Monday, 15 November 2021 00:00

እውነት በሦስት መነፅር

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 • በጋዜጠኝነት፣ በዳኝነት፣ በእውቀትና በትምህርት ሦስት መሠረቶች።
 • እውነቱን እንነጋገር፤ ሙሉውን እውነት፣ እና እውነትን ብቻ! (ይሄ ለፍ/ቤት ምስክሮች ነው)።
  • Relevance,Completeness, Accuracy…(የጋዜጠኝነት መርሆች) ናቸው።
            
             ሃሳብንና ንግግርን፣ መረጃንና ትምህርትን፣ እንዴት እናስተናግዳለን?
በአስተዋይነት፣ ከእውኑ ዓለም ጋር አመሳክረን እውነትነቱን ለማረጋገጥ፣ አነፃፅረንም ትክክልነቱን ለመገንዘብ እንጥራለን?
እውነትን ከሚበርዙ ግንዛቤን ከሚበክሉ፣ ከውሸትና ከስህተት የፀዳ መሆኑን እናጣራለን?
እውቀትን እንዳያዛባና ትኩረትን እንዳይበትን፣ አንኳር ጉዳይን እንዳይዘነጋና ቁምነገርን እንዳያጓድል፣ ምሉዕነቱን ጠንቅቀን በቅጡ ለመረዳት እየመረመርን እናሰላስላለን?…
ቀላል ጥያቄ ይመስላል።እውነትንና ውሸትን፣ ትክክልና ስህተትን ለይተን ለማወቅ፣ ከምር ከልብ ደንታ አለን? ቀላል ስራ አይደለም። በእርግጥ፣ “መረጃ” ሞልቶ ተትረፍርፏል። የመረጃ ዘመን ነው። ነገር ግን፣ ዓለማችን በ”መረጃ”  ተጥለቀለቀ ማለት፣ ስራ ቀለለ ማለት አይደለም። ለእውነት የመታመን ፅኑ ስነምግባርና ስልጡን ባሕል ከሌለ፣ ምን ዋጋ አለው?
እውነተኛ መረጃ በእጥፍ ሲበረክት፣ የውሸት መረጃ መቶ እጥፍ የሚባዛ ከሆነ፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይከፋል። ወሬ በበዛበት ዘመን፣ የትኛው እውነት የትኛው ውሸት እንደሆነ ማወቅ፣ እጅግ ከባድ ስራ ሆኗል። አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ የማይቻል የማይሞከር ስራ እየመሰለ ነው - እውነትን ማግኘትና እውነትን መመስከር። መዘዙ ደግሞ ብዙ ነው። እውነት የሁሉም ነገር መሠረት ነዋ።
ከስነምግባር መርሆች መካከል በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ አትርሱ - “እውነት፣ መንገድና ሕይወት” የሚለውን ትምህርት አስታውሱ። “አትዋሽ፣ እውነትን ተናገር” የሚል የስነምግባር መርህ፣ የበርካታ ሺህ አመታት እድሜ ባለፀጋ መርህ ነው።
“በሃሰት አትወንጅል፣ በሃሰት አትመስክር” እየተባለም በሕግ መፃሕፍት ውስጥ ተደጋግሞ ተፅፏል። ከሃሙራቢ የመጀመሪያ አንቀፆችና ከሙሴ አስር ትዕዛዛት ጀምሮ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። ቋሚ የሕግ፣ የዳኝነትና የፍትህ መርህ ነው። ከእውነት ውጭ፣ የሕግ ዳኝነት ሊቃና፣ ፍትህ ሊፈፀም አይችልም።
እና ምን ትላላችሁ? ለእውነት ደንታ አለን? የነጠረውንና የተዘባረቀውን፣ የተጓደለውንና የተሟላውን፣ የተበረዘውንና የጠራውን እውነት፣ ለይተን እንመሰክራለን ወይ?
ለፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን ለመስጠት የሚቀርቡ ሰዎች፣ እውነትን የመናገር ፍላጎት ባይኖራቸው አስቡት። ደንታ ማጣት ሲለመድ፣ እውነትን የመመስከር ሃላፊነትና ግዴታም ሲላላ፣ ነገሩ ሁሉ፣ ከንቱ ብክነት፣ ቀሽም ድራማ ከመሆን አያልፍም። ከብክነትና ከድራማነት ካለፈም፣ ንፁህ ሰዎች ያለጥፋታቸው የቅጣት ሰለባ ይሆናሉ - በክፉ ሰዎች ጭፍን ጥላቻ እየተጠለፉ፣ በሐሰት ውንጀላና በሐሰት ምስክርነት ይፈረድባቸዋል። ተጎጂ ሰዎች ያለ ካሳና ያለ ፍትህ የጥቃት ሰለባ ይሆናሉ። ለአጥፊ ወንጀለኞች ይመቻቸዋል- በሐሰት ምስክርነት ወንጀለኞች ከዳኝነት እያመለጡ።
ለዚህም ነው፤ የሃሰት ውንጀላ ብቻ ሳይሆን፣ የሐሰት ምስክርነት፣ ከወንጀል ተርታ የሚመደበው። የሚያስቀጣም ነው። ምን ማለት ነው? ለፍርድ ቤት የምስክርነት ቃል የሚሰጥ ሰው፣ እውነትን የመናገር ግዴታ አለበት።
“የነጠረ እውነት”
“እውነትን መናገር´ ማለት ግን፣ የጓዳና የጓሮውን መዘክዘክ፣ የባጥ የቆጡን “መረጃ” መናገር ማለት አይደለም። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያተኮሩና ተዛማጅ መረጃዎችን በትክክል መናገር ማለት ነው - እውነትን መናገር ማለት።
“እውነቱን ያውጣ፣ እውነቱን ይናገር” ብለዋል የአገራችን አበውና እመው። (የፆታ አድልዎን ማስቀረት ይሻላል ብዬ ነው። የጥንት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ እናቶችም፣ ብልህነትን አስተምረዋል፣ ምክርን አበርክተዋል።) እውነትና እውቀት፣ የፆታ ጉዳይ ሳይሆን፣ የአስተዋይነትና የአዋቂነት ጉዳይ ነው።
እናም፣ የአገራችን አዋቂዎች፣ “እውነት ይውጣ” ከማለት ይልቅ፣ “እውነቱ ይውጣ” ብለው መናገራቸው አለምክንያት አይደለም። “እውነት ይነገር” ከማለት አልፈው፣ “እውነቱ ይነገር” ብለዋል። ከአዋቂዎች የመነጨ አባባል ነው። እውነትን መናገር ማለት፣ በዋናው ጉዳይ ላይና በተዛማጅ ነገሮች ዙሪያ ላይ በትክክል አተኩሮ፣ እውነትን መናገር ማለት እንደሆነ አስተምረዋል - የአገራችን አዋቂዎች።
በፈረንጅ አገራትም፣ ይህን ያስተማሩ አዋቂዎች፣ “the truth” የሚለውን አባባል ተጠቅመዋል።  
በጋዜጠኝነት ሙያ፣ “Relevance” ከሚለው መርህ ጋር ይቀራረባል። አዳዲስ መረጃዎችን ለአንባቢ፣ ለአድማጭና ለተመልካች የሚቀርብ የዜና ዘገባ፣ ከርዕሰ ጉዳይ መረጣ ጀምሮ እስከ ዝርዝር መረጃዎቹ ድረስ፣ ይህን መርህ የተከተለ መሆን አለበት። ርዕሰ ጉዳዩ ለአንባቢዎቹ ፋይዳ ሊኖረው ይባል። መረጃዎቹ ደግሞ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸው
በርዕሰ ጉዳይ ላይ ያላተኮረ ንግግር፣ አራምባና ቆቦ እየረገጠ፣ ስለ ዝንብና ስለ ዝናብ፣ ስለ ዘምባባና ዝባዝንኬ፣ ያለ ፍሬን ያለ መሪ እየተቅበዘበዘ መቀባጠር፣ ወይ ስካር ወይ ቅዠት እንጂ፣ ቁም ነገር አይሆንም። በጉዳዩ ላይ ያተኮረና በዙሪያው ያጠነጠነ እውነተኛ መረጃ ነው - እውነቱን መናገር ማለት።
“ምሉዕ እውነት”
“እውነቱን መናገር” ማለት፣ ግማሹን አስቀርቶ፣ ግማሹን እውነት ብቻ መናገር ማለት አይደለም። በጋዜጠኝነት ሙያ፣ “Completeness” የተሰኘውን መርህ መጥቀስ እንችላለን።
“እከሌ በፍርሃት እየሮጠ፣ እገሌ ደግሞ በንዴት ሊይዘው እየሮጠ ነበር” የሚለውን ምስክርነት ተመልከቱ። በቁንፅል ሲታይ፣ “እውነተኛና ትክክለኛ መረጃ” ሊሆን ይችላል። የሁለቱን ሰዎች አኳሃን በደንብ ያስተዋለ ሰው፣ ያየውን ይመሰክራል። ማን ከማን ለመሸሽ፣ ማን ማንን ለመያዝ፣ ማን “በፍርሃት”፣ ማን “በንዴት” እየሮጠ እንደሆነ መገንዘብ አያቅተውም።
እገሌ እከሌን ሲያሯሩጠው ሲያሳድደው አይቻለሁ ብሎም ሊመሰክር ይችላል። ውሸት አይደለም።
ነገር ግን፣ እከሌ ለሽሽት የሮጠው ለምንድነው? እከሌ የእገሌን ማጅራት መምታቱና ቦርሳ ቀምቶ ከአካባቢው ለማምለጥ መሮጡስ? ይህን እውነታ ያየ ሰው፣ አይቶ እንዳላየና ምንም እንዳልተፈጠረ፣ መረጃውን ሳይናገር ሲያስቀር፣ ማን በንዴት ማን በፍርሃት እየተሯሯጡ እንደነበሩ ብቻ ሲናገር፣…  እንዲህ አይነት የፍርድ ቤት ምስክርነት፣ እውነቱን በምልዐት አውጥቶ መናገር መመስከር ማለት አይደለም።
እስረኛው፣ “ቁራጭ ገመድ ሰርቀሃል ብለው 10 ዓመት ፈረዱብኝ” ብሎ ማማረሩን ታውቃላችሁ? ቁራጭ ገመዱ ጫፍ ላይ፣ በሬ ታስሮበት ነበር። ይህን ሳያውቅ ነው ገመዱን ሰርቆ የወሰደው? በሬውንም ጭምር?
እውነቱን መናገር ማለት፣ በዋና ጉዳይ ላይና በዙሪያው ላይ በማተኮር እውነትን መናገር፣ ከዚህም ጋር፣ ቁምነገርን ሳያጓድሉ አሟልተው እውነትን መናገር ማለት ነው።
ሰነጣጥቆ ሸርፍራፊ ብቻ መናገር አይደለም - እውነቱን መናገር። እየቆነጠሩና እያጎደሉ ሳይሆን፣ ሳይደብቁ ሳይሸሽጉ፣ በምልዓት በግልጽ አውጥቶ መናገር ነው - እውነቱን መናገር (“the whole truth” እንዲሉ)።
የጠራ እውነት
“እውነቱን በምልዓት” መናገር ማለት፣ የባጥ የቆጡን ሳይቀባጥሩና ቁምነገርን ሳያጓድሉ መናገር ማለት ብቻ አይደለም።
Accuracy  ከተሰኘው የጋዜጠኝነት መርህ ጋር ይዛመዳል። ለምሳሌ መረጃዎችን ከሁለት ከሦስት ምንጮች ማጣራት የግድ ነው።
እውነታውን የሚበክል፣ የሚበርዝና የሚያዛባ የሐሰት ወሬን ሳይጨምሩ መናገር ያስፈልጋል። ከጭፍን ምኞትም ሆነ ከምናብ ፈጠራ የፈለቀ ሃሳብን እንደ እውነተኛ መረጃ አስመስሎ ሳይወሰልት፣ ሐሰትን ሳይጨምር እውነትን ይናገራል - የእውነት ምስክር።
በአጠቃላይ፣ እውነቱን አንጥሮ፣ አሟልቶና አጣርቶ መናገር ማለት ነው - እውነትን መናገር ማለት።
ዝባዝንኬ ሳይቀባጥር በጉዳዩ ላይ ያተኮረ የነጠረ እውነትን፣
ቁምነገርን ሳያጓድል የተሟላ እውነትን
ሐሰትን ሳይቀላቅል የጠራ እውነትን።         
ለዚህም፣ በውጭው ዓለም፣ ለምስክርነት ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎች፣ “the truth, the whole truth, nothing but the truth”… የሚል አባባልን በመጠቀም፣ ቃል ይገባሉ።
ይሄ መመዘኛ፣ የሃሳብና የንግግር፣ የእውቀትና የትምህርት ጉዳዮች ሁሉ ላይ ይሰራል። የእውቀትና የትምህርት “ዘርፎች”፣ በጣም አስፈላጊ የሚሆኑት ለምን ሆነና!
አንደኛ ነገር፣የትምህርት ወይም የእውቀት ዘርፎች፣ ጉዳያቸው (ስኮፓቸው) በትክክል መታወቅ አለበት - በዝባዝንኬ ተቀብረው እንዳይቀሩ፣ በጉም ባክነው እንዳይጠፉ፣ “ጭብጥ” እንዲኖራቸው።
ሁለተኛ ነገር፣ የእውቀት እንዲሁም የትምህርት ዘርፎች፣ ቅጥ ያለው መዋቅር (Structure) አላቸው። ሊኖራቸው ይገባል።  የእውቀት ዘርፍ፣ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮችን ማሟላቱን፣ በተዋረድ፣ በእርከን፣ በቅደም ተከተል አሰናስሎ ማደራጀቱን  ማረጋገጥ ያስፈልጋልና። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን፣ ያንን በምልዓት ያሟላ መሆን አለበት።
ሦስተኛ ነገር፣ የዕውቀት ዘርፎች፣ የእውቀት ዘዴ አላቸው (Methodology):: እንደየዘርፋቸው ተስማሚና ተገቢ የሆነ ሳይንሳዊ ዘዴማለት ነው። በዚህ ዘዴ ተፈትሾ፣ ተፈትኖ ያላለፈና ያልተጣራ መረጃ፣ በዘፈቀደ እንዳይካተትና እውቀትን እንዳይበርዝ መከላከል የግድ ነው።
የእውቀት ዘዴ፣… የመረጃ ማሰባሰቢያና የማገናዘብ ዘዴ፣ የመላምትና የሙከራ ዘዴ፣ የማጣሪያና የመመርመሪያ ዘዴ፣… የማወቂያም ዘዴ፣ የማጣሪያ ዘዴ ነው። ይሄኛው መረጃና ሃሳብ ከተዛማጅ መረጃዎችና ሃሳቦች ጋር እንዴት ተጣጥሞ ይገናዘባል? ካልተገናዘበስ ይቃረናል? በአጠቃላይ እውነትን የማንጠር፣ የማሟላትና የማጥራት ምርምር፣ የእውቀት ዘርፍ ባህርያት ናቸው።     
እና ምን ትላችሁ?
እውነትንና እውቀትን፣… ከየትም ቦታና ጊዜ፣ ከማንም ሰው ንግግርና ፅሁፍ ሲመጣ፣ ከእውነታ ጋር አመሳክረን፣ አንጥረንና ምልዓቱን ፈትሸን፣ አጣርተንና አገናዝበን፣ “አዎ፤ እውነት ነው” ብለን እንቀበላለን፤ “አዎ፤ እውቀት ነው” ብለን እናፀድቃለን። ፅድቅ ማለት፣ እውነት ማለት አይደል!




Read 9322 times