Sunday, 31 October 2021 19:22

"ስጠኝ..” ብቻ ሳይሆን “አስተወኝም...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፤ አሁን አሁን እኮ የሆነ መሥሪያ ቤትን ዓመታዊ እቅድ ምናምን ስንሰማ፣ “ይህን ሁሉ በዓመት የሚሠሩት፣ ገንዘቡ ከየት ነው የሚመጣው፣ የወርልድ ባንክን ካዝናዎች በቁጥጥር ስር አደረጉ እንዴ!” ልንል ምንም አይቀረን!-;

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!‘
አሁን እኮ “ገንዘብ ስጠኝ...” ማለት ብቻ አይበቃም፣ “ሀብታም አድርግኝ…” ማለት ብቻ  አይበቃም፡፡ አሁን “ሚሊየነር አድርገኝ…” ነው የሚባለው፡፡ እናላችሁ... በሀብታምነት ‘ኦሪጂናል ሀብታምነት’ እና ‘ከማን አንሼ’ ያለ ነው የሚመስለው። እኛ ምስኪኖቹ ‘ሰፊው ህዝቦች’ ደግሞ (ቂ…ቂ…ቂ…) “የዲታነት ፕሪሚየር ሊግ እና የጤና ቡድን አለው እንዴ!” እንላለን፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ ለስንት ዘመን እዛ ላይ ጉብ ብሎ የኖረው ‘አርሴ’ በዛ ሰሞን እንደሆነው ‘ወራጅ ቀጠና’ ውስጥ የሚገቡ አሉ ማለት ነው፡፡ (እነ እንትና፣ አጅሬው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብቶ ነው በአንዴ ከራዲሰን ብሉ ወደ እንትና ሹሮ ቤት የወረደው!
አሀ…የምን የሹሮ ፍቅር! የሹሮ ፍቅር እንዲሁ በፊፍቲ ምናምን እድሜ መግቢያ ላይ በድንገት ቀብ ያደርጋል እንዴ! እንደዛ ከሆነ ከእኛ ጋር ከመጋፋት ደግሞ የሹሮ ራዲሰን ብሉ ይፈልጋል! ‘ቮታችንን’ ፈልጎ ለመመሳሰል ነው እንዳይባል ወንበሩ ሁሉ ተይዞ አልቋል፡፡ (ለምን ይዋሻል… እንደ አንዳንድ በፈረንጅ አፍ ‘ዊይርድ’ ምናምን ሊባል እንደሚችል አይነት ‘ውክልና’ ከሆነ፣ አይደለም ለሹሮ ቤታችን ድንኳን ሰባሪ፣ የተመረጠበት ወንበር የትኛው ህንጻ ውስጥ እንዳለ ሊረሳ ለሚችለው "ሰርቲፋይድ ጣጤ’ ጮክ ብለን ነበር ድምጻችንን የምንሰጠው፡፡ አሀ…የስታንድ አፕ ኮሜዲው ተሳትፎ እኛስ ለምን ያመልጠናል! (ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ‘ጊዜውን የቀደመ ደራሲ’… አለ አይደል… ‘ጣጤ’ የምትለዋን ቃል በዜማዋ አሪፍነት ‘ሮማንቲክ’ ብሏታል፣ ወይ ከዕለታት አንድ ቀን ይላታል፡፡)
እናላችሁ…አሁን “ሚሊየነር አድርገኝ…” ነው የሚባለው አሉ፡፡ ጥያቄ አለን…አንድ ሰው ሚሊየነር የሚባለው ሚሊየኗ ስንት ላይ ስትደርስ ነው! በኋላ በይገባኛል ጥያቄ እንዳንተራመስ ግልጽ ይደረግልና! አንድ ሰሞን ከሚሊየኗ ጋር በተያያዘ ስለ መርካቶዎች የምንሰማው ነገር ነበር፡፡ ለምሳሌ ስለሆነ ሰው ሲወራ....
“እሱ እኮ ቅልጥ ያለ ሀብታም ነው፣” ይባላል፡፡
“ምን ያህል ቢኖረው ነው ቅልጥ ያለ ሀብታም የሆነው?”
“እንደሰማሁት ከሆነ ሠላሳ ሚሊዮን ገደማ አያጣም ነው የሚባለው፡፡”
ይህን ጊዜ መርካቶዎች ትን እስኪላቸውና “ኸረ እበካህ አንድ ነገር ሆነህ ጦስ እንዳታመጣብን ቀስ ብለህ ሳቅ!” እስኪባሉ ድረስ በሳቅ ይንፈራፈራሉ አሉ… ከእንትን ሀገር በመጣውና ዋጋው ከሚሊየኗ ያለው እርቀት ብዙም ባልሆነው ሶፋ ላይ፡፡)
“በሠላሳ ሚሊየን ብር ነው ቅልጥ ያለ ሀብታም የሚኮነው!” ብለው ማታ በ‘ቦትል’ ሺቫዝ ሬጋላቸው ዙሪያ፣ በወጣቶቹ ቋንቋ፣ ሙድ ይይዙበታል፡፡ (እነ እንትና… ገና ሳትናገሩት የምታስቡትን አውቃለሁ፤ በሆዳችሁ …“አሁንም ለእሱ ውድ ውስኪ ሺቫዝ ሬጋል ነው!” እንደምትሉ ይገባኛል። ስሙኝማ… ይልቁንም ሎካል ጂን ስንት ደረሰች?) እናላችሁ…. በሺቫዝ ዙሪያ ሙድ መያዙ ይቀጥላል…
“ስማ… እንትና ቅልጥ ያ ሀብታም መሆኑን ሰማህ!”
“አትለኝም!”
“ከተማው ውስጥ ቅልጥ ያለ ሀብታም ሆኗል እየተባለ ‘ኪንግ ኦፍ ኪንግስ’ ሆኗል አሉ፡፡”
“አጅሬው ስንት ቢደርስ ነው!”
“ከታማኝ ምንጮች እንደሰማነው…” (መሀል ላይ ሳቅ ሲያቋርጥ በሦስት ጉንጭ ሺቫዝ ይስተካከላል) “እና ከታማኝ ምንጮች እንደሰማነው ሠላሳ ሚሊየን…”
አድማጮቹ ከመደንገጣቸው የተነሳ…አለ አይደል… ምድረ ብርጭቆ ወደ ከንፈሮች የምታደርገውን ጉዞ አቋርጣ መንገድ ላይ ቀጥ!
“እና…. እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ!”
“ታዲያ ምን እናድርገው!”
“ሠላሳ ሚሊዮን! ሠላሳ ሚሊዮን ብቻ!  ቢያንስ፣ ቢያንስ ያሳለፍነው ጊዜ ትዝ ብሏችሁ ትንሽ እንኳን አታዝኑም!”
“እኮ ምን እናድርግ!”
“በቃ ለእሱ ቅርብ የሆንነው ሰብሰብ ብለን የሆነ ኤቨንት እናዘጋጅና እናቋቁመዋ! አይታያችሁም! ግን ስሙኝ...  በሠላሳ ሚሊዮን ምስኪን ቤተሰቦቹን ምንድነው የሚያበላቸው!”
“በአንተ ቤት እኛን አናግረህ ከሹሮ ቤቶች ጋር ልታጣላን ነው፡፡” (ቂ…ቂ…ቂ…)
የምር ግን… ለክፉም ለደጉም፣ ሚለየነር የሚባለው ብሪቱ ስንተኛው ሚሊዮን ቁጥር ላይ ስትደርስ ነው?
እናላችሁ… ምኞታችንን እንደ እቅድ እያየነው ነው የምንቸገረው፡፡
“ለአዲሱ ዓመት ምን አቅደሀል?!”
“ስማኝ የዛሬ ዓመት ጂ ፕላስ ቱዬን ገጭ አድርጌ፣ ምን አለ በለኝ፣ የሚቀጥለውን እንቁጣጣሽ እናንተን ሰብስቤ ሰከንድ ፍሎር ቴራሱ ላይ ግሪላችንን እያንጨረጨርን፣ ፏ  ባንል ምን አለ በለኝ!”
ዓመቷ ደግሞ በአንድ ጊዜ ሽው ትልና እንቁጣጣሽ ይመጣል! መቼም የዘንድሮ ሰው ሲጥል እንጂ ሲማታ አይታይም እንደሚባለው፣ እየሠራ መሆኑን ሳያሳውቅ ጨርሶ፣ ሰርፕራይዝ እንደሚያደርጋችሁ ትጠብቃላችሁ፡፡ እናማ ጷግሜ ስትገባ “እህ አጅሬው፣ እንቁጣጣሽ ደረሰ እና…” ፊቱ ጭምድድ ብሎ ስታዩ መሀል ላይ ታቋርጣላችሁ፡፡
“አንተ ምን ሆነሀል!  ደህና አይደለህም እንዴ!”
“ስንት ነጃሳ እያለ እዚህ ሀገር ምን ደህንነት አለ!”
“እኮ ምን ሆንክ?”
“ምን ቀበሌዎች እየነጀሱኝ…”
“ብለህ፣ ብለህ ከቀበሌ ጋር መጋጨት ጀመርክ ማለት ነው!”
“ምን እጋጫለሁ፣ እነሱ ሊገጩኝ ነው እንጂ!”
“ምን አድርግ ብለው!”
“የሁለት ዓመት ተኩል ውዝፍ የቤት ኪራይ ስላለብህ፣ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ካልከፈክ እቃህን አውጥተን፣ ደጅ እናሰጣልሃለን እያሉ እየፎከሩብኝ ነው፡፡”
ቆይ፣ ቆይማ! የጂ ፕላስ ቱዋ ነገር የት ደረሰ! አሀ…ጓደኛየው በይሉኝታ ዝም ቢል እኛ እንጠይቃለና! የቀበሌ ቤት ኪራይ እየወዘፉ ነው ጂ ፐላስ ቱ!
እናላችሁ… ምኞትና እቅድን መለየት እያቃተን ትሪፓችን መከራዋን እየበላች ነው።
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፤ አሁን አሁን እኮ የሆነ መሥሪያ ቤትን ዓመታዊ እቅድ ምናምን ስንሰማ “ይህን ሁሉ በዓመት የሚሠሩት ገንዘቡ ከየት ነው የሚመጣው፣ የወርልድ ባንክን ካዝናዎች በቁጥጥር ስር አደረጉ እንዴ!” ልንል ምንም አይቀረን!
እናላችሁ…ጥያቄያችን ሁልጊዜ “ስጠኝ፣” “ጨምርልኝ፣” “ገንዘቤን ተራራ አደርግልኝ”…ብቻ ሆኖ መቅረት አለበት እንዴ! ለምሳሌ…“በአዲሱ ዓመት በትንሽ ትልቁ መቅናት አቆማለሁ…” ማለት ለጊዜው ቢከብድም ዓለም አትጠፋም፡፡ አሀ... ቀላል መቀናናት ነው እንዴ ዘንድሮ ያለው!… በጓደኛዋ አዲስ ባክአወት የምትቀና መአት አለች። (ባክአውት የሆነ የልብስ አይነት ነው፡፡ የትርጉም ስህተት እንዳይፈጠር ለማለት ያህል ነው፡፡) በጎረቤቱ አዲስ ሙሉ ልብስ አንጀቱ እርር ብሎ የተልባ ምትክ ሲግት የሚያነጋ መአት ነው።  እመኑኝ… የማይቀናበት ነገር የለም ለማለት ምንም አይቀረን!
ደግሞላችሁ… “በሆነ ባልሆነ የሰውን ስም በሀሜት በየቦታው የምጎትተውን ነገር አስተወኝ!” ማለትም አንድ ነገር እኮ ነው፡፡ ቀላል መተማማት ነው እንዴ ዘንድሮ ያለው!
በመናገራችሁ ትታማላችሁ፡፡
“እሱ ሰው ግን ምላሱ የሆነ የሚጠዘጥዘው ነገር አለ እንዴ! ሥራው  መለፍለፍ ብቻ እኮ ነው!”
“ልፍለፋ ነው ብለህ ነው፣ እኔ ብዙ ጊዜ ቁም ነገሮችን ሲናገር ነው የምሰማው፡፡”
“እንዲህ እያላችሁ ነው እኮ የልብ ልብ የምትሰጧቸው!”
ዝም ስትሉ ትታማላችሁ….
“እሱ ሰውዬ ግን እንዴት እንደሚደብረኝ ነገር…አይናገር፣ አይጋገር በቃ ጭጭ ብሎ ሰው የሚለውን ይቀዳል፣ ይቀዳል…”
“አንዳንድ ሰው እኮ በተፈጥሮው ብዙ መናገር አይወድም…”
“ይሄኔ የምንለውን እየቀዳ የሆነ ቦታ ሄዶ ሪፖርት ሳያቀርብ አይቀርም…”
አለባበሳችሁ እንደነገሩ ከሆነ ትታማላችሁ….
“እንደው ይቺን ሴት ምን ማድረግ ይሻላል!”
“ምን አደረገችህ?”
“አለባበሷን አታይም! ቡቱቶ ሊመስል ምንም አልቀረው እኮ…”
ከለበሳችሁ ትታማላችሁ…
“እንትና ዛሬ እንዳማረባት...”
“ምን ያምርባታል፣ እሷ ልጅ ግን እንዲህ ተብለጭልጫ የምትወጣው ቢዙ ሳታሯሩጥ አትቀርም!”
እናላችሁ...   “ስጠኝ...” #ጨምርልኝ; ከማለት በተጨማሪ እንደ እንጉዳይ እየተባዙ ያሉ አጓጉል ባህሪያትን  “አስተወኝ...” ብንል ኖሮ አገራችን እንዴት የተሻለች በሆነች ነበር!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1195 times