Monday, 08 November 2021 00:00

“ሀገራችን የገጠማት አስከፊ ፈተና በውይይትና በድርድር ሊፈታ ይገባል!!” - ኮንግረስ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ሀገራችን  ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት እጅግ አስቸጋሪና አስከፊ የሆኑ ሁኔታዎችን ሲጋፈጡ የኖሩ ቢሆንም፣ በተለይ ከ2008 ዓ.ም ሕዝባዊ ንቅናቄ ጀምሮ እስካሁኗ ቀንና ሰዓት ድረስ እጅግ ከባድ የሆነ የስቃይና የመከራ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ። ሀገራችንና ሕዝባችን ይህን እጅግ ከባድ የሆነ የስቃይና የመከራ ጊዜ እንዲያሳልፉ ካደረጋቸው ሁኔታዎች አንዱና ዋነኛው የሀገሪቱ የውስጥ ችግርና የሰላም እጦት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የውጪ ኃይሎች ተፅዕኖና ጫናም የሀገራችንና የሕዝባችንን ስቃይና መከራን እጅግ ያከበደ ሆኗል።
ሀገራችንና ህዝባችን እያሳለፉት ያለውን ይህን ስቃይና መከራ ለማስቀረት ሲባል በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ እንደዚሁም የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ተቆርቋሪ ወገኖች ለመንግስትም ሆነ ለግጭት ተሳታፊ ሀይሎች ሁሉ ልዩ ልዩ ምክረ ሀሳቦችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ከነዚህ ምክረ ሃሳቦች አንዱና ዋናኛው ማንኛውንም የሀገሪቱን ፖለቲካዊ  ችግሮችን ተከትለው የሚመጡ ግጭቶችን ሁሉም ወገን ከኃይል ይልቅ በሰላማዊና በውይይት የመፍታት አማራጭን ማስቀደም እንደሚገባ ሲገልጹና ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በመሆኑም ለሀገራችን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮች ዋነኛው የመፍትሄ መንገድና ቁልፍ አማራጭ ሰላምና ሰላማዊ መፍትሔ ብቻ ነው። ስለዚህ ከማንኛውም አስፈላጊ ከሆነ ወገንና አካል ጋር ሁሉ በሰላም መነጋገር፣ መወያየትና መደራደር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይም በሰላም መደራደር በሁሉም ወገኖች ዘንድ አስፈላጊ መሆኑ ከልብ ሊታመንና ሊሰመርበት ይገባል። የሀገራችን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታትና ለማስተካከል ሰላማዊ የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርቡ ወገኖችን ምክረ-ሃሳብም ሆነ ጥያቄ ሁሉም ወገን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድና ከምንም ነገር በላይ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይገባል።
በተለይም ሀገርንና ህዝብን እየመራ ያለው መንግስት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን እንኳን ሆደ ሰፊ ሆኖ የሰላም አማራጭን ሊያስቀድም ይገባል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ሰሜን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነትም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው ግጭት ሁሉ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለውም ሆነ መቋጫ ሊበጅለት የሚችለው በሰላማዊ መፍትሄ አማራጭ፣ በውይይትና በድርድር ነው።
ስለዚህ በሀገራችን ሰላምን ለማረጋገት መጣርና የሰላም አማራጭን የማስቀደም ኃላፊነትና ግዴታ የመንግስት ወይም የመንግስታዊ አካል ጉዳይ  ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብና የዜጎችም የጋራ ጉዳይ ነው። እንደዚሁም የኢትዮጵያን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታትና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ከችግር፣ ከስቃይና ከመከራ ለመታደግ ይመለከተናል፤ ያገባናል፤ ባለድርሻ አካል ነን የሚሉ ወገኖችን ሁሉ የሚመለከት ኃላፊነትና ግዴታ ነው።
በሀገራችን በቀጣይ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የብሔራዊ መግባባትና የሰላም ውይይት መድረክም ከላይ እንደገለፅነው፤ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነ የሰላም መፍትሔ ለማምጣት የታለመና በዚሁ ልክ የታመነ ሊሆን ይገባል። ከዚህ በኋላ በሀገራችን ለፖለቲካ ትርፍና ፍጆታ ተብሎ የሚደረግ ሩጫም ሆነ የሚዘጋጅ መድረክ ካለ ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደታየው ሁሉ ምንም ፋይዳ የማያመጣና ውጤት አልባ ሆኖ ሊጠናቀቅ የሚችል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ስለዚህ መድረኩ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ሀሳብ በአግባቡ በማስተናገድ፣ ሀሳቦች በግልፅና በተገቢው መንገድ ለውይይት የሚቀርቡበትን ሁኔታ መፍጠር መቻል አለበት። ስለዚህ፡-
1. በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችም ሆኑ በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት እያካሄዱ ያሉ ክፍሎች ሁሉ ውጊያና ግጭት አቁመው ወደ ሰላም መንገድና እርቀ ሳላም ውይይትና ወደ ድርድር መድረክ እንዲመጡ አጥብቀን እንጠይቃለን።
2. በሀገራችን በሰላም ሚኒስቴርና በሌሎች ወገኖች የጋራ አስተባባሪነት በቀጣይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የብሔራዊ መግባባት፣ የውይይትና ድርድር መድረክ ሁሉንም ወገን የሚያስተናግድ አሳታፊ፣ አካታች፣ ግልፅ ለሰላምና ለእውነተኛ ብሔራዊ መግባባት ዓላማ ቅድሚያ የሚሰጥ እንዲሆን፤
3. በመድረኩ ላይ የሚመለከታቸው ወገኖችና ባለድርሻ አካላት አለን የሚሏቸውን ምክንያቶች፣ ሃሳብና አጀንዳዎችን በአግባቡ የሚያቀርቡበትና የሚያስተናገዱበት ግልጽና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር፤
4.  የብሔራዊ መግባባት ውይይት በዋናነት የሕዝብ ለሕዝብ፣ የዜጎች፣ ለዜጎች፣ ማኅበረሰቦች ከማኅበረሰቦች፣ ብሔሮች ከብሔሮችና ከብሔረሰቦችና  የተለያየ ሀሳብ፣ አቋምና ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ሁሉ የጋራ መግባባትን ለማምጣት የሚካሄድ ስለሆነ አዘጋጁ አካል መድረኩ ይህን በአግባብ ማካተቱንና ከሁሉም ወገን የሚቀርቡ ሃሳቦችንና አጀንዳዎችን  ያስተናገደ ወይም የሚያስተናግድ መሆኑን እንዲያረጋግጥ፤ ይህንን እንደ አስፈላጊነቱ ለሕዝብ በግልፅ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን።
5. የመድረኩ አዘጋጅ አካል በእንደዚህ ዓይነት ሀገራዊና ሕዝባዊ መድረኮችና ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ሲገባቸው ተገቢ ባልሆነ መንግድ እየተገፉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ድርጅቶችን፣ ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን፣ ሙያ ማኅበራትንና ሌሎችም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ አካላትን እንዲያካትትና ማካተቱም በአግባቡ እንዲረጋገጥ እንጠይቃለን።
ክብር፣ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ!!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም


Read 2245 times