Saturday, 27 November 2021 13:38

የ42 ቤተሰቦችን ሕይወት የታደገ በጎ ተግባር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የአርባ ሁለት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ የአሞስ አባወራና እማወራዎችን ህይወት የለወጠ፣ ለዓመታት የዘለቀ የጉስቁልናና የስጋት ኑሮአቸውን የቀየረ ተግባር በሃይኒከን ኢትዮጵያ መከወኑን ሰማንና ወደ ስፍራው አቀናን። በተለምዶ ቀጨኔ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ኑሮአቸውን መስርተው ዓመታትን የዘለቁት እነዚህ አምስት የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች  ከእነ አርባ ሁለት ቤተሰቦቻቸው፣ በዕድሜ ብዛት አርጅቶ በፈራረሰና በወላለቀ ቤት አይሉት ጉሮኖ ውስጥ ሕይወታቸውን ሲገፉ ኖረዋል።
ሃይኒከን ኢትዮጵያ፤ ይህንን ከዛሬ ነገ ቤቱ በላያችን ላይ ይፈርስብናል በሚል ስጋት ተጨንቀው በሰቀቀን ውስጥ የሚኖሩትን አባወራዎች እምባ ለማበስና ስጋት ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባር በመከወን የአምስቱን አባወራዎች ቤት አፍርሶ፣ ባለ 3 ፎቅ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ቤት ሰርቶ በነጻ በሚያስረክብበት ዕለት ነበር ከስፍራው የተገኘነው።በዕድሜ  ብዛት ፈራርሶ ሊወድቅ ባዘመመው በዚህ “ቤት” ውስጥ ለዓመታት ከኖሩት  እማወራዎች መካከል አንደኛዋ ወ/ሮ ታዛ ትረፍ ናቸው። እኚህ እናት እንደሚናገሩት፤ በዚህ አሮጌና የፈራረሰ ቤት ውስጥ ለዓመታት ኖረዋል። ልጆች ወልደው ያሳደጉትም በዚህ ጎጆ  ውስጥ ነው፤ ከዛሬ ነገ ቤቱ በላያችን ላይ ፈረሰ፤ ከነልጆቼ ይፈጀኝ ይሆን የሚል ፍራቻና ስጋታቸው አብሮአቸው ዓመታትን አስቆጥሯል።
ወ/ሮ ታዛ ስድስት የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ይዘው የሚኖሩባት ይህቺ ደሳሳ ቤት፤ ከማርጀቷ የቤቷ ጥበት መፈናፈኛ አሳጥቷቸው መኖራቸውንም ይናገራሉ። አምስት ካሬ ሜትር በማትሞላ ቤታቸው ለዓመታት ሲኖሩ ልጆቻቸውን ከአልጋቸው ስር ለማስተኛት ተገደው ህይወታቸውን መግፋታቸውንም ይገልጻሉ። “ተመስገን ዛሬማ ልጆቼ ከአልጋ ስር ወጥተው አልጋ ላይ ሊተኙልኝ ነው” ይላሉ፤በደስታ ተውጠው። ሃይኒከን ካሰራው ባለ 3 ፎቅ ህንጻ እኚህ ሴት 64 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሳሎን ሁለት የመኝታ ክፍሎች፣ መፀዳጃ ቤትና ኩሽና ያለው ቤት ተረክበዋል። ይህ ዳግም የመፈጠር ያህል ነው- ይላሉ ስለ ሁኔታው ሲናገሩ።በእድሜ ብዛት ፈራርሶ ሊወድቅ የተቃረበውና በጭቃና በእንጨት የተሰራው ይኸው አሮጌ ፎቅ ፈርሶ በቦታው ላይ ባለሶስት ወለል  ዘመናዊ ህንፃ በመስራት ለነዋሪዎች ያስረከበው ሃይኒከን ኢትዮጵያ፤ ባለፈው ዓመት ከረዩ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ 53 ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶችን አስገንብቶ ለነዋሪዎቹ ማስረከቡ የሚታወስ ነው። በመጪው ዓመትም በጨርቆስ አካባቢ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን ለመርዳት ዕቅድ እንዳለውም የሃይኒከን
 የውጪ ግንኙነት ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ በሻህ ተናግረዋል።

Read 1279 times