Saturday, 13 November 2021 12:37

የህወኃት ታጣቂዎች በአንድ ከተማ ብቻ ከ70 በላይ ሴቶችን በቡድን አስገድደው ደፍረዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “4 ታጣቂዎች በቡድን በሴት ልጄ ፊት ደፍረውኛል
                                       
           የአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችን በሃይል የተቆጣጠሩት የህወኃት ታጣቂዎች፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ ዘረፋ፣ አካላዊ  ጥቃቶችና የአስገድዶ መደፈር ወንጀል መፈፀማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ታጣቂዎቹ በሃይል በተቆጣጠሯቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች፣ ሴቶች ልጆቻቸው ፊት ሳይቀር በቡድን ተደፍረዋል የሚለው ሪፖርቱ፤ ታጣቂዎቹ ሆስፒታሎችንና የህክምና ተቋማትን መዝረፋቸውንና ማውደማቸውን በዚህም በርካቶች በህክምናና መድሃኒት እጦት ለስቃይ መዳረጋቸውን አምነስቲ አረጋግጧል።
በአማፅያኑ ተወርረው ከተያዙ አካባቢዎች አንዱ በሆነው በንፋስ መውጫ የአምነስቲ የምርመራ ቡድን ያነጋገራቸው ሴቶች በህወኃት ታጣቂዎች በቡድን መደፈራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከ16ቱ  ሴቶች 14ቱ በቡድን በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መደፈራቸውን ነው ለአምነስቲ ያረጋገጡት፡፡
አብዛኛዎቹ ሴቶች መሳሪያ ፊታቸው ተደቅኖ አዋራጅ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸመባቸው፣ ክብረ ነክ በሆነ መልኩ መድፈራቸውንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
ታጣቂዎቹ በንፋስ መውጫ አካባቢ በነበሩባቸው ዘጠኝ ቀናት ብቻ ከ70 በላይ ሴቶችን አስገድደው መደፈራቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
የአምነስቲ የምርመራ ቡድን ካነጋገራቸው የጥቃቱ ሠለባዎች መካከል የ45 ዓመት እድሜ ጎልማሳዋ በእምነት አንዷ ስትሆን በታጠቁ ሶስት የህወኃት ታጣቂዎች መደፈሯን አስረድታለች፡፡
“በነሐሴ 14 እ.ኤ.አ ምሽት ላይ አራት  የህወኃት ታጣቂዎች ወደ ቤቴ ቀጥታ መጡ፤ ቡና እንዳፈላላቸው ጠየቁኝ፤ ከሁኔታቸው ግን  ሌላም ፍላጎት እንዳላቸው ተጠራጥሬ ነበር፤ ይህን ስመለከት ሴት ልጆቼን ወደ ሌላ ቦታ ላኳቸው፤ ነገር ግን  ልጆቼን መልሼ እንዳመጣቸው አስፈራሩኝ፤ እኔም አይሆንም አይመጡም አልኳቸው፤ ይሄን ጊዜ ስድብ ጀመሩ፡፡ ማንነት ተኮር ስድቦችን ይሰድቡኝ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ከመካከላቸው አንደኛው እሷን ልንሰድብ አይገባም ሴት ነች እናታችን ነች” ብሎ ሲቃወም ከቤት እንዲወጣ አደረጉትና፣ ሶስቱ ብቻ ቤት ውስጥ ቀሩ። ከዚያም በየተራ ደፈሩኝ” ብላለች፡፡
የዚያው የንፋስ መውጫ ነዋሪ የሆነችው የ30 ዓመቷ ገበያነሽ በበኩሏ፤ “እነሱ ያደረጉን ነገር ለመናገር ይከብደኛል” ትላለች፡፡ በጣም አሰቃይተው ደፍረውኛል፤ ሶስት ሆነው በህጻናት ልጆቼ ፊት ነው የደፈሩኝ፤ አንደኛው ልጄ የ10 ዓመት ነው፤ ሌላኛው 9 ዓመቱ ነው፤ በፊታቸው ነው የደፈሩኝ፤ ልጆቼ የሚያደርጉትን --- እያዩ ያለቅሱ ነበር። ሰዎቹም  የሚያደርጉትን አድርገው ቤት ውስጥ ያለኝን ምግብ ሁሉ ነው ዘርፈውኝ የሄዱት ከቤቴ ውስጥ ሽሮ እና በርበሬ ሳይቀር ነው የወሰዱብኝ፤ በተደጋጋሚ በጥፊ መትተውኛል፤ ክብረ ነክ ስድብ ይሰድቡኝ ነበር፤ ሲደፍሩኝም መሳሪያቸውን ፊት ለፊቴ ደቅነው ተኩሰን እንገልሻለን እያሉ ያስፈራሩኝ ነበር” ብላለች፡፡
የ28 ዓመቷ ሃመልማል፤ በነፋስ መውጫ ከተማ እንጀራ በመሸጥ ነው የምትደራደረው። አራት የህወኃት ታጣቂዎች በቡድን ሆነው በገዛ ሴት ልጄ ፊት ነበር የደፈሩኝ፡፡
“ሁለት ልጆች አሉኝ፤ አንደኛዋ የ10 ዓመት፣ ሌላኛዋ የ2 ዓመት ነች፡፡ በእለቱ ልጆቼን ይገድሉብኛል ብዬ በጣም ፈርቼ ነበር፡፡ “ልጆቼን አትንኩብኝ እኔን የፈለጋችሁትን አድርጉ” ብዬ ለመንኳቸው። በወቅቱ የ2 ዓመቷ ልጄ እንቅልፍ ተኝታ ነበር፤ ነገር ግን የ10 ዓመቷ ልጄ እየተፈራረቁ ሲደፍሩኝ ያደረጉትን ሁሉ ትመለከት ነበር።"
ሌላኛዋ የ30 ዓመቷ መስከረም በተመሳሳይ በ3 ታጣቂዎች በቡድን መደፈሯን፣ ከአቅሟ በላይ መደብደቧን፣ በመሳሪያ ሰደፍ መመታቷን ታስረዳለች፡፡
እጅግ አፀያፊ ዘር ተኮር ስድቦችን ሁሉም የጥቃቱ ሠለባዎች መሰደባቸውን ለአምነስቲ አስረድተዋል፡፡
በቡድን የተደፈሩ ሴቶች በሙሉ በቤታቸው ውስጥ የነበሩ መገልገያ እቃዎች፣ ጌጣ ጌጦች የምግብ ግብአቶች በሙሉ እንደተዘረፈባቸውም ተናግረዋል፡፡
በተደጋጋሚ በታጣቂዎቹ መደፈሯን የምትናገረው ፍሬ ሕይወት፤ ተንቀሳቃሽ ስልኳንና ጥሬ ገንዘብ እንደተዘረፈች፤ ትእግስት የተባለች ሌላኛዋ የመደፈር ጥቃት የደረሰባት ደግሞ የሱቅ እቃዎቿ በሙሉ እንደወደመባትና ጌጣጌጦቿን በሙሉ እንደዘረፏት አስረድታለች፡፡
የአምነስቲ መርማሪ ቡድን ካነጋገሯቸው 16 የመደፈር ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች መካከል 15ቱ ባጋጠማቸው ጥቃት ምክንያት ለከፍተኛ አካላዊና ስነ- ልቦናዊ ጉዳት  መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል።
አብዛኛዎቹ ለጭንቀት መዳረጋቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ የ20 ዓመቷ ሠላማዊት በበኩሏ በቡድን ባጋጠማት መደፈር በአሁኑ ወቅት ነፍሰ ጡር መሆኗ መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
በአጠቃላይ የህወኃት ታጣቂዎች የፈፀሙት ጥቃት የጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል መሆኑን ነው አምነስቲ ያረጋገጠው፡፡
መንግስት የጥቃቱ ሠለባዎቹን ጤንነት እንዲከታተል እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ምርመራ እንዲካሄድም አመነስቲ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ባስቀመጠው ጥቆምታዎቹ አስገንዝቧል፡፡

Read 10436 times