Monday, 01 November 2021 00:00

የአፄ ኃይለ ስላሴ ህገ መንግስት በ90ኛ ዓመቱ ምን ይነግረናል

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 የዛሬን አያድርገውና፣ ያኔ ከመቶ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት፣ የስልጣኔና የካፒታሊዝም አስተሳሰብ፣ የጨለመን የሚያበራ፣ የታፈነን የሚያናፍስ አስተሳሰብ ነው ተብሎ ተሞግሶ ነበር። የእውቀትና የነፃነት፣ የሰላምና የብልፅግና መንፈሱንም በመላው ዓለም እያዳረሰ ነበር - የካፒታሊዝም አስተሳሰብ።
አእምሮንና የግል ነፃነትን፣ የግል ንብረትንና የገበያ ነፃነትን፣ የግል ማንነትንና የሕግ የበላይነትን የሚያከብር አስተሳሰብ፣ ሰፊ ተቀባይነት ቢያገኝ አይበዛበትም። ዛሬ ዛሬ፣ በአሜሪካ ጭምር እየተሸረሸሩ ቢመጡም፣ እነዚህ የስልጡን ፖለቲካ መሰረታዊ ሃሳቦች ነበሩ - የአሜሪካ ጠንካራ መሠረቶች። ለአሜሪካ ብቻ አይደለም። የአንዱ አገር ስኬትና ስልጣኔ፣ ለሌሎች አገራትም፣ እግጅ አስተማማኝ አርአያ መሆኑ አይቀርማ። ለኢትዮጵያም ጭምር ጠቅሟል።
አስቡት። አብዛኞቹ አገራት፣ ማንም ሳያስገድዳቸው ነው፤ ሕገመንግስት ማርቀቅና ማፅደቅ የጀመሩት - በየራሳቸው ፍላጎት፤ በአሜሪካ አርአያነት። በአንድ አገር የተጀመረ ጥሩ ሃሳብ፣ ወደ ሌሎች አገራትም ይዛመታል። የትኛውም ሕገመንግስት፣ አነሰም በዛም፣ ለይምሰልም ሆነ በቅንነት፣ ስለ ሰዎች መብትና ነፃነት ሳይናገር አያልፍም። ሕገመንግስት በሚል ስም የተዘጋጀ ሰነድ ሁሉ፣ ስለ ፍትህ ሥርዓትና ስለ ሕግ የበላይነት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በርካታ አንቀፆችን ይፅፋል።
አዎ፣ አንዳንዱ ሕገመንግስት፣ ስለ ግለሰቦች ነፃነት እየፃፈ፣ በተከታዩ አንቀፅ ሃሳቡን ያፈርሰዋል። አዎ፣ አንዳንዱ ሕገመንግስት፣ ለይስሙላ ብቻ እየሆነ፣ የመብትና የነፃነት አንቀፆቹ በቅጡ የማይተገበሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
እንዲያም ሆኖ፣ ሕገመንግስት ጥሩ ነው። ለጊዜው ያልተተገበሩ የነፃነት አንቀፆችና ጥሩ ሃሳቦች፣ ከጊዜ በኋላ፣ ጥቅም ሊያስገኙ ይችላሉ። ከጊዜ በኋላ፣ ጥሩ ሃሳብን ከልብ የሚገነዘቡ ከምር የሚተገብሩ ቀና ሰዎች ሊመጡ ይችላሉና።
“ሕጋዊ ሥርዓት” ማበጀት፣ ቁልፍ “የአገር አስተዳደር” ሥራ እንደሆነ ገብረህይወት ባይከዳኝ የገለፁት፣…. “አገር ማለት፣ ሕግና ሥርዓት ማለት መሆኑን” ለማስረዳት ብቻ አይደለም። እንዴት? የሕጋዊ ሥርዓት አስፈላጊነት፣ ለተራ ዜጎች ብቻ አይደለም። ይሄ ብቻ ከሆነማ፣ ድሮም የነበረ አስተሳሰብ ነው። ነባር ነው። ገብረህይወት ባይከዳኝ የገለፁልን አዲሱ አስተሳሰብ ምንድነው? “መንግስትም የሕግ ተገዢ ለመሆን የሚገደድበት ነው” - ሕጋዊ ሥርዓት። ይሄ፣ አዲስ የስልጣኔ ሃሳብ ነው። ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ ይህን የፃፉት፣ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ነው። ድንቅ ነው። ሥልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ፣… ሃያልነቱ ያኔ ገና አልተዳፈነም ነበር።
ልዑል ተፈሪ መኮንንም፣ “የአገሪቱ ንጉሣዊ አስተዳደር፣ ለሕጋዊ ስርዓት ተገዢ ቢሆን ይበጃል” ማለታቸው፣ በያኔው ዘመን ምሁራን ዘንድ ደህና ተሰሚነት አስገኝቶላቸዋል (constitutional monarchy እንዲሉ)። ዘውድ ጭነው “ንጉሠ ነገስት ኃይለስላሴ” ተብለው ከተሰየሙ በኋላም፣ ወዲያውኑ ሃሳባቸውን በተግባር ለማሳየት ሞክረዋል።
ምንም ሆነ ምን፣ ለወግ ያህልም ሆነ ለቁምነገር፣ ሕገመንግስት እንዲዘጋጅና እንዲታወጅ አድርገዋል። ያ የመጀመሪያው ሕገመንግስት፣ ባለፈው ሐምሌ 90ኛ ዓመቱን ደፍኗል።
ነባርና አዲስ ሃሳቦች - በሕገ መንግስቱ አንቀፆች።
አዎ፣ በ1923 ዓም የታወጀው ሕገመንግስት፣ ነባር ሃሳቦችን የያዘ ነው። ቢሆንም ግን፣ በአዲስ የስልጣኔ አስተሳሰብ የተቃኘ ሰነድ ነው። የሕገመንግስቱ አንቀፆች፣ ይህን ይመሰክራሉ።
አንቀፅ 6፣ 9 እና 10፣ ንጉሡ እጅግ ሰፊ ስልጣን እንደሚኖራቸው የሚያውጁ አንቀፆች ናቸው። ነገር ግን፣ ንጉሡ ለሕግ ተገዢ እንደሆኑም እነዚያው አንቀጾች ይገልፃሉ።
ንጉሡ ሉዓላዊ ስልጣን አለው ይላል - አንቀፅ 6። ነገር ግን፣ ስልጣኑን፣ ሕግን በተከተለ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ይላል - ራሱ አንቀፅ 6።
“በአደጋ ወቅት፣ የአገሪቱ ምክርቤቶች በእረፍት ላይ ከሆኑ፣ ንጉሡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት ይችላል። ምክርቤቶቹ ሲሰበሰቡ ግን፣ የንጉሡን አዋጅ ይመረምራሉ። አዋጁ፣ በአገሪቱ ሁለት ምክርቤቶች ዘንድ ተቀባይነት ካላገኘ፣ እንደተሻረ ይቆጠራል ይላል - አንቀፅ 9።
የንጉስ ስልጣን እንዲህ በግልጽ የሚገደብ ሃሳብ፣አዲስ የስልጣኔ ሃሳብ ነው፡፡
አዎ፣ ሕገመንግስቱ፣ የተዋጣለት ስልጡን ሕገመንግስት ነው የሚባል አይደለም። የአንደኛው ምክር ቤት አባላት፣ በየአካባቢው ሹሞች የሚመረጡ ቢሆኑም፣ የሌላኛው ምክር ቤት አባላት ግን፣ በንጉሡ የሚሰየሙ ናቸው። አዎ፣ ንጉሡ ለህግ ተገዢ መሆኑን የሚገልፁ አንቀፆች ቢኖሩም፣ ይህን ለመቆጣጠር የሚችል የሕግ ሥርዓት አልተፈጠረም።
ቢሆንም ግን፣ የሕገመንግስቱን ፋይዳ መዳኘት የሚገባን፣ “ምን አይነት ነባር የኋላቀርነት ሃሳቦችን ይዟል?” በሚል ጥያቄ ብቻ አይደለም። “ምን አይነት አዲስ የስልጣኔ ሃሳቦችን አምጥቷል?” የሚል ጥያቄ ብናነሳ፣ የሕገመንግስቱን ፋይዳ ይበልጥ ለመገንዘብ ይረዳናል። ደግሞስ፣ ነባር ሃሳቦች በህገመንግስቱ ውስጥ መካተታቸው ምን ይገርማል? አስገራሚው ነገር፣ አዲስ የስልጣኔ ሃሳቦች በሰፊው መካተታቸው ነው።
ንጉሡ፣ ሰፊ ስልጣን ቢኖራቸው አይገርምም። ድሮም የነበረ ነገር ነው። በተቃራኒው፤ “የንጉሡን ስልጣን መገደብ ተገቢ ነው፤ የመንግስትን ሥልጣን መገደብ ስልጣኔ ነው” የሚል ሃሳብ መምጣቱ ነው፣ አዲሱ ነገር። ከስልጡን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚመነጩ አንቀፆች፣ በህገ መንግስት ውስጥ ገብተው መፅደቃቸው ነው - አዲሱ ታሪክ። የዛሬ 90 ዓመት የተሰራ ታሪክ።
ዋናው ቁምነገር፣ “የንጉሥ ትዕዛዝ፣ የምክር ቤትም ሆነ የየትኛውም አካል ይሁንታ አያስፈልገውም” የሚለው ነባር ኋላቀር አስተሳሰብ መዳከሙ ነው። “ንጉሥ፣ የሕግ ጌታ እንጂ የሕግ ተገዢ አይደለም” የሚለው  ኋላቀር አስተሳሰብ እየተሸረሸረ፣ በምትኩ “የሕግ የበላይነት አስተሳሰብ” ለምልክት ያህል ማቆጥቆጡ ነው - ትልቁ ቁምነገር።
የዳኝነት ስልጣንና ሃላፊነት ላይ ባተኮረው በሕገ መንግስቱ ምዕራፍ 6 ስር፣ ምን ዓይነት አንቀፆች እንደተጻፉ እንመልከት።
የዳኝነት ሃላፊነት - ባለሁለት ስለት። ጋሻም ጦርም ነው፡፡
ዳኞች፣ እንደ ንጉሡ ሆነው፣ ዳኝነትን እንደሚሰጡ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 50 ተገልጿል። ይሄ ነባር ሃሳብ ነው። ቢሆንም፣ በዘፈቃ፣ በዘልማድ፣ በንጉሡ ፍላጎትና ተዕዛዝ የሚዘወር አይሆንም፡፡ ፍርድ ቤት፣ በንጉስ ፍላጎት ብቻ የተከፈተ ወይም የተዘጋ፣ መረን የተለቀቀ ወይም የተቀየደ አይደለም- ዳኝነት ማለት።
ዳኞች ፍትህን የሚፈፅሙት በሕግ መሰረት እንደሆነ፤ የዳኝነት መዋቅሩም ሕግን ተከትሎ እንደሚደራጅ እዚያው አንቀፅ 50 ላይ ተገልጿል።
ዳኞች የሚሰየሙት በሕግ ላይ ባላቸው ችሎታ ነው ይላል አንቀፅ 51።
ዳኝነት የሚከናወነው፣ ለዜጎች ክፍት በሆነ መንገድ ነው (አንቀፅ 52)።
የዳኝነት የስልጣን አይነትና መጠን፣ (በአስተዳደራዊ ወሰንና በቦታ፣ በጉዳይ አይነትና ክብደት፣ በቅደም ተከተልና በእርከን) መልኩና ልኩ በህግ የሚፀና ነው ይላል (አንቀፅ 53)።
እነዚህ ዳኝነትን የሚመለከቱ አንቀፆች፣ መቼም ቢሆን ልናከብራቸው የሚገቡ፣ከሞላ ጎደል፣ በሕግ የበላይነት አስተሳሰብ ላይ የቆሙ ተገቢ ሃሳቦችን የያዙ ናቸው።
በእርግጥ፣ በቁንፅል ከታየ፣ “የሕግ የበላይነት” እና “በሕግ መግዛት” ሊምታቱብን ይችላሉ። ነገር ግን፣ ከምር አገናዝበን ስናስበው፣ የሕግ የበላይነት፣ እንዲሁ አየር ላይ የተንሳፈፈ መና አይደለም።
 “የህግ የበላይነት”፣ትርጉም የሚኖረው፣ እውነትንና እውቀትን፣ ሕይወትንና ኑሮን ከማክበር የሚነሳ ሲሆን ነው። አለበለዚያማ እውነትን በማስረጃ አረጋግጦ፣ ህግን አውቆ፣ በህጋዊ ስርዓት ዳኝነትን መስጠት የሚሉት ነገር ትርጉም አይኖርም። የግለሰብን ህልውና ማለትም የግል ማንነትንና የግል ሃላፊነትን ከማክበር የማይነሳ ከሆነማ፣ አንድ ሰው በፈፀመው ጥፋት ሌላ ሰው ላይ ቅጣት ፍርጃ እንደመጫን ይቆጠራል፡፡ ለዚህ ለዚህማ፣ለዘፈቀደ ፍርጃማ፣ያ ሁሉ የሕግና የስርዓት ጣጣ ለምን ያስፈልጋል?
ሕጋዊ የዳኝነት ስርዓት፣ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው፣ እያንዳንዱን ሰው፣ እንደየስራው በትክክል ለመዳኘትና ለመመዘን ነው። በሌላ አነጋገር፣ “የግለሰብ ሕልውናን፣ ነፃነትንና መብትን ማክበር” የሚል ሃሳብ ወይም አዝማሚያ በውስጡ የያዘ መርህ ነው - የሕግ የበላይነት መርህ። ይህንንም ከሕገመንግስቱ አንቀፆች መገንዘብ ይቻላል - በ1923 ዓ.ም ከፀደቀው ሕገ መንግስት።
ከአገልጋይነት ወደ ግለሰብ ነፃነት።
ዜጎች በነባሩ ሃሳብ “አገልጋይ” ናቸው። “subjects” የሚለው ነባር አባባል፤ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የነፃነትና የመብት ባለቤት እንደሆነ የሚገልፅ አዲስ ሃሳብ፣ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ሰፊ ቦታ አግኝቷል። ንጉሡና  ሌሎች ባለስልጣናት፣ የዜጎችን ነፃነትና መብት የማክበር ግዴታ እንደሚኖርባቸው የህገ መንግስቱ አንቀፆች ያረጋግጣሉ። በዘፈቀደ ዜጎችን ማሰር አይቻልም።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ሕግን በተከተለ መንገድ ካልሆነ በቀር፣ አይያዝም፣ አይፈረድበትም፣ በእስር አይቀጣም ይላል - አንቀፅ 23። “የእያንዳንዱን ዜጋ ሕልውና፣የግል ነፃነትና መብትን ማክበር” ከሚል ሃሳብን የሚመነጭ  አንቀፅ ነው። ግን፣ ከዚያም በላይ ነው። በመንግስት ላይ ህጋዊ ሃላፊነትንና ግዴታን ይጭናል።
መንግስት፣ የዜጎችን ሕልውና የማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበርም ሃላፊነት እንዳለበት ይገልፃል - አንቀፁ። ይህን ሃሳብ በተግባር የሚተረጉም ነው - ሕጋዊ የዳኝነት ሥርዓት።
ማንም ሰው፣ ያለ ጥፋቱ ለቅጣት አይዳረግም። አጥፍቶ እንደሆነም፣ በሕጋዊ የዳኝነት ስርዓት ተመርምሮ፣ ጥፋተኝነቱ መረጋገጥ፣ የጥፋቱም መጠን መመዘን አለበት።
ጥፋተኛ ሰው፣ የስራው ያህል፣ በህጋዊ ሥርዓት፣ የሕግ ዳኝነት ያገኛል።
ተጎጂና ከሳሽ ዜጋም፣ በሕጋዊ ስርዓት የፍትህና የካሳ ዳኝነትን ያገኛል።
ሕጋዊ የዳኝነት ሥርዓት፣ ባለሁለት አፍ ስለት ነው። ጋሻና ጦር ነው፡፡
በአንድ በኩል፣ ማንም ሰው ያለ ጥፋቱ፣ በዘፈቀደ የጥቃትና የቅጣት ሰለባ እንዳይሆን፣ ለእያንዳንዱ ዜጋ ሕጋዊ ዋስትና ይሰጣል።
በሌላ በኩል፣ ማንም ሰው የወንጀል ሰለባ እንዳይሆን፣ ጥፋተኞችን የስራቸውን ያህል የሚቀጣ ሕጋዊ የፍትህ መሳሪያ ነው- እንደ ጦር። የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ለመጠበቅ፣ ነፃነትን የሚጥሱ ወንጀለኞችንም ለመቅጣት የሚያገለግል ነው - ሕጋዊ የዳኝነት ሥርዓት።
የግል ሃሳብ፣ የግል ንብረት፣የግል ማንነት-(የግል ነፃትና ሃላፊነት)
በምዕራፍ ሦስት ሥር የተዘረዘሩት 12 አንቀፆችን ተመልከቱ (አንቀፅ 18-29)።
የዜጎች መብትና ሃላፊነት ላይ ያተኮረው ምዕራፍ፤ ሁለት ግዴታዎችን ይዘረዝራል።
አንደኛ፣ አገሬው፣ ታክስ የመክፈል ግዴታ አለበት። ይላል አዲስ ነገር አይደለም። ያኔም፣ ዛሬም፣ እዚህም እዚያም አገር፣ የታክስ እዳ አነሰም በዛ ነበረ፤ አለ።
ሁለተኛው ግዴታ፣ የጦር ሃይል አባላት፣ ለንጉሡ ታማኝና ታዛዥ መሆን አለባቸው የሚል ነው - አንቀፅ 20። ይህም የተለመደ ነው። የመንግስት መሪ፣ በየአገሩ፣ የጦር ሃይል ጠቅላይ አዛዥ አይደል? የጦር አባላት ለመሪያቸው ታዛዥ ካልሆኑ፣ ምኑን አዛዥ ሆነው። በዚያ ላይ፣ ወታደራዊ ተቋማት፣ ለሲቪል ተቋማት ተገዢ ካልሆኑ፣ ከጥቅማቸው አደጋቸው ይበዛል።
የሆነ ሆኖ፣ አንቀፁ የታማኝነትና ታዛዥነት ሸክምን እንዲሁ በደፈናውና የሚጭን አይደለም። የጦር አባላት ታዛዥነት፣ ሕግን በተከተለ መንገድ መሆን እንዳለበት በአንቀፁ ተገልጿል። ንጉሡ፣ በዘፈቀደ፣ ሕገወጥ ትዕዛዝ መስጠት የለበትም። የዜጎችን ሕልውና፣ ነፃነትና መብትን የሚያጠፋ ትዕዛዝ፣ ሕጋዊ አይደለም።
በእርግጥ፣ ጦርነት ወይም ክፉ አደጋ ሲያጋጥም፣ ንጉሡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት ይችላል። የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚገድብ፣ “የሰዓት እላፊ” መመሪያ የሚያውጅበት ጊዜ ይኖራል። የንብረት መብትንም ሊገድብ ይችላል። ምርቶችን ወደ ውጭ አገር መሸጥ አይቻልም ብሎ ለጊዜው መከልከል አንድ ምሳሌ ነው። እንዲያም ሆኖ፣ የገደብና የክልከላ አዋጅ፣ ለጦርነትና ለአደጋ ጊዜ ብቻ ነው። ለዚያውም፣ የአገሪቱ ምክር ቤቶች፣ ሕጉን መሻር ይችላሉ።
በአጭሩ፣ ንጉሡ፣ በዛም አነሰ፣ ለሕጋዊ ስርዓት ተገዢ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ፣ በሕገመንግስቱ ውስጥ ሰርጿል።
ከሁለቱ የታክስ እና የታዛዥነት ግዴታዎች ውጭ፣ በምዕራፍ 3 የተዘረዘሩ ሌሎች አንቀፆች ስለ መብትና ነፃነት የሚያወሩ ናቸው።
እናም፣ እንዲህ ይላሉ። በሕግ በተዘረዘሩ መስፈቶች መሰረት፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በጦር ሃይልና በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ስራ መቀጠርና ሃላፊነትንም መያዝ እንደሚችል አንቀፅ 19 ይገልፃል። ሃላፊነት እንደድሮ፣ በዘር ሐረግ የታጠረ አይደለም። ባይተገበር እንኳ፣ ሃሳቡ ስልጡን ሃሳብ ነው፡፡
በሕግ ከተቀመጡ ወሰኖች በስተቀር፣ ማንኛውም ዜጋ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት አለው ይላል አንቀፅ 22።
በሕግ ከተቀመጡት ሁኔታዎች በስተቀር፣ በማንኛውም ዜጋ መኖሪያ ቤት ላይ ፍተሻ ብርበራ አይደረግም - አንቀፅ 25።
በሕግ ከተቀመጡት ሁኔታዎች በስተቀር፣ የኢትዮጵያውያን የግል የመልዕክት ልውውጦችን ገልጦ የማየት መብት ማንም የለውም፤ የግል ሚስጥርን የመበርበር መብት ማንም የለውም - አንቀፅ 26።
“ለወንጀል ምርመራ፣ በፍርድ ቤት ተመርምሮና ተፈቅዶ”…. የሚሉ የፍተሻ ሕጎች ይኖራሉ። እንዲህ አይነት ሕጋዊ የቁጥጥር አሰራሮች የሚያስፈልጉት፣ “የሰዎች የግል ሃሳብና መልዕክት፣ መከበር አለበት” በሚል አስተሳሰብ ነው። ይህን የመጣስ ስልጣን ያለው ሰው የለም - ተራ ወንጀለኞችም ቢሆኑ፣ ንጉሡም ቢሆኑ።
በሕግ በተቀመጠ የጋራ አስገዳጅነት ካልሆነ በስተቀር፣ ማንም ቢሆን የኢትዮጵያውያንን ተንቀሳቃሽ ወይም ተንቀሳቃሽ ያልሆነ የግል ንብረትን የመውሰድ፣ የንብረት መብትን የመጣስ ስልጣን የለውም - አንቀፅ 27።
በተከታታይ የተዘረዘሩት አንቀፆች፣ “Bill of Rights` ተብለው ከሚፈረጁ አንቀጾች ጋር ይመሳሰላሉ። በእርግጥ፣ አንቀፆቹ፣ በተገቢው መጠን የጠሩ የነጠሩ አንቀጾች አይደሉም ማለት ይቻላል።
ቢሆንም ግን፣ የሚናቁ አይደሉም። ሕገ መንግስቱ፣ የአገሪቱ የመጀመሪያ ህገ መንግስት መሆኑን፣ የዛሬ 90 ዓመት የተሰናዳ እንደሆነም ማስታወስ ያስፈልጋል። ታዲያ፣በዚህ አይን ስናየው፣ ጥሩ የስልጣኔ ጅምርና ቡቃያ አይደለም? የአንቀፆቹን ትርጉምና ያቀፉትን መሰረታዊ ሃሳብ አስተውሉ።
የግል ሃሳብና መልዕክትን፣ የግል ሕይወትንና እንቅስቃሴን፣ የግል መኖሪያ ቤትንና የግል ንብረትን መዳፈር፣ የግል ነፃነትንና መብትን መጣስ ክልክል ነው፤ ወንጀል ነው። የሚዳፈርና የሚጥስ፣ በሕግ ተዳኝቶ የስራውን ያገኛል። ግን በዘፈቀደ አይደለም። ተጣርቶ ተረጋግጦ ነው። ንፁህ ሰዎች ያለ ጥፋታቸው የቅጣት ባለዕዳ መሆን የለባቸውም።
ለዚህም ነው፣ ሕግን በተከተለ አሰራር ካልሆነ በቀር፣ የዘፈቀደ እስርና ቅጣት ክልክል የሆነው - አንቀፅ 23።
ግን፣ ባለስልጣናትና የመንግስት ተቋማት፣ “በሕግ በተቀመጠው መሰረት” እያሉ፣ የግል ነፃነትንና የንብረት መብትን መጣስ አይችሉም? ይችላሉ እንጂ።  ነገር ግን፣ ድሮም ይችሉ ነበር። አዲስ ነገር አይደለም። አዲሱ ነገር ሌላ ነው፡፡፣ “የሰዎችን ነፃነት መጣስ የባለስልጣን ወይም የመንግስት መብት አይደለም” የሚል ሃሳብ ጎልቶ መምጣቱ ነው አዲሱ ነገር። በአቋራጭ ያሻቸውን እንዳይሰሩ የሚከለክል ሕግና ሥርዓት መኖር እንዳለበት፣ በሕገመንግስቱ ተጠቁሟል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በሕጋዊው ስርዓት ተቋቁመው ከሚሰሩ ፍርድ ቤቶች፣ ዳኝነት የማግኘት መብት አይነፈግም ይላል - አንቀፅ 24።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በመንግስት ላይ ቅሬታ የማቅረብ የክስ መብት አለው ይላል አንቀፅ 28።
አዎ፣ የህገ መንግስቱ አንቀጾች የተሟሉ፣ የተጣሩና አስተማማኝ ናቸው ማለት አይቻልም። የስልጡን ፖለቲካ ትክክለኛ ቅርጽና ይዘትን አሟልተዋል የሚያስብሉ አይደሉም።
አገራዊ የመንግስት መዋቅርን እንጂ ፣የየአካባቢው መዋቅርንና ሃላፊነትን የሚያብራሩ አንቀፆች የሉም። ይሄ ትልቁ ጉድለት ነው።
ሌሎች ጥሩ ጥሩ አንቀጾች መኖራቸውን ግን መርሳት የለብንም። አዎ፤ ሁሉም ጥሩ አንቀጾች ተግባራዊ እንዲሆኑ መጠበቅ የዋህነት ነው። ነገር ግን፣ወደ ተግባር የሚያራምዱ ጥሩ ሃሳቦች ናቸው።
የግል ነፃነት (የሃሳብ ነፃነት)መርህ፣ የግል ንብረት መብት መርህ፣ እንዲሁም፣ የግል ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ የዳኝነት መርህ…. እንደ ዋና የሕገመንግስት መርሆች ተጠቅሰዋል። ትክክለኛ ሃሳቦችና መርሆች፣ ቀስ በቀስ ወደ ተጣራና ወደ ተሟላ ሃሳብና መርህ ለመጓዝ ይረዳሉ። ቀስ በቀስ ወደ ተሻለ ተግባር ሊገፋፉ ይችላሉ።
በእርግጥም፣ መንግስታዊ ተቋማት በሕግና ሥርዓት የሚዋቀሩ፣ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ሰዎችን በብቃት ደረጃ አመዛዝነው የሚቀጥሩ መሆን አለባቸው። ይህን የህገ መንግስት መርህ በተወሰነ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል - ንጉሡ።
ትምህርት እንዲስፋፋ ጥረዋል - የአገሪቱ ተስፋ ትምህርትና እውቀት እንደሆነ ገብቷቸው ነበር። ትልቁ ማተሚያ ቤት ሲቋቋም፣ ብርሃንና ሰላም ተብሎ የተሰየመው፣ በአጋጣሚ አይደለም።
ትምህርትና እውቀት፣ እንደ ችቦ እንደ ፋና ነበር የሚመሰለው - እንደ ብርሃን ምንጭ፣ የሌሊቱን ጨለማ አሻግረው፣ ወደ ብርሃናማ ቀን የሚያደርሱ።
ከጊዜ በኋላም፣ከህገ መንግስት በተጨማሪ፣ ዝርዝር የወንጀል፣ የፍትሀ ብሔርና ሌሎች ህጎች ተዘጋጅተው ስራ ላይ ውለዋል።
በጥቅሉ ሲታይ፣ በ1923 ዓ.ም የፀደቀው ህገ መንግስት፣ የስልጣኔ አስተሳሰብን የተላበሰ በጎ ጥረትና ጅምር ነበር። የበጎ ጥረትና የጥሩ ጅምር ታሪክን ማስታወስና ማክበር ያስፈልጋል። በተቃና የጤንነት መንገድ መጓዝ ከፈለግን ማለቴ ነው።

Read 1459 times