Sunday, 31 October 2021 16:17

(IVF) በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

ምቹ ክሊኒክ ሀያ ሁለት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በአዲስ አበባ ይገኛል፡፡ በዚህ ክሊኒክ ከሚሰጡት የተለያዩ ሕክምናዎች መካከል ከፍተኛውን ቦታ የሚይዘው ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና ነው፡፡ በዚህ ክሊኒክ ተገኝተን ዶ/ር ቶማስ መኩሪያ በ22 የሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመካንነት ማእከል ዋና ኃላፊን አነጋግረናል፡፡ ዶ/ር ቶማስ መኩሪያ መረጃውን እንደሚከተለው አብራርተውልናል፡፡
IVF ማለት የህክምናው ዘዴ እንደሚከተለው ነው፡፡
ከሴትዋ እንቁላል ይወሰዳል፡፡ ለማሳደግ የሚረዱ መድሀኒቶች ይሰጣሉ፡፡ ከወንዱ ደግሞ ዘረመል ይወሰድና በላቦራቶሪ ጽንስ ይመሰረታል፡፡ ከ3-5 ቀን ጽንሱ በላቦራቶሪ ካደገ በሁዋላ ወደ ማህጸን ይገባል፡፡ ማህጸን ይህንን ከውጭ የሚሰጠውን ጽንስ ተቀብሎ ለማሳደግ እንዲዘጋጅ የሚያደርጉ መድሀኒቶችም ይሰጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና የሚሰጥበት የህክምና ተቋም በፐብሊክ ሆስፒታል ደረጃ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ ስራው የተጀመረውም ከሁለት አመት በፊት በ2011ዓ/ም ነው፡፡ ከዚያ በፊት በግል ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ የመካንነት ችግር የገጠማቸው ሰዎች በላቦራቶሪ አማካኝነት ልጅ እንዲወልዱ የሚያደ ርገው ሕክምና አልነበረም፡፡
የመካንነት ችግር በየፐብሊክ ሆስፒታሉ እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅም ምን ያህል ሰፊና ጥያቄውን መመለስ የሚያስፈልገው የህክምና አገልግሎት መሆኑን ባለሙያዎች ተረድተውት ነበር፡፡ ይህን አገልግሎት ለመስጠት የተዘገየበት ምክንያትም በጣም ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ማፍሰስ አስፈላጊ በመሆኑ ሁኔታውን ከሌሎች ሰዎች ጋር መነጋገር ግድ በመሆኑ ነበር። ስለዚህም በጊዜው የነበረው አመራር ከፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሀ ጋር በመወያየት ፕሮፌሰር ሰናይት ከሚሺጋን ዩኒቨርስቲ እና ሰርት ከሚባል መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፍ እንዲገኝ ረድተዋል፡፡ ባጠቃላይ ይህንን ማእከል ለማቋቋም ወደ 3.5 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ ሲሆን ግማሹን መንግስት ሲሸፍን የተቀረው መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተደረገ ድጋፍ እንዲቋቋም ተደርጓል ብለዋል ዶ/ር ቶማስ፡፡  
ክሊኒኩ ሲቋቋም ለአምስት መቶ ሰዎች የሚሆን መገልገያ የሚሆን ድጋፍ ተደርጎ ነበር። ይህ በድጋፍ የተሰጠ መገልገያ ካለቀ በሁዋላ ግን ድጎማው ስላልቀጠለ የተወሰነ ችግር ማጋጠሙ አልቀረም። የመካንነት ችግር በሀገር ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ያለ ስለሆነ አቅም ያላቸው ወደውጭ ሀገር በመሄድ ስለሚያሰሩ ብዙ ገንዘብ ማለትም ወደ 10.5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ሀገሪቷ እንድታጣ የሚያስችላት ነው፡፡  ይህንን የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ለማስቀረት እና ሌሎችን አቅም የሌላቸውንም ለመደጎም እንዲረዳ ክሊኒኩ የራሱን ገቢ በመፍጠር አገልግሎቱን መቀጠል የሚቻልበት መንገድ ተቀየሰ። በዚህም ሁለት አይነት የህክምና አሰጣጥን በመንደፍ በአሁኑ ወቅት የግል እና የመደበኛ በሚል ታካሚዎችን በመለየት በግል የሚታከሙት ሙሉ በሙሉ ለሚሰጣቸው አገልግሎት እስከ 120.000 (መቶ ሀያ ሺህ ) ብር ይከፍላሉ፡፡ በዚህ በሚገኘው ገንዘብ በመደበኛው አገልግሎት ተጠቃሚ ለሚሆኑ እና ለክሊኒኩ የተለያዩ ወጪ ዎችን ለመሸፈን ጥረት ይደረጋ፡፡
ዶ/ር ቶማስ አክለውም በክሊኒኩ አገልግሎትን ለማግኘት ከመላዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሀገራት ማለት ከኤርትራ፤ ከሱዳን፤ ከጂቡቲ፤ ከሱማሌ ይመጣሉ፡፡ ተገልጋዩ በጣም ብዙ ስለሆነ ተራ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ለምሳሌም አንድ ሰው በመደበኛው አገልግሎት IVF (ልጅ ለማግኘት) እስከ ሶስት አመት ወረፋ ሊጠብቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ የመደበኛው አገልግሎት የሚሰጠው ወረፋ በመጠበቅ ሲሆን የግል ተጠቃሚዎች ግን ቅድሚያን ያገኛሉ፡፡ የግል ታካሚዎች ምናልባትም በአንድ እና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ IVF ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከግል ታካሚዎች በሚገኘው ገንዘብ መደበኛው አገልግሎት ድጎማ ተደርጎለት ይሰጣል ብለዋል፡፡
በመደበኛው አገልግሎት IVF የሚሰራላቸው ለአገልግሎት ሳይከፍሉ ለመድሀኒቶች ብቻ ቢበዛ እስከ አርባ እና ሀምሳ ሺህ ዝቅተኛው ደግሞ እስከ ሀያ ሺህ ብር ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ በግል የሚታከሙ ደግሞ እስከ 120 ሺህ ብር ይከፍላሉ፡፡ ይህ አገልግሎት በውጭ ሀገር ይሰጥ ቢባል ማረፊያና ትራንስፖርት የመሳሰሉትን ሳይጨምር ለህክምናው ብቻ ከ500.000 አምስት መቶ ሺህ እስከ 600.000 ስድስት መቶ ሺህ ብር ድረስ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ስር የተቋቋመው ምቹ ክሊኒክ በመጀመሪያ ስራውን ሲጀምር የማርገዝ እድሉ ያላቸው እየታዩ አገልግሎትን ስላገኙ እስከ 60% የሚሆን እርግዝና እንዲከሰት እድል ፈጥሮአል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ክሊኒኩ ሁሉንም ታካሚ እንደ ወረፋው እየተቀበለ የሚሰራ በመሆኑ አገልግሎቱን ከሚያገኙት መካከል እርግዝና የሚከሰተው እስከ 40% ለሚሆኑት ነው ብለዋል ዶ/ር ቶማስ፡፡
የመካንነት ችግር ወንዶቹንም ሴቶቹንም በእኩል ደረጃ የሚያጠቃ ነው፡፡ ስለዚህ ወንዱ ላይም ይሁን ሴትዋ ላይ ያለው ችግር ሲታይ ምናልባትም በቀላሉ የሚፈታ ሆኖ እስከ IVF መድረስ ሳያስፈልግ በቀላሉ በመድሀኒት ወይንም በኦፕራሲዮን ልጅ ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ከበድ ያለ ችግር ከሆነ ደግሞ IVF እንዲደርሱ ተደርጎ በላቦራቶሪ እገዛ ልጃቸውን እንዲያገኙ ይሆናል፡፡       
ዶ/ር ቶማስ እንዳሉት በIVF ሁሉም ሴቶች ማርገዝና ልጅ መውለድ ይችላሉ የሚል የተሳሳተ እምነት አለ፡፡ አንዲት ሴት እራስዋ እንቁላል ከሌላት በስተቀር እንቁላልን በሕክምናው መፍጠር ስለማይቻል እርግዝና እንዲፈጠር ማድረግ አይቻልም፡፡ አንዲት ሴት ካረጠች ወይንም እንቁላልዋ አስቀድሞ መፈጠሩን ካቆመ እርግዝናን መሞከር ስለማትችል ከሌላ ሴት እንቁላል ተወስዶ ከባልዋ ዘረመል ጋር ተዳቅሎ ልጅ ማግኘት ትችላለች። ይህ የሌላዋ ሴት እንቁላልና የባለቤትዋ ዘረ መል ከተደባለቀና በላቦራቶሪ ካደገ በሁዋላ እርግዝናውን እስዋ እንድታረግዘው ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ አሰራር ግን በኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ በሕግ ማእቀፍ ውስጥ ያልገባ እና ያልተፈቀደ ስለሆነ በአሁኑ ሰአት እየተሰራ አይደለም፡፡ አንዲት ሴት እድሜዋ ለማረጥ ከመድረሱ በፊት እንቁላል ልታጣ የምትችለው በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን ከነዚህ መካከልም ሕመም፤ ኢንፌክሽን፤ የተለያዩ አይነት ሕክምናዎች ሊያስከትሉት ከሚችለው ጫና ሊሆን ይችላል፡፡
ዶ/ር ቶማስ እንዳስረዱት በአገራችን ይህ አገልግሎት እጅግ በመዘግየቱ ምክንያት ብዙዎች ልጅ ሳይወልዱ እድሜአቸው በማረጡ ፍላጎታቸውን በጣም ይገልጻሉ፡፡ ከሌላ ሴት እንቁላል ማግኘት እና በማረጥ እድሜ ካለችው ወይንም እንቁላልዋ በተለያዩ ምክንያቶች ከተቋረጡት ባል ዘረመል ጋር ተዳቅሎና አርግዘው ልጅን መውለድ የሚፈልጉ እጅግ በጣም በርካቶች ናቸው፡፡ በእኛ ሀገር ይህንን አገልግሎት መስጠት ባለመቻላችን ብዙዎች ውጭ ሀገር በመሄድ ብዙ ገንዘብ ከፍለው ያውም የራሳቸው ዜጋ ካልሆኑ ሴቶች እንቁላል በመግዛት ልጅ እንዲወልዱ የሚደረግበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ይህ ከሚሆን ግን አገልግሎቱን በህግ አጽድቆ በኢትዮጵያ መስጠት ቢጀመር በጣም ጥሩ እንደሚሆን እንደባለሙያ እምነቴ ነው ብለዋል ዶ/ር ቶማስ መኩሪያ፡፡
ለIVF አገልግሎት በምቹ ክሊኒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመታየት ከ5000 (አምስት ሺህ) በላይ ጥንዶች ተመዝግበው ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በቀን ቅዳሜና እህድን ጨምሮ ቢያንስ 50-ሀምሳ ጥንዶች ይታያሉ፡፡ እስከአሁን ድረስ ከሶስት ሺህ በላይ ጥንዶች IVF የተሰራላቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 40% ማለትም ወደ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ወይንም አንድ ሺህ ሶስት መቶ ያህል እርግዝናዎች ተፈጥረዋል፡፡ ልጆችም ተወልደዋል፡፡
IVF ከተሰራ በሁዋላ ልጅ እንዳይረገዝ የሚያደርጉ ምክንያቶች ያጋጥማሉ፡፡ ከማህጸን ግድግዳ ጋር አለመገናኘት ወይንም አለመጣበቅ፤ የእንቁላሉና የዘረ መል ጥራት የጽንሱንም ጥራት ስለሚወስነው በመሳሰሉት ምክንያቶች ጉድለት ካለ ከማህጸን ግድግዳ ጋር ተጣብቆ ማደግ ስለሚሳነው ተመልሶ ሊወርድ እንደሚችል ማወቅ ይጠቅማል፡፡
ዶ/ር ቶማስ እንደገለጹት ክሊኒኩ በአሁኑ ወቅት ደረጃውን ጠብቆ አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ባለሙያዎች አሁን ካለው በበለጠ እንዲኖሩ፤ በኢኮኖሚ አቅሙን እንዲጎለብት የመሳሰሉት ስራዎች ትኩረትን ይፈልጋሉ፡፡

Read 13191 times