Saturday, 13 November 2021 13:17

አለም የ2 ቢ. የኮሮና ክትባት መርፌዎች እጥረት ያሰጋታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በመጪው የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ የኮሮና ክትባቶችን በስፋት ለማዳረስ የተያዘው ዕቅድ በክትባት መርፌዎችና ሲሪንጆች እጥረት ሊስተጓጎል እንደሚችልና አለማችን ተጨማሪ 2 ቢሊዮን ሲሪንጆች እንደሚያስፈልጓት የአለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ የኮሮና ክትባት ምርት በአለማቀፍ ደረጃ እያደገ ቢሆንም ክትባቱን ለመስጠት የሚያገለግሉ ሲሪንጆችና መርፌዎች ምርት ግን ምንም አይነት መሻሻል ያላሳየ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ክትባቶችን በስፋት በማዳረስ የቫይረሱን ስርጭት በአፋጣኝ ለመግታት የተያዘው አለማቀፍ ጥረት ሊስተጓጎል ይችላል፡፡
በመላው አለም እስካሁን ድረስ ከ7.25 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የኮሮና ክትባቶች መሰጠታቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፣ በቀጣይ ክትባቶችን በስፋት ለማዳረስ ቢታቀድም የክትባት ሲሪንጅ እጥረቱ ደህንነታቸው ባልተጠበቀ መርፌዎችና ሲሪንጆች ወደ መጠቀም ወይም መላልሶ ወደ መጠቀም ሊያመራ እንደሚችል አመልክቶ፣ ይህም ሌላ የጤና ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አሳስቧል፡፡
ሲሪንጆችንና መርፌዎችን በበቂ መጠን ከማምረት ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለው እጥረት አምራች አገራት ከሚጥሏቸው የወጪ ንግድ ክልከላዎችና የትራንስፖርት ችግሮች ጋር በተያያዘ ሊባባስ እንደሚችል የጠቆመው ድርጅቱ፣ አገራት ስጋቱን ሰበብ አድርገው መርፌዎችንና ሲሪንጆችን ከሚገባው በላይ እንዳይከዝኑም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Read 1786 times