Sunday, 07 November 2021 17:25

የኮሮና ሟቾች ቁጥር ከሚባለው 5 ሚሊዮን በ3 እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባለፉት 22 ወራት በመላው አለም ለሞት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር በሳምንቱ መጀመሪያ ከ5 ሚሊዮን ማለፉን መረጃዎች ቢጠቁሙም፣ ትክክለኛው ቁጥር ግን ከተባለው እስከ ሶስት እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ከ250 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃው ቫይረሱ በመላው አለም ለሞት ከዳረጋቸው ሰዎች መካከል ብዛት ያላቸው ሰዎች የሞቱት በአሜሪካ መሆኑንና በአገሪቱ እስካለፈው ሰኞ ድረስ ከ740 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ብራዚል በ607 ሺህ፣ ህንድ በ458 ሺህ ሟቾች በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ እንደሚከተሉም አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኮሮና ከልብ ህመምና ከስትሮክ ቀጥሎ በአለማቀፍ ደረጃ ለበርካታ ሰዎች የሞት ምክንያት የሆነ 3ኛው ገዳይ በሽታ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ከ5 ሚሊዮን በላይ ነው ቢባልም ከመመርመር አቅም ማነስና በኮሮና መያዙ ሳይታወቅና ሳይመዘገብ በየቤቱ የሚሞተው ሰው እጅግ በርካታ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ቁጥሩ ከተባለው በእጅጉ እንደሚበልጥ መነገሩንም አመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ ያደጉ አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በስፋት በማዳረስ ብዙ ዜጎቻቸውን ለመከተብ መቻላቸውን ያመለከተው ዘገባው፤ ክትባት በስፋት መዳረሱ የሞት መጠኑን በተወሰነ መልኩ ሊቀንሰው ችሏል መባሉንም ጠቁሟል፡፡
ኮሮና ከ8.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያጠቃባትና ከ218 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገባት አፍሪካ፣ ከመላው አለም እጅግ አነስተኛ ክትባት የተዳረሰባት አህጉር መሆኗንና ከ1.3 ቢሊዮን ህዝቧ ውስጥ መከተብ የቻለችው 5 በመቶውን ብቻ እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1135 times