Monday, 25 October 2021 00:00

1.3 ቢ. የአፍሪካ ህዝብ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋ በእጅጉ ተጋልጧል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    - አደገኛ ሙቀት ከ2 ቢ. በላይ የከተማ ነዋሪዎችን ተጎጂ አድርጓል

              በአፍሪካ የሙቀት መጠን ከተቀረው አለም በባሰ ከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ላይ እንደሚገኝና በዚህም ሳቢያ በአህጉሪቱ የሚኖረው 1.3 ቢሊዮን ህዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚፈጠሩ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆኑን ተመድ ባወጣው ሪፖርት አስጠንቅቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሜትሮሎጂ ድርጅት ከሰሞኑ ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ኦል አፍሪካን ኒውስ እንደዘገበው፣ 54ቱ የአፍሪካ አገራት ለአለማቀፉ የበካይ ጋዝ ልቀት ያላቸው ድርሻ 4 በመቶ ያህል ብቻ ቢሆንም፣ መላው የአህጉሪቱ ህዝብ ግን ያለሃጢያቱ በአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ሰለባ እየሆነ ይገኛል፡፡
በመጪዎቹ አስር አመታት ውስጥ 118 ሚሊዮን ያህል እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የድርቅ፣ ጎርፍና የከፍተኛ ሙቀት ሰለቦች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሪፖርቱ ማስጠንቀቁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ አደገኛ የሆነ እጅግ ከፍተኛ የሙቀት ክስተት ከአለማችን ከተሞች መካከል ግማሽ ያህል በሚሆኑት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝና ክስተቱ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ2 ቢሊዮን በላይ የከተማ ነዋሪዎችን ተጎጂ ማድረጉን አንድ አለማቀፍ ጥናት አስታውቋል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ አጥኚዎች የተከናወነውና ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው ይህ ጥናት፣ አደገኛ የሆነ ከፍተኛ ሙቀት ተጋላጭነት በአለማቀፍ ደረጃ ባለፉት 34 ያህል አመታት በ200 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
በአለማችን በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ ሙቀት የተጋለጡባቸው ቀዳሚዎቹ ከተሞች የባንግላዲሽዋ ዳካ እና የህንዶቹ ዴልሂና ካልካታ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ ባንግላዲሽ በየአየር ንብረት ለውጥና የህዝብ ብዛት ከመጠን ያለፈ ሙቀት ተጋላጭነትን ከሚያሳድጉ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀሱም ተዘግቧል፡፡


Read 2671 times