Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 September 2012 12:59

በ7 ብር ጐመን ዘር ጀምሮ ከ3 ሚ.ብር በላይ ያፈራው የሆለታ ወጣት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የደረጃ ተማሪ ነበር፡፡ ከክፍሉ 2ኛ፣ 3ኛ እየወጣ ነው 11ኛ ክፍል የደረሰው፡፡ ለትምህርት የነበረው ፍቅር ከፍተኛ ቢሆንም አልዘለቀበትም፡፡ የቤተሰቡ አስተዳዳሪ የነበሩት ገበሬ አባቱ በሞት ሲለዩዋቸው ትልቅ ወንድ ልጅ እሱ በመሆኑ የቤተሰብ ኃላፊነት ወደቀበትና ትምህርቱን አቋርጦ ወደ እርሻ ገባ፡፡ ዛሬ ከ6 ዓመት በኋላ ሚሊዮን ብሮች እያንቀሳቀሰ ሲሆን በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን፣ ድካምና ጥረቱ እውቅና አግኝቶ “የ2004 ዓ.ም የልማት ጀግና” በመሆን የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ እንደ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች፣ ቤተሰቡ የሚተዳደረው አባት እያረሱ በሚገኘው ገቢ ነበር፡፡ የአብዛኛው አርሶ አደር ሕይወት ደግሞ በዓመት አንድና ሁለት ጊዜ በሚጥል ዝናብ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ ለነገ ለተነገ ወዲያ፣ ለከርሞ፣ ለሁለት፣ ለሦስትና ለአምስት ዓመት ለቤተሰብ ቀለብ ተብሎ የሚቀመጥ እህል፤ ለልጆች ትምህርት ቤት ተብሎ የሚቆጠብ ገንዘብ አይኖርም፡፡

በዚህ ጊዜ ነፍስ ያወቀ፣ ጠና ያለና የደረሰ ልጅ ከሌለ የቤተሰቡ ዕጣ - ፈንታ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ከቤት የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ቤተሰቡ ሲራብ፣ ሲጠማ፣ ሲታረዝ፣ ትምህርት አይታሰብም፡፡ ልጆች ነፍሳቸውን ለማሰንበት ምግብ ፍለጋ ይሰደዳሉ፣ ጐዳና ይወጣሉ፣ ቤተሰብ ይበተናል፡፡ ወጣት ፍሰሐ ከበደ ቤተሰቡ እዚህ ደረጃ ደርሶ እንዳይበተን፣ ወንድምና እህቶቹ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለመታደግ ነው፤ የሚወደውን ትምህርት አቋርጦ አባቱን ተክቶ ወደ እርሻ ለመግባት የወሰነው፡፡ ነገር ግን ያላሰበው ችግር አጋጠመው፡፡ ገበሬ ለመሆን ፍላጐትና ጉልበት ብቻ አይበቃም - ገንዘብም ያስፈልጋል፡፡ እሱ ደግሞ ምንም ገንዘብ አልነበረውም፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ከትምህርቱም ሳይሆን፣ ያሰበውንም ሳያሳካ መሃል መንገድ ላይ በመቅረቱ ክፉኛ አዝኖ ሲተክዝ ያዩት ጓደኞቹ “አይዞህ! በርታ! ችግር ያልፋል፡፡ እኛም አለንህል…” በማለት አፅናኑት፡፡ አንዳንድ ጊዜ “መውለድ ቋንቋ ነው” የሚባለው እውነት ነው፡፡ ከእናት ከአባት ከተወለደ ወንድም የበለጠ የሚወድና የሚያቀርብ የሚያዝንና የሚጨነቅ ጓደኛም አለ፡፡ ፍሰሐ፤ “ዛሬም በጣም የምወደውና የማከብረው ጥሩ ወንድሜ ነው፡፡ አንለያይም አብረን ነን” የሚለው ጓደኛው ኃይለማርያም ቲመርጋ፤ አንድ ፓኬት የጥቅል ጐመን ዘር ገዝቶ “እንካ በዚህ ወደ እርሻ ግባ” ብሎ ሰጠው፡፡ ያ መነሻ ሆኖት ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ በቃ፡፡ ፍሰሐን ያነጋገርነው፣ ከሐምሌ 23-27 ቀን 2004 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች 7ኛው ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ ልምድና ተሞክሮውን ለጉባኤተኞቹ ለማካፈል በተገኘበት ወቅት ነበር፡፡ ለስኬቱ ያበቃውን በመንገዱ ላይ የጋጠሙትን ችግሮችና እንዴት እንደተወጣናቸው…ሙሉ ታሪኩን ራሱ ያጫውተናል፡፡

የት ተወለድክ? መቼ?

አዲስ አበባ ውስጥ በልደታ ክፍለ ከተማ በ1977 ተወለድኩ፡ዕድገትና ትምህርቴ ግን ሌላ ቦታ ነው፡፡

የት ነው?

ዕድገቴ፣ በአዲስ አባ ዙሪያ ዞን በውልመራ ወረዳ ሆለታ ከተማ አካባቢ በሚገኝ 1ኛ ወልፈታ ቀበሌ ገ.ማ ነው፡፡ 1ኛ ደረጃ የተማርኩት በአባ ወልደማርያም ት/ቤት ሲሆን፤ 2ኛ ደረጀን በሆለታ የካቲት 25 አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ 11ኛ ክፍል ተምሬ በቤተሰብ ችግር ምክንያት አቋረጥኩ፡፡

ጓደኛህ ገዝቶ የሰጠህን የጥቅል ጐመን ዘር ምን አደረግኸው?

ወደ ቤት ይዤ ሄጄ፣ እናቴ የምታስተዳድረው የቤተሰብ መሬት ስላለ፣ እናቴን “ለዚህ ጐመን መዝሪያ ቦታ ስጪኝ” አልኳትና ሁለት ቦይ መሬት ሰጠችኝ፡፡ ጐመን ዘሩን አፍልቼ በተሰጠኝ ቦታ ላይ ችግኙን ተክዬ ብዙ ተረፈኝ፡፡ ቦታ ስላልነበረኝና መሸጥም ስላልቻልኩ የተረፈኝን ችግኝ ለሚፈልጉ ሰዎች ሰጠሁ፡፡ ያንን ጥቅል ጐመን 200 ብር ሸጥኩት፡፡

ያንን ብር ምን አደረግህበት?

በ60 ብር ድንች ገዝቼ በዚያቹ አንድ ቦይ የ20 ብሩን ተክዬ ቀሪውን በ40 ብር ሸጥኩ፡፡ ያንን ድንች 280 ብር ሸጥኩ፡፡ በመሃሉ ደግሞ፣ ጐመኑን በሸጥኩ ጊዜ አንድ ስኒ የባሮ ሽንኩርት ዘር በ5 ብር ገዝቼ ስለነበር፣ ያንን ዘር አፍልቼና ተክዬ በጥሩ ዋጋ ሸጥኩ - 140 ብር፡፡ እንደዚያ እያደረኩ ሳገላብጥ ቆይቼ በዓመቱ መጨረሻ ሲሰላ ከወጪ ቀሪ 600 ብር አገኘሁ - በ1998 ዓ.ም ማለት ነው፡፡

በሚቀጥለው ዓመት፣ እናቴ የምታስተዳድረውና መኖሪያ ቤታችን ያረፈበት 1000 ካ.ሜ የቤተሰብ መሬት አለ፡፡ ያንን ቦታ እናቴ ማረስ ስለማትችል ለሌሎች ሰዎች በኮንትራት አስይዛ ነበር የምትተዳደረው፡፡ ስለዚህ “ይህን መሬት ለሌላ ሰው አታኮናትሪ፤ እኔ እሠራበታለሁ” በማለት ጠየቅኋት፡፡ እሷም ልጅነቴን አይታ “አይሆንም፤ አትችልም” አለችኝ፡፡ “እችላለሁ ግድ የለም፡፡ ቀደም ሲል ቢሆን ላታምኚኝ ትችያለሽ፡፡ አሁን ግን እየሠራሁ ያገኘሁት ነገር አያሳምንም ወይ?” በማለት አግባባኋት፤ ተነጋገርን፤ አመነችኝና ፈቀደችልኝ፡፡

ያንን መሬት አርሼ እናቴ ከሌሎች የምታገኘውን ከፍዬ፣ ወንድሞቼን እያስተማርኩና ቤተሰቡን እየረዳሁ በዓመቱ መጨረሻ 1,400 ብር አገኘሁ፡፡ ይሁን እንጂ ያ ገንዘብ ለዘርና ለማዳበሪያ መግዣ ስላልበቃኝ ከሰዎች ጋር የእኩል ለመሥራት ጠየኩኝ፡፡ ሰዎቹም “አንተ ጐበዝ ሰው ስለሆንክ የእኩል ሳይሆን በነፃ ሊሰጥህ ይገባ ነበር” በማለት የእኩል እንድሠራ ፈቀዱልኝ፡፡

በሚቀጥለው ዓመት የቤተሰቡን መሬት፣ ታናናሽ ወንድሞቼን እያስተማርኩበት፣ በጣም የምወዳት አክስቴና ባሏ ስለሞቱ ወላጅ አጥ ልጃቸውን አምጥቼ እየረዳሁና እያስተማርኩ ለቤተሰቡ ቀለብና ወጪ መድቤ፣ ከሌሎች ጋር እኩል መሥራቱንም ትቼ፣ በግሌ አንድ ሄክታር መሬት ኮንትራት ይዤ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በ2000 ዓ.ም ከዚያ መሬት ላይ ወደ 28ሺህ ብር አገኘሁ፡፡ ያንን ብር አላስቀመጥኩትም - ሠራሁበት፡፡ ሰፊ መሬት ቢሆን ኖሮ ከዚህም በላይ አገኝ ነበር በማለት ወደ ሦስት ሄክታር መሬት ተኮናትሬ፣ በ9ሺህ ብር የድንች ዘር ገዝቼ ለማዳበሪያና ለጉልበት ሠራተኞች ከፍዬ ብዙ ብር ወጪ አደረግሁ፡፡

የድንች እርሻው አምሮበት ደርሶ፣ ገዥዎችም መኪና ይዘው መጥተው በዋጋ ተስማምተን ጥሩ ገቢ አገኘሁ ስል ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ፡፡ በአካባቢያችን የወጨጫ ተራራ አለ፡፡ መጋቢት 23 ቀን 2000 ዓ.ም ኃይለኛ ዝናብ ጥሎ ስለነበር ከተራራው የወረደው ጐርፍ የድንች ማሳውን በሙሉ አጥለቀለቀውና ምርቱ ተበላሸ፡፡ በእጄ ያለው ብር ትንሽ ስለነበር ምንም ሊያንቀሳቅሰኝ አልቻለም - ባዶ እጄን ቀረሁ ማለት ይቻላል፡፡

መጀመሪያ አካባቢ ወደ እርሻው ማየት አስጠልቶኝ ነበር፡፡ ጊዜው ወደ ክረምት እየተቃረበ ስለነበር፣ በቀረችኝ ትንሽ ገንዘብ ለስላሳ፣ ቢራ፣ ወይን፣ …የሚሸጥባት አነስተኛ ግሮሰሪ ከፈትኩ፡፡ ጓደኞቼም እኔን ለመደገፍ እየመጡ “አይዞህ፣ ምንም አይደለም፡፡ እኛም ከጐንህ ነን” እያሉኝ ምሽቱን እኔ ጋ እያመሹ አጽናንተውኛል፡፡ እኔም “በፊትም ምንም ሳይኖረኝ ነው ሠርቼ ያገኘሁት፡፡ ተስፋ አልቆርጥም አልኳቸው፡፡ ግሮሰሪዋ አሁንም አለች፡፡ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት ወደ እርሻው ተመልሼ እንዴት መሥራት እንዳለብኝ ዕቅድ እያወጣሁ ቆየሁኝ፡፡

በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ የተነሳሁበትን ጥቅል ጐመን፣ ድንች፣ ቀይስር፣ ሽንኩርት ዘሮች ገዝቼ 2ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ ዘራሁ፡፡ ከዚያ ማሳ ጥሩ ምርት አግኝቼ 14ሺህ ብር ያህል ሸጥኩት፡፡ ያንን ገንዘብ አላስቀመጥኩትም፤ መሬት እየፈለኩ አስፋፋሁት፡፡ በፊት ብቻዬን ነበር የምሠራው፡፡ አሁን ግን ብቻዬን ማዳረስ ስላልቻልኩ ሠራተኞች ቀጥሬ ቀን እናርሳለን፤ ማታ ባትሪ በአፋችን ይዘን ውሃ ከመስኖ ቀድተን እናጠጣለን፡፡

አንድ ቀን ማታ ለብቻዬ ውሃ ሳጠጣ የተፈጥሮ ሳይሆን ሰው ሠራሽ ችግር ተፈጠረ - ውሃው ተቋረጠብኝ፡፡ ምን ተፈጠረ? ብዬ ሮጬ ስሄድ ውሃው ጋ የአጐቴ ልጅ መጥረቢያ ይዞ ቆሟል፡፡ እሱ በዕድሜ ትልቅ ከመሆኑም በላይ በጉልበትም ይበልጠኛል፡፡ ቢይዘኝ አልቋቋመውም፡፡ ቢሆንም “ለምንድነው ውሃውን የመለስክብኝ?” በማለት ጠየኩት፡፡

”እዚህ ማልማት አትችልም” አለኝ፡፡ የአጐቴ ልጅ ነው፡፡ ምን አስቦ ነው? ብዬ በጣም አዘንኩ፡፡ ከዚያም፣ “የፈለከውን ታደርገኛለህ እንጂ ብዙ ገንዘብ ያወጣሁበትና የደከምኩበት አትክልት ሲበላሽ ዝም ብዬ አላይም” ብዬ እሱ በሌላ መስመር እንዲሄድ ያደረገውን ውሃ ወደኔ ማሳ መለስኩ፡፡ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ ያጐቴ ልጅ ምን ተሰምቶት እንደሆነ አላውቅም፤ ምንም ሳይለኝና ጉዳት ሳያደርስብኝ ጥሎኝ ሄደ፤ እኔም ወደ ሥራዬ በሰላም ተመለስኩ፡፡ ከዚያ እርሻ ጥሩ ገቢ አገኘሁ፡፡ ያንን ገንዘብ ማስቀመጥ የለም፡፡ ማስፋፋት፣ እንደገና ሌላ መሬት ፈልጐ ማስፋፋት፣ ካፒታልና ሠራተኛ መጨመር ሆነ፤ በ2002 ዓ.ም ገቢዬ 700ሺ ብር ደረሰ፡፡

አሁን ምን ያህል መሬት እያለማህ ነው? ምን ያህል ሠራተኞችስ አሉህ?

አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት…እያልኩ አሁን 11 እና 12 ሄክታር መሬት እየተኮናተርኩ ነው፡፡ የአባ ወልደማርያም ት/ቤት ባወጣው ጨረታ ተሳትፌና አሸንፌ 23 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ አስቆፍሬ ሰፊ ኩሬ በማዘጋጀት እያለማሁ ነኝ፡፡

በፊት በበሬ ነበር የማርሰው፡፡ አሁን ግን በ2004 ትራክተር ተከራይቼ ነው ያረስኩት፡፡ በእርሻ ወቅት እየመጡ የሚሠሩ 25 የኮንትራት ሠራተኞች ሲኖሩ አራት ሰዎች ደግሞ በቋሚነት አብረውኝ እየሠሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ጥሩ ውጤት ላይ ደርሻለሁ፡፡

ምን ምን ነበር የምታመርተው? ከአትክልት ምርት ውጭ የምትሠራው ነገር አለ?

አዎ! እኔ በዋናነት የተሰማራሁት በአትክልት ምርት ነው፡፡ ጥቅል ጐመን፣ ባሮ (ቀይ ሽንኩርት) ድንች፣ ቀይ ስር፣…አመርታለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የእርሻ መሬት እየፈለኩ፣ በኮንትራትም ሆነ የእኩል በመሥራት ስንዴ፣ ሽምብራ፣ ጓያ እዘራለሁ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ከብቶችም እነግድ ነበር፡፡ ከሳ ያሉ ከብቶችና በጐች ገዝቼ እያደለብኩ መሸጥ ጀምሬ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ 18 በጐችና 37 ከብቶች አደልቤ በመኪና ጭኜ ሸጫለሁ፡፡ ወፈር - ወፈር ያሉ ከብቶችንም እየገዛሁ ሳልቀልብ አትርፌ፤ መሸጥ ጀምሬ ነበር፡፡ ነገር ግን ንግዱ የእርሻ ጊዜዬን ስለሚሻማብኝ ብዙ አልሠራሁበትም፤ ትቼዋለሁ፡፡

የስኬትህ ምስጢር ምንድነው?

ምንም ምስጢር የለውም፡፡ ያው ተስፋ ያለመቁረጥ፣ ጠንክሮ መሥራት፣ በሁሉም መልኩ ለሰው ቀና መሆን፣ የጓደኞችና የሰዎች ድጋፍ…ናቸው፡፡ ሌላው ደግሞ በአንድ ጊዜ መተኮስ ሳይሆን በሂደት እየሠሩ ማደግና መለወጥ በሚለው አምናለሁ፡፡

እኔ ካለኝ፣ ለብቻዬ መብላትና ማደግ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዬና በዙሪያዬ ያሉ ወጣቶችም እንዲለወጡ እፈልጋለሁ፡፡ ለምን? ቢባል አሁን ስላገኘሁ የነበርኩበት ሁኔታ አይረሳኝም - ሁሌም አስበዋለሁ፡፡ በሰዎችና በጓደኞቼ ቀና ድጋፍና ትብብር ነው ለዚህ የበቃሁት፡፡ እነሱም ድጋፍ ካገኙ ሊለወጡ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ ሰው ተለውጦ ማየት ደግሞ የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡

ስለዚህ በ2004 ዓ.ም መሬት ቆፍረውና አዘጋጅተው ዘር ያልነበራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ዘር ከቤት ስላልነበረኝ ከአሰላ አካባቢ ሦስት መኪና የድንች ዘር አስመጥቼ፣ “ድንች የምትፈልጉ ወስዳችሁ ትከሉ” አልኳቸው፡፡ እነሱ የፈለጉትን ያህል ከወሰዱ በኋላ ቀሪውን ለራሴ ተጠቀምኩበት፡፡ የእርሻ ስሜት ያልነበረው አንድ ሾፌር ልጅ አለ፡፡ ወሬውን ሰምቶ መጥቶ “ይህን ነገር እኔም መስራት እፈልጋለሁ፡፡ ለምን አትሰጠኝም?” አለኝ፡፡ “አንተ መሥራት ከፈለክ ደስ ይለኛል፡፡ እኔ የሥራ ሰው እወዳለሁ፡፡ እሠራለሁ ብቻ ሳይሆን፣ መሥራት ምን እንደሆነ አውቀህ ነው መግባት ያለብህ” አልኩት፡፡ “እሺ! ምንድነው ማወቅ ያለብኝ ነገር?”  በማለት ጠየቀኝ፡፡ “በመጀመሪያው አገኛለሁ ብቻ ብለህ ገብተህ ካላገኘህ ልትጐዳ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ወደፊት እንደገና ሠርቼ ማግኘት እችላለሁ ብለህ ካመንክ ውሰድ” አልኩት፡፡ የፈለገውን ያህል ከወሰደ በኋላ “ማስተከያ የለኝም” አለኝ፡፡ ከኪሴ ከፈልኩለት፡፡ “ማዳበሪያም የለኝም” አለ፡፡ ያንንም ገዛሁለት፡፡ ሌላም የሚያስፈልገውን አድርጌለት ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ያ ልጅ “ባዶ እጄን ፍሰሐ ጋ ሄጄ ባደረገልኝ ድጋፍ አሁን ተጠቃሚ ሆኛለሁ” በማለት እየተናገረ ነው፡፡

ለዘሩ ግዥ ምን ያህል አወጣህ?

50 ኩንታል ለሚጭነው መኪና 27ሺህ ብር፣ 42 ኩንታል ለጫኑት መኪኖች ለአንዱ 26ሺህ ለሁለቱ 52ሺህ ብር፣ በአጠቃላይ ከሌሎች ወጪዎች ጋር ተደምሮ ወደ 80ሺህ ብር ወጪ አድርጌአለሁ፡፡

አሁን ካፒታልህ ምን ያህል ደርሷል?

ሰዎችን ስለምረዳና ስለምደግፍ፣ ወንድሞቼን ስለማስተምርና ቤተሰብ ስለማስተዳድር፣ ብዙ ሰው ገንዘብ የምይዝ አይመስለውም፡፡ እኔ ግን በሂሳብ ነው የምሠራው፡፡ በየዓመቱ ከማገኘው ገቢ፣ ይህን ያህል መረዳት ላለበት ሰው፣ ይህን ያህል ተቀማጭ፣ ይህን ያህል ደግሞ መንቀሳቀሻ…እያልኩ አስልቼ ነው እንጂ “ምንም ሳይኖረኝ ተነስቼ አይደል እዚህ የደረስኩት” በማለት ዝም ብዬ የማባክነው ነገር የለም፡፡ አሁን በሆለታ ከተማ ሁለት ቦታ ገዝቻለሁ፡፡ ቤት ሠርቻለሁ፤ ቤተሰባችን ከብቶች አልነበሩትም፡፡ አሁን ግን የእርሻ በሬዎችና ለቤተሰቡ ጥቅም የሚሰጡ ከብቶች አሉ፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ እነዚህ በቋሚ ንብረት የሚያዙ ሲሆን 1.8 ሚሊዮን ብር ይገመታሉ፡፡ 1.8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተንቀሳቃሽ ንብረትም አለ፤ በአጠቃላይ 3.6 ሚሊዮን ብር ያህል ካፒታል ይገመታል፡፡

ከቤተሰብ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ኡይ! እኔ እናቴን በጣም ነው የምወደው፡፡ እሷ ለእኔ ሁሉም ነገር ናት፤ እኔም ለእርሷ እንደዚያው ነኝ፡፡ የከተማ ቦታ ገዝቼ እዚያ ግቢ ብላት እምቢ ስላለችኝ ሌላ አካባቢ የሠራሁትን ቤት ትቼ፣ እሷ አጠገብ ቤት ሠርቼ አንድ ሰፈር ነው የምንኖረው፡፡

ትዳር መሥርተሃል?

አዎ! በ1998 ከወ/ሮ ጽጌ ቲመርጋ ጋር ትዳር መሥርተን የአራት ዓመት ወንድና የሁለት ዓመት ሴት ልጅ አፍርተናል፡፡ አሁን ያለሁበት ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተችው ባለቤቴ ናት፡፡ የእኔ ሥራ ከቤት ውጭ ያለው ነው፡፡ የእሷ ግን በሁለቱም ነው፡፡ እርሻውም ላይ እየሠራች የቤት ውስጡንም ትሸፍናለች፡፡ ልጆች የማሳደግ ከባድ ትግል፣ ፈተናና ጫናም ሳይዘናጋ ማለት ነው፡፡ እኔ እንዳሁኑ ከአካባቢው ወጣ ስል እሷ ናት እኔን ተክታ ሥራውን የምትመራው፡፡ እርሻው ቦታ ስታሠራና ስትሠራ ቆይታ፣ ወደ ቤት ተመልሳ ደግሞ ለሠራተኞቹ የሚበሉት ነገር ሠርታ ትወስዳለች፡፡ ዘና ታደርገናለች፡፡ እሷ፣ በቤትም በውጭም አለኝታዬና ለዚህ ያበቃችኝ ቀኝ እጄ፣ ሚስቴም፣ እናቴም፣ ሁሉም ነገሬ ናት፡፡

አስተምሯቸዋለሁ ብለህ ትምህርትህን ያቋረጥክላቸው ወንድሞችህ የት ደረሱ?

ሁለት ወንድምና ሁለት እህቶች አሉኝ፡፡ አንድ የዘመድ ልጅም ከእኔ ጋር በመኖር እየተማረ ነው፡፡ አንዱ ወንድሜ በ2004 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቆ አሁን ሥራ ይዟል፡፡ ሌላኛው ወንድሜ ደግሞ ሾፌር መሆን ስለፈለገ በትምህርት አልገፋም፡፡ አሁን መንጃ ፈቃድ እንዲያወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረኩለት ነው፡፡ የጭነት መኪና ለመግዛት እያሰብኩ ሰለሆነ የእሱ መንጃ ፈቃድ ማውጣት በጣም ጥሩ ነው፡፡

የወደፊት ዕቅድህ ምንድነው?

በፊት በበሬ ነበር የማርሰው፡፡ በ2004 ዓ.ም በበሬ ማዳረስ ስላልተቻለ ትራክተር ተከራይቼ ነው ያረስኩት፡፡ ወደፊት ግን የራሴን ትራክተር የመግዛት ዕቅድ አለኝ፡፡ ሌላው ደግሞ ዘመናዊ መሳሪያዎች በመጠቀም በአግሮ - ኢንዱስትሪ፣ ምርቶቼን ፕሮሰስ በማድረግ እሴት ጨምሬ የማቅረብ ዕቅድ አለኝ፡፡

ለሰዎች ካደረግኸው ድጋፍ ደስ የሚልህና የማትረሳው አለ?

አዎ! ታምራት ገ/የሱስ የተባለ የአክስቴ ልጅ አለ፡፡ ታምራት ባለ ትዳርና የልጆች አባት ነው፡፡ ታምራት ከቁጠባ ማህበር ገንዘብ ተበድሮ ዕዳውን መክፈል ስላቃተው ባለቤትና ልጆቹን ጥሎ ከአገር ለመሰደድ መወሰኑን ሰማሁ፡፡

አፈላልጌ አገኘሁትና “እዚህ ሠርተህ ማግኘት እየቻልክ ለምንድነው እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ውሳኔ ላይ የደረስከው?

ችግርም ከመጣ እኔ አለሁልህ፤ የትም አትሄድም” ብዬ መሬት፣ ዘር፣ ማዳበሪያና ውሃ ሰጥቼ እንዲያለማ አደረኩ፡፡ ታምራትም ምርቱን ሸጠና ዕዳውን ከፈለ፡፡ ሳር ቤት ውስጥ ነበር የሚኖረው፡፡ አሁን፣ ስደቱና የቤተሰቡ መበተን ቀርቶ ቆርቆሮ ቤት ሠርቶ ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር በደስታ እየኖረ ነው፡፡

ለወጣቱ የምታስተላልፈው መልዕክት አለህ?

አዎ! ወጣቱ ከትንሽ ተነስቶ በሂደት ማደግ አይፈልግም - በአንድ ጊዜ መክበር ነው ፍላጐቱ፡፡ ስለዚህ አርአያ ለመሆን 20 ወጣቶችን አደራጅቼና እንዳይበታተኑ አብሬ ተደራጅቼ የዶሮ እርባታ ለመጀመር ቤት ሠርተን ፈቃድ አውጥተን ጨርሰናል፡፡ በሚቀጥለው ወር 1,000 ጫጩቶች እናስገባለን፡፡

በመጨረሻም፤ እኔ እንዳድግና ትልቅ ቦታ እንድደርስ ለሚፈልጉትና የተቻላቸውን ድጋፍ ሁሉ ሲያደርጉልኝ ለነበሩት ለአቶ ዲሪባ ፈይሳና ለወ/ሮ አፀዱ ወልዴ እንዲሁም ለመላ ቤተሰባቸው የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

 

 

 

Read 5860 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:12

Latest from