Monday, 22 November 2021 00:00

የጋዳፊ ልጅ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደሩ ተቃውሞ ገጠመው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      የፊሊፒንሱ መሪ ከልጃቸው ጋር ላለመፎካከር በምርጫ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ

                          በቀጣዩ ወር በሚካሄደው የሊቢያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ፣ በአገሪቱ ወታደራዊ አቃቤ ህግ በወንጀል ስለሚፈለጉ በምርጫው መወዳደር የለባቸውም የሚል ተቃውሞ እንደገጠማቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በደቡባዊ ሊቢያ በምትገኘው ሴብሃ ከተማ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት የ49 አመቱ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በመፈጸማቸው ጉዳዩ ተጣርቶ ብያኔ እስኪሰጥ ድረስ ከምርጫው ይታገዱ ሲል የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለምርጫ ኮሚሽን አቤቱታ እንዳቀረበባቸው ነው ዘገባው የገለጸው፡፡
አቃቤ ህግ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከሚፈለጉት የጋዳፊ ልጅ በተጨማሪም በፕሬዚዳንትነት ሊወዳደሩ የተዘጋጁትና በአሰቃቂ ወንጀሎች የሚጠረጠሩት የምስራቃዊ ሊቢያ አማጺ ጦር አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ካሊፋ ሃፍታርም ከምርጫው እንዲታገዱ መጠየቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
አባቱ ሙአመር ጋዳፊ በ2011 በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተከትሎ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውሎ ከስድስት አመታት እስር በኋላ የሞት ፍርድ የተላለፈበትና ፍርዱ ተፈጻሚ ሳይሆን የቀረው ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ፣ ከሰሞኑ በፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደር በይፋ ማስታወቁ በጎም መጥፎም ምላሽ እንዳገኘ ዘገባው ገልጧል፡፡
ከጋዳፊ ሞት ማግስት ጀምሮ በጊዜያዊ መንግስት ስር ሆና ወደከፋ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ የገባችው ሊቢያ፣ በቀጣዩ ታህሳስ ወር ከቀውስ ያወጣታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡
በሌላ የምርጫ ዜና ደግሞ፣ የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱሬቴ በመጪው አመት በሚካሄደው የአገሪቱ ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ከምትወዳደረው ልጃቸው ሳራ ዱሬቴ ጋር ላለመፎካከር ሲሉ በምርጫው እንደማይወዳደሩ በይፋ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዱሬቴ ምንም እንኳን በአገሪቱ ህገመንግስት መሰረት ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር ባይችሉም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር አስበው የነበረ ቢሆንም ልጃቸውን ላለመጋፋት ሲሉ ሃሳባቸውን መሰረዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሰውዬው ከወራት በፊት ባደረጉት ንግግር  ከፖለቲካው ራሳቸውን እንደሚያገልሉ አስታውቀው  እንደነበርም አስታውሷል፡፡

Read 2750 times