Sunday, 31 October 2021 18:01

ስንሞግተው የሚሞግተን ታሪክ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ተፈሪ መኮንን ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም ተወለዱ። በሶስተኛ ዓመታቸው ላይ እያሉ እናታቸውን ወይዘሮ የሽመቤትን በሞት አጥተዋል።
አባታቸው ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል በ13 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ ሰጥተው የጋራ ሙለታ አውራጃ ገዥ አድርገው ሾሟቸው። አባታቸው ራስ መኮንን መጋቢት 13 ቀን 1998 ዓ.ም አረፉ።
ከመጋቢት 1998 እስከ መስከረም 1909 ዓ.ም ድረስ   የደጃዝማች ተፈሪ ሕይወት መሾም መሻር፣ መገፋትና መታቀፍ የተፈራረቀበት  ጊዜ ነበር።
መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከስልጣን ወርደው ወ/ሮ ዘውዲቱን ምኒልክ የአባታቸውን አልጋ ወርሰው እንዲነግሱ ሲደረግ፣ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ራስ ተብለው አልጋ ወራሽ ሆኑ። ይህንን ቦታ ለማግኘት እራሳቸው ስለአደረጉት ጥረት የሚያመለክቱ መረጃዎች የሉም። “የአምላክ ፈቃድ ስለሆነ ነው” የሚሉ ግን ብዙዎች ናቸው፤ እሳቸውን ጨምሮ።
አዲሱ የንግሥት ዘውዲቱና የአልጋ ወራሹ ተፈሪ መኮንን መንግስት በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ለመጨበጥ ቢችልም፣ በሰላም መቀጠል አልቻለም። በቶራ መስክ በሰገሌ  የተከፈተው የእርስ በእርስ ጦርነት በርካታ ውዝግቦችን ለማስተናገድ ተገድዷል። የልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን፣ የንግሥት ዘውዲቱ አልጋወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን መሆን ያስቆጣቸው እንደነበሩም መጥቀስ ይቻላል።
ራስ ተፈሪ ንጉስ ሆነው ዘውድ እንዲጭኑ፣ ንግሥት ሳያማክሩ በራሳቸው ውሳኔ የፈለጉትን እንዲፈጸሙ የተደረገበት መንገድ አነጋሪ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ለምሳሌ ሊጋባ በየነ፤ አልጋ ወራሹ አልጋ ወራሽ እንጂ፣ የንግሥት ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ መሆን የለባቸውም ብለው የተቃወሙና ያመፁም መሆናቸውን ማስታወስ ይገባል። የኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማህበር አባል መሆን፣ የመጀመሪያው አይሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና የዘውዲቱ ሆስፒታልመቋቋም የአልጋ ወራሹ በአውሮፓ ያደረጉት ጉብኝት፣ ሥራ በንግሥቷ ዘመነ መንግሥት የተፈፀሙ ተግባራት ናቸው። እነዚህን ተግባራት የአልጋ ወራሹ ብቻ በማድረግ የታሪክ ሽሚያ የተፈጠረበት ጊዜም እንዳለ መታየቱ ሳይጠቀስ አይታለፍም። የደጃዝማች ከበደ ተሰማን የታሪክ ማስታወሻ ማየት ለነገሩ ማጥሪያ ይጠቅማል።
“ከመኳንንቱ የጥንት ልማድ ጠባቂዎች የሆኑትን አንዳንዶቹ የተሾሙበትን አገር እንደ ፈቃዳቸው ለመግዛት ያሰቡበትን አሳብ አስቀርተን፤ የተበደለ ሲጮህ፣ ጌታነታቸውን ሳንመለከት ስንፈርድባቸው፣ በግዛታቸው ከሚገኘው ገቢ ገንዘብ እንዲቀረጥ … ይህን የመሰለውን ወደ መንግሥት አግባ ስንላቸው፣ በሹም ሽሮ ከአንዱ አገር ወደ አንዱ ስናዘውራቸው ሐዘን ይሰማቸው ጀመር” የሚሉት ንጉሠ ነገሥቱ፤ ባለሙሉ ሥልጣን አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን፣ የደጃዝማች ባልቻን ግዛት ለሌላ ሰው በመስጠትና ሰራዊቱ ወደ አዲሱ ተሿሚ እንዲሄድ በማድረግ ደጃዝማች ባልቻን ከጥቂት ሰዎቻቸው ጋር እንዲቀሩ ማድረጋቸውን እናስታውሳለን። በደጃዝማች ባልቻ የተሞከረው ይህ መንገድ የታጠቁትን ባላባቶችና ባላባታዊውን ሥርዓት በማደከም ማዕከላዊ መንግሥቱን በማጠናከር ያደረገውን አስተዋፅኦ መቀበል ያስፈልጋል። ይህ ባይሆን ኖሮ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ ወደ ጫካ የገቡት ደጃዝማቾችና ፊታውራሪዎች በቀላሉ ይሸንፉ ነበር ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።
ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ከምንሊክ ቀጥሎ ከፍፃሜ ያልደረሰው ለባሮች ነፃነት የመሥጠት ተግባር የተቋጨው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው። ንጉሠ ነገስቱ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች፣ የአለም ጤና ድርጅት አባል እንድትሆን ከማድረጋቸውም በላይ በፍትሐ ነገስት መሠረት ሲካሄድ የቆየውን የአካል ቅጣት (እጅ እግር መቁረጥ) ያስቀሩም ናቸው። ዛሬም ድረስ አገራችን እየሰራችበት ያለው የፍትሐብሔርና የንግድ ሕግ በቅርቡ እስከተሻሻለበት ጊዜ ድረስ ሲያገለግል የቆየው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የንጉሡ መንግሥት አበርክቶዎች ናቸው። በፊት ፈሰስ፣ የጢስ፣ የማር፣ የፈረሰኛ ወዘተ እየተባለ ይከፈል የነበረውን ግብር ወደ አንድ የታክስ ሥርዓት ማምጣት መቻሉ የዚያ መንግስት አገልግሎት መሆኑ ሊታመን ያስፈልጋል።
ንጉሠ ነገስቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የበጎ አድራጎት ስራውን ገና ልጅ እያሉ የጀመሩት ቢሆንም “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት” የሚል ድርጅት በማቋቋም በጤና ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በእናቶች ጤና፣ በእድሜ የገፉ ሰዎችን መጦሪያ ቦታ በማዘጋጀት አይነ ስውራንን በልዩ ልዩ ሙያ በማሰልጠን ለፍሬ እንዲበቁ አድርገዋል።
ሚያዚያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም  በራሳቸው ገንዘብ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በማቋቋም የትምህርት ስራን ጉዳዬ ብለው የያዙት ንጉሠ ነገሥቱ፤ እራሳቸው የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ከመሥራታቸውም በላይ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለትምህርት ወደ ውጭ በመላክ ተምረው ሲመለሱ አገራቸውን በልዩ ልዩ ኃላፊነት ላይ እየተመደቡ እንዲያገለግሉ አድርገዋል።
በአራዳ ዘበኞች ላይ የነበረው የሀገሪቱን ዘመናዊ የወታደር አደረጃጀት በአይነትና በመጠን በማሳደግ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል፣ የፖሊስ ራዊት ከማቋቋማቸውም በላይ ኤርትራ ስትገነጠል ፈረሰ እንጂ በምስራቅ አፍሪካ አለ የተባለ የባሕር ኃይልም አቋቁመው ነበር።
በማይጨው ጦርነት በቂ አመራር አልሰጡም፣ አስተዳደራቸውን ዘመናዊ ማድረግ አልቻሉም፣ ለህዝብ በፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀት መብት አልፈቀደም፣ የኤርትራንና የኢትዮጵያን የፌደሬሽን ግንኙነት ባያፈርሱ ኑሮ ጦርነት ውስጥ አንገባም ነበር፣ ብሔረሰቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ በመዝጋቱ አገሪቱን የብሔረሰቦች እስር ቤት አድርገዋታል ወዘተ ወዘተ የሚሉ ክሶች በንጉሡ ላይ ይቀርባሉ። በአንጻሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የምትሳተፍባቸው ሁኔታዎች በተወሱ ቁጥር የሚጠራው የአሳቸው ስምና መንግሥት ነው። የአፍሪካ አገሮች ነፃነትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የንጉሡ ድካም ውጤት መሆኑን ከመናገር ደግሞ ቦዝነን አናውቅም።  ስንሞግተው እየሞገትነው፣ ያለው የንጉሡ ታሪክ አንድ ቦታ አንድ አይነት የአክብሮት ማሳያ ሥራ ይጠብቃል።
መጪው ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ የጫኑበት ቀን መሆኑ የጽሁፌ መነሻ ነው።

Read 1572 times