Sunday, 31 October 2021 15:22

ኢትዮጵያ ከአጎዋ እንዳትሰረዝ የማግባባት ስራ እየተሰራ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ በአጎዋ ተጠቃሚነት የመቀጠል ያለመቀጠል ጉዳይ በቀጣይ ቀናት ውሳኔ ያገኛል

ምርታቸውን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ የማስገባት እድል ከሚሰጠው የአጎዋ ስምምነት ኢትዮጵያን ለመሰረዝ የአሜሪካ መንግስት ማቀዱን ተከትሎ፣ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እቅዱን ለማስለወጥ የተደራጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ከአጎዋ እድል ተጠቃሚነት የሚያሳግድ ምክንያት እንደሌለ የሚያስረዱት በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን የህዝብ ጉዳይ  ኮሚቴ ሠብሳቢ አቶ መስፍን ተገኑ፤ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ስምምነት የምትሰረዝበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡
ለ21 ዓመታት በዘለቀውና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ የአፍሪካ ሃገራትን ተጠቃሚ ባደረገው የአጎዋ ስምምነት መሰረት በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ወደ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ከማድረጋቸው ባሻገር ለሃገሪቱም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በአጎዋ ስምምነት ላይ የተጠቀሱ  የስምምነቱ መመሪያዎችን ያስታወሱት አቶ መስፍን ከእነዚህ መመሪያዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተቀመጠውን በመጥቀስ፤ “ኢትዮጵያ ጥሰቶችን እየፈፀመች ነው” በሚል ክስ ከእድሉ ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ በተለያዩ አካላት  ማግባባቶች እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ውንጀላ ትክክል አለመሆኑን ራሳቸው የሚመሩት ኮሚቴ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት  ማስረዳቱን እንዲሁም 10 ሺህ ሰዎች የፈረሙትን የተቃውሞ ፊርማ ማስገባታቸውን  ገልፀዋል፡፡
በመጪው ሳምንት በጉዳዩ ላይ 19 ድርጅቶች ያሉበት የአጎዋ ጉባኤ በቀረበው ሃሳብ ላይ በድምጽ ብልጫ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ የታወቀ ሲሆን በዚህም በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የማግባባት ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአገዋ አባልነት የምትሰርዝ ከሆነ 1 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የስራ እድል በማጣት በቀጥታ ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡

Read 9885 times