Print this page
Sunday, 31 October 2021 16:18

ጓሣና ድንግል ያለ አንድ ቀን አይበቅል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የልምድ አዋላጅ የሚባል ለብዙ ዓመታት የሠራ ነገረ ፈጅና ነገር የበላ ጠበቃ የተባለ፤ስመ-ጥሩ ጠበቃ፤በውርስ ምክንያት ጭቅጭቅ ላይ ያሉ ቤተሰብ አባላትን ሊያማክር ሲጠብቅ፤በቀጠሮ ቦታ ላይ ሳይመጡለት ይቀራሉ፡፡
ቆሞ ተስፋ ሳይቆርጥ ሲያስብ ቆይቶ ቢያንስ የጥብቅና ገቢውን የነጠቀው ማን እንደሆነ ለማወቅ ወደ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራ፡፡
ልደታ ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ገደማ ቆሞ ግራ ቀኙን ሲያማትር ፣አንድ ሌላ ጠበቃ ያገኛል፡፡ ቀልደኛ ወዳጁ ነው፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፤
“ወዳጄ እንደ ምን ከርመሃል?”ይለዋል፡፡
“ደህና ነኝ፡፡ አንተስ ወዳጄ? ስራ እንዴት ይዞሀል?”
“ምንም አይል፡፡ ምን የእኛ ነገርኮ ዛሬ፡-
‹ነገረ-ፈጅ፣
 ከርሞ ልቡን ይፈጅ›
እንደሚባለው ሆኗል፡፡ የቀጠሮ ብዛት እንጀራ አላስበላ ብሎናልኮ፡፡” አለው፡፡
“ይሁን እስኪ፡፡ እንዲያውም የዛሬዎቹ ደንበኞቼማ ከናካቴው አልመጡም፡፡ እስኪ ዘወር ዘወር ብዬ ልያቸው  “ብሎት ደንበኞቹን ፍለጋ ሄደ፡፡
ከሩቅ ደንበኞቹ ሲመጡ ተመለከተና ወደ ታችኛው በር እያመሩ መሆኑን ሲገነዘብ፣ ፈጠን ብሎ ሊደርስባቸው ይሮጥ ጀመር፡፡ ሊከተላቸው እየሞከረ ሳለ፣ከሌላ ወጣት ጠበቃ ጋር እንደ ሆኑ አየ፡፡ አዲሱ ቀልጣፋ ጠበቃ ገበያውን እየነጠቀው መሆኑን ተገነዘበ፡፡
አሁን ፈጥኖ እየሮጠ ሊከተላቸው ቢሞክርም የሚደርስባቸው አይደሉም። እያለከለከ ሊከተላቸው ሞከረ፡፡ ነገር ግን ሊደርስ አልቻለም፡፡ ልቡ ልትፈነዳ ስትቃረብ ደክሞት ቆመና፤እንዲህ አላቸው፡-
“የው፤ በዚህ አይነት ፍርድ ቤቱን ታልፉታላችሁ!”
እነሱ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
“The dog barkes but the caravan goes” ይላሉ ፈረንጆቹ፡፡ “ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሎቹ ግን መጓዛቸውን ቀጥለዋል” እንደ ማለት ነው፡፡ በማንም ጩኀት ሳይበገር መንገዱን የሚቀጥል ሰው እግቡ ይደርሳል ወይም የልቡን ያደርሳል ነው፡፡ አልመንና አቅደን የተጓዝነውን መንገድ አለማቋረጥ የልበ ጥሩነትም ፣የልበ ሙሉነትም ዕፁብ ተግባር ነው፡፡ ማቀድ ዝግጁነትን፣ ዝግጁነት ደግሞ ለፍጻሜ መብቃትን ያመላክታል፡፡ ለዳገት የጫንከው ፈረስ፤ ሜዳ ላይ እንዳይደክም በጽናት እንንቀሳቀስ፡፡ ያለንን ምጥን “ሐብትና ሀይል በእግባቡ መጠቀም ፤ብክነትን መከላከል ዋና ነገር ነው ፡፡
ገናላደርግ ነው ፤ልዋጋ ነው ብሎ መፎከር ሳይሆን፤ ካደረግን በኋላና ካሸነፍን ወዲያ መናገር ብልህነት ነው ማወቅ ላይ ብልህነት  (WISDOM) ካላከልንበት፣ አልፈን ተርፈንም ወደ ተግባር ክልለወጥነው ግብረ ቢስ-ነባቤ ብቻ ይሆንና ፍሬ-አልባ እንሆናለን፡፡የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ ለምንም አይበጅም፡፡
ምንም ነገር ስንሰራ ፍጥነትን ግምት ውስጥ እናስገባ፡፡ ”የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው”ማለት ብቻ ሳይሆን “ደህና ቦታ ፈጭተሽ ፤ዱቄቱን አምጪው” ማለት መልካም ነው፡፡” በዱሮ በሬ ያረሰ  የለም “የሚለውንም፤ ”ዱሮም ታርሷል፤ዛሬ የተሻለ ይታረሳል፤ነገ እጅግ የበዛ ይታረሳል!” እንበለው፡፡ ለውጥ እጃችን ላይ ነው ያለው፡፡ እጃችንን አንጠፈው፡፡ መንፈሳዊ ፉክክራችንን አናቋርጥ፡፡ የተሻለ አለም እንፍጠር፡፡ አዲሱ እንደሚያሸንፍ አንርሳ (THE NEW IS INVINCIBLE- እንዲል መጽሐፉ) አዲስ ለውጥ እናፍራ፡፡ ለዋጭም ተለዋጭም እንሁን!
ለውጣችንም የወረት አይሁን፡፡ የአንድ ሰሞን ንግግር ሳይሆን ዘላቂ ህይወትን ለመምራት የሚበጅ ስልት እናኑር ፡፡
ገጣሚው፤እንዳለው፡-
“ማሸነፍን እናስብ
መሸነፍ እንዳለ አንርሳ
መሸነፍ ሲደርስብንም
ማሸነፍ እንዳለ እናውሳ
መውደቅ ከመነሳት ጋር
የሳንቲም ሁለት ገጽታ
አገለባበጡን ማወቅ፤ ብቻ ነው ድል ሚያስመታ
 በዘውድና በጎፈር፤ በሰው በአውሬ ጨዋታ!
ውሉ የሚለይበት ነው፤ ቀን ውለን የማታ የማታ!
አፈራርቀን መያዝ ስንችል፤ ቅን ፍጥነትን ከዝግታ
 -ሩጫን ከልባም ፋታ!!”
ሁሉንም ነገራችንን የበሰለ ዕድልና፤ የበሰለ ጊዜ እንዳያመልጠን አድርገን እንያዘው፡፡ አበው፤ "ጓሣና ድንግል ያለ አንድ ቀን አይበቅል” የሚሉን ይሄንኑ ሊያስረግጡልን ነው!!    

Read 13244 times
Administrator

Latest from Administrator