Saturday, 13 November 2021 14:36

ፍቱን መድሃኒት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ለዚህች ሀገር ችግር - መፍትሔ ጥቆማ
አንድ ሀሳብ ነበረኝ - ይሄ ሕዝብ ቢሰማ!
ህላዌ ነታችን
ልቃቂት ፈትላችን
ቁጢቱ ሲመዘዝ - ድውሩ ፈትላችን
"ወፌ ቆመች" ብለን ......
ድኸን በመጣነው - ረጅም መንገዳችን
በነፋስ አውታር ላይ
በእሳት ሰረገላ
ሽምጥ ሲመለስን - ድንገት ተገናኘን -
ከሸክላነት ገላ!
ያኔ
ከፈጣሪ ሃሳብ - ከአፈር ተፈጥረናል
መላእክት ታዞልን - ከአውሬ
ተጫውተናል
ርቃን ገላ ሆነን በጸጋው ሞቀናል
ፍጥረቱን ስንገዛ .........
ባይገባን ነው እንጂ - ለካ በክብራችን -
ከብሔር ድመናል!
አወይ የዚያን ጊዜ
ምስጢሩ ከፍ ሲል - የእግዜር ዘር ይዘናል
ዝቅ ሲል ነገሩ - የጥንቱ ጭቃችን - አፈር
ይቀርበናል!
እንደ ታላቅ ዥረት - ፈስሰን ላናበቃ
ከእድሜ በላይ ሆነን - ስንተኛ ስንነቃ
ስንበላ ስንጠጣ - በማይጎድፍ ጸጋ
ከቶ መች ነበረን?
የሚበርደን ክረምት - የሚሞቀን በጋ ?!
ደግ ታሪክ ሆኖ - ይህ ሁሉ ካለፈ
እኔ ምክር አለኝ ............
ለዚህ ዘመን ችግር - ሃቅ እውነት የጻፈ!
ትውልድ ያስታረቀ - በደልን ያራቀ
የእሳት እንባን ጠርጎ - ፊትን ያደረቀ
ምቹ ቅዱስ አልጋ - በልብ የጸደቀ
ሰው ሆኖ መኖር ነው ................
ፍቱን መድሃኒቱ - ከጥንት የታወቀ !
ጥበቃ
ኢትዮጵያን እናፍርስ - ብለው ሲማማሉ
ክብርዋን ለማዋረድ - ስምዋን ሲታገሉ
ህልማቸው ጉም ሆኖ - ተነነ በአፍታ
ዛሬም እሳት ሆኖ ………………
ቅጥርዋን ይጠብቃል - የሰማዩ ጌታ!
     (ነፃነት አምሳሉ)


Read 1214 times