገር ይቻላል። ትክክለኛ ፋኖዎች ለሀገራቸው ከሌላው እኩል እየተዋደቁና ህይወት እየሰጡ ከሌላው ያነሰ ትኩረትና ሎጂስቲክ ሊኖራቸው አይችልም። የጠላት ሀይል “ስንቄንም ትጥቄንም ከጠላቴ” እያለ እየመጣ ብዙ ጥፋት እያደረሰ ነው። በእኛ በኩል ደግሞ “ስንቃችን ከወገናችን” በሚል ከሁሉም ቦታ የስንቅ ዝግጅት እየተደረገ እየቀረበና እየተከፋፈለ ነው ያለው። እርግጥ፣ በጦርነት ጊዜ የሎጂስቲክ አቀራረብ የራሱ ሂደት አለው።
በከተማ ያለው አቀራረብ ጦር ሜዳ ላይ ሊሆን አይችልም። ከዚያ ውጪ ስንቅ በማቅረብ በኩል በተለይ የጎንደርና የአካባቢው ህዝብ በደንብ እየሰራ ነው። የክልሉም ሎጂስቲክ ለሰራዊቱ በሚገባ እያቀረበ ይገኛል።
ነገ እሁድ በሸራተን አዲስ ሆቴል ለህልውና ዘመቻው የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደምታካሂዱ ሰምቻለሁ። እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ? እነማን ናቸው የሚሳተፉት? ምን ያህል ገንዘብ ለማሰባሰብ ታቅዷል?
እሁድ በሸራተን ሆቴል የምናካሂደው ፕሮግራም ለህልውና ዘመቻው የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ነው። እንደሚታወቀው ብዙ ሃይል ግንባር ነው ያለው። ይህ ሀይል ሎጂስቲክ ያስፈልገዋል። ስንቅና ትጥቅ ደግሞ ለጦርነት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ወገኖቻችን ለሀገርና ህዝብ ህልውና ግንባር ሆነው ደማቸውን ሲያፈሱ፣ አጥንታቸውን ሲከሰክሱ፣ ቀሪው ደግሞ በደጀንነት መደገፍ አለበት። ከዚህ አንፃር፤ በአይነትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ሀብት ለማሰባሰብ የጎንደር ከተማ ያዘጋጀው ፕሮግራም ነው። በሸራተን ነገ የሚካሄደው ቀደም ሲል ከተማ አስተዳደራችን ይሰራው የነበረው የሀብት ማሰባሰብና ሎጂስቲክ የማሟላት አንዱ አካል ነው።
በዚህ ፕሮግራም ግባችን፣ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ ነው። ለዚህ ደግሞ ኮሚቴው ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። በዋናነት እንዲሳተፉ የምንፈልጋቸው የጎንደር አካባቢ ተወላጆች ይሁኑ እንጂ “የጎንደር፣ የአማራና በጥቅሉ የኢትዮጵያ ጥቃት ያገባኛል” የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲሳተፍ ጥሪ የተደረገበት ነው። ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ አደርጋለሁ የሚል ሁሉ የሚሳተፍበት ነው እንጂ የተገደበ አይደለም። ነገር ግን የጎንደር አካባቢ ተወላጆች ከገንዘቡም በላይ አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲገነዘቡ በማድረግ ለዚህ የህልውና ዘመቻ ሁሉም የሚችለውን ማድረግ እንዲችል ትልቅ የምክክር መድረክም የሚፈጠርበት ነው።

Read 3008 times