Sunday, 07 November 2021 17:15

"አያ፤ የብሳና ዛፍ ይሸብታል ወይ?” ቢለው፤ ለዛፍ ሁሉ ያስተማረው ማን ሆነና ነው!” አለው

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 አለቃ ገብረ ሃና ከዕለታት አንድ ቀን መንገድ እሄዳለሁ ብለው ይነሳሉ፡፡
“ማዘንጊያ” ይላሉ ሚስታቸውን
“አቤት” ይላሉ ሚስት
“መንገድ ልሄድ አስቤያለሁ”
“ወዴት?”
“ወደ ቆላ ወርጄ የታመመ ጠይቄ፣ የተጣላ አስታርቄ እመለሳለሁ!”
“እንግዲያው ባዶ ሆድዎን አይሄዱም፤ ቆይ ቁርስ ደርሷል፡፡”
“ባዶ ሆዳችንን አደል የተፈጠርን?”
“ቢሆንም ወንድ ልጅ የሚገጥመው ስለማይታወቅ ባዶ ሆዱን አይወጣም”
“ሴትስ የሚገጥማት ታጣለች ብለሽ ነው? ካልሽ እንግዲህ ቶሎ አቅርቢልኝና ፀሃዩ ሳይገርር ልነሳ”
ወ/ሮ ማዘንጊያ ጉድ ጉድ ብለው ቁርስ አቀረቡና አብረው በልተው ተሰነባብተው ተለያዩ፡፡
አለቃ ቆላ ወርደው የታመመ ጠይቀው፣ የተጣሉትን ሁለት ሰዎች ሊያስታርቁ ግቢያቸው ሲደርሱ ጭራሽ ተጋግለው ቡጢ ሊቀማመሱ ግራ ቀኝ ሲሉ ያያሉ፡፡ ከሰዎቹ አንደኛው የተማረና አዋቂ የሚባል ነው፡፡
ሌላኛው ምንም ያልተማረና መሀይም ነው፡፡ መሀይሙ የተማረውን፡-
“አንተ ደንቆሮ! ዶሮ ራስ!” ይለዋል፡፡
“አፍህን ዝጋ ነግሬሃለሁ!” ይላል የተማረው
“ደንቆሮ! ደደብ! ቆርቆሮ!” ይላል መሀይሙ፡፡
“ምንም ልሁን አፍህን ካልዘጋህ ዋጋህን ታገኛለህ!” ይላል የተማረው
አለቃ፤  “ተው እንጂ፤ ተው አይሆንም!” ይላሉ ሊገላግሉ መካከል ገብተው፡፡
መሀይሙ አሁንም፤ “ደንቆሮ! አለቃ፤ ይሄኮ ደደብ ነው!” ይላል፡፡
አለቃ፤ ሁለቱንም በተለያየ አቅጣጫ ገፍተው ይለያዩዋቸዋል፡፡
ይሄኔ አንድ መንገደኛ ድንገት ይደርሳል፡፡ አለቃን ያውቃቸዋል፡፡ ወደሳቸው ቀረብ ብሎ፤
“አለቃ ምን እያደረጉ ነው?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡
አለቃም፤ “ስድብ ቦታውን ስቶብኝ፤ ቦታ ቦታው እየመለስኩ ነው!” አሉ፡፡
* * *
በሀገራችን ቦታውን የሳተ ብዙ ነገር አለ፡፡ ዲሞክራሲ ቦታውን ስቷል፡፡ ዲሞክራቱ አፉን ዘግቶ ተቀምጦ ሐሳዊ - ዲሞክራቱ ከጣራ በላይ ይጮሃል፡፡ የተማረው ፀጥ ብሎ መሀይሙ ያለ እኔ ማን አለ ይላል፡፡
“ምሁሩ ስፒከር ነገር የለው፣ መሀይሙ ባለ አምፕሊፋየር ነው፤” እንደተባለው ነው፤ ይሄ ክፉ
እርግማን ነው፡፡ የሀገራችን ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት
ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት!” ይለናል፡፡ ቋንቋ ለቋንቋ ከመጠፋፋት ይሰውረን፡፡ ቋንቋ ለቋንቋ ካልተደማመጥን፣ ቋንቋ ለቋንቋ ካልተግባባን ለፍትሕ አንመችም፡፡ ቋንቋ ለቋንቋ ካልተናበብን ለሃይማኖት፣ ለጐሣ፣ ለእርስ በርስ ግጭት እንዳረጋለን፡፡
ተወያይተን መፍታት የምንችላቸውን ነገሮች፣ ተጋጭተን ወይም ተዋግተን ካልፈታን ብለን ያዙኝ ልቀቁኝ እንላለን፡፡ ከዚህ እርግማን ይሰውረን፡፡ አንድን ነገር ባንድ ጥሞና መፈፀም ሲገባን፣ ሁለት ሶስት ነገር ካልፈፀምን ብለን ስንራኮት አንዱንም ሳንጨብጥ እንቀራለን፡፡
“ራስ ሴላስ መስፍነ ኢትዮጵያ” የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይለናል፡-
“ዐባይን ከምንጩም ከመድረሻውም በአንድ ጊዜ ለመጨለፍ አይቻልም፡፡ የእናትየው አበባ ሳይረግፍ ልጅ እንቡጥ ትታቀፋለች፡፡ አባትየው ዓለምን ለመተው ዝግጁ ሳይሆን ልጅ እውስጥ ገብቼ ልፈትፍት ይላል፡፡ በአንድ ጊዜ ደግሞ ለሁለት ትውልድ ቦታ የለም!”
አባት ታጋይ ቦታውን ለመልቀቅ ዝግጁ ሳይሆን ተተኪ ትውልድ ቦታውን ልውረስ ይላል እንደ ማለት ነው፡፡ መተካካት ቀላል የማይሆነው ለዚህ ነው፡፡ ወጉ እንጂ ግብሩ ሩቅ ነው፡፡ የ60ዎቹ ዓመታት ታጋዮች፣ በየትኛውም መልኩ ተደራጅተው ይታገሉ የነበሩት ጊዜው የፈቀደውን ያህል ብስለት ነበራቸው፡፡ ትምህርቱ፣ ዕውቀቱ፣ ቅን ልቦናው ነበራቸው፡፡
ትግላቸው ዛሬ አቁሟል? ወይም ነገም ይቀጥላል? የትላንቱ ታሪክ የት ጋ ቆሞ አዲሱ ታሪክ የት ጋ ጀመረ?
ታሪክ ተመራማሪዎች ይፈትሹት፡፡ አንድ ዕውነት ግን አለ፡፡ ያ የዱሮው አስተሳሰብ ዛሬ፤ ሁሉም
ጥላውን ያጠላባቸዋል፡፡ የትግል ልምዳቸው ያው የትላንትናው ነው፡፡
“የነቃ፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ ኃይል ያሸንፋል!” ነው የሁሉ ነገር መፍትሔያቸው፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ ዛሬ ቋንቋ ለቋንቋ መግባባት ያቃተው፡፡ ከንግግር ከውይይት ይልቅ ጦር መነቅነቅ ይቀናናል (Not the word but the sword እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡) ያደግነው በህቡዕ ትግል (Clandestine Struggle) ውስጥ ነውና በሁሉም ወገን ያለን ፖለቲከኞች፤ በሰላም አገርን እናስብ ሲባል የባቢሎንን ግንብ እንደምንገነባ ሁሉ ቃል ለቃል መግባባት እርም ይሆንብናል፡፡ ፅንፍ መለየት (Polarization) ብቻ መፍትሄ ይመስለናል፡፡
ለሀገር ስንል ግማሽ መንገድ እንኳ አብረን እንሂድ መባባል ሽንፈት ይመስለናል፡፡
ገጣሚው እንዳለው፤
“ከዋሸህ ሽምጥጥ፤
ከመታህ ድርግም!”
የሚል ፅንፈኛ መርህ ብቻ ሆኗል የሚገዛን! ትላንት ያልነውን ዛሬ ለመሻር ከቶም ዐይናችንን አናሽም፡፡ ለእለት ፖለቲካ እስከበጀን ድረስ መካድና መካካድ አይገደንም። ዋሽተን ማጣፊያው ሲያጥረን “ፖለቲካ እኮ ነው!” እንላለን፡፡ የመዋሸት ሊቼንሳ አለን እንደማለት፡፡
መንግስትም፣ ፓርቲም፣ ተቃዋሚም፣ ደጋፊም ይሄ ሊቼንሳ ያለው ነው የሚመስለው፡፡ አገር ያጠፋው አገር አለማሁ ይላል፡፡ ሙሰኛው የፀረ ሙስና ህግ አውጪ ይሆናል፡፡ ግፈኛው ስለ ፍትሕ ይሰብካል፡፡
መሀይሙ የተማረውን ቀጪ ተቆጪ ይሆናል፡፡ ቦታ ቦታው ያልተመለሰ አያሌ ወንጀለኛ በናጠጠባት አገር ዕድገት ማምጣት ከባድ ፈተና ነው፡፡ መንግሥት ይዋሻል ወይ? ሙሰኛ አለ ወይ? ፓርቲ ይሰርቃል ወይ?
ተቃዋሚ በአገር ላይ ያሴራል ወይ? ወዘተ ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም፡፡ መልሱ፤
"አያ፤ የብሳና ዛፍ ይሸብታል ወይ?” ቢለው  “ለዛፍ ሁሉ ያስተማረው ማን ሆነና ነው” አለው፤ የሚለው ተረት ነው፡፡



Read 10909 times