Print this page
Sunday, 07 November 2021 17:11

የሴት ልጅ ግርዛት….ለምን?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

በስዊድን የሚኖር አንድ ግለሰብ በሰጠን ጥቆማ መሰረት እንደተረዳነው በስዊድን አገር እንኩዋንስ ሴቶቹ ወንዶቹም እንዲገረዙ የሚያበረታታ ህግ የለም፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደገለጸው::
‹‹…ስለሴቶቹ መገረዝ ጭርሱንም የሚነሳ ርእስ አይደለም፡፡ ስለወንዶች ግን የሚሰጡት መልስ ህጻኑ ይስማማኛል ወይንም አይስማማኝም ብሎ ምርጫውን በማይሰጥበት እድሜ የህጻኑን ገላ መቁረጥ በህጻኑ ሰብአዊ መብት ላይ ጥሰት መፍጠር ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ስለዚህ ስደተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎ ልጆቻቸውን ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ወይንም ወደሀገራቸው በመሄድ አስገርዘው ስለሚመጡ ይህንን ለመከላከል ሲባል ለተወሰኑ ክሊኒኮች ፈቃድ ተሰጥቶ በሰፊ ወረፋ እና በከባድ ክፍያ ለወንዶች ልጆች ግርዛት ይፈጸማል፡፡ ስለሴቶች ግዛት ግን ወሬውም የለም ብሎናል…››
ይህ ጉዳይ ከአሁን ቀደም ከሌላም አገር የተሰማ መረጃ ለመሆኑ ከአስር አመት በፊት በዚሁ አምድ ለንባብ የቀረበው ጽሁፍ ያስረዳናል፡፡ በአንድ ወቅት በጎረቤት ሀገር ኬንያ ናይሮቢ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ (የሥነጾታና የሥነተዋልዶ መብትን በተመለከተ) አንዲት ወ/ሮ አንድ ጥናት ያቀርባሉ፡፡ በቅድሚያ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ ወ/ሮ ማርታ ተሾመ ይባላሉ፡፡ በአውስትራሊያ ጤና ጥበቃ የህፃናትና ማህበረሰብ ጤና ዳይሬክቶሬት ናቸው፡፡
‹‹…የመጣሁት ከአውስትራሊያ ነው፡፡ የጥናቴ ትኩረት ደግሞ በአውስትራሊያ ስላለ የሴቶች ግርዛት ልምድን ይመለከታል›› አሉ፡፡ ታዳሚዎቹ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተገኙ ናቸው፡፡ አብዛኛው እርስ በርስ ተያየ፡፡ ለየራሱም አጉተመተመ፡፡ ከጎኑ ከተቀመጠ ጋርም የሚያወራ ሠውም ይታያል፡፡ ምን ማለታቸው ነው? ሳይሉ አልቀሩም፡፡ ተናጋሪዋ ቀጠሉና የሴቶች ግርዛትን ወደ አውስትራሊያ ይዘውት የሄዱና እዚያም ልጆቻቸውን የሚገርዙትና የሚያስገርዙት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሄዱ ስደተኞች መሆናቸውን በተለይ ደግሞ ሶማሊያውያንና ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት አብራሩ…››
የሴት ልጅ ግርዛት እጅግ አስከፊና ዘግናኝ እንዲሁም ሰብአዊ መብት መጣስ እስከሚባል የሚገለጽ መሆኑ ለብዙ አመታት ሲነገር ቆይቶአል። ቢሆንም ግን ዛሬም መፈጸሙ ያልቆመ አስቸጋሪ ድርጊት መሆኒን የሚያሳየው በ2020 ለንባብ የበቃው የUNFPA ዘገባ ነው፡፡ የሴት ልጅን ግርዛት በሚመለከት ዛሬም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሳሉ ይላል ፡፡ ወደ UNFPA ጥያቄዎቹና መልሶቻቸው ከማምራታችን በፊት ስለድርጊቱ ከአሁን በፊት ያነጋገርናቸው የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የገለጹትን እና ከአሁን የተለያዩ ምንጮእን እማኝ በማድረግ ከተሰሩ ስራዎች ጥቂት እናስነብባችሁ፡፡
ሴት ልጅ በግርዛት ምክንያት በህይወት ዘመንዋ ሦስት የስቃይ ምዕራፎችን ታልፋለች፡፡ አንዱ በመጀመሪያ ስትገረዝ፣ ሁለተኛው ይህች የተገረዘች ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነት ስትፈጽምና በኋላም ስትወልድ ነው ይባላል፡፡ በስቃይ እግርና እጇ ተይዞ አይኗ ታፍኖ አካሏ ይተለተላል፡፡ ይህችው ህፃን በኋላ እናት ስትሆን ሴት ልጇን ይዛ እንደገና ታስገርዛለች፡፡
በብልት አካባቢ /artries/ የሚባሉ ደም የሚያመጡ ትላልቅ የደም ሥሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሥሮች በግርዛት ሳቢያ ሲነኩ ያች ልጅ ከባድ ውስብስብ ችግር ውስጥ የምትገባ ሲሆን በደም መፍሰስ ምክንያትም ግርዛት እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በድርጊቱ ሳቢያ የሚኖረው ህመምና ስቃይ ህፃናቶቹ የሚቋቋሙት አይደለም፡፡ በዚሁ ምክንያት የሽንትና የብልት መስመር ተቀላቅሎ ለፌስቱላ ህመም ልትዳረግ ትችላለች፡፡ ለተለያዩ ቁስለቶች /infections/ የመጋለጥ /የፊኛ፣ ሽንት መቋጠርና አጠቃላይም የመሽናት ችግር፣ በወሲባዊ ግንኙነት ጊዜ ህመም፣ በወሊድ ጊዜ የሰውነት ያለመለጠጥ ስቃይ፣ የወር አበባ በቀላሉ ያለመውረድና ከፍተኛ የህመም ስሜት የመሳሰሉት ሁሉ ከሴት ልጅ ግርዛት ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ችግሮች ናቸው። በግርዛቱ ልዩነት አይነት ስቃዩ ሊበዛም ሊያንስም ይችላል እንጂ አብዛኞቹ ሴቶች የሚጋሩት ተመሳሳይ ህመም አለ፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት እንደሀገርና አካባቢው ወይንም እንደልማዱ ስለሚለያይ በአራት አይነት /type/ ይከፈላል፡፡ ይህም ቀላል ከሚባለው ከመጀመሪያው ደረጃ የሴቶችን ብልት እስከመተልተል /መዝጋት/ ደረጃ የሚደደርሱ ናቸው፡፡
ከላይ ያለውን ሽፋን በእንግሊዝኛ /clitories/ ተብሎ የሚጠራው ወይም የሴቶች የወሲብ ስሜት እንዲቀሰቀስ የሚረዳውን አካል ሽፋን ወይም የሴትነት መለያዋን ሽፋኑን ማንሳት ወይም ራሱን መቁረጥ ፡፡
ይህንኑ ክሊቶሪስ Clitories ሙሉ በሙሉ እና የሴትዋን ብልት ከንፈር አብዛኛውን ወይም በጠቅላላው ማንሳት፡፡
የውጪውን የሴቷን ብልት ከንፈር ሙሉ በሙሉ፣ ከላይ እስከታች እንዲነሳ ማድረግና /infibulation/ በዚህም ብልቱን በመስፋት ለማጥበብ ይሞከራል፡፡ ይሄ ከፍተኛ ክፍተት የሚፈጥር በመሆኑ ለብዙ ህመም የሚያጋልጥ ነው፡፡ ይህ የግርዛት አይነት ግራና ቀኝ ያለው ክፍል ተጣብቆ እንዲዘጋ የማድረግ ሂደት ነው። ይህ የግርዛት አይነት በኢትዮያ በሱማሊያና አፋር ክልሎች በብዛት የሚታይ ነው፡፡
አራተኛው ምድብ ደግሞ በመርፌ /ወይም በተለያዩ ስለቶች/ ግራና ቀኙን ተልትሎ፣ ቆርጦ ወይም አቃጥሎ መዝጋት ወይም ከንፈሩን የመለጠጥ የማስረዘም ሁኔታ ይኖራል፡፡ የዚህ አላማም ምንም አይነት ወሲባዊ ግንኙነት እንዳይደረግና ለወሲብ እንዳይጋብዝ ማድረግ ነው፡፡
በዚሁ ግርዛት ስም የሚፈጸሙ በርካታ ድርጊቶች በተለያዩ የአለም ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የሴቶች ብልት ውስጡ ተቧጦ እንዲቆስል ይደረጋል። ይህም እንዲጠነክርና እንዲጠብ በሚል የሚሠራ ነው፡፡ አሁንም በተመሳሳይ እውስጡ የሚያቃጥል ኬሚካል ወይም ቅጠላ ቅጠል ሌላም ሌላም ነገር በመጨመር ለማጥበብ የሚሞከርበት ሁኔታ አለ፡፡
የግርዛት አይነቶቹ ከመጀመሪያው ሁለተኛው፣ ከሁለተኛው ሦስተኛው፣ እየከፋ ስቃዩም እየጨመረ በጤና በኩልም የበለጠ ውስብስብ ችግር እየፈጠረ የሚሄድ ነው፡፡ ይህ የሴቶች ግርዛት ለምን እንደሚደረግ የተገረዙት ሴቶች በውል የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ አብዛኞቹ የሚያስታውሱት ስቃዩን ነው፡፡ የሴቶች ግርዛት የሚካሄደው በዚህ እድሜ ነው የሚል ገደብ የለውም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ገና አራስ ቤት/ እንደተወለደች/ ልትገረዝ ትችላለች፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ እድሜያቸው ሰባት፣ ስምንት፣ 13 ወይም ሊያገቡ ሲሉ፣ አንድ ከወለዱ በኋላ በድጋሚ የሚገረዙበት ሁኔታ ሁሉ እንዳለ መረጃዎች ጠቁማሉ፡፡
ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት አንዲትን ከወደሐረር የመጣች ሴት ለማዋለድ የነበራቸውን ገጠመኝ እንደሚከተለው ነበር ያወጉን፡፡
‹‹…ሴቶች ለመውድ ወደ ሆስፒታል ሲመጡ በቅድሚያ አዋላጅ ነርሶች ያዩዋቸዋል፡፡ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በመስጠትም ያዋልዱአቸዋል። አንድ ቀን ግን እኔ ተጠራሁ፡፡ ሐኪም የሚጠራው ከባድ ነገር ሲኖር የወላድዋንም ሆነ የምትወልደውን ህጻን ነብስ ለማዳን ሲባል መሆኑ ግልጽ ነው። እኔም የገጠማቸው ይሄው ነው በማለት ፈጠን ፈጠን በማለት ወደማዋለጃ ክፍሉ ዘለቅሁ። ስደርስ ግን የገጠመኝ ሌላ ነገር ነው፡፡ ነርሶቹ ምም አልደነገጡም፡፡ እርስ በርሳቸው እየተያዩ ፈገግ ይባባላሉ፡፡ ሴትየዋም ከምጥ ስሜት ውጭ ምንም አይታይባትም፡፡ ምን ሆናችሁ ነው ብዬ ጠየቅሁ፡፡ አረ ዶ/ር እስቲ ተመልከቺ ….ሴትየዋ ብልትዋ ላይ ቁልፍ አለ ተባልኩ፡፡ የምን ቁልፍ ብዬ ስመለከት ….እውነትም የብልትዋን ከንፈሮች ያገናኘ የሚያብረቀርቅ ቁልፍ አለ፡፡ እኔም ወደሴትየዋ መለስ አልኩና…. የምን ቁልፍ ነው ብዬ ጠየቅሁዋት…..ባለቤቴ ነው የዘጋው…. አለችኝ፡፡ ምን ማለት ነው….ብዬ ስጠይቃት…ሁልጊዜ ከግንኙነት በሁዋላ በወርቅ ቁልፍ ይዘጋዋል…..ስለሚወደኝ ሌላ ወንድ ጋ እንዳልሄድ ብሎ ነው… አለችኝ፡፡ አሁን እንዴት ትወልጃለሽ ….ብዬ ስጠይቃት….እሱ ከደጅ አለ….ቁልፍ ተቀበሉት…አለች፡፡ ነርስ ሄዳ ብትጠይቀው…የሚያዋልዳት ዶ/ር ይምጣ …የሚል መልስ ሰጠ…እኔም ሄድኩና ምን እያደረገ እንደሆነ ስጠይቀው…ያደረገው ትክክለኛ ነገር መሆኑን …በወለደች ቁጥር ከምትሰፋ…በቁልፍ መዝጋት የሚሻል በመሆኑ እና ስለሚወዳት በወርቅ ቁልፍ መዝጋቱን ተናገረ፡፡ ከዚያም መክፈቻውን ከደረት ኪሱ አውጥቶ ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር ለኔ ሰጠኝ፡፡ ካዋለድሻት በሁዋላ መልሰሽ ዘግተሸ መክፈቻውን አምጭ… አለኝ፡፡ በጣም ነበር ያዘንኩት….እኔ ስራዬን ስጨርስ ቁልፉን ከነመክፈቻው ከራስጌዋ አስቀምጬላት ሄድኩ። ሴትየዋ ሰብአዊ መብቷን እንዴት እንደተነጠቀች እና ለተለያዩ መመረዞች ልትጋለጥ እንደምትችል መገመት አያዳግትም…ነበር ያሉት ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ፡፡
የሴቶቹን ጸባይ ለመግራት፣ እንዳይንቀዠቀዡ፣ የወንድ ፍላጎት እንዳይኖራቸው፤የንጽህና ወይም የድንግልና መገለጫ፣ ከልጅነት ወደ አዋቂነት መሸጋገሪያ በሚሉና ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተያይዞ የሴቶች ብልት ትልተላ ይካሄዳል፡፡
በቀጣይ እትማችን ከUNFPA ያገኘነውን በFGM የሚነሱ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን እናስነብባችሁዋለን፡፡

Read 10510 times