Sunday, 07 November 2021 17:35

«የጠወለገች ቅጠል»

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(6 votes)

የልባችን አፈር ላይ የበቀለው የታሪክ አበባ አንድ ቀን ውሃ ሳናጠጣው፣ ፀሃይ ሳናስነካው ይደርቅና ዛሬም በትላንት ከፈን ተገንዞ  እንቡጥ ፅጌረዳነቱ በጠወለጉ ቅጠሎች ይገለፃል። ያቺ የጠወለገች ቅጠል ህይወትን  የምናይባት ብርሃን የነበረች ናት...  የፍቅርን “ሀሁ” የቆጠርንባት፣ የሃዘንን ህመም ያየንባት፣ ጉድፋችንን መመልከቻ መስታወት ነበረች።
ያቺ የጠወለገች ቅጠል፣ የጊዜን ሞሳ በአንቀልባ ይዘን እሹሩሩ ያልንባት፣ ሞትን በህይወት የተካንባት የሁልጊዜ ንቃት ነች።  ያቺ የጠወለገች ቅጠል የዘለዓለም ንግርት ናት። በዚያች የጠወለገች ቅጠል ላይ የተፃፈው የመጠላለፍ ታሪክ የኛ ነው። በዚያች የልጅነት ቡረቃ፣ እዚያ ዳር አፈር ፈጭተን በተጫወትንበት፣ ውሃ በተራጨንበት ምድር ላይ እንደ ጠላት ለመተያየት የደረስን የውሸት ጓደኞች እኛ ነበርን። እሷ እያለች እንዳልነበረች በዝምታ የረሳናት እኛ ነን።
 ያንን ዐይን ለዐይን እየተያዩ የማውራትን ድንቅ የጓደኝነት  ስሜት፣ በድን በመሰለ ሬሳ ለወጥነው። እንደ አቅሚቲ የገዛናትን ስጦታ ተዓምር በሚመስል መደነቅ እንዳልተሰጣጣን... ፈልጋን እንዳልመጣች፣ ፈልገናት እንዳልሄድን፣ እንደ ይሁዳ ለአንድ ዲታ ስመን አሳልፈን ሰጠናት። ጓደኝነታችን ላይ የክህደት ጭቃ ቀባን...የቅራኔ እሾህ አበቀልን...መዋደድን በገንዘብ ለወጥን...እንደ ይሁዳ፡፡ በዚያም ገንዘብ ሳንጨፍር፣ እንደ ልጅነታችን ሳንቦርቅ እዚህ የስደት ዓለም ውስጥ ያለ ከልካይ ገባን። ያ የልጅነት ዘመን ይናፍቀኛል። ደግሞም እፀየፈዋለሁ።  የዋህነት፣ ተቃቅፈን የተኛንበት፣ ጎርምሰን ሲጋራ ተቀባብለን ያጨስንበት..ከቤቷ ጠላ ይዛ ስትመጣ...ያ ጉርድ ቀሚሷን እየሳበች “አትጨማለቅ በደንብ ጠጣ” ስትለኝ፣ ደግሞ ስንስቅባት...ከእናቷ የሰረቀችውን ገንዘብ ለእኛ አምጥታ ስትሰጠን...ጉንጬን እየሳመች ንፁህ ጓደኝነቷን ስትገልፅ ...ይሄ ሁሉ ይታየኛል። እንዲህም ሆና ወደ እዚያ የሞት ደፍ መራናት። ተያይዘን ጠፋን። ሁላችንም ሞኞች ነበርን...ያቺ ትዕግስት ዛሬ እንዴት ሆና ይሆን?
በትዝታ ታንኳ የዃሊት እጓዛለሁ። ያ መንደር፣ ያ የበቀልንበት፣ እትብታችን የተቀበረበት...ሮጠን ያልጠገብንበት ...ጊዜ እንዲሁ ሊረሳ ጫፍ ደረሰ። ስንሰባሰብ ሳቅ ይበዛ ነበር። አሁን ግን ክህደት የእንባን ትዝታ መርቆልናል። ሚኪያስ፣ ትርሲት...እኔ... አለሙ...ያቺን ምስኪን ትዕግስትን ሽጠናት ነበር...እንጠጣ ብለን ይዘናት ወጣን። እንደ የዋህነቷ እኛን አምናን ወጣች። በዚያ  እድሜዋ ውስጥ ማመን ነበር። ልጅነት የማመን እሴት ነው። በዚያ ጊዜ ነበር ለአንድ ሽማግሌ የሰጠናት። ወደ እዚያ ስትሄድ ስመናት ነበር። አይዞሽ ብለን አበረታናት። ባትፈልግም ጥቂት ብራንዲ ጋበዝናት። ልብሷን አሰማመርነው።  ሽቶ  አርከፈከፍን... ያ ሽቶ ዘለዓለም ከሰውነቷ አይጠፋም። ጠረኑ የክህደት ነው። እንባዋ ቢመጣም እኛን ብላ ሁሉን አደረገች። ሂጂ ወዳልናት ቦታ ሄደች።  ደጋግመን ሳምናት...ትከሻዋን ቸብ አድርገን ገፋናት...እሷ የዋህ ነበረች...እሷ ምስኪን ወፍ ነበረች... እሾህ ሲያደማት ዜማዋ እንደሚያምር ወፍ ናት። ስቃይዋ ሳቅ ነበር። መበደሏ በዝምታ ክርታዝ የተሸፈነ ሰመመን ነው። እሷ የዓለም ታሪክ ላይ የበቀለች ምስኪን ነበረች።  አንድ ክፍል ውስጥ ከተትናቸው። ድንግልናዋ በማታፈቅረው ሰው ተደፍራ ተቋጨ። እዚያ መሃል ጠፋች። የማናውቃት ሴት መሰለች።  ተስፋ መቁረጥ ሊበላት እንደ አሞራ ዞራት...ሙት ነበረች። የእኛ ክህደት ገድሏታል...ጓደኝነት እንዲህ ነበር የሚገለፀው? ....
“እንዲህ ታደርገኛለህ?!” ብላ አለቀሰችብኝ።
ምንም እንደማላውቅ ነገርኳት። እና በዚያ ሽማግሌ የተጀመረው በሌላ ወንድ ቀጠለ። እኛ ሳናውቀው ተለወጠች። ለሁሉም ወንድ እግሯን የምታነሳ ሴት ሆነች። እኛ ህይወቷ ላይ ጥቁር ጠባሳ ነን። መዋደድ አልገዛንም ነበር። ፍቅርን ከገንዘብ አሳንሰናል። እምነትን በክህደት ለውጠናል። እኛ እንደ እሷ የዋህ ባንሆንም ሞኞች ነበርን። ክህደት ያደፍጣል እንጂ ድንገት እንደማይመጣ አውቃለሁ። ሁሉም ነገር የውሸት ነበር። ፍቅራችን ሀሳዊ፣ መተቃቀፋችንም የማስመሰል ድርጊት ነው። ስሞሻችን ጊዜያዊ ነበር። ዓይናችን ታውሯል።   የጓደኝነት መሬት ላይ የበቀልን አረም ነበርን።  እኛ መጥፎዎች ነን። አሁን እንኳን ጊዜ ሄዶ ሁሉን ነገር አልቀየረም።
ከዓለሙና ትዕግስት  ውጪ ሁላችንም ወደ ስደት ተጓዝን። ስሄድ እንባዋ ደም ሆኖ ይጠይቀናል አልኩ።  ሴተኛ አዳሪ የመሆኗ ጉዳይ እኛ ነን።  ግን ትረሳናለች? ጓደኝነት ይሄ ነው? ቅር ይላል። የራሴ ባሉት ጓደኛ መከዳት አንገት ያስደፋል። አሁን ሁላችንም ተጠፋፍተናል። አንደዋወልም... የት እንደደረሱ አላውቅም ...የት እንደደረስኩ አያውቁም።
ማህበረሰብ ተቀባብሎ አማት። “ደግሞ በልጅነቷ ወንድ ላይ” አላት። የእኛን የመጠላለፍ ታሪክ አያውቁምና። የእኛን የመበዳደል ሴራ አይረዱምና። ትዕግስት በቤተሰቧ ሳይቀር ተወገዘች። “አንድ ሃጢያት የሌለበት ሰው የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውር” የሚሉ ሰዎች እሷ ላይ በርትተው በምላሳቸው  ድንጋይ ወገሯት...ይሄኔ በማለት እና በመኖር መሃል ድንበር እንዳለ ገባን። ሰዎች የሚሉትን አይደለም የሚኖሩት አልን..ሰዎች ባያውቁትም ስስ አውሬ ልባቸው ላይ አለ ተባባልን። ይሄ የሚገለጠው በክፉ ጊዜ መሰለን። መውደቅ ሁሉንም ያሳያል እያልን ያቺ የሰፈራችን አስፋልት ላይ አዘገምን...መውደቅ ውድ ነገር ነው። ታድያ ትዕግስት ላይ ያልተከፈተ አፍ፣ ያልተረጨ እርግማን አልነበረም። ሟች አባቷ እንኳን እንደ ባዳ ቡና ላይ አማት...መተማማት የሃበሻ ታሪክ ቢሆንም፣ በቤተሰብ አያምርም። የራስ የሚሉት እንደ ባዳ ሲያማ ቅር ይላል። እና ትዕግስት እንዲያ ነበረች።
...ተለወጠች። ከቤተሰቧ ወጥታ ሴተኛ አዳሪነትን መተዳደሪያ አደረገች። እኛም ራቅናት። ይዘናት በገባነው ዓለም አፍረን ሸሸናት። ከጓደኝነት እሷ ጎደለች። አገለልናት...አንድ ቀን ሰፈር ውስጥ ሆኜ አየዃት። በጭለማ ውስጥ ሆና ወንድ ትጠብቅ ነበር።  ያኔ የተሰማኝ ሃጢያት በንስሃ አይፀዳም። አይታኝ እንዳላየችኝ አለፈችኝ። ዝምታዋ ጦር ነበር። ፀጥታዋ የበቀል ፍላፃ ነው። ከዚያ በኋላ አላየኋትም። ወደ እዚህ ሃገር መጣሁ።
የዚህ ሃገር ሰዎች ከስራ ውጪ ምንም  አያውቁም። እንደዚያ የጓደኝነት ፍቅር አያሳዩም። ሁሉም በራሱ መንገድ ይጓዛል። እኔም ብቻዬን ቀረሁ። ከጥቁር ትዝታዬ ጋር...እናም ህይወት እንዲህ ቀላል አልነበረችም። የመኖር ጣዕም አልገባኝም። የምቀርባቸው አንዳንድ ሴቶች ቢኖሩም የልቤን ደሴት አያዩም። ነፍሴን አይቀርቧትም። የበደል ታሪኬን አያውቁትም። በአንዲት እንስት ህይወት ላይ ጥቁር ጠባሳ ሆኜ ልቧ ላይ መቀመጤን አይረዱም። ሰዎች የልብሴን ንፁህነት፣ የመኪናዬን ማማር፣ የመነፅሬን ብራንድ ያያሉ። እነሱ ያቀረቀረች ነፍሴን አያዩም።  ወደ ሃገር ቤት ልሄድ ተነሳሁ። ቤተሰቦቼን ልጠይቅ፣ ለሰራሁት ሀጢያት ንስሃ ባይሆንም ልክስ ፈለግሁ...
እዚህ ሃገር የሚኖሩ ሰዎች ግብዣ አደረጉልኝ። የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ሄደን በላን...ጠጅ አስቀዳንና ቻው ተባባልን... ብዙ ስጦታ ያዝኩ። ትዕግስትን ካገኘዃት የይቅርታ ደብዳቤ ልሰጣት ፃፍኩ። ምናልባት ከዘጠኝ አመት በኋላ ትረሳኝ ይሆናል። ምናልባት እንደ የዋህነቷ ይቅርታ አድርጋልኝ ይሆናል። ከዓለሙ ውጪ ሌሎች በዓለም ሃገራት እንደ አሸዋ ተበትነዋል። ጓደኝነት ጉድፍን መተያያ መስታወት ነበር። ሳንክደው በፊት ውብ ነበር። በገንዘብ ሳንቀይረው በፊት ሃይል ነበረው። አሁን የልባችን ተራራ ላይ የበቀለ ባይተዋር  ታሪክ ሆኗል።
*   *   *
በሃገሬ ሰማይ ስር ስውል ሁሉም ነገር አዲስ መሰለኝ። ወደ እዚያ የልጅነት እርግማን መንደር አዘገምኩ። መንደራችን አልተለወጠችም። የምንቀመጥባት ድንጋይ እንዳለች ናት። አዳዲስ ሆቴሎች ተከፍተዋል። ልጆች እዚህ መንደር ላይ ይጫወታሉ። የማያቸውን ሰዎች ሁሉ አላወቅኳቸውም። ዐይኔ ዓለሙን ፈለገ። እናቴ እልል እያለች ተቀበለችኝ። ቤታችን አሁንም  ያው ነው። ከዘጠኝ አመት በኋላ የተለወጠ ነገር የለውም። ግቢው እንደ ድሮ በአበባ አሸብርቋል። አበቦች በንፋስ ሃይል ዝቅ ሲሉ ለመሬት ሰጋጅ ይመስላሉ። ሁሉም ነገር ውብ ይመስላል። አንዳንድ ነገሮች እንዲህ ናቸው፤ አይቀሩም። የትደበሰበሰ ሞት አይደለም - ግልፅ የወጣ ህይወት እንጂ። እናቴ በግ አረደች። ውጪ ግቢው ውስጥ ሆነን ተቀመጥን። ጥብሱ ተጠበሰ፣ ዱለቱ ተሰራ፣የቀይ ወጥ መረቅ እንጀራው ላይ ፈሰሰ። ሁሉንም ጎረቤቶች ስትጠራ ስለ ዓለሙ ጠየቅኋት።
“አይ እሱ እኮ...” አለችኝ።
“ምን ሆነ?”
“አደገኛ ሌባ ሆኗል። እስር ቤት ቤቱ ነው። አሁን እስቲ እንደለመደው ሰርቆ ካልተያዘ እጠራዋለሁ” አለችኝ።
“ትዕግስትስ?” ስላት፣ አሁንም ምፀቷን ቀጥላ እንዲህ አለችኝ...
“አይ ታማለች...የዘመኑ በሽታ ነው ይላሉ ...ነገ ከነገ ወዲያ ሄደህ ትጠይቃታለህ”
አዘንኩ...እንባዬ መጣ። ወደ መታጠቢያ ቤት ገብቼ አልቅሼ ወጥቶልኝ፣ ፊቴን ታጥቤ ወጣሁ። ዓለሙን አገኘሁት። የድሮ ወዙ ጠፍቶ አመድ ይመስላል። ፊቱ እሱን አይመስልም። ሰውነቱ ከስቷል። አንዲት ሹራብ አድርጎ በደንብ ተመለከተኝ። ከዚያ፤ “ጓደኛዬ” ብሎ አቀፈኝ።
እኔም አቀፍኩት...ላብ ላብ ይሸታል። የዚህን ያህል እራሱን ለምን ጣለ? አላውቅም...
“እንዴት ነህ?” አለኝ።
“ደህና ነኝ...”
“አይ ሰው! ሌላ ሰው መሰለክ አይደለም እንዴ... ትዝ ይልሃል ኣ ያ ጓደኝነት...ሁሌም ቢሆን አስታውስሃለሁ። ማዘርን ስጠይቃቸው ደህና ነው ይደውላል ይሉኛል። ኦህ! አቤ...ናፍቀኸኝ ነበር ታውቃለህ?”
“እኔም ናፍቀኸኛል በጣም”
“እና እንዴት ነው የውጪ ኑሮ”
“ምንም አይልም... ያው ስራ ነው፣ ድካም ነው...አንዳንዴ ይሰለቻል"
እና ተሰነባብተን ስሄድ ደግሞ እንደሚመጣ ነገረኝ። ብዙም ነገር አላወራሁትም። ፈርቼው ነበር። በጣም ተለውጧል። ለምን እንደሆነ አላውቅም አዲስ ሰው ነው የመሰለኝ....
ሲነጋ ትዕግስት ጋር ልሄድ ተነሳሁ። ጊዜ ማባከን አልፈለኩም። ሄጄ ይቅርታ እጠይቃታለሁ። የይቅርታውን ደብዳቤ እሰጣታለሁ። አብሪያት እሆናለሁ። ሁሉንም ነገር እነግራታለሁ።
የቤታቸውን ግቢ ሳንኳኳ እናቷ ከፈቱልኝ።
“አበበ... “ እያሉ ሰላም አሉኝ።
ወደ ውስጥ ገባሁ። ትዕግስት የተኛችበት ቦታ በመጋረጃ ተጋርዷል። ውስጥ ላይ መብራቱ በርቷል። አጠገቧ ያለው ወንበር ጋ ተቀመጥኩ። ልትነሳ ሞከረች ግን አልቻለችም። ያ ሉጫ ፀጉሯ በሻሽ ተሸፍኗል። አይኖቿ ተጎልጉለው የወጡ ይመስላሉ። ከስታለች።  እንደ ልጅነቷ ንፍጣም ሆናለች። የትልቅ ሰው ጊዜ ሲወድቅ ወደ ልጅነት የሚወስድ መሰለኝ። እጇን ጨበጥኳት። ያተኩሳል...
እንደምንም ከአፌ ቃላት ወጣ፤ “እንዴት ነሽ?”
“ደህና ነኝ “ ብላ አቃሰተች...
ምን እንደምላት ግራ ገባኝ። ለትንሽ ደቂቃ ዝም አልኩ። እንባዬ መጣ...እንዳታየኝ ውጪ ውጪውን ማየት ጀመርኩ። ትንሽ ቆይቼ ማውራት ቀጠልኩ...
“ይቅርታ አድርጊልኝ ትዕግስት!  እዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የከተትንሽ እኛ ነን። ሁሉንም ነገር አውቃለሁ” ብዬ እላይዋ ላይ አቀረቀርኩ። ተንሰቅስቄ ማልቀስ ጀመርኩ...
“ምን ሆነህ ነው? ያ እኮ  ልጅነት ነው አቤ...እኔ አንድም ቀን እንዲህ አደረጉኝ ብዬ ወቅሻችሁ አላውቅም። በእርግጥ እወዳችሁ ነበር። እንዲያ ስታደርጉኝ አልቅሻለሁ። ግን ይሄ የእናንተ ጥፋት አይደለም። መርጬ የገባሁበት ህይወት ነው። እንዴት እንዲህ ታለቅሳለህ...ምን አደረከኝ እና...ወጣት ናችሁ! ገንዘብ ያጓጓችኋል...እኔ ቂም አልያዝኩም...እኔ በእናንተ ላይ ቂም ይዤ አላውቅም። ሁሉም ነገር ያልፋል እኮ አቤ...ዛሬ የሚያሰቃየኝ ነገር ነገ እስከ መረሳት ይደርሳል። ትላንት የበላነውን እራት እንኳን ማስታወስ ይከብደናል። ሁሉም ነገር ይቀራል...ለዚህ አፈር ሰውነት እንዴት ቂም ልያዝ...ለዚህ ቅራሬ ህይወት እንዴት ቂም እይዛለሁ...ትላንት ትላንት እያልኩ በትላንት ታሪክ ተቀብሬ መኖር አልፈልግም። እናንተንም ቢሆን አሁን ድረስ እወዳችኋለሁ። ያ ልጅነት እንዴት ይረሳል? ተያይዘን የሄድንበት መንገድ ምስክር አይሆንም? ፍቅራችን እኮ የውሸት አልነበረም።
የውሸት ጓደኝነት አልነበረም ያለን። ግን ገንዘብ ለውጦታል። ብትክዱኝም ትወዱኛላችሁ። ብትሄዱም ትመጣላችሁ። ባትወደኝ እዚህ ድረስ መጥተህ ትጠይቀኝ ነበር? ዓለሙ ሲያየኝ ይሸሽ ነበር። አንድ ቀን ጠርቼው ቡና አፈላሁለት...እኔ አሁንም እንደምወደው ነገርኩት። አሁንም ፍቅራችን አለ። አሁንም ሞቶ አልተቀበረም...አሁንም የምንዋደድ ጓደኞች ነን። አሁንም በእኔ ውስጥ ትኖራላችሁ ... የተሳሳታችሁት ፍቅርን በመሸጣችሁ ነው። ከእኔ ገንዘብ ማስበለጣችሁ ልክ አይደለም። ይሄ ግን ወጣትነት ነው። የመሸዋወድ ታሪክ በእኛ ጓደኝነት ብቻ አልተፃፈም። የመከዳዳት ታሪክ የዓለም ታሪክ ነው። ወጣትነት ትንሽ የሃፍረት ትርክት አያጣውም። ዓለም እንዲህ ነች። እኔ አሁን ድረስ በመኖሬ ደስተኛ ነኝ። እንደ እናንተ አይነት ሰው በማወቄ እፈነድቃለሁ። ለልቤ ከሰጣችሁት ክህደት በላይ ፍቅራችሁ ይበልጥብኛል። ከመሄዳችሁ ይበልጥ መምጣታችሁን እናፍቃለሁ። እናንተ ጓደኞቼ ብቻ አልነበራችሁ። እናንተ የወጣትነቴ አለም ናችሁ። እናንተን መጥላት አልችልም። እናንተ ላይ ቂም መያዝ አልችልም።  መጥፎ ነገር ቂም ነው - አቤ። እንዲህም ሆኜ ጥሩ ኑሮ እንዲገጥማችሁ እፀልያለሁ። አምላኬ ደግሞ ይሰማኛል። የእሱ ጆሮ የማይሰማው ፀሎት የለም። እግዜር የሁሉም ነገር መዳኛ ነው። እሱ ተስፋ ነው። ክርስቶስ ቂም አላስተማረኝም። ክርስቶስ ያስተማረኝ ፍቅር ነው።  ይቅርባይነትን ነው የሰጠኝ። እና እንዲህ መሆንህ ደስ አይልም። እኔ ነኝ ጨክኜ በእናንተ ላይ ቂም የምይዘው? አየህ አይደል... ብዙ የምፈልጋቸውን ነገሮች ሳገኛቸው እንደማልፈልጋቸው አረጋግጫለሁ። እውነት መስሎኝ የተከተልኩት መንገድ ሁሉ የሃሰት ነበር። ትላንት ያመንኩትን ዛሬ ክጃለሁ። ህይወቴ ስህተት ነበር ታውቃለህ! ያመንኩትም ሃሳዊ ነቢይ ነበር። ምናልባት ማመን አይገባኝ ይሆናል.. ምናልባት እውነትን አላውቃት ይሆናል.... ምናልባት ውድ የመሰለኝ ህይወት  እርካሽ ነው... ህይወቴን በገባኝ ልክ ኖሪያታለሁ... ሞቼ የእዝኔን ቆሎ ዘግኛለሁ...ህይወት ግን እንደገባኝ አልነበረችም...ሞቴም ትንሳዬ አልነበረውም... ጉዞዬ መዳረሻ የለውም። አሁን ህመም ላይ ነኝ። አሁን የስጋ ሞቴን ልሞት አንድ ጋት ይቀረኛል። በዚህም ውስጥ ይቅር የማልለው ሰው የለም። ምድር ላይ አንድም ሰው ቢሆን አትጥላ ...ጥላቻ  ሆድ ውስጥ እንደተቀመጠ መርዝ ነው። አንድ ቀን ይገድልሃል...እኔ ማንንም አልጠላም... ጓደኞቼ ለምን እጠላለሁ... የአንተን ፈገግታ ማየት ጤና ሆኖ ከመኖር ይበልጣል። የጓደኞቼን እቅፍ ማግኘት ዓለምን እንደመ ጨበጥ ነው።”
ማሳል ጀመረች። እንባዬ ጉንጬ ላይ እንደ ምንጭ ይፈሳል...ዛሬም የዋህ ናት - ጊዜ አለወጣትም።  እንደ ወፍ የዋህ ናት። የምትደነቅ ሴት ናት።  ከዚህ በሽታ ጋር ሆና እንኳን አንዲትም ክፋት፣ አንዲትም መጥፎ ነገር  አትናገርም። ይህቺ ሴት ቅድስት ናት። ከዚህ አስከፊ ህይወት ጋር ግብግብ ገጥማ እንኳ  አምላኳን ትወዳለች። ጊዜ የልጅነት ልቧን አለወጠውም። እምነቷን አልቀየረውም። ፍቅሯን አልበረዘውም። “የጓደኞቼን እቅፍ ማግኘት ዓለምን እንደ መጨበጥ ነው” አለች። እንባዬ አልቆመም... ንግግሯ ሲረዝምብኝ  ካቀረቀርኩበት ቀና ብያለሁ።
“አንተ ግን እንዴት ነህ? ወፍረሃል ልበል? ድሮ እኮ ቀጭን ነበርህ.... ድሮ እንዴት ይጣፍጥ ነበር! ለምንድነው አሁን እንደ ድሮ የማይሆነው? ፍቅርህ ብቻ አይቀየር አየህ...ፍቅር ለመስጠት ትላንት ዛሬ ካልክ ጥሩ አይሆንም።”
እናቷ በመሃል መጡና ምግብ እንድበላ ጠየቁኝ። “እሺ” አልኳቸው። እጅ ውሃ አምጥተው አስታጠቡኝ። እንጀራ ትሪ ላይ አድርገው ይዘው መጡ። ወጡን እየጨለፉ እንጀራው ላይ አፈሰሱት። ምስር ወጥ ነው። እየጣፈጠኝ መብላት ጀመርኩ። ለትዕግስት አጎረስኳት። እንደ ድሮ ሳቅ እያለች፣ ያ ሰፊ አፏን ከፈተች።
“እና አቤ አንዲትም ፀፀት እንዳይሰማህ! ከዚህ ሁሉ ዓመት በዃላ የምን ፀፀት ነው ደግሞ። እኔ ኑሮዬን በገባኝ ልክ፣ በተረዳሁት መጠን ኖሪያለሁ። አንዲትም ነገር አልፀፀትም። ብቻ አንዳንዴ እናንተን እናፍቃለሁ። ዓለሙም እንደ ድሮ አይደለም። ሁሉም ነገር ተቀይሯል አሁን። እኔም ከህመም ጋር ነኝ። አልቆጭም ታውቃለህ? መኖር ሲረዝም ደስ አይልም። ህይወቴን ሲቀጥሏት አልወድም። አሁን ሞቴን ነው የምናፍቀው...አሁን ሁሉንም ነገር ትቼያለሁ...”
“ብዙ ነገር ነው የቀለለኝ” አልኳት...
“ብላ እስቲ አሁን ...”
ምግቡን ጨርሼ ተሰነባብቻት ወጣሁ።  ልቤ ላይ የተሰነቀረው ጦር ሲነቀል ተሰማኝ። ደብዳቤውን ግን ሳልሰጣት እረስቼው ወጣሁ። እናም ገረመችኝ.. አንዳንድ ሰው አለ...ሰዎች ላልፈፀሙበት በደል ቂም የሚይዝ...አንዳንድም ሰው አለ...ተበድሎም ቂም የማይቋጥር ... ሰዎች መንገዳቸው ተቃራኒ ነው። ለአንዱ ለጥ ያለው መንገድ ላንዱ እንቅፋት ይበዛዋል። አንዱ የወደደውን አንዱ አይወድም...አንዱ የጠላውን አንዱ አይጠላም...ሰዎች ስንባል ጉዟችን ለየቅል ነው።
ቀኖች  እየፈጠኑ ወደ ሳምንታት ፣ ሳምንታት ደግሞ ወደ ወራት መቀየር ጀመሩ። ጊዜ እንደ አሞራ ክንፍ አብቅሎ ይጓዛል። ወደ እዚያ ባዕድ ሃገር ልመለስ ስል ሁሉንም ነገር አየሁ። አካባቢውን ቃኘሁ። ያደግሁበትን ትንሽ ዓለም አስተዋልኩ። በእርግጥ ሁሉም ነገሮች ከንቱ ነበሩ። መሄዴን ልነግራት ወደ ትዕግስት አመራሁ። ትንሽ ብር ልሰጣት ፈለግሁ። ቤታችን ትንሽ ይራራቅ ነበር። ስደርስ ግቢያቸው ክፍት ነው። ሴቶች  ነጠላ አዘቅዝቀው ለብሰው ይገባሉ። ካፖርት ያደረጉ ትልልቅ አባቶች ይወጣሉ። ለቅሶ ሰማሁ። ልቤ ፈራ። ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኝ ቆምኩኝ። እያመነታሁ ወደ ውስጥ ገባሁ። የትዕግስት እናት ደረታቸውን ይደቃሉ... ብዙዎች እንባቸውን ይህቺ የደም መሬት ላይ  ይዘሩ ነበር። አንድ ትልቅ ሰው አግኝቼ ማን እንደ ሞተ ስጠይቃቸው፣ ትዕግስት አሉኝ። ሁሉም ነገር ተቋጨ። እንዲህ ባለ ጥቁር ሃዘን ተጠናቀቀ...
በየዋህነት ኖራ በየዋህነት የሞተች አንዲት ሴት አውቃለሁ። በፍቅር ኖራ በፍቅር የሞተች አንዲት ሴት አውቃለሁ። ቁስሏ ላይ እንጨት ለሰደዱ ፣ የሃፍረት ዓለም ውስጥ ይዘዋት ገብተው ላፈሩባት የነቁጥን ያህል ቂም ያላዘች አንዲት ሴት አውቃለሁ። ይህቺ ሴት አበባ ነበረች...አሁን ግን ጠውልጋ የጠፋች ቅጠል ናት። ይህቺ ሴት ሟች ብትሆንም ዘለዓለም የልቤ መሬት ላይ ትበቅላለች። ይህቺ ሴት ኃጢያተኛ ፃድቅ ነች። ይህቺ ሴት ለተጠሙ ሁሉ የህይወትን ማይ የምታጠጣ ቸር ናት። እንባዬ መቆሚያ እንደሌለው ምንጭ ይፈሳል። ለዚህች ሴት እንባ ቢያፈሱላት፣ ደረት ቢደቁላት፣ ጥቁር ቢለብሱላት፣ አመድ ነስንሰው ቢቀመጡላት፣ ፀጉር ቢነጩላት ያንሳታል። ንፁህ ሆኖ የተፈጠረ ብዙ አውቃለሁ፤ ንፁህ እንደ ሆነ የሞተ ግን አንድ እሷን አወቅሁ። አሁን ሄዳለች። እነዚያ የዋህ ዓይኖቿ ተከድነዋል። ሰውነቷ በድን ሆኗል፡፡ ስቃይዋ መቋጫ አግኝቷል። አሁን አትሰማኝም...የሃዘኔን ጥልቀት አትረዳም። እንባዬን አታይም...እድሜዬን ሙሉ ልቤ ላይ የተሰካውን ጦር የነቀለች ያቺ የጠወለገች ቅጠል ናት።
አባባ ሆና ስትፈካ አቅፈን እንዳልሳምናት ስትደርቅ ግን አውጥተን ጣልናት። ማንም ይቁም እንጂ ወዳቂ መሆኑ ገባኝ። ማንም እንደ አበባ  ይመር እንጂ ወይቦ እንደሚጠወልግ፣ ጠውልጎም እንደሚጠፋ  ተረዳሁ። መረዳቴ ከሃዘኔ ጋር ተዛንቆ አስለቀሰኝ።
“ሞት ጥልቅ ዝምታ ነው” አልኩኝ...



Read 1733 times