Monday, 01 November 2021 05:18

ብሔራዊ ውይይትና የኦፌኮ አወዛጋቢ መግለጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ያልተሳተፈው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በሚቀጥለው ወር ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ብሔራዊ ውይይት ላይ ለመሳተፍ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል፡፡
እነዚህም በሠሜኑ ያለው ጦርነት እንዲቆም፣ የታጠቁ ሃይሎች የውይይቱ አካል እንዲሆኑ፣ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ተፈተው በውይይቱ እንዲሳተፉ እንዲሁም አወያዩ  በአለማቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት የታመነ አካል እንዲሆን የሚሉ ናቸው። የኦፌኮ መግለጫ  እያወዛገበ ሲሆን ብዙዎችም ትችት እየሰነዘሩበት ይገኛል።
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በብሔራዊ ውይይቱና አወዛጋቢ በተባለው የፓርቲው መግለጫ ዙሪያ ከኦፌኮ ዋና ፀሃፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል። እነሆ፡-


ኦፌኮ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠበትን መግለጫውን ያወጣው በምን መነሻ ነው?
ባለፉት ሶስት ዓመታትም ሆነ ቀደም ብለው በነበሩ ዓመታት የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ፣ በኢትዮጵያ ስር የሰደደና ከምንጊዜውም እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት የሚያግዝ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ ሲጠየቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ደግሞ ስንጠይቀ የነበረው ዝም ብሎ በመግለጫ ብቻ ሳይሆን ይመለከታቸዋል ላልናቸው ሁሉ ጉዳዩን በትኩረት እንዲይዙት ደብዳቤዎችን ጭምር በመፃፍ ነው፡፡ በተለያዩ መድረኮች ላይም ይሄን መልዕክታችንን ሳናስተላልፍ የቀረንበት ጊዜ የለም፡፡
ለምሳሌ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ ለኢፌድሪ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤትና ለሌሎችም ፅፈናል አሳውቀናል፡፡ ያግዙናል ይተባበሩናል ብለን ላሰብናቸው በሙሉ ደብዳቤ ስንፅፍ፣ ለመገናኘት ብዙሃን መግለጫ ስንልክ ቆይተናል፡፡ ይሄን መግለጫም ልናወጣ የቻልነው አሁን የሃገራችን የኢትዮጵያ ሁኔታ ቀውሱ በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም በሃገር ውስጥም ሆነ በዓለማቀፍ ደረጃ  ወደ መጥፎ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን ስለተረዳን ነው፡፡ ይሄን መጥፎ መንገድ ለማስተካከል አሁንም የተወሰኑ እድሎች ስላሉ እነዚያን እድሎች ለመጠቀም የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ይቻል እንደሆነ ብለን ነው ለመንግስት፣ ለገዢው ፓርቲ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለአለማቀፍ ህብረተሰብም ይሄንን ጥሪ ያደረግነው፡፡
በመግጫው አንዱ የጠየቃችሁት ጦርነት እንዲቆም ነው። ጦርነቱ እንዴት ነው መቆም የሚችለው? ይሄን ስትሉ ፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁሞ እርምጃ ወስዶ እንደነበር ምን ያህል ግምት ውስጥ አስገብታችኋል?
የመንግስትን ጥረት እናስታውሳለን። ጦርነቱን በተናጥል ለማቆም ያደረገውን ጥረት እናስታውሰለን፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ ማቆም የነበረበት ስፍራውን ለቆ አልነበረም። የተናጥል ተኩስ አቁሙ እርምጃ ቴክኒካዊ ችግር ነበረበት፡፡ ተኩስ ማቆም ይገባ የነበረው መንግስት የያዘውን ሳይለቅ የሚነጋገሩበት ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ነው። ይሄን ጦርነት ለማስቆም ገለልተኛ አካልት ሁኔታውን ማመቻቸት እንዲችሉ እድሉን መስጠት ይገባል፡፡ ጦርነቱን እንዴት ማስቆም ይቻላል በሚለው ላይ ራሱ ይሄን የሚያመቻችቹ አካላት ይኖራሉ፡፡ ይሄን ምናልባት ለአለማቀፋም ሆነ ለሀገር ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው አካላት ማሳወቅና ጥሪ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ህወኃትና ሸኔ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶች ናቸው። እናንተ በመግለጫችሁ እንደጠቀሳችሁት፣ እነዚህን ድርጅቶች እንዴት ነው የብሔራዊ ውይይት አካል የሚሆኑት?
በሀገራችን ላይ ሽብርተኛ ናቸው የተባሉትም ሆነ አሸባሪ ያሏቻው ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ያውም የፖለቲካ ጉዳይ የለያያቸው። አንዳንድ ጊዜ ተመዝኖ መታየት ያለበት ነገር አለ፡፡ ኦፌኮ ማንም ቡድን ተደራጅቶ ብረት ይዞ እንዲንቀሳቀስ ፍላጎት የለም፡፡ ከመንግስት ውጪ ማንም ታጥቆ እንዲንቀሳቀስ አንፈልግም፡፡ ሆኖም ግን በህዝብ የተመረጠ ህጋዊ እምነት የሚጣልበት መንግስት እስከሌለ ድረስ እነዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች የሆነ ቦታ ላይ እየፈነዱ ይነሳሉ፡፡ እነዚህን ሃይሎች ወይም ቡድኖች እንደ ምንም ብሎ ተነስቶ “አሸባሪ” ማለት ማህበረሰቦችን ወዳልተፈለገ ሁኔታ የሚመራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንድ አካል አሸባሪ ተብሎ ሲፈረጅ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ትህነግ “እኔ ብቻ ካልመራሁ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር መጥፋት አለባት ብሎ ይናገራል” ነው የሚባለው፡፡ ይሄ ለኔ የስልጣን ጥያቄ ነው፤ የስልጣን ሽኩቻ ነው፤ ይሄን ስልጣን ደግሞ ያገኙት እርስ በእርስ በመገለባበጥ ነው እንጂ የህዝብ ድምጽ ታክሎበት አይደለም። ሁሉም ነገር በህዝብ ድምጽ እንዲወሰን እድል ቢሰጥ፣ ዛሬ የገባንብት ቀውስ ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ደርጅቶች በሽብር መፈረጅ እኮ አንዳንዴ ለሃገር ሰላም ተብሎ ተገምግሞ ውሳኔው ሊታጠፍ ይችላል፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ተገምግሞ የማይታጠፈውና የሰላም አማራጮች የማይፈተሹት? ሁላችንም ኢትዮጵያውያን አይደለንም እንዴ? እኛ ከዚህ አንጻር ጉዳዩ ተገምግሞ ሊፈተሸ ይገባዋል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ይሄን የምንለው ዝም ብለን አይደለም። የእነዚህ ድርጅቶች በሽብርተኛ መፈረጅ በሃገሪቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ምን ያህል ቀነሰ? የሚለውን ገምግመን ነው፡፡ ምናልባት በዚህ ጦርነት አንዱ ሃይል አሸናፊ ሆኖ ቢመጣ ወይም መንግስት ቢያሸንፍ የወደመውን መልሶ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ ነው የሚወስድብን? ጦርነቱ አሁን ባለበት ቢቋጭስ ምን ያህል ነው የምናተርፈው? አሁን ባለው እልህ መጋባት ምን ያህል ርቀት መጓዝ  እንችላለን? እነዚህ ጥያቄዎች እኛ እንደ አንድ የሃገሪቱ ዜጎችም ሆነ እንደ የፖለቲካ ፓርቲ በእጅጉ ያሳስበናል። ይሄን ስንል እኛ ያቀረብነው ሃሳብ ብቻ ተቀባይነት ይኑረው ብለን አይደለም። ሌላ አሳማኝ ሃሳብ ካለም ወደ መድረኩ መጥቶ መልካምና አሳማኝ ከሆነ እንቀበላለን። እኛ በዚህ መግለጫችን ከወትሮው በተለየ ተማፅኖ ነው ያቀረብነው። ስለ ሃገራችን የሰላም መንገዶች ነው ተማፅኖአችን፣ ከተሳሳተው አቅጣጫ እንመለስ፤ ከእልህ እንውጣ፤ ሰከን እንበል፤ ስለሁላችንም የጋራ አገር ኢትዮጵያ እናስብ፤ ከጥላቻ መንፈስ መውጣት እንጀምር ነው ያልነው፡፡
በመግለጫችሁ ገለልተኛ አደራዳሪ ወይም ሶስተኛ ወገን እንዲያደራድር ጠይቃችኋል። ይሄን ስትሉ ምን ዓይነት አደራዳሪ ወገን ነው ከሃገር ውስጥ ነው ከውጭ?
እኛ ይሄን ሃሳብ ያቀረብነው ለሃገራችን ሠላም በማሰብ ነው፡፡ ገለልተኛ አካል ስንልም ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ድርድሩ እርባና ቢስ እንዳሆን በማሰብ ነው፡፡ በጦርነቱ በለው፣ ግፋበት፣ ቀጥቅጠው ሲሉ የከረሙ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ወይም ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አሉ፡፡ ድርድሩ ወይም የውይይት መድረኩ ከእነዚህ አጋፋሪነት ነፃ መሆን አለበት፡፡ በስም እገሌ እያልን መጥራት በሚያስፈልግበት ጊዜ ልንጠራ እንችላለን፡፡
አሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍ በኩል ልዩነቶች ግልጽ ሆነው ነው የሚታዩት፤ ለድርድሩም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በአንድ ወገን ከገዢው ፓርቲ ጋር በአንድ ጎራ የቆሙ አሉ በሌላ በኩል በተቃራኒው የቆሙ አሉ። ስለዚህ እነዚህ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በሃገራቸው ችግር መፍትሔ ማምጣት አለባቸው፡፡ ይሄን የአደራዳሪነት ሚና የሚወጣ ከሃገር ውስጥ የማይገኝ ከሆነም ከውጪ ማምጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሃገር ውስጥ ማግኘት ይቻላል።
እናንተ የምትፈልጉት ድርድር ውጤቱ ምን ድረስ እንዲሆን ነው? በአንድ መግለጫችሁ ምርጫ ድጋሚ እንዲካሄድ ጠይቃችኋል፡፡ ከዚህ አንጻር የምርጫውን ጉዳይ ታሳቢ ታደርጋላችሁ?
ይሄን ነገር ደጋግመን ተነጋግረናል፡፡ እኛ የተደረገው ምርጫ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ ነው ብለን አናምንም፡፡ መንግስት አሁን ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በፍጹም ዲሞክራሲያዊና ህዝብ አሳታፊ ምርጫ ተካሂዶ ነው መንግስት የተመሰረተው የሚለውን ግን እኛ አንቀበለውም፡፡ ድርድሩ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የሚደረስበት ስምምነት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ያለፈው ምርጫ ሰላምን አውርዷል እንዴ?  ሰዎች ይሄን ጥያቄ ልብ ብለው ቢጠይቁ መልካም ነው፡፡
የማያስማማ ሁኔታ እስካለ ድረስ በየትም ሃገር እንደሚደረገው ድጋሚ ምርጫ ሊደረግ ይችላል፡፡ እኛ ይሄን መግለጫ ያወጣነው ለሚያመዛዝኑት ነው፡፡ አኛም እኮ ከማንም ባላነሰ ሃገራችንን የምንወድ ዜጎች ነን። እኛ ይሄን ስንል ስልጣን ለመቀማት ወይም ለመጋራት ፍላጎት ኖሮን አይደለም። የኛ አላማ ኢትዮጵያን ማዳን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከወደሙ ማንን ልናስተዳድር ነው? ይሄ ሁሉ ጥፋትና ውድመት እንዲቆም ነው ፍላጎታችን። ያለፈውን መንግስት እኮ የታገለው ብዙ መከራ በመቀበል ነው፡፡ ለዚያ መከራ ግን ሂሳብ እናወራርዳለን ማለት አንችልም፡፡  በይቅርታና በወይይት መሻገር አለብን፡፡

Read 2327 times