Sunday, 31 October 2021 18:48

ግዕዝን ጨምሮ የጥንት ትምህርቶችን የሚያስተምር ዘመናዊ ት/ቤት ሊከፈት ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ግዕዝን ጨምሮ ቅኔ፣የኔታ ቤትና ሌሎችንም የጥንት ትምህርቶች ከዘመናዊ ትምህርት ጎን ለጎን ለማስተማር ያለመ አዲስ ት/ቤት ሥራ ሊጀምር ነው፡፡ ት/ቤቱ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር ከሚተዳደሩት አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነውና እስራኤል ኤምባሲ ጀርባ በሚገኘው አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን  ግቢ ውስጥ በ2 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በቀጣዩ 2015 ዓ.ም ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምር የት/ቤቱ ባለቤት ደራሲ ይባቤ አዳነ ገልጸዋል፡፡ የእኛ ሀብት የሆነውና “አሁን ትልልቅ የአውሮፓ ሀገራት በዩኒቨርስቲ ደረጃ እያስተማሩበት ያለው ግዕዝ ትምህርት በሀገራችን ያን ያህል ትኩረት አግኝቷል ለማለት ያስቸግራል” ያሉት ደራሲ ይባቤ አዳነ በሚከፍቱት ት/ቤት ከየኔታ ቤት ጅምሮ ግዕዝ ቅኔና ሌሎችም ትውልድን የሚያንፁ የግብረ ገብ ትምህርቶች ከዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ጎን ለጎን እንደሚሰጡ ባለፈው ቅዳሜ የግንባታው ማስጀመሪያ ስነ-ሥርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡ ት/ቤቱ ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ኮሌጅ የሚዘልቅ ሰንሰለት ያለው ሲሆን ግንባታውም ሆነ ሌላው ጉዳይ በዚያው መጠን እያደገ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡ ከግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥተርዓቱ መልስ በቤልቪው ሆቴል በተደረገ ምክክር የደብሩ አስተዳዳሪና ካህናት፣ደራሲ፣ሀያሲና መምህር ሀይለመለኮት መዋዕል፣ መምህር ታዬ ቦጋለ፣ተቋራጩ ድርጅትና አርክቴክቸራል ዲዛይኑን የሰሩት ባለሙያዎች የታደሙ ሲሆን ደራሲና መምህር ሀይለመለኮት መዋዕልና መምህር ታዬ ቦጋለ ይህንን የተቀደሰ ሀሳብ ለመደገፍና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
የት/ቤቱ ባለቤት ደራሲ ይባቤ አዳነ ቦታውን ከቤተክርስቲያኗ በጨረታ ያገኙ ሲሆን የትውልድ መቅረጫ ቦታ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ደራሲው “ሰገነት አሳታሚ” የተባለ ድርጅት ያላቸው ሲሆን “በመማርና በማንበብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” በሚል ለህብረተሰቡ ይጠቅማሉ ያሏቸውን ነገር ግን የህትመት ብርሃን ያላገኙ መፅሀፍትን በማሳተም ስራ ላይ ከማሰማራታቸውም በላይ፣ “ሰባት ቁጥርና  ህይወት”፣ “የእግዜር ድርሰት” አክሳሳፎስ፣ “የከተማው አህያ” ስልጡን ድንቁር” የተሰኙና ሌሎችም መፅሀፍት ደራሲ ናቸው፡



Read 20134 times