Sunday, 31 October 2021 18:08

ሱዳን ከየት ወዴት…?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እ.ኤ.አ በ2019…
በአምባገነናዊ አገዛዝ ለዘመናት ስትንገሸገሽ ኖራ፣ ሽራፊ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ እንደ ሰበብ ሆኖ በአልገዛም ባይነት ፈንቅሎ አደባባይ ያስወጣት ሱዳን፣ ለ30 አመታት አንቀጥቅጠው የገዟትን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር፣ በህዝባዊ አመጽ ከመንበረ ስልጣን አውርዳ፣ የዲሞክራሲ ብርሃን ፈነጠቀልኝ ብላ እልልታዋን አቀለጠች፡፡
246 ሱዳናውያንን ህይወት ቀጥፎ፣ ከ1 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለመቁሰል አደጋ ዳርጎ በስኬት የተጠናቀቀው ህዝባዊ አብዮት፤ አገሪቱን ከአልበሽር ነጥቆ የጦር ሰራዊቱና ሲቪሉ ለተጣመረበትና ወደ ዲሞክራሲ ያሻግራታል ተብሎ ተስፋ ለተጣለበት ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት አስረከባት፡፡
እየዋለ እያደር ግን፣ ጦሩና የሲቪል አመራሩ በፖለቲካ ሽኩቻ እርስ በእርስ መጠላለፋቸውን ተያያዙት፡፡ በስልጣን ሽሚያ የተጠመዱ ወታደሮችና ሲቪሎች ሱዳንን ዕጣ ይጣጣሉባት ያዙ፡፡
ከአንድ ወር በፊት በሲቪል መንግስቱ ላይ የከሸፈ መፈንቅለ መንግስት መሞከሩ ተነገረ፡፡ ይህን ተከትሎ በሲቪሉና በወታደሩ መካከል ያለው ፍጥጫ የበለጠ ተካረረ፤ የፖለቲካ ውጥረቱና ትኩሳቱ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መሄዱን ቀጠለ፡፡
በስተመጨረሻም የጦር ሃይሉ በአገሪቱ ልዑዋላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አል ቡርሃን መሪነት ባለፈው ሰኞ  ባካሄደው መፈንቅለ መንግስት፣ የሲቪሉን መንግሥት በታትኖ፣ ስልጣኑን መረከቡን አወጀ፡፡
ጄኔራሉ በዕለቱ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው በሰጡት መግለጫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፤ ሲቪል አስተዳደሩ መፍረሱንና ባለስልጣናቱ መታሰራቸውን፣ በመላ ሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን፤ በሐምሌ ወር 2023 ምርጫ ተደርጎ ህጋዊ መንግስት እስኪቋቋም ድረስም አገሪቱን የሚገዛት ወታደሩና ወታደሩ ብቻ እንደሆነ በይፋ አስታወቁ፡፡
በጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን የሚመራው የሱዳን የጦር ሃይል፣ በአገሪቱ የሽግግር መንግስት ሲቪል አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግስት በመፈጸም የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን፣ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውንና ሌሎች ታዋቂ ፖለቲከኞችን ማሰሩ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን ትኩስ ወሬ ሆነ፡፡
የጦር ሃይሉ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መንጠቁን የተቃወሙ በርካታ ሱዳናውያን፣ የካርቱምን ጎዳናዎች አጥለቀለቋቸው፤ መንገዶችን በጎማ ጭስና በድንጋይ በመዝጋት ንዴታቸውን በእሳት ነበልባል ገለጹ፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውን በቁጥጥር ስር ለማዋል እስከ አፍንጫው ታጥቆ የወጣው የጄኔራሉ ጦር በወሰደው እርምጃ፣ ከ10 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ140 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆሰሉ፡፡
ወታደሮች ተቃውሞውን አስተባብረዋል ያሏቸውን ግለሰቦች በቤት ለቤት አሰሳ እያደኑ፣ ወደ እስር ቤት ማጋዛቸውንና ተቃውሞው መባባሱን ተከትሎም፣ የጦር ሃይሉ በኡምዱርማን ከተማ የሚገኙትን የመንግስት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች መቆጣጠሩንና የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
የሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ሰራተኞችንና ከድንገተኛ ህክምና ውጭ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች በስራ ማቆም አድማ ላይ ሲሆኑ፣ የንግድና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን የዘገበው ቢቢሲ፤ ከሰኞ ጀምሮ ተዘግቶ የቆየው የካርቱም አለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ረቡዕ ማለዳ መከፈቱን አስታውሷል፡፡
የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት በአለም ዙሪያ ከሚገኙ በርካታ አገራት መንግስታትና ተቋማት ከፍተኛ ውግዘት የገጠመው ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ የወታደሩን ድርጊት በጽኑ በመኮነን የጸጥታው ምክር ቤት በሱዳን ላይ ፈጣንና ከበድ ያለ እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
አሜሪካ መፈንቅለ መንግስቱን ከማውገዝ ባለፈ በፍጥነት ባሳለፈው ውሳኔ፣ ለሱዳን ሊሰጠው የነበረውን የ700 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ማገዱን ያስታወቀ ሲሆን፣ በአፋጣኝ ወደ ሲቪል መንግስት አስተዳደር እንድትመለስ ጠይቋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ሱዳንን ከአባልነት በፍጥነት ያገደ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረትም፣ መፈንቅለ መንግስቱን በማውገዝ ወታደሩ ያሰራቸውን ፖለቲከኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ግን የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ የአረብ ሊግ፣ የሱዳን ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስበው በመግለጽ ጦሩ አገሪቱን ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ከሚያስገቡ ድርጊቶች እንዲታቀብ ያሳሰበ ሲሆን ሩስያና እንግሊዝን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መንግስታትም ውግዘት አሰምተዋል።
ጄኔራል አል ቡርሃን በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ "ሚኒስትሩን ያሰርናቸው ለደህንነታቸው ሰግተን ነው፤ ነገሮች ሲረጋጉ በሰላም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ አትስጉ" በማለት ህዝቡንም የተቀረውን አለምም ለማረጋጋት ሞከሩ፡፡
በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተነስተው በጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ቤት ከባለቤታቸው ሙና አብደላ ጋር በእስር ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ፣ በዚያው ዕለት አመሻሽ ላይ ከእስር ተለቅቀው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸው ተነገረ፡፡ ሃምዶክ ከእስር መለቀቃቸውን ተከትሎ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በስልክ መወያየታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከአንድ ቀን እስር ቢፈቱም፣ ሚኒስትሮችና ፖለቲከኞች እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ግን አሁንም ባልታወቀ ስፍራ በእስር ላይ እንደሚገኙና ምናልባትም ነውጥ በመቀስቀስ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚችል መነገሩን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከውጭም ከውስጥም ውግዘቱ የበረታባቸው የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ጄኔራል አል ቡርሃን ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ ጦሩ መፈንቅለ መንግስቱን ለማድረግ ውሳኔ ላይ የደረሰው አገሪቱን ካንዣበበባት የቀውስ አደጋ ለመታደግና ህዝቡን ከከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት ለማትረፍ ከማሰብ ቅንነት ብቻ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ “ቅን ሃሳብ” በወለደው መፈንቅለ መንግስት ሲቪሉን ገፍትሮ መንበሩን ለብቻው የተቆናጠጠው ወታደሩ፤ ሱዳንን ወዴት ሊያቀናት እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር እንደሚያዳግት ነው የፖለቲካ ተንታኞች የሚናገሩት፡፡


Read 1418 times