Monday, 01 November 2021 05:20

(የሔርማን ሔሰ ኪናዊ ጉዞ)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

በዝብርቅርቅ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ምልዑነትን መሻት...
"--የጎልድመንድ ልጅነት ልክ እንደ ሔርማን ሔሰ ሁሉ የሆነ ግር የሚል የተረሳ፣ የበደነ፣ የባከነ የሕይወት ገጽ አለው፡፡ እናቱ ገና ሕይወትን በቅጡ ከመረዳቱ በፊት በለጋነቱ ጥላው ኮበለለች፡፡ ጥቂት ከፍ አንዳለ አባቱ ወደ ማያብሮን የወንዶች ገዳም ወስደው ለመንፈሳዊ ትምህርት ትተውት ተመለሱ፡፡--"


ዓለማየሁ ገላጋይ ከዓመታት በፊት በዚህችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ‹‹ሳያቸው የሚያስቁኝ አምስት መጻሕፍት›› በሚል ርዕስ ስር ለማድነቅ ሲባል ብቻ ስለተጻፈ አንድ የሂስ መጽሐፍ በግርምት አትቶ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ግን ግን ምክንያታዊ እስከሆነ ድረስ ለማድነቅ ሲባል ብቻስ ሂሳዊ ምልከታ ቢጻፍ ችግሩ ምንድን ነው? ሒስን በአሉታዊ የመበላላትና ስህተት ፈላጊነት ጽንፍ የቀነበበው አቀራረባችን፣ ለዓለማየሁ ገላጋይ አድናቆትን ሚዛንን መሳት አድርጎ አቅርቦለት ይሆን የሚል ጥርጣሬ አለኝ። እነሆ ጀርመን ስዊዘርላንዳዊውን ደራሲ ሔርማን ካርል ሔሰን ለማድነቅ ሲባል ብቻ የተጻፈውን ይህን መጣጥፌን እንድታነቡልኝ የአክብሮት ግብዣዬ ነው፡፡
ሔሰ የፈጠራ ስራዎቹን በከፍተኛ ደረጃ የሰራባቸው ከ1900-1945 እ.ኤ.አ የነበሩት ዘመናት ዓለም በተለይም አውሮፓ በሁለት ታላላቅ ጦርነቶች የታመሰችባቸው ጊዜያት ሆነው አልፈዋል፡፡ በእነዚህ ሁለት ጦርነቶች የደረሰው እልቂት፣ ውድመት፣ የተፈጠረው ጥርጣሬ፣ ያስከተሉት የህዘብ ለህዝብ መቃረን፣ በሰዎች እምነት፣ ተስፋ ላይ የተከሰተው ባዶነትና ፍርሀት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ህዝብን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚፋንኑ ኃይሎች፣ ያለ ማንም ከልካይ የሰው ልጅን ወደ እሳት ሲጥሉ፣ ሔስ የውጥንቅጡ አስኳል በሆነች ጀርመን ውስጥ ቅዝዝ ብሎ ታዝቧል፡፡ የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር መውረዱንና ራስን የመፈለግ አታካች ሂደቱ ብዙ እጥፍ መቅለሉን እንዳስተዋለም መገመት አይከብድም፡፡ ዘመኑን ሙሉ ብቸኛ የነበረውን የፍሬድሪክ ኒቼን ስራዎች፣ የሲግሞንድ ፍሮይድና ካርል ዩንግ ሳይኮ አናሊሲስ ስራዎች እንዲሁም የምስራቃውያኑን የህንድና ቻይና ፍልስፍናዊ አስተምህሮቶችም በጥልቀት አጥናቷል፡፡
በሌላኛው ጽንፍ ሕይወቱን ያጠኑት ባለሙያዎች እንዳቀረቡት፤ ሔስ ከልጅነቱ ጀምሮ የከባድ ድብርት ተጠቂ ነበር፡፡ እንዲያውም በ15 ዓመት ዕድሜው ራሱን ለማጥፋት ሞክሮ ለጥቂት ከሞት ተርፏል። እነዚህ ሁሉ ውትብትብ ትርክቶች በልቡ የፈጠሩትን ድብልቅልቅ ሰው የመሆን ቁጭትና ሐዘን በተከታታይ ለንባብ ባበቃቸው Demain, Siddhartha, narcissus and golmund, journey to the east እና the glass bead መጻሕፍቱ እየመላለሰ አቀንቅኖታል፡፡
ሔሰ በየመጻሕፍት ውስጥ ሁሉ የሕይወትን ሁለት ተቃራኒ ጽንፎች የሚወክሉ ሁለት ተቃርኖን የተሸከሙ ገጸባህሪያትን ይፈጥራል፡፡ ሁለት ብቻ… ደሚዬን ላይ ደሚዬንና ሲንክሊየር፣ ሲድሀርታ ላይ ሲድሀርታና ጎቪዳ [ቫሱዳቫ] ናርሲስ ኤንድ ጎልድ መንድ (ዕድል ፈንታ) ላይ ናርሲስ እና ጎልድመንድ… በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚከሰቱት ሌሎቹ ገጸባህሪያት ታሪኩን ለማስቀጠል ሲባል ታይተው የሚጠፉ ዓይነት ቢሆኑም፣ ሁሉም በነፍሳችን ጥልቅ ስርቻ የሚፈጥሩት ንዝረት፣ ከአዕምሮአችን እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል፡፡
ሔርማን ካርል ሔሰ እንደ ኤድ ጋላን ፖ ዓይነት ትንፋሽ ቀጥ የሚያደርጉ ፈጣን ትረካዎችን ለሚፈልጉ አንባቢዎች ሁሉ ሽራፊ ገጽ የለውም፡፡ ቢፈልጉ ገለል ብለው የሲድኑ ሼልደንና ዳን ብራውንን አጓጊ ቅዠቶች ሊያግበሰብሱ ይችላሉ። ሔሰ በየመጻሕፍቱ ሁሉ አንባቢዎቹን የሚያጓጉ ታሪኮች ለመፍጠር ከመጨነቅ ይልቅ የእያንዳንዱን ሰው ነፍስ ልክ መዳፉ ላይ እንዳለች የባልጩት ስባሪ ጠንቅቆ እንደሚያውቃት ሁሉ ወደ ውስጥ፣ ወደ ውስጥ ገብቶ፣ ፅንፍ በሌለው የነፍሳችን ሕዋ የተረሱትን፣ የመከኑትን፣ ያንቀላፉትን፣ የበደኑትን የእያንዳንዳችንን የልጅነትና የሰውነት ሕልሞች ለማንቃት ይታትራል፡፡
ለሔስ ሕሊናና ፈቃድ፣ የሕይወት አባታዊ ጎኖች ናቸው፡፡ በአንጻሩ ጥበብ፣ መሻት፣ ፍትወት ዓይነት ልስልስ ሽልምልም ስሜቶች፣ የሕይወት እናታዊ ጎኖች ይባላሉ፡፡ በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ ጽንፎች የሚመላለሱ ገጸባህሪያቱን በንጽጽራዊ የጽህፈት ስልት አሳስቦ፣ ግር የሚል ሌላ የሕይወት ፈርጅ ለመፍጠር ይታትራል፡፡ ይሄው ሂደት በተለይ የሚያስደንቅ ከፍታ የታየበት በሰላምይሁን ኢዶሳ (ቤቢ)፤ ‹‹ዕድል ፈንታ›› በሚል ርዕስ  የተተረጎመው Narcissus and Goldmund ስራው ይመስለኛል፡፡
‹‹…ሞትና ሐሴት አንድ ናቸው። የሕይወት እናት ፍቅር ወይም መሻት ተብላ ልትጠራ ትችላልች፡፡ ሞት፣ መቃብር ወይ ደግሞ መበስበስ ተብላም ልትጠራ ትችላለች፡፡ እናትየው ሔዋን ነች። የደስታም የሞትም ምንጭ እሷው ነች። እስከ ዘላለም ትወልዳለች፤ እስከ ዘላለም ትገድላለች፡፡ ፍቅሯ ከጭካኔ ጋር ተዋህዷል። ጎልድመንድ ምስሏን በውስጡ ተሸክሞ በቆየ ቁጥር ምስሏ የበለጠ ተምሳሌትና የተቀደሰ እየሆነለት መጥቷል፡፡ መንገዱ ወደ ቃላት ወይም ንቁ ወደ ሆነ የህሊና ጎዳና ሳይሆን ማንነቱን በጥልቀት ወደ ማወቅ፣ ወደ እናቱ፣ ወደ መሻት፣ ምናልባትም ወደ ሞት እንደሚወስደው አውቋል፡፡ የሕይወት አባታዊ ጎኖች ማለትም ህሊናና ፈቃድ የእርሱ ቤት አይደሉም፡፡ ናርሲስ ግን በዚያ ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡…›› ገፅ 132
ይህ መጽሐፍ የተዋቀረባቸው ተቃራኒ አውታር ገፀባህሪያት፣ ናርሲስ እና ጎልመንድ ይሰኛሉ፡፡ ናርሲስና ጎልድመንድ በኪነት ዓለም ከፍ ብለው የተከተቡ፣ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚወክለው የትልቁ አዳም ሁለት ፍጹም የተራራቁ የኑረት ቅኝቶች ናቸው፡፡ ናርሲስ ፍጹም ራሱን የገዛ፣ የተከበረ፣ ቁጥብና ጨዋ የደብር አበምነቴ፣… ጎልድመንድ የነፍስ መሻቱን ብቻ በስግብግብነት እየተከተለ፣ በቤት የለሽ ግድየለሽ አዙሪት ለዓመታት እየተንከራተተ፣ ልክ በአበባ ላይ ጣፍጭ ብናኝ እንደምትቀስም ንብ፣ በሚያልፋቸው አካባቢዎች ሁሉ ከሚያገኛቸው ሴቶች ጋር ሁሉ ለፍቅር የሚቃትት፣ ድንጉጥ ፈሪ ግን ደግሞ ደፋርና ጀብደኛ፣ ብዙ ዓይነት ቅዝምዝም የሕይወት ቅኝቶች እያዳፉ እያባበሉ፣ ወደ ሕይወት ይሉት የኦናነት አዘቅት የሚያንደረድሩት ጉስቁል መንገደኛ…
የጎልድመንድ ልጅነት ልክ እንደ ሔርማን ሔሰ ሁሉ የሆነ ግር የሚል የተረሳ፣ የበደነ፣ የባከነ የሕይወት ገጽ አለው፡፡ እናቱ ገና ሕይወትን በቅጡ ከመረዳቱ በፊት በለጋነቱ ጥላው ኮበለለች፡፡ ጥቂት ከፍ አንዳለ አባቱ ወደ ማያብሮን የወንዶች ገዳም ወስደው ለመንፈሳዊ ትምህርት ትተውት ተመለሱ። በገዳሙ ውስጥ ፍጹም የተገራውንና የሰዎችን እጣ ፋንታ በማጥናት የተካነውን ረቂቅ ሰው፣ በጊዜው የገዳሙ መምህር (በኋላ የገዳሙ አበምነቴ) ናርሲስን አገኘ፡፡ ግር የሚለውና ግን ደግሞ የሚያሳዝን ሙዚቃ እንደ መስማት ነፍስን የሚያርበተብተው በጣም አስፈላጊው ጓደኝነት የተመሰረተው በእንዲህ ዓይነት ሂደት ነበር፡፡
በጎልድመንድ ልጅነት ውስጥ የተረሳውን የእናትነት፣ የሕይወት እናታዊ ጎኖች ጥሪ የተገነዘበው ናርሲስ፣ ጎልድመንድ ገዳሙን ጥሎ እጣ ፋንታውን ፍለጋ እንዲወጣ ውትወታውን ቀጠለ፡፡ ጓደኝነታቸውን በመጠቀም በአስጨናቂ ጥያቄዎች ከበባ ያንቀላፋ ደመነፍሱን አነቃለት፡፡ ልጅ እግሩና ደመግቡው ጎልድመንድ ከአውሮፓ ህዝብ ግማሽ ያህሉን ከጨረሰው ብላክ ዴዝ (black death 1346-1353) ጥቂት ዓመታት በፊት ናርሲስ ያነቃለትን ደመነፍሱንና የእናቱን ጥሪ ተከትሎ ከገዳሙ ወጣ፡፡ አዲስ በተቀበለው የተንከራታችነት አዙሪታዊ ሕይወት እስከ ጽንፍ በተዘረጋው አዳለጭ ህዋ፣ ለማንም ሳያሸረግድ፣ ለማንም ሳያጎበድድ መሻቱን ብቻ ተከትሎ፣ ከቤት ቤት ከሀገር ሀገር ቃተተ፡፡ ከልጅነት ዘመኑ የተቀሰሙት የእናቱ ሽርፋራፊ ምስሎች ሁሉንም ሴቶች በምትወክለው በትልቋ ሔዋን (ምናልባት በማርያም) ምስል ዳብሮና በልጽጎ ከፍ ባለው አድማስ ላይ በራዕይ ተንጸባርቆ ይታየው ጀመር፡፡ በመጀመሪያው ስግብግብ አዙሪትና በቸነፈሩ ዘመናት የገጠመው መሳከርና ለሕይወት መበርገግ ሊገልጹት የሚቻል አይደለም፡፡ ከ"ዕድል ፈንታ" ገጽ 49 ጅምሮ አብዝቼ ልጥቀስ፡-
‹‹…ከዘመናት በፊት የጠፋችው እናቱ ከፊቱ ድቅን ትልበታለች፡፡ ጉዳዩ ትልቅ ደስታ የሚፈጥር ቢሆንም የሚያባብለው ጥሪዋ ግን የት ይሆን የወሰደው?- ወደ ጥርጣሬ እና ወደ ተወሳሰበ ነገር? በእርግጥ ወደ እብደት ምናልባትም ወደ ሞትም ሊሆን ይችላል፡፡… ለእርሱ እናት ማለት ረድኤት ያላት ፍጡር ማለት ብቻ አይደለም፡፡
ፍቅርና ጣፋጭ፣ ረጋ ያለ አስተያየት ወይም ደስታና ተስፋ የሚሰጥ፣ በፈገግታና በማጽናናት የታጀበ መደባበስ ብቻም አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዚህ የሚያባብል ውጫዊ ወለል በታች ፣ የሆነ ቦታ በጣም የሚያስደነግጥ ፍርሀትና የጨለመ ስስት ያለበት፣ በኃጥያትና በሐዘን የተሞላ፣ ውልደትና ሞትን የሚያመጣ ነገር ሁሉ ያለበትም ጭምር ነው[…] ሁሉም ነገር ቶሎ ይጠወልጋል፡፡ እያንዳንዱ መሻት በፍጥነት ይዝላል፡፡ ከአጥንትና ከትቢያ በስተቀር ምንም የሚቀር ነገር የለም፡፡ አዎ አንድ ነገር ግን ይቀራል- መሰረታዊ፣ ጥንታዊ፣ ዘላለም ወጣት የሆነች እናት፡፡ከሚያሳዝነው እንዲሁም ጨካኝ ቢሆንም ፍቅር ከሚታይበት ፈገግታዋ ጋር እንደገና ለአፍታ ታየችው- ክዋክብት ጸጉሯ ውስጥ የሚርመሰመሱባት ግዙፍ ምስል፡፡ እያለመች የዓለም ጠርዝ ላይ የተቀመጠች እና በሚጫወቱ እጆች አበባ በአበባ ላይ እንዲሁም ሕይወት በሕይወት ላይ እየቀጠፈች፣ በቀስታ ስር ወደሌለው ባዶነት ጣለቻቸው፡፡››
ሔስ በየመጻሕፍቱ ሁሉ ሁለት ተቃራኒ አስተሳሰብና አኗኗር የሚያራምዱ ገጸባህሪያትን እየፈጠረ በየዘመኑ የደረሰበትን የአስተሳሰብ ልክ (perception) ከፍ ባለ አቅም ሲያቀነቅን ይታያል፡፡ ሔሰ በጎልድመንድ የሕወይት ሽንቁር የጻፈው ስለ አንድ ሰው ምናልባትም ስለ ራሱ ወይም ሁሉንም ሰብዓውያን ስለሚወክል ስለ ትልቁ አዳም ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይሄው ሂደት ጉዞ ነው… ራሱ ሔሰም እንዳለው፤ ራስን የመሆን ራስን የመፈለግ አታካች ጉዞ … ምልዑነትን የመሻት ጉዞ…
ምልዑነት ፍፅምና የሚመስላቸው ሰዎች ካሉ ተሳስተዋል፡፡ ምልዑነት (totality) በስኬት፣ በብልሀት፣ በጥበብ ብቻ ሳይሆን በውድቀት፣ በሽንፈት፣ በውርደት ጭምር የሚደረስበት ሂደት ነው፡፡ አንድ ሰው ሕይወትን በምልዓት ኖረ ለመባል ምንምን ሳይፈራ፣ ለምንም ሳይደነግጥ፣ በሚያዳልጠው ህዋ ላይ እልፍ ጊዜ ወድቆ እየተነሳ መመላለስ ይኖርበታል፡፡ በሔሰ አዕምሮ የተፈጠረው ጎልድመድ ለዚህ የምልዓት ሕይወት የቀረበ የምናብ ዓለም ሰው ይመስላል፡፡ ሆኖም እጣ ፈንታዎቻችን አብዛኛዎቹ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በሌሎች ሰዎች እጅ ላይ ናቸው፡፡ ሔሰ መጠላለፉ መወታተቡ ለብዙ ንጥቂያና ጭቆና እንዲሁም ኢፍትሃዊነት እንደሚጋብዝ በጎልድምን የሕይወት ቅኝቱ አጉልቶ አቅርቦታል፡፡
ለመሆኑ ሔሰ ምልዑነትን በዋነኛነት እንዲያቀነቅን ገፊ ምክንያቱ ምን ነበር? Jeffrey Shannon የተባለ የwestern Kentucky university አጥኚ ‹‹In the search of new totality; Herman hesse’s Demain›› በተሰኘ ጥናቱ እንዲህ ይላል፡-
‹‹Following the world war one the average man of early twenty century was faced with a massive void in his life as he saw those beliefs to which he had previously held tight, disappear or become disproven with frightening rapidity. Man’s totality in the sense was destroyed and it fell in to the writers of the time to fill that void and to create new totality. In an attempt to do that Herman Hesse penned Demain the story of youth under the pseudonym Emil Sinclair…››
የሔሰ ጎልድመንድ ለሐብትም ሆነ ለተረጋጋ ሕይወት ግድየለሽ መስሎ ሕይወትን በሚረዳበት ልሙጥ አተያይ እየተዳኘ ዘመኑ ሙሉ ተንከራቷል፡፡ የኪነት መክሊቱን ተጠቅሞ በተንከራታችነት ዘመኑ በልቡ የታተሙትን ስዕሎች፣ በንድፍና በቅርጽ ሕልው ሊያደርጋቸው ሞከሯል፡፡ ሔሰ በዚህ መጽሐፉ እያንዳንዱ ደስታ ከሐዘን ጋር ያለው መቀራረብ በቅጡ ለማሳየት ታትሯል፡፡ መጽሐፉ ተጀምሮ እስኪያልቅ ልብን በሚከብዱና ነፍስን በሚያስደነብሩ መንታ ትርጉም ያዘሉ ላቅ ያለ የሕይወት መረዳት የተሸከሙ ሐተታዎች የተሞላ ነው፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ የሕይወት ጥናት ነው ማለቱ ይቀላል፡፡
ሆኖም ይህ የሚያስደንቅ ስኬቱ መጻሕፍቱን የንባብና የጥናት ተመራጭነት አግዷዋቿል፡፡ Mellisa beck የተሰኘች የስነፅሑፍ አጥኚ፣ በአሜሪካ የጀርመን የሥነ- ጽሑፍ ሳምንት በተዘከረበት ወቅት Narcissus and Golmund በሚለው መጽሐፉ ላይ ለሂሳዊ ዳሰሳ ተጋብዛ ቃል በቃል እንዲህ ብላለች፡- ‹‹እንደዚህ መጽሐፍ ለሂሳዊ ጥናት አስቸጋሪ የሆነ ሌላ መጽሐፍ መኖሩን አላውቅም፡፡››
የእነ ሲድኒ ሼልደን መጻሕፍት እንደ ፓስቲ በወረፋ በሚሸጡበት ዘመን፣ የሔስን ስራዎች ለአማርኛ አንባቢ ላስተዋወቁት ተርጓሚችዎ ያሬድ ብርሃኑና ሰላም ይሁን ኢዶሳ ያለኝ አድናቆት ልዩ ነው፡፡ በተለይ ሰላምይሑን ከሔስ የትረካ ስልት ጋር ለመስማማትና የአማርኛን ልቡሰ ጥላ ሀሳቦች ገላጭ ቃላት ለመጠቀም ያሳየው አቅም እንዳስገረመኝ መደብቅ አልሻም፡፡

Read 1021 times