Saturday, 13 November 2021 13:07

የሰው ነገር - ሦስት ይቀናዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ሦስቱ መሰረታዊ መብቶች (የሕይወት፣ የነፃነትና የንብረት)።
      • የኒውተን ሦስት የፊዚክስ ህጎች፤ • የአርስቶትል ሦስት የሃሳብ (የሎጂክ) ህጎች፣
      • ሦስቱ የኢየሱስ እሴቶች- (እውነት፣ መንገድ፣ ሕይወት)
      • ሦስቱ የአየንራንድ እሴቶች- (አእምሮ፣ አላማ፣ የራስ ክብር)፣ ብዙ ነው።


           የኢትዮጵያ አዋቂዎች የሰውን ተፈጥሮ ሲገልጹ፣ በሶስት ገጽታ ይተነትኑታል- ነባቢ፣ ለባዊ፣ ሕያዊ ይሉታል። “ይተነትኑታል” መባሉ ትክክል ነው።
እያንዳንዱ ሰው፣ አንድ ውሁድ ተፈጥሮ ነው- ምሉዕ ተፈጥሮ። ለግንዛቤ እንዲመች፣ ለእውቀት የሚጠቅም ውጤታማ ዘዴ ለማበጀት ነው፤ በሦስት ገፅታ መተንተንና ማፍታታት ያስፈልጋቸው።
በእርግጥ፤ የሰውን ነገር እንዘርዝረው ከተባለ፣ ለቁጥር ለስፍር እንደሚያስቸግር ያውቃሉ። የሰውነት ክፍሎች አይነትና ብዛት፣ አኳሃንና ተግባር ቢቆጠር፣ እልፍ አእላፍ ነው። በስሜት ህዋሳቱ የሚገኘው የቀለምና የድምጽ አይነትና ብዛትስ፣፣ የማስተዋልና የትኩረት፣ የሃሳብና የእውቀት አይነትና ብዛትስ፣ ተዘርዝሮ ያልቃል? ባሕርይና መንፈሱ፣ ልማዱና ራዕዩ፣ አቅምና ብቃቱ፣ ከእርምጃ እስከ ሩጫና እስከ አክሮባት፣ የመናገርና የማንበብ፣ የማድነቅና የማፍቀር ብቃቱ…
ምኑን አንስቶ ምኑን መተው ይቻላል? “ምኑ ቅጡ!” ብለው አልተቀመጡም… አዋቂዎች። እልፍ አእላፉን ዝርዝር አዋህደን ለመገንዘብ እንድንችል ነው፤ በሶስት ማዕቀፍ አዋቅረው ያስተማሩን።
ለስፍር ቁጥር የሚያስቸግሩ ዝርዝሮችን በቀላሉ አቅፈን፣ በቅጡ እውቀት ለመጨበጥ ይረዱናል- ነባቢ፣ ለባዊ፣ ሕያዊ የተሰኙት ማዕቀፎች።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
በአንድ በኩል፤ ውሁድና ምሉዕ የሰው ተፈጥሮን በሦስት ፈርጅ ለመተንተን ያለግላል- የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ገጽታዎችን አፍታትቶ ለመገንዘብ።
 በሌላ በኩልም፤ መተንተኛዎቹ፣ ማቀፊያዎች ናቸው። እልፍ ዝርዝሮችን በሦስት ማዕቀፍ አዋህደው፣ እውቀትን ያስጨብጣሉ። የተግባር፣ የሃሳብና የባሕር አይነቶችን በፈርጅ በፈርጃቸው በማዕቀፍ አበጅተን እውቀትን እናደረጃለን።
በእርግጥ፣ ይሄ አዲስ ዘዴ አይደለም። በሦስት ገፅታ መተንተን፣ በሦስት ማዕቀፍ ቅጥ ማስያዝ፣ በአዋቂዎች ዘንድ በጣም የተለመደ ነው። እንዲያውም፣ “በሦስት ያልተፈረጀ፣ በሦስት ያልታቀፈ ምን አለ?” ያሰኛል።
ፈላስፎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሳይንስ ተመራማሪዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ሌላ ሌላውም ሰው ሁሉ፣ በየፊናውና እንደየእውቀቱ፣ ፈርጅና ማዕቀፍ ያበጃል- በሦስት በሦስት።
ሦስቱ መሰረታዊ መብቶች (የሕይወት፣ የነጻነትና የንብረት)።
የኒውተን ሦስት የፊዚክስ ህጎች።
 የአርስቶትል ሦስት የሃሳብ (የሎጂክ) ህጎች።
 ሦስቱ የኢየሱስ እሴቶች (እውነት፣ መንገድ፣ ሕይወት)።
 ሦስቱ የአየን ራንድ እሴቶች (አእምሮ፣ አላማ፣ የራስ ክብር)።
 ብዙ ነው።
በጥንት አባባል እንጀምር? በየት በኩል ወዴት እንሂድ? መነሻ፣ መሄጃና መድረሻ ማወቅ ይጠቅማል። ሦስት የጉዞ ገፅታዎች መሆናቸው ነው።
ያለህበትን ቦታና ሁኔታ ማወቅ፣ መነሻህን ማወቅ  እንደማለት ሊሆን ይችላል።
ምኞትሽን፣ አላማሽንና ግብሽን መምረጥሽ፣ የእንዳንዱ ምዕራፍ መድረሻዎችሽን እንደመወሰን  ማለት ነው።
ሁለቱን የሚገያናኝ፣ ከመነሻ ወደ መድረሻ የሚወስድ ተግባርና ጥረት ደግሞ ከመሃል አለ- መሄጃ አቅጣጫ፣ መንገድና እርምጃ።
ለነገሩ፣ ቅጥ ያለው ማንኛውም የሰው ሃሳብና ተግባር ሁሉ፤ የምክር ንግግርም ሆነ መሳጭ ትያትር፣ ሦስት ክፍሎች እንዳሉት ታላቁ ፈላስፋ አስተምሯል- Beginning, Middle, end. እጥር ምጥን ያለ የእውቀት ማዕቀፍ ድንቅ ነው። ነገር ግን  ማወሳሰብም ይቻላል።
 “ጅማሬው፣ ከመነሻው ተነስቶ እስከየት ድረስ ነው? መሃሉስ፣ ምን ያህል ነው? መጨረሻውስ ከየት ይጀምራል?” እንዲህ እንዲህ እየተባለ፣ ነገር እየተመዘዘ እየመነዘረ ፣ መላቅጡ የሚጠፋ ከሆነ፣ ነገሩ ሁሉ ትርጉም ያጣል። ልኩን አለመሳት ያስፈልጋል።
ሦስት ፈርጀ ሦስት ማዕቀፍ - ተፈጥሯዊ ወይስ ምናባዊ?
ጊዜን በፈርጅ ለመተንተን፣ በፈርጅ ለማቀፍ… ትናንት፣ ዛሬ፣ ነገ እንል የለ! የትናንት ማብቂያ፣ የዛሬ መነሻ የትኛው ነው? የዛሬ መቋጫ፣ የነገ መዳረሻስ?
እለታዊ ጉዳይ ላይ፣ ማለዳ ጀምበር ስታበራ፣ ትናንት አብቅቶ፣ ዛሬ ተወልዷል ልንል እንችላለን።  ትክክለኛ ዘዴ ነው- ሃሳባችንን ቅጥ እናስይዝበታለን። “የእለት መሸጋገሪያማ እኩለ ሌሊት ነው” ብለን ሌላ የልኬት ችካል ብናበጅም ያስኬዳል። ቅጥ ማስያዣ ነው።
እውነተኛና ትክክለኛ ሃሳቦች፣ የእውኑ ተፈጥሮና የአእምሮ ጋብቻ ናቸው ይላል- ሊዮናርድ ፔኮፍ። እውኑን ተፈጥሮ የተከተሉ አእምሯዊ ማዕቀፎች  ናቸው- ትክክለኛ ሃሳቦች።
“ትናንት፣ ዛሬና ነገ” ብለን ስንናገር፣ የተፈጥሮን ዑደት በአእምሮ የመገንዘብ ጉዳይ ነው፤ ግንዛቤንም በቅርቡ ማዕቀፍ አስይዞ ስያሜ ሰጥቶ እውቀትን መጨበጥ፣ የአእምሮ ስራ ነው። “ዛሬ” ስንል እውኑ ዓለም ውስጥ፣ ተፈጥሯዊ “ታፔላዎችን” በማንበብ  አይደለም። “ዛሬ” የሚል ባንዲራ የምታውለበልብ እለት ወይም በቀስተደመና የራሷን ስም የምታውጅ ቀን አይተን አናውቅም።
 ግን ደግሞ፣ “ዛሬ” የሚለው ሃሳብና ስያሜ፣ ከባዶ የመጣ፣ የምናብ የዘፈቀደ ፈጠራ አይደለም። ከማለዳ እስከ ማለዳ፣ ወይም ከእኩለ ሌሊት እስከ እኩለ ሌሊት፣ ተፈጥሯዊው ዑደት፣ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። የዘፈቀደ ምናባዊ ፈጠራ አይደለም።
“ዛሬ የሚለው ማእቀፍ ወይም ፍሬ ሃሳብ፣ እውኑን ዓለም፣ ተፈጥሯዊውን ዑደት በአእምሮ የመገንዘብ፣ አቅም የመያዝ፣ እውቀት የመጨበጥ ፍሬ ነው። የእውኑ ዓለምና የአእምሮ ጋብቻ።
“በእርግጥ፣ ትናንት፣ ዛሬን፣ ነገ…ስንል፣ እለታዊ ጉዳዮችን ለመረዳትና ለመግለጽ ላይሆን ይችላል። ድሮ ለማለት ስንፈልግ፣ ትናንት ብለን በጥቅሉ እንናገራለን። ያለፈው ዘመን ታሪክን ለመጥቀስም እንጠቀምበታለን። የቅርብ ዓመታትን ሁኔታ ለመግለጽ፣ ዛሬ፣ የዛሬ ዘመን፣ ዘመናዊ… እንላለን። ከ5፣ ከ10 ዓመት በኋላ፣ መጪውን ጊዜ አሻግረን ለማማተር፣ ነገ፣ የነገ ዘመን፣ የነገ ሕይወታችን… እንላለን።
ቢሆንም ግን፤ የዕለት ጉዳይ ሲሆንና የዓመታት ጉዳይ ሲሆን፣ ልዩነታቸውን ልካቸውን ለይተን መረዳት አያቅተንም። ልካቸውን አለመሳት ማለት ይሄው ነው።
የጅማሬው ማብቂያ፣ የመጨረሻው መጀመሪያ እያልን ልኩን ስተን ቢምታታብንም፣ ተፈጥሮ ላይ መፍረድ የለብንም። አእምሮን ማጣጣል አይገባንም። ባለሦስት ፈርጅ ባለሦስት ማዕቀፍ እውቀትን መውቀስ የለብንም።
አንድ ኪሎግራምና አንድ ኩንታል እኩል አይደሉም ብለን፤ “አንድ” የተሰኘው ቁጥር ላይ እንደማማረር ይሆናል። ለነገሩማ አንድ ኪሎ ግራም ወርቅና አንድ ኪሎ ሜትር፣ እኩል አይደሉም ብለን ልናወግዝ ነው? መመዘንና መመተርን  ከእንግዲህ  እርም ልንል ነው?
ከእውኑ ተፈጥሮና ከእውኑ ገፅታ ጋር የሚገጣጠም መሆን አለበት ሃሳባችንና መለኪያችን። ክብደት  ያለው ነገር፣ ክብደት ባለው ነገር ይመዘናል፤ አንድ ግራም ሁለት ግራም እየተባለ። ርዝመት ያለው፣ ርዝመት ባለው ነገር ይመተራል፤ አንድ ስንዝር ሁለት ስንዝር፣  አንድሜትር ሁለት ሜትር እየተባለ።
እውኑ ነገር አለ። መለኪያው አለ። ቁጥሩ (ልኩ) አለ። ሦስቱን አዋህደን ማገናዘብ ይኖርብናል- የሂሳብ መሰረታዊ ገጽታዎች ናቸውና።
(Atribute, unit, magnitiude)… እነዚህ የልኬት (የመጠን) ገጽታዎች ናቸው (Measurement)::
(Substance, unit, multitude)… እነዚህም የቆጠራ (የልኬት) ገጽታዎች ናቸው።  አንድ መኪና፣ ሁለት መኪና… አንድ ጥንቸል፣ ሁለት ጥንቸል፣… አንድ አተም፣ ሁለት አተም… እንላለን።
የነገሮችን መጠን፣… ርዝመታቸውን ወይም ክብደታአውን መለካት ብቻ ሳይሆን፤ የነገሮችን ብዛት፣ ቁሳቁሶቹን ራሳቸው መቁጠርም የሂሳብ ዘዴ ነው።
ለማንኛውም፤ የመጠን ልኬትም ሆነ የቆጠራ ልኬት፣ የሶስት ፈርጆች ውህደት ነው።
1. የነገሮችን ተመሳሳይ ገጽታ ማስተዋል፤ የመጀመሪያው ቁም ነገር ነው። ትኩረታችን፣ ለምሳሌ የነገሮች ርዝመት ላይ ሊሆን ይችላል። ወይም የነገሮች ክብደት ላይ።
2. ለልኬት የሚያመች አስተማማኝና ተጨባጭ መለኪያ መያዝ ሁለተኛው ቁምነገር ነው። ርዝመት ለመለካት፣ “የተወሰነ ርዝመት ያለው” መለኪያ እንጠቀማለን- “አንድ ክንድ” ወይም “አንድ እርምጃ” ወይም “አንድ ሜትር” ሊሆን ይችላል- መለኪያችን አሀድ (unit)።
3. ስንት ክንድ? ስንት እርምጃ? ስንት ሜትር? እያልን በቁጥር መለካት ሦስተኛው ቁም ነገር ነው።
የመጠን ልኬትና የቆጠራ ልኬት እዚህ ላይ ነው መገናኛቸው። ርዝመት እንደ ቁሳቁስ፣ አንድ፣ ሁለት፣ እየተባለ አይቆጠርም። ነገር ግን፣ አንድ ስንዝር፣ ሁለት ስንዝር፣ ዘጠኝ ሜትር አስር ሜትር ብለን መጠኑን ስንለካ፣ ከቆጠራ ጋር ይመሳሰላል።
ስናጠቃልለውም በሦስት ማዕቀፍ ነው።
ምን ለመለካት- ርዝመትን። በምን መለካት- በስንዝር። እንዴት  መለካት-በቁጥር።
የተራቀቁ የፊዚክስ ልኬቶች፣ ስሌቶች፣ ቀመሮች ሁሉ፣ በእነዚህ ሦስት ፈርጆች ውህደት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
ከመጠን ልኬትና ከቆጠራ ባሻገር፣ በሰፊው ስለሳይንሳዊ ዘዴ እንነጋገር? እዚህ ላይ የሚጠቀስ ትልቅ ሰው አለ- ፍራሲስ ቤከን። የሳይናሳዊ ዘዴ ዋና ዋና ገጽታዎችን በቅጡ አሟልቶ ያስተማረ የመጀመሪያው ሰው ነው ይሉታል።
እውቀት ማለት፣ የእውኑ ዓለም እውቀት  ማለት አይደል?
ስለዚህ፣ እውኑን ዓለም ማስተዋል፣ ዋና የእውቀት መሰረት ነው- የእውነተኛ መረጃዎች ምንጭ ነውና። የመጀመሪያው ስራ በሉት።
እውነተኛ መረጃዎችን አረጋግጦና አመሳክሮ፣ በወጉ መዝግቦና አነጻጽሮ፣ በጥንቃቄ አገናዝቦና አመሰላስሎ፣ ወደ “ጠቋሚ ሃሳብ” መሸጋገር፣ ሁለተኛው ትልቅ ስራ ነው።
በእርግጥ ጠቋሚ ሃሳብ፣ የድምዳሜ ሃሳብ ወይም የተጣራ የእውቀት ግኝት ማለት አይደለም። እውኑን ዓለም ከማስተዋልና እውነተኛ መረጃዎችን ከማገናዘብ የመነጨ ነው- ጠቋሚ ሃሳብ። ነገር ግን፣ የጠራ የነጠረ የተሟላና የተረጋገጠ ሃሳብ ለመሆን ገና ይቀረዋል።
መመርመሪያ ማረጋገጫ መላ ያስፈልጋል-  በጥንቃቄ የተዘጋጀ “የመፈተኛ ሙከራ” የሚመጣው እዚህ ላይ ነው።
በጥቅሉ፣ እውኑን ዓለም ማስተዋል፣ ጠቋሚ ሃሳብና፣ መፈተኛ ሙከራ (Observation, Hypothesis, Experiment)… እነዚህ በአንድ በኩል ሳይንሳዊ ዘዴን ለመተንተን የሚያገለግሉ ገጽታዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሳይንሳዊ ዘዴ እልፍ አእላፍ ተግባራትንና ሂደቶችን በሦስት ፈርጆች ቅጥ ለማስያዝ የሚችሉ ማዕቀፎች ናቸው።

Read 1280 times