Thursday, 25 November 2021 06:38

እምብዛም የማናውቃቸው የህወሐት ጄኔራሎች

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(2 votes)

    በ1983 ዓ.ም ሕዝቢ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ደርግን ጥሎ ሥልጣን ከያዘ በዃላ የቀድሞው ሰራዊት “የደርግ ወታደር” የሚል ታርጋ ተለጥፎለት ተሸማቅቆ እንዲበታተን ተደርጓል። በምትኩ አሸናፊዎቹ የሕወሓት ተዋጊዎች ወደ መደበኛ ሰራዊትነት ተቀይረው ላለፉት 27 ዓመታት የሀገሪቱ ወታደራዊና የደህንነት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተቆጣጥረው  ቆይተዋል። በመገናኛ ብዙኃን ሲገለፁ የሚሰሙት የማዕረግ እድገቶችም አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች የአንድ ቀዬ ልጆች የሚመስሉ ሰዎች ነበሩ። በእነዛ ዓመታትም ከብርጋዴር እስከ ሙሉ ጄኔራል የደረሱ በመቶ የሚቆጠሩ የሰራዊት አባሎችን ማፍራት ተችሏል። አንዳንዶቹ በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል በተለያዩ የአዛዥነት ደረጃዎች ላይ ቢሰሩም፣ በሕዝብ ዘንድ የታወቁ ናቸው ለማለት ያስቸግራል። እንደውም ከሙያቸው ይልቅ ሀብት በማጋበስና ውድ በሚባሉ ቦታዎች ሕንፃ ገንብቶ በማከራየት በሰፊው የሚታሙ ነበሩ፡፡ ይፃፍ አይፃፍ ባልታወቀ ሕግ የመከላከያና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች አመታዊ ዕቅድ አፈፃፀም ፓርላማ ቀርቦ ውይይት አይደረግበትም። ፓርላማው ጥርስ ባይኖረውም ለምክር ቤቱ ሪፖርት አለማድረጋቸው የሚታሙበት ሙስና እንዲንሰራፋ በስሱም ቢሆን አስተዋፅኦ ማድረጉ አልቀረም። ቀጥሎ እንደምናየው ሀሜቱ ከባዶ አየር የተነነ አይደለም።
በሙያዊ ክህሎታቸው፤ በትምህርት ባዳበሩት ዕውቀትና በተፈጥሮ በታደሉት ግልፅ ሰብዕና በሕብረተሰቡ ዘንድ እውቅና ካላቸው መካከል በየካቲት 1988 ጀሚል ያሲን በተባለ ግለሰብ የተገደሉት ሜጀር ጄኔራል ሓየሎም አርዓያ፤ ሜጀር ጄኔራል ፃድቃን ወልደትንሳይና በከፊልም ቢሆን ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) ይጠቀሳሉ። በሌላም በኩል አስቸጋሪ በሆነ ሽግግር ወቅት ላይ ከቤታቸው ሆነው ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እያሉ በጠባቂያቸው የተገደሉት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የሕዝቡን ከበሬታ አግኝተዋል። በርግጥም ተሰውተዋል።
 ሌሎች እስከ ሊውተናንት ጄኔራል ደረጃ ያላቸው መኮንኖች በስምም ሆነ በገፅታ ለሕብረተሰቡ እንግዳ ናቸው። በማዕረግ እድገት ስማቸውን ስንሰማው የነበሩ መኮንኖች፣ ከትግራዩ ጦርነት ጋር ተያይዞ  በነዛው መገናኛ ብዙኃን በተፈላጊነት ሲጠሩ አድምጠናል። ሰዎቹ እጅ ሰጥተው ራሳቸውን ካላሳወቁ በስተቀር የመንግሥት አካላት ስለ ማንነታቸው እርግጠኛ አይመስሉም።በደህንነት አካላት በሚወጣው መግለጫ ስማቸው ሲምታታ ይታያል። በመንግሥት የሚተዳደሩትን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሕይወት ያሉትን እንደተደመሰሱ፤  ያልተያዙትን እንደተያዙ አድርጎ የሚወጣው ለቅስቀሳ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ሰዎቹንም ካለማወቅ የተነሳ ነው። አሁን ዘመናዊ መገናኛ በተስፋፋበት ወቅት ያሉት ጄኔራሎች በደርግ ጊዜ የነበሩትን ሻለቆችም ሆነ ሻምበሎች ያህል እንኳ አለመታወቅ ከሕብረተሰቡ የራቁበትን ደረጃ ያሳያል። ባለፉት ወራት በተፈላጊነት ሲጠሩ ከነበሩት ጥቂቶች እጅ ሲሰጡ የተወሰኑት ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ሌሎች ደግሞ ትግራይ በመግባት ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የሚያካሂደውን ጦርነት በመምራት ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም ይህን ይመስላሉ፡-
 
1.ሜጀር ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳይ
ሜጀር ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳይ ቀድሞ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩ ሲሆን በሕወሓት ውስጥ ክፍፍል ከተፈጠረ በዃላ ቦታቸውን ለጄኔራል ሳሞራ የኑስ አስረክበዋል። ከዛም የእንግሊዝ መንግሥት እየከፈላቸው በደቡብ ሱዳን በአማካሪነት ሰርተዋል። በዃላም ወደ ንግዱ በመግባት ራያ ቢራን ካቋቋሙት መካከል አንዱ ሆነዋል። በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያም ጥናታዊ ፅሁፎችን በጋዜጦችና በተለያዩ መድረኮች ያቀርቡ ነበር።
 በኢትዮጵያ መንግሥትና በአማፂያኑ ሃይሎች መካከል ጦርነት ሲነሳ አዛዥ እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቃቸው አሌክስ ደዋል ዘግቧል። የሕወሓት መገናኛ ብዙኃን ግን “የሴንትራል ኮማንድ አባል” ማለትን ይመርጣሉ። የ68 ዓመቱ ፃድቃን በዩኒቨርሲቲ ይከታተሉት የነበረውን የባዮሎጂ ትምህርት አቋርጠው ሕወሓትን እንደተቀላቀሉ ይነገራል።

2. ሊውተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ (ወዲ ወረደ)
 በ1951 ዓ.ም መቀሌ ከተማ እንደተወለዱ የሚነገርላቸው ወዲ ወረደ በመከላከያ ሚኒስቴር የሥልጠና ክፍል ሃላፊ የነበሩ ሲሆን በሱዳን የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሃይል አዛዥ በመሆን ለሁለት አመታት ያህል አገልግለዋል።የተባበሩት መንግሥታት ጦር ወታደራዊ ቆብ ጭነው ከባን ኪ ሙን ጋር የተጨባበጡባቸው ቀናት የሩቅ ትዝታ ሆነዋል። ከ30 ዓመታት የምቾት ኑሮ በኋላ በረሃ መውረድ ቀላል ፈተና አይደለም። አሁን እንደ አዛዥ መግለጫ የሚሰጡት እሳቸው ናቸው። ከእስር ማዘዣ በተጨማሪ ንብረታቸው እንዲታገድ ከተወሰኑባቸው መካከል ይገኙበታል።

3. ሊውተናንት ጄኔራል ብርሃነ ነጋሽ (ወዲ መድህን)
 ፈረስ ማይ አካባቢ የተወለዱት ወዲ መድህን የመከላከያ ምህንድስና መምሪያ ሃላፊ ነበሩ። በአድዋ ንግሥተ ሣባ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ነው በ1968 ዓ.ም ሕወሓትን የተቀላቀሉት። የኤርትራ ሃይሎች ምፅዋን ለማስለቀቅ ባደረጉት ጦርነት፣ ክፍለ ጦር ይዘው ከሻቢያ ጎን መሰለፋቸው ይነገራል። ከሰራዊቱ በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ የመከላከያ ሚኒስቴር ደኤታ ሆነው አስር ዓመት ያህል አገልግለዋል።
4.ሜጀር ጄኔራል ዮሃንስ ወልደጊዮርጊስ (መዲድ)
ዮሃንስ ወልደ ጅወርጊስ በሚለውም ስም ይታወቃሉ። ትውልዳቸው አክሱም ሲሆን 60ኛ ዓመታቸውን ደፍነዋል። በትጥቅ ትግል ላይ ሜይ ዴይ የተባለ ክፍለጦር ይመሩ ነበር።  ሕወሓት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በሆለታ ጦር አሰልጣኝነት፤ በሰሜንና ምእራብ እዝ ምክትል አዛዥነት እንዲሁም ሶማሊያ የዘመተው ጦር አመራር አባል በመሆን ተሳትፈዋል። በኋላም የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነበሩ። አሁን ተመልሰው የትጥቅ ትግሉን እንደ አዲስ ጀምረዋል።
 
5.ብርጋዴር ጄኔራል ተክላይ አሸብር (ወዲ አሸብር)
ወዲ አሸብር በአሁኑ ሰዓት አመራር እየሰጡ ከሚገኙት አንዱ ናቸው። በፊት በደሴ ቡሬ ግንባር የልዩ ጦር አዛዥ ነበሩ። አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ ሶስት የሚገኘው ብሌን ሕንፃ ባለቤት ናቸው። ነገር ሸትቷቸው እንደሆነ ባይታወቅም በውክልና ነበር ስራውን የሚያካሂዱት። ሕንፃው በርካታ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ድርጅቶች ተከራይተውታል። ከእስር ማዘዣው በተጨማሪ ንብረታቸውም ላይ እግድ ወጥቷል።
 
6.ብርጋዴር ጄኔራል ምግበይ ሃይለ
ብዛና በተባለ የቀድሞ አክሱም አውራጃ የተወለዱት ምግበይ ሃይለ፣ ሕወሓትን የተቀላቀሉት በ1971 ነው። ለውጡን ተከትሎ በ2011 በጡረታ ተገልለዋል። በአሁኑ ወቅት በአመራር ሰጪነትና በአሰልጣኝነት እየሰሩ ይገኛሉ። በአዲስ አበባና በመቀሌ ቪላዎችን ገንብተዋል። መንግሥት በሁለቱም ላይ እግድ አውጥቷል።
 7.ሜጀር ጄኔራል አብርሃ ተስፋይ (ድንኩል)
በሶማሊያው የአፍሪካ ሕብረት ጦር አመራርነት የተሳተፉት የ56 ዓመቱ መኮንን፤ በአሁኑ ወቅት የትግራይን ሃይል ከሚመሩት መካከል ናቸው። የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አብርሃ ተስፋይ የብላቴ ማሰልጠኛ ሃላፊ ሆነውም ሰርተዋል።
 
8.ብርጋዴር ጄኔራል ኃይለሥላሴ ግርማይ (ወዲ ዕምበይተይ)
በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የተወለዱት ወዲ ዕምበይተይ፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽሬ ተከታትለዋል። ሕወሓት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በሰሜን ሸዋና  በአንዳንድ የጎጃም ክፍሎች በነበሩ ጦርነቶች ተሳትፈዋል። ከስታፍ ኮሌጅ ዲግሪ እንዳገኙ የሚናገሩት ኃይለሥላሴ ግርማይ፤ በካርቱም አገናኝ መኮንን ሆነውም ሰርተዋል። በጡረታ ተገልለው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጦርነት ከአመራር ሰጪዎች አንዱ ናቸው። ያለምንም ተቀናቃኝ ሰተት ብለው ጦር እየመሩ ደሴ መግባታቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል። የአራት ልጆች አባት የሆኑት ዕምበይተይ፤ ሀብት በማጋበስ ስማቸው በተደጋጋሚ ከሚነሳ የህወኃት ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው፡፡ የንብረት ዕገዳው እሳቸውንም አካትቷል።
9.ሜጀር ጄነራል ዘውዱ ኪሮስ
በኢትዮጵያ ታሪክ ለሜጀር ጄኔራልነት የበቁ የመጀመሪያ ሴት  መኮንን ናቸው። በ1972 ሕወሓት አቢ አዲን ሲቆጣጠር ነው ድርጅቱን የተቀላቀሉት። ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ኪሮስ፤ በሱዳን የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሃይል ምክትል አዛዥ ሆነውም ሰርተዋል። አሁን ጦርነቱ ላይ ከሕወሓት ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው።
 
10. ሜጀር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ
 የኢትዮጵያ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ(ኢመደኤ) ሃላፊ ነበሩ። ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር በቅርበት ሰርተዋል። ምናልባትም ሁለቱም በማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ አብረው ሳይማሩ አልቀሩም። የአራት ልጆች አባት የሆኑት ተክለብርሃን እርስበርስ በሚጋጩ አነጋገሮቻቸው ይታወሳሉ። ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት፡  “የትግራይ ህዝብ ቀጣይ ጥቅሙና እድሉ አሁን እየተመሰረተች ባለችው ኢትዮጵያ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የትግራይ ህልውና የሚባል ነገር ለይተን ማየት አንችልም” (ውራይና መፅሔት)። ከሥልጣን ሲነሱ፡ “እኛ በመታገላችን ምክንያት ለኢትዮጵያ የተረፈ ትሩፋት ሊኖር ይችላል። ዓላማችን ግን ኢትዮጵያ አልነበረችም” (ትግራይ ሚዲያ ሃውስ)። ትምህርታቸውን ከስድስተኛ ክፍል አቋርጠው ሕወሓትን የተቀላቀሉት በ1972 ዓ.ም ነው። በ1983 ለውጡ ሲመጣ በመከላከያ ውስጥ በመረጃ ሰራተኛነት ቀጥሎ የቴክኒካል መረጃ ሃላፊ ከዛ ኢመደኤ  በ1999 ሲቋቋም ሃላፊ ሆነው በአቶ ተመስገን ጥሩነህ እስከተተኩበት 2011 ዓ.ም ድረስ መሥሪያ ቤቱን መርተዋል። የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ዋልደን ከተባለ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዳገኙ ይናገራሉ። በሃላፊነታቸው ጊዜያት ሃገሪቱን ከዘመናዊ መረጃ አውታሮች ጥቃት መከላከል ቀርቶ የመሥሪያ ቤቱንም መረጃዎች ማዳን አልቻሉም። የስለላ መተግበሪያ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጋር ያደረጉት መልዕክት ልውውጥ፥ የሰራተኞች ስምና የይለፍ ቃሎች ሳይቀር ተበርብረው በድረገፆች ላይ ተለቅቀዋል።
 
11. ሜጀር ጄኔራል ገብረ ኣድሃና (ገብረ ዴላ)
ቀድሞ እንደርታ አውራጃ በሚባለው የደቡብ ትግራይ ክፍል ዴላ በምትባል የገጠር ከተማ የተወለዱት ገብረ ኣድሃና፤ ሕወሓትን የተቀላቀሉት በ1972 ነው። በተዋጊነት በቆዩባቸው አመታት በአብዛኛውን በከባድ መሣሪያና የእግረኛ ሰራዊት ክፍል ነው የሰሩት። ሁመራ፥ ደብረታቦር፥ ነፋስ መውጫ ከዋሉባቸው ግንባሮች መካከል  ይጠቀሳሉ። ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው የሚናገሩት ጄኔራሉ፤ የወታደራዊ ደህንነት ክፍል ሃላፊ ነበሩ። አልሸባብን ለመውጋት ሞቃዲሾ ዘምተዋል። በሱዳን የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሃይል አዛዥ ሆነውም ሰርተዋል። የ58 ዓመቱ መኮንን በትግል ጊዜ ከተገናኟት የህክምና ባለሙያ ባለቤታቸው ሁለት ልጆች ሲያፈሩ፣ በ2010 በጡረታ ተሰናብተዋል።
 
12. ሊውተናንት ጄኔራል ፍሰሃ ኪዳኑ (ማንጁስ)
በ1957 ዓ.ም እንደተወለዱ ይናገራሉ። በግብርና ከሚተዳደሩ ቤተሰቦች ከ11 ወንድምና እህቶች ጋር ነው ያደጉት። በመከላከያ ስር ከሚገኘው ስታፍ ኮሌጅ ተመርቀዋል። የምዕራብ እዝ አዛዥ ሆነው የሰሩት ማንጁስ፤ ጥሎባቸው ከገንዘብ ጋር አይተጣጡም። ቦሌ ክፍለ ከተማ ግሩም ቪላ ሰርተው ለስዋዚላንድ ኤምባሲ በዓመት 66 ሺህ ዶላር ያከራዩት ያኔ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር። በዛ ላይ ደግሞ መንግሥት በአሜሪካ የሚሊታሪ አታሼ አድርጎ ሾማቸው። ቀድሞ በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪነት መሳተፋቸው ሳይዘነጋ ማለት ነው። የሊውተናንት ጄኔራልነትን ማዕረግ ከፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ተቀብለው ድግሱንም ባግባቡ ሳያወጡ፣ ከወራት በኋላ ከሃላፊነት ተነስተዋል። በቅርቡም መንግሥት ከእስር ማዘዣ በተጨማሪ የንብረት እግድ አውጥቶባቸዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት አስሩ በተለያየ ደረጃ በጦርነቱ እየተሳተፉ ሲሆን የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ከብርሃን ርቀዋል። ማንጁስ አታሼ ስለነበሩ አሜሪካ መቀመጫ አመቻችተው ይሆናል።



Read 6635 times