Sunday, 07 November 2021 17:07

ኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገዷ ያለው አንድምታ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

 • መንግስት አሜሪካ ውሳኔዋን ዳግም እንድታጤነው ጠይቋል
 • ውሳኔው ከ200 ሺ በላይ ዜጎች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ሲሆን የ1.ሚ ሰዎችን ህይወት ይጎዳል ተብሏል
 • በአጎዋ የምናገኘው ገቢ ከ150 ሚሊዮን የሚበልጥ ብር አይደለም
  • ኢትዮጵያ ያለ አጎዋ ኖራለች፤ ወደፊትም ትኖራለች - የኢኮኖሚው ባለሙያ
                  
            አሜሪካ የተለያዩ ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ ግዛቷ ለማስገባት ከሚፈቅደው የአጎዋ ስርዓት (Africa Growth and Opportunity Act) ኢትዮጵያን መሰረዟን አስታውቃለች፡፡ መንግስት ውሳኔው ከ200ሺ በላይ በሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑንና ከአንድ ሚሊዮን  በላይ ዜጎችንም እንደሚጎዳ በመግለጽ አሜሪካ  ውሳኔዋን ዳግም ታጤነው ዘንድ ጠይቋል።
የአሜሪካ መንግስት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የሚሰጠው ከቀረጥና ኮታ ነጻ የሆነው የንግድ ችሮታ (አጎአ)፤ ከ3 ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ በ2025 የሚጠናቀቅ ሲሆን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ “ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጽማለች” በማለት ነው ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያገዷት።
በአሜሪካ የንግድ ፖሊሲ ከፍተኛ ባለስልጣን በሆኑት አምባሳደር ካትሪን ታያ ይፋ የተደረገው  የፕሬዚዳንቱ የእገዳ ውሳኔ፤ ኢትዮጵያ በሁለት ወራት ውስጥ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ከቻለች በተጠቃሚነቷ ልትቀጥል እንደምትችልም በውሳኔው  ተገልጿል።
በአሜሪካ መንግስት የተላለፈው ውሳኔ ዕድሉን በመጠቀም ምርቶቹን ወደ አሜሪካ በሚልኩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚሰሩትን ከ200ሺ በላይ ሰራተኞችን በተለይም በአገሪቱ ከተከሰተው ህግ የማስከበር ዘመቻ  ጋር  ምንም ግንኙት የሌላቸውን ሴቶችና ህፃናት በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ መንግስት አስታውቋል።
የንግድ ሚኒስቴርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርውሳኔውን አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ፤ ይህ በአሜሪካን መንግስት የተጣለው እገዳ የንፁሃን ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል። የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ በአጎዋ አማካኝነት ሲገኙ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች በማስቀረት፣ በርካታ ዜጎችን በተለይም ሴቶችና ህጻናትን ይጎዳል ብለዋል በመግለጫቸው።
ኢትዮጵያ ከዚህ የቀረጥ ነፃ ዕድል መጠቀም የሚገባትን ያህል አለመጠቀሟን ለአልዐይን ኒውስ የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና ዋና የንግድ ተደራዳሪ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ፤ ኬንያ ወደ አሜሪካ በየዓመቱ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኤክስፖርት ስታደርግ፣ ኢትዮጵያ የምትልከው ግን ከ300 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ነው ብለዋል። ከዚህ ውስጥም ግማሽ ያህሉ በአጎዋ የሚሄድ አለመሆኑንና በአጉዋ ዕድል ተጠቅመን የምንልከው ግማሽ ያህሉን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። የቡና ምርታችን ቀድሞውንም ቀረጥ የሌለበት በመሆኑ የቡና ኤክስፖርት በአጎዋ ተጠቃሚነታችን ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ማሞ አጎዋ የሚመለከተው የአልባሳት ዘርፍንና  የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ብቻ ነው ብለዋል፡፡ የአጎዋ መነሳት የኢትዮጵያ ምርቶች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ውጤቶች ላይ  የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዲዘጉና  ሰራተኞችም እንዲበተኑ ያደርጋልም ብለዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ ታምራት በበኩላቸው፤ ዕገዳው ጉዳት አይደለም ያለው ይላሉ፡፡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሰጥታው የነበረውን ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት ዕድል መሰረዟ አገሪቱ ሌሎች አማራጮችን ለማየት የሚያስችላት ዕድል የሚፈጥርለትና ከጥገኝነት የሚያላቅቃት ይሆናል ብለዋል ባለሙያው፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከሰሀራ በታች  ላሉ የአፍሪካ አገራት የሚሰጠው ከቀረጥ ነፃ የንግድ ችሮታ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን የተፈረመና ለአፍሪካ አገራት የተሰጠ ዕድል ቢሆንም አገራችን በዚህ ዕድል የሚገባትን ያህል ሳትጠቀም ቆይታለች። ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ፤ከዚህ ቀደም የአጎዋ ዕድል የማብቂያ ዘመኑ ተቃርቦ በርካታ የአፍሪካ አገራት እዚሁ አገራችን ውስጥ በኢሲኤ አዳራሽ ተሰባስበውና መክረው አቤቱታ በማቅረብ  እንዲራዘም ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ አጎዋ የተፈቀደው ለተወሰነ ጊዜ እንጂ ለዘለዓለም አይደለም ብለዋል።
“ከዚህ በበለጠ ደግሞ አሜሪካ እድሉን እሷ የምትለውንና የምትፈልገውን አንቀበልም ባልን ቁጥር ለማስፈራሪያነት የምታነሳብን ልምጭ አደርጋዋለች፤ ይህንን ካላደረጋችሁ ዋ እያለችንና እንደ ህጻን እያስፈራራችን እስከ መቼ እንዘልቃለን፤አንድ ቦታ ላይ ማቆም አለብን ብዬ አምናለሁ። በቃ የምንልበት ጊዜ መኖር አለበት ብለዋል። የመፍትሔ  ሃሳብ ሲያቀርቡም፤
“ኢትዮጵያ ያለ አጎዋ ኖራለች፤ ወደፊትም ትኖራለች። መቁረጥ መቻል አለብን፤ ሌሎች አማራጮችን ማየት፣ይኖርብናል፡፡ ወደ አሜሪካ የምንልካቸውን ምርቶች ለአገር ውስጥ ገበያ በስፋት በማቅረብ ከውጪ የሚገቡትን በማስቀረት የውጪ ምንዛሪን ማዳን የምንችልባቸውን መንገዶች ማየት ያስፈልጋል” ይላሉ፡፡
ምርቶቻችንን ለአፍሪካ ገበያ የምናቀርብበትን መንገድም መፈለግ አለብን። የአፍሪካ ገበያ እንደምናስበው ቀላል አይደለም፤ በጣም ሰፊ ነው። የተሻሉና ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ይዘን መግባት እንችላለን። ሁልጊዜ በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካ ጥገኝነት ስር  መውደቅ ትርፉ የምላችሁን ሁሉ አድርጉ የሚል ባርነት ነው። ለእኔ ውሳኔው ከአሜሪካ እስር ነፃ የምንወጣበትና ሌሎች አማራጭ ዕድሎችን ለማየት የምንችልበት በጎ አጋጣሚ ነው-ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ። አያይዘውም “እያንዳንዱ ዜጋ በዚህ የፈተና ወቅት አገሩን ማገዝና ከአገሩ ጎን መቆም ይኖርበታል። በአገሩ ምርት መኩራት፣ የአገሩን ምርት ለመጠቀም መፍቀድና የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ማድረጊያ መንገድ ሁሉ መዝጋት መቻል አለበት” ሲሉ የመከሩት ዶ/ር ተስፋዬ፤ “ይህ በአሜሪካ መንግስት የተላለፈው ውሳኔ ግን አገሪቱ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም የሚያሳይና አድሏዊነቷን የሚያረጋግጥ አሳፋሪ ተግባር ነው” ብለዋል።
ውሳኔው ከመጪው የፈረንጆቹ አዲስ አመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።


Read 9995 times