Saturday, 27 November 2021 14:01

የልጅ ምርቃት!

Written by  ነፃነት አምሳሉ-
Rate this item
(1 Vote)

  #እምዬ ኢትዮጵያ፤ እድሜሽ እድሜ ይውለድ! ክብርሽ ሰማይ ይንካ! ባንዲራሽ ምድርን ያድምቅ! ህዝብሽ ደምቆ ይፍካ! እጅሽ ሙሉ ይፈስ! እግርሽ ጸንቶ ይኑር! ስምሽ ሞገስ ያግኝ! ጆሮሽ እልልታን ይስማ! ፈጣሪ አብሮሽ ይስራ! ልጅሽ ወጥቶ ይግባ! ወንዝሽ በዝቶ ይፍሰስ! ተራራሽ ጠላት ይምታ!
ሜዳሽ እህል ይሙላ!--;
         
           እንደምወድሽ አውቃለሁ! ግን ፍቅሬን ልጻፈው ስል አብሮኝ የኖረው የፈደል ክምር፣ ንፋስ እንደበተነው ጉም ከልቤ ማሳ ላይ ጠፍቶ፣ ጣቴ ብእሩን እያሽከረከረ ይቆዝማል፡፡ በየትኛው የስነጽሁፍ ዘውግ ብከትብሽ “እፎይ” እላለሁ ብዬ ከትምህርት ቤት ቆይታዬ በቃረምኳት እፍኝ ዕውቀት፣ የሃሳብ ሂሳብ እየሰራሁ እጠበባለሁ፡፡ ነፍሴ ጾም እንደ ዋለ አስቀዳሽ፣ ፍቅርሽን ተርባውና በሀሩር ሙቀት ነድዶ ውሃ እንደሚጠማው ዋሊያ፣ ጣእምሽን ተጠምታው፣ በደረቀ ጉሮሮዬ በለሆሳስ ዜማ አዜምሻለሁ፡፡
እንዲያውም ባይገርምሽ! የማልጋፋሽ ባለጋራ ሆነሽብኝ ሰዎች፣“አበደ እንዴ?” እያሉኝ እኔ ግን በመውደድሽ እጣን ታጥኜ፣ መንገድ ላይ ለብቻዬ አዋራሻለሁ፡፡ ለኔ ብቻ በሚሰማኝ ጉምጉምታ አንጎራጉርሻለሁ፡፡ ለወትሮ በተናጋሪነቴ የሚታወቀው አንደበቴ፣ ያንቺን ስም ሲያነሳ፣ እንደ ጨቅላነቱ ዘመን ደርሶ ይንተባተባል! ምን አለፋሽ? ምላሴ ሁሉ ይጎላደፋል!  
ታዝበሽኝ ከሆነ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ስምሽን የጠራ ሁሉ ያሸንፈኛል፡፡ ስምሽ ሲነሳ ጉልበት አጣለሁ፤ እብረከረካለሁ፤ መንፈሴ ይታወካል፤ ባር ባር ይለኛል፤ ለዘመድ ቀብር እምቢ እሚለኝ ዕንባ ከየት መጥቶ እንደሚተናነቀኝ እንጃለት! ኮስታራው ሃሞቴ ቆፍጣናነቱን ጥሎ እንደ እናት አንጀት ይንሰፈሰፋል፤ ተራራን የሚዘለው አጥንቴ እንደ ወንዝ ዳር ቄጤማ ደርሶ ይልፈሰፈሳል፡፡ አሁን ይህን ፍቅር ምን ይሉታል?
ለምን ጠርቼ እንደማልጠግብሽ እንጃልኝ፡፡ እጥልሻለሁ! አነሳሻለሁ! እንደ ጀግና ኒሻን አጌጥብሻለሁ! እንደ ፍቅረኛ ገላ በሀሳቤ አቅፍሻለሁ! እንደ ህጻን ልጅ ቡረቃ አጫውትሻለሁ! እንደ አዛውንቶች የዋርካ ስር ወግ የቡና ቆሎዬን እየቆረጠምኩ፣ በወፎች ዜማ ታጅቤ እተርክሻለሁ፡፡ አድማስሽን በምናብ እጆቼ ዳስሼ፣ ከህመሜ እፈወስብሻለሁ፡፡
---
ደራሲው በቀመረው ሰዋሰው ሲጽፍሽ አንብቤሽ ዓይኔ እንባ እስኪሚቋጥር አጠናሻለሁ! ባለዜማው ሲያንጎራጉርሽ ሰምቼ የልቤን ደጃፎች፣ እንደ ቱርክ ምቹ ምንጣፍ እዘረጋልሻለሁ፡፡ እቴዋ! ለካ የህፃናት የመንገድ ዳር አኩኩሉ ጨዋታ ድምቀቱ፣ የልጆቹ ጩኸት ሳይሆን የአንቺ ሰላም ውሎ ማደር ነውሳ?! የሠርግ ለት ጭፈራ የሚደምቀው በአጃቢዎች እልልታ  ሳይሆን ባንቺ ምርቃት ሲታጀብ ነው፡፡ የሀዘን ቀን ልቅሶ ተረስቶ ህይወት እንደ አዲስ የሚጀምረው በእናትነትሽ ቡራኬ ነው፡፡ የሰማይ አእዋፍና የምድር አራዊት ዳንኪራ፣ የማሳሽ በረከት ነው፡፡ ሽበት ጌጥ የሚሆነው አንቺ ስትመርቂ ነው፡፡ ታዲያ ይህን እያየሁ ፍቅርሽ እስከሞት ቢበረታብኝ ማን ይኮንነኛል?
  ሰአሊው በብሩሽ ሲራቀቅብሽ፣ እኔ በህሊናዬ ሰሌዳ ላይ እየሳልኩሽ፣ በፍቅርሽ ቀለም ላይ እዋኛለሁ! ቀራጺው ድንጋይ ጠርቦ ህላዌነትሽን ፊቴ ለፊቴ ላይ ሲያቆመው፣ በምናብ ዓለም ተሰውሬብሽ፣ አድማሳትን አካልዬ፣ ‹ማን እንዳንቺ› ብዬ እያደገደኩ እዘረጋለሁ፡፡
እናትዋ! አትጠራጠሪ! ጣርያሽ ላይ የማጣት ሸረሪት አድርቶ ቁልቁል ቢመለከተኝም፣ ነገ በጣጥሼው እንደምጥለው አትጠራጠሪ፡፡ ደጃፍሽ ላይ አመድ ሞልቶ አላስኬድ ቢለኝም፣ ነገ ከነሀስ የነጠረ የክብር ዱካ ተጫምቼ፣ ለመጪው ትውልድ አፍ አውጥቶ የሚያወራ ስም ጥዬ እንደማልፍ አትጠራጠሪ፡፡ ምሰሶሽ ተንጋዶ ቤትሽ ‹ልፍረስ ልፍረስ› እያለ አንድ ሐሙስ የቀረው ቢመስልም፣ በማገርሽ ፈንታ አጥንቴን ሰክቼ፤ በጭቃሽ ፈንታ ሥጋዬን አቡክቼ ቤትሽን እንደማጸናው አትጠራጠሪ፡፡ ከአዝመራሽ ገብቶ የዘራሽውን የስንዴ ዘር  የሚለቅመውን አውሬ በነፍሴ ተወራርጄ እንደምገድልልሽ አትጠራጠሪ፡፡ የተራቆተው ገላሽን ለመሸፈን ክር በመርፌ ከትቼ ሳይሆን፣ በእድሜዬ ሰበዝ ነፍሴን ሰፍቼ፣ ዘመኔን እንደምሸልምሽ አትጠራጠሪ! አውድማሽን በከብት እበት ሳይሆን በደሜ ፍሳሽ ለቅልቄ ምድርሽን በመስዋዕትነቴ እቀድሰዋለሁ፡፡ አይጥ ጎተራሽን ነድሎ ጥሪትሽን ሜዳ ሊበትነው ጥርሱን ስሎ መንጋ አጃቢ አስከትሎ እያፏጨ ቢመጣም፣ እሾህን በእሾህ ለመመለስ ሺ ጥበብ ያደለኝ ወዳጅሽ፣ ከጎተራሽ ፊት ሆኜ እዋደቅልሻለሁ!
ዐለሜዋ! ከማድጋሽ ቀድተሸ÷ ከአዝመራሽ ቆርጠሽ÷ ከመሶብሽ አጥፈሽ÷ ከጠቦትሽ አርደሽ “በሞቴ! አፈር ስሆን! አንድ ያጣላል!” እያልሽ ደግሰሽ ያበላሻቸው እኚያ ውለታ ቢስ ጣት ነካሽ ጎረቤቶችሽ፣ ቀን ዘመመ ብለው ፊታቸውን ቢያዞሩብሽ፣ እኔ ግንባሬን ለጥይት ሰጥቼ ድንበር ላይ የምቆምልሽ የወንድም ጋሻሽ ነኝ፡፡
እኔ ያንቺ ወዳጅ፣ የፍቅርሽን ጉርሻ ከድቼ በመከራሽ ሰዓት ስሜ የምሸጥሽ ይሁዳ አይደለሁም፡፡ ገረጣሽ ብዬ ባንዲራሽን በሌላ አልሸቅጥም! ጎበጥሽ ብዬ የታሪክሽን ምርኩዝ አልሰብርም! ከሳሽ ብዬ ያበላኝ መዳፍሽ ላይ ምራቄን አልተፋም፡፡ አሞሽ በተኛሽ  ቀን መኝታሽን እንጥፌ÷ ገላሽን አጥቤ÷ ከጎተራው እሸቱን÷ ከማድጋው ጠላውን÷ ከቀፎው ማር ወላላውን ቆርጬ እጠግንሻለሁ እንጂ እንደ ባዳ ሰው ለመድሃኒት መዋጫ የሻገተ እንጀራ አልሰጥሽም፡፡ ቀን ያገኘ ተባይ ገላሽ ላይ ድብብቆሽ ሲጫወት የጀርባ ላይ ቅማልሽን በእሳት መዳፌ አቃጥለዋለሁ እንጂ የአገልግል ምሳ ልኬልሽ ‹መጥቶ ነበር በሉልኝ› አልልሽም፡፡ ድንኳን ደጃፍሽ ላይ ተተክሎ ወጪ ወራጁ ከንፈር እየመጠጠ ‹መዓት ወረደባት› ሲሉሽ፣ የሀዘንሽን ዳስ ከስሩ መንግዬ እጥላለሁ እንጂ የእዝን እንጀራ አሸክሜ ጓዳሽ አልገባም፡፡   
ልጅሽ ብሆንም እመርቅሻለሁ!
እምዬ ኢትዮጵያ! እድሜሽ እድሜ ይውለድ! ክብርሽ ሰማይ ይንካ! ባንዲራሽ ምድርን ያድምቅ! ህዝብሽ ደምቆ ይፍካ! እጅሽ ሙሉ ይፍስ! እግርሽ ጸንቶ ይኑር! ስምሽ ሞገስ ያግኝ! ጆሮሽ እልልታን ይስማ! ፈጣሪ አብሮሽ ይስራ! ልጅሽ ወጥቶ ይግባ! ወንዝሽ በዝቶ ይፍሰስ! ተራራሽ ጠላት ይምታ! ሜዳሽ እህል ይሙላ! በባእድ ሀገር ያለው ቀና ብሎ ይሂድ! ጥሪትሽ ላይ በላዩ ይብዛ! መሶብሽ ላይ ለምለም እንጀራ አይጥፋ! ድንበርሽ በእሳት ይታጠር! መሀልሽ በገነት ደስታ ይሙላ! ድምቅምቅ በይልኝ እምዬ ኢትዮጵያዬ!


Read 1957 times