Sunday, 31 October 2021 15:59

በውል ያልተቋጨው የኮንሶና አካባቢው ግጭትና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ላለፉት 4 ዓመታት የአርሶ አደሮች ማሳ አልታረሰም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሁለት ዓመት ት/ቤቶች እንደተዘጉ ናቸው

ባለፈው ሁለት ዓመት ት/ቤቶች እንደተዘጉ ናቸው
         የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ክልል ኮንሶ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣አሌ እና ጉማይሌ ወረዳዎች የሚቀርቡ አስተዳደራዊ ጥያቁዎችን ተከትሎ ሲፈፀሙ የነበሩ ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶችን ያጣራበትን የምርመራ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢሠመጉ በዚህ ባለ 31 ገፅ ሪፖርቱ፣ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢዎቹ ሰገን ዞን በሚል በአንድ ዞን ስር መጠቃለላቸውን ተከትሎ በሚነሱ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ሳቢያ አካባቢው ለዓመታት አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማስተናገዱን አመልክቷል፡፡
በተለይ በ2011 ዓ.ም ወትሮም ተቀባይነት ያላገኘው የሰገን ዞን መፍረሱን ተከትሎ እንደገና ዞኖችንና ልዩ ወረዳዎችን ለማዋቀር የተደረገው አስተዳደራዊ ጥረት ተቃውሞ በመቀስቀሱ በአካባቢው ከ2001 ጀምሮ ላለፉት 4 ዓመታት ያልተቋረጠ ግጭት  መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡
በአካባቢው ለምን እንዲህ ያለ ጥያቄ አቀረባችሁ በሚል በመንግስት ሃይሎች በተከታታይ በሚወሰዱ እርምጃዎች፣ ከ2011 ጀምሮ ከ80 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪ መፈናቀሉን፣45 ሺህ ያህል ህዝብ መኖሪያ ቤቱንና ንብረቱን በእሳት ተቃጥሎ መወድሙንና ተጎጂዎች ያለ ጠያቂ ሜዳ ላይ ተበትነው መቅረታቸውን፣ 181 ንፁሀን ዜጎች በተለያዩ ጊዜ ያተረ ከቡርጂ፣ከኮንሶና ከአማሮ ወረዳዎች በታጠቁ ሃይሎችና በክልሉ ልዩ ሃይል መገደላቸውን የኢሠመጉ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
በዚህ ባልተቋረጠ ግጭትና ሁከት በቢሊዮኖች የሚገነት ንብረት መውደሙን፣ የቀረውም በተደራጁ ቡድኖች መዘረፉን፣ ከ2011 ጀምሮ የአርሶ አደሩ ማሳ ጦሙን እያደረ ማሳቸውን ለማረስ ሲሞክሩ በክልሉ ልዩ ሀይል የተገደሉ ሰዎችም በርካቶች ናቸው ይላል ሪፖርቱ፡፡ “የማህበረሰቡ ማህበራዊና ኦኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ለሙሉ ተገቷል፤ ገበያ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር  ተዘግቷል፣ ትራንስፖርት ከተቋረጠ አምስት ወራት አስቆጥሯል፤ወደ 22 የሚጠጉ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለሁለት ዓመት እንደተዘጉ ናቸው፤ ለ17 ቀበሌያትና በአቅራቢያው ላሉ ህዝቦች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባው የሰገን ከተማ ሆስፒታል የእስረኞች ማጎሪያና የወታደር ካምፕ ሆኗል፤ የኦርቶዶክስና ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም የእስልምና መስጊዶች ተዘግተዋል፤ የተጀመሩ የመንግስትና የግል የልማት ስራዎች አብዛኞቹ ባሉበት ቆመዋል” ይላል የኢሠመጉ ሪፖርት፡፡
በአካባቢው የተፈጸሙ ግድያዎችም እጅግ ኢ-ሰብአዊና ነውረኝነት የተሞላባቸው መሆኑን ያመለከተው ኢሠመጉ፤ ለአብነትም በኩስሜ ወረዳ ከተገደሉ 28 ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ኩሴ ዱባሮ የተባሉን ግለሰብን ከመኪና ካወረዱት በኋላ በህይወት እያለ እጁን በመቁረጥና መልሰው በራሱ እጅ ማለትም በቆረጡት እጅ እየደበደቡ አሰቃይተው ከገደሉት በኋላ አስክሬኑን ደብዛውን ማጥፋታቸውን ኋላ በተደረገ ምርመራ፣ አስክሬኑን ሽንት ቤት ውስጥ ተጥሎ መገኘቱን፤ ሌሎች 3 ሰዎች ደግሞ እስካሁንም የት እንዳደረሷቸው እንደማይታወቅ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
አካባቢው አሁንም ወደ መደበኛ ሠላምና መረጋጋት አለመመለሱን የጠቆመው የኢሠመጉ ሪፖርት፤ ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ አካባቢውም ወደ ሠላማዊ መንገድ እንዲመለስ ያግዛሉ ያላቸውን ምክረ ሃሳቦች አቅርቧል፡፡
ለተጎጂዎች ተገቢው ካሳ እንዲሰጥና የመልሶ ማቋቋም ስራ እንዲሰራ፣ የአካባቢውን ሠላም በማስጠበቅ ሁኔታውን የበለጠ ለመጣራት የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር፣ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት የሆኑት ችግሮችና ጥያቄዎችን ከሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመመካከር ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ በዜጎች ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ያደረሱ የመንግስት አካላት ለህግ እንዲቀርቡ እንዲሁም መንግስት አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በመመርመር፣ ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርግና ዜጎች ከሚደርስባቸው ጥቃት የሚከላከላቸው ተቋማዊና ህጋዊ ስርዓት እንዲዘረጉ ኢሠመጉ አሳስቧል፡፡
      

Read 11078 times