Saturday, 20 November 2021 14:25

የህወኃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ንፁሀን ላይ በስፋት ግድያ ፈፅመዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በሐምሌና ነሐሴ 2013 ወር  የህወኃት ታጣቂዎች በወረሯቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች 184 ንፁሃንን መግደላቸውን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት በህወኃት ታጣቂዎች ከተገደሉት 184 ንፁሃን መካከል 150 ያህሉ “ለፌደራል መንግስት ታግዛላችሁ፤ መረጃ ታቀብላላችሁ” በማለት የረሸናቸው መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የህወኃት ወረራ በሃይል ተቆጣጥሯቸው በነበሩ ጥቂት የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው በዚህ ማጣራት፣ ታጣቂዎቹ ከመንግስት ጋር ትሰራላችሁ ያሏቸውን ሰዎች በከተማም በገጠርም ሲገድሉ እንደነበር ሪፖርቱ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
“የቆሰሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን በቤታችሁ ደብቃችሁ ተንከባክባችኋል” በሚል ምክንያት  በታጣቂዎቹ የተገደሉ እንዳሉም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በዚህ የህወኃት ታጣቂዎች የሰላማዊ ሰዎች ግድያ  “ለመንግስት ትሠልላላችሁ” በሚል በጎዳና ላይ የሚኖሩ የአዕምሮ ህሙማንንም  መገደላቸውን የኢሠመኮ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በነዚህ የህወኃት ታጣቂዎች ቀደም ሲል ይዘዋቸው በነበሩ እና ኋላም በመከላከያ ሠራዊት ተመትተው በለቀቋቸው አካባቢዎች ፈፅመዋቸው ከነበሩ የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋ ባሻገር አሁንም በሃይል በወረሯቸው አካባቢዎች ከወትሮ የከፋ ጭፍጨፋ እየፈፀሙ መሆኑን በመንግስት በኩል እየተገለፀ ይገኛል፡፡
ከንጹሃን ሰዎች ግድያ ባሻገር ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር ድርጊት በስፋት መፈፀሙን የጠቆመው የኢሠመኮ ሪፖርት፤ በዚህ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል  ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል አንዲት ከተማ ብቻ የታጣቂው ሃይሎች ከ70 በላይ ሴቶች ላይ አስገድዶ ጥቃት መፈፀማቸውን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ሰሞኑን በመከላከያ ቁጥጥር ስር የዋሉ የህወኃት ምርኮኞች ለመንግስት ቴሌቪዥን በሰጡት ቃል፣ “አማራን ጨፍጭፉ፣ዝረፉ፣ አውድሙ፣ሴቶቹን ድፈሩ እያሉ ነው የሚልኩን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ያንንም ሲፈፅሙ እንደነበር በአንደበታቸው አረጋግጠዋል፡፡

Read 10979 times