Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 11:34

የተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ፈተናዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሽግግር - ፓርቲዎች ወደሚፎካከሩበት እውነተኛ ምርጫ

እመርታ - የዜጎችን ኑሮ ወደ ሚያሻሽል የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ

የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብና ማስነገር ብቻውን በቂ አይደለም። በተጨባጭ የዜጎችን ኑሮ የሚሻሽል የነፃ ገበያ ስርዓት ማስፋፋት ያስፈልጋል - ዘመኑ የቢዝነስ ዘመን ነውና። አመት እየቆጠሩ የፖለቲካ ምርጫ ማካሄድ ብቻውን በቂ አይደለም። የአገራችን የፖለቲካ ምርጫዎች፣ ዜጎች በነፃነት የሚሳተፉበትና ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት መሆን አለበት - ዘመኑ የ”ዲሞክራሲ” ዘመን ነውና። አንድ ሁለት የቲቪ ቻናሎችን መጨመርና

የኤፍኤም ጣቢያዎችን ማበራከት ብቻውን በቂ አይደለም። የግል ነፃ ሚዲያ እንዲስፋፋ መፍቀድ ይገባል - ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነውና።ዜጎች ህግ አክባሪ እንዲሆኑ መጠበቅ ብቻውን በቂ አይደለም። ከሁሉም በፊት መንግስት ራሱ የህግ ተገዢ በመሆን የህግ የበላይነትን ማስፋፋት ይኖርበታል - ዘመኑ የመንግስት ገናናነትን ሳይሆን የመንግስት ቅነሳን የሚጠይቅ ነውና። ከጓዳ እስከ አደባባይ የዜጎችን ህይወት ለመቆጣጠር ከታች እስከ ላይ “1ለ5” በቡድንና በተዋረድ ከማደራጀት ይልቅ፤ እያንዳንዱ ሰው እንደዝንባሌው እንዲሰራና እንደፈቀደው እንዲተባበር የሚያነቃቃ የነፃነት መንፈስን ማስፈን ያስፈልጋል - ዘመኑ የፈጠራ ዘመን ነውና። በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በፕሬስ ነፃነት፣ በህግ የበላይነትና በነፃነት መንፈስ ዙሪያ የተጠቀሱት አምስት ፈታኝ ስራዎች  በሙሉ፤ ስልጣኔን የመገንባት የረዥም ጊዜ ፈተናዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

ቅድሚያ ለእርጋታ - ሹመት ያዳብር

በእርግጥ ከዋና ዋናዎቹ ፈታኝ ስራዎች በፊት መቅደም ያለበት ሌላ ስራ አለ - የተረጋጋ  ሁኔታን መፍጠር። “ኖርማላይዜሽን” ልንለው እንችላለን። ለምሳሌ፣ በፖለቲካው መስክ፣ መሪዎችን በጊዜ መሰየም ወይም መመደብ፣ አንድ የማረጋጊያ ስራ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። ከሁለት ወራት በፊት በነበረው “ኖርማል” ሁኔታ፤ ኢህአዴግ ሊቀመንበር ነበረው፤ መንግስትም ጠቅላይ ሚኒስትር ነበረው። ይህንን ማሟላት ያስፈልጋል።

በእርግጥ፤ “ሊቀመንበር የመምረጥ ጉዳይ ተራ ነገር ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትርን መሾም አያቻኩልም” ብሎ መናገር ይቻላል - አንዳንዴ ኢህአዴግ እንደሚለው። ነገር ግን ተራ ነገር አይደለም። አዎ፤ መቻኮልና መደናበር ተገቢ አይደለም። ነገር ግን፤ “ተራ ነገር ነው” ብሎ ጉዳዩን ማቃለልም፣ የትም የማያደርስ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን አያልፍም። ደግነቱ፤ ሰሞኑን አርብ እና ቅደዳሜ 180 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት የድርጅቱን ሊቀመንበር እንደሚመርጥ ተገልጿል። የኢህአዴግ ሊቀመንበር ተሰየመ ማለት፤ የመንግስት መሪ ማን እንደሚሆን ታወቀ ማለት ነው - በፓርላማ በሚፀድቅ ሹመት የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ ይይዛል። መሪዎችና ምክትሎች ተሰይመው ሲሟሉ፤ ቢያንስ ቢያንስ በቅርፅ ደረጃ የተረጋጋ ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው።

ቅድሚያ ለኑሮ - የዋጋ ንረት ይቁም

በኢኮኖሚ በኩልም እንዲሁ፤ የብዙዎችን ኑሮ ያናጋው የዋጋ ንረት ሙሉ ለሙሉ መረጋጋት አለበት። ከመስከረም 2003 ዓ.ም አንስቶ እንደገና ያገረሸው የዋጋ ንረት፤ በ2004 ጨርሶ ባይቃለልም ቀስ በቀስ የመረጋጋት አዝማሚያ ሲታይበት ቆይቷል። ከአርባ በመቶ በላይ ደርሶ የነበረው የዋጋ ንረት ባለፈው ሰኔ ወር ወደ 20 በመቶ ረገብ ብሏል። ከዚያ ወዲህ ግን፤ የመረጋጋት አዝማሚያው ተስተጓጉሏል። በሃምሌ እና በነሐሴ፣ የአገሪቱ የዋጋ ንረት እዚያው ባለበት 20 በመቶ ላይ እየረገጠ ነው። ቀላል ሸክም አይደለም። አምና በአንድ ሺ ብር የወር ገቢ ሲተዳደር የነበረ ቤተሰብ፤ ዘንድሮ 1200 ብር ገቢ ካላገኘ ኑሮው ወደ ታች ይወርዳል። ወይም ደግሞ፤ አምና 12 ሺ ብር ባንክ ውስጥ ያስቀመጠ ሰው፤ በአመት ውስጥ የተቀማጭ ገንዘቡ ዋጋ በሁለት ሺ ብር ይቀንስበታል - የዋጋ ንረት ማለት የብር መርከስ ማለት ስለሆነ።

በዋጋ ንረት ሳቢያ የሚመጣው ችግር እጥፍ ድርብ ነው። የዛሬውን ኑሮ ያናጋል። በዚያ ላይ ደግሞ፤ የወደፊት ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ያዳክማል። ለምን? በየጊዜው ብር እየረከሰ መሆኑን እያወቁ፣ ብር ቆጥቦ ማስቀመጥ ሞኝነት ይሆናላ። በሌላ አነጋገር፤ ለአምስት አመታት እየጦዘና እየረገበ፤ እያገረሸና እየተከመረ የመጣውን የዋጋ ንረት፤ የዛሬንና የወደፊትን ህይወት የሚያበላሽ ነው። በተለይ አሁን አሁን፤ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ይዋል ይደር የሚባል ስራ አይደለም። ለምን ቢባል፤ ባለፉት አመታት የዋጋ ንረት በላይ በላዩ እየተደራረበ ጫናው ከብዙ ዜጎች አቅም በላይ ሆኗል። አሁን ሌላ ተጨማሪ የኑሮ ውድነትን መሸከም ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።

እናም ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊወስዳቸው ከሚገቡ የመጀመሪያ እርምጃዎች መካከል አንዱ፤ የዋጋ ንረቱን በፍጥነት ማረጋጋት ሊሆን ይገባል። ደግሞም ቀላል ነው። እንደቀድሞው ሳይሆን፤ የዋጋ ንረቱ መንስኤ ዛሬ አወዛጋቢ አይደለም። የኑሮ ውድነትን በነጋዴዎች ላይ የማሳበብ ፈሊጥ፣ ጊዜው አልፎበታል። ጊዜው ባያልፍበት እንኳ፤ የትም እንደማያደርስ በተደጋጋሚ አይተነዋል። ደግነቱ ዛሬ፤ የብር ህትመት ዋነኛው የዋጋ ንረት መንስኤ መሆኑን መንግስት በግልፅ አምኗል። ያው፤ ብር በገፍ ሲታተም ብር ይረክሳል። ብር እንዳይረክስና የዋጋ ንረት እንዳይቀጥል፣ የብር ህትመትን ገታ ማድረግ ነው መፍትሄው። ይህም ብቻ አይደለም።

የብር የመግዛት አቅም ባለፉት አመታት እየረከሰ ቢመጣም፤ ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሬ ግን ለሁለት አመታት ብዙም ለውጥ አልተደረገበትም። ግን አያዛልቅም። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የብር-የዶላር ምንዛሬ መስተካከሉ የማይቀር ነው። በእርግጥ፤ የስልጣን ሽግግሩ መሬት እስኪይዝ ድረስ የዶላር ምንዛሬው ለሚቀጥሉት ጥቂት ወራት፤ እዚያ ባለበት ደረጃ ላይ ማቆየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሳይስተካከል እንዲቆይ ሲደረግ ግን፤ በዚያው መጠን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይበልጥ ፈታኝ እየሆነ እንደሚመጣ መዘንጋት የለበትም። የግድ ሆኖ፣ የምንዛሬ ማስተካከያ ሲደረግ ደግሞ፤ የዋጋ ንረት እንደሚባባስ ሳይታለም የተፈታ ነው። እና ምን ተሻለ? እንግዲህ፤ በዚህም ተባለ በዚያ፤ ምንዛሬውን የማስተካከል ጥያቄ፤ ፈጠነም ዘገየ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ አይካድም። ከምንዛሬ ማስተካከያ ጋር አብሮ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም የሚቻለው፤ ከወዲሁ የዋጋ ንረትን በደንብ አረጋግቶ በመዘጋጀት ብቻ ነው።

በአጠቃላይ፤ በተደራራቢ የዋጋ ንረት የተናጋውና ጫና የበዛበት የዜጎች ኑሮ ወደ ባሰ ደረጃ እንዳያመራ ለመጠበቅ፤ የወደፊቱ ቁጠባና ኢንቨስትመንት ይበልጥ እንዳይዳከም ለመከላከል፤ እንዲሁም የማይቀረውን የምንዛሬ ማስተካከያ ተግባራዊ ለማድረግ፤ በቅድሚያ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ያስፈልጋል - የብር ህትመትንና ስርጭትን ገታ በማድረግ።

ቅድሚያ ለመደበኛ ስራ - በሙስና እንዳይዝረከረክ

ሶስተኛው የማረጋጊያ እርምጃ፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን የሚመለከት ነው - መደበኛ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ። ያዘኑ ዜጎችምኮ፤ በህይወት መኖርና ኑሯቸውን ማሻሻል ይፈልጋሉ። የመንግስት መስሪያ ቤቶች በዜጎች ላይ ተጨማሪ እንግልትና እንቅፋት መፍጠር የለባቸውም። ለነገሩ ድሮም በእንግልትና በእንቅፋት የተሞሉ ናቸው፤ ነገር ግን ሌላ ተጨማሪ ጣጣ ማምጣት አይኖርባቸውም።

ቢሮክራሲው አለወትሮው ታታሪ ይሁን እያልኩ አይደለም። እንዲያውም፤ “ከመደበኛ የስራ ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜ ቅዳሜ እንሰራለን” የሚለው ቅስቀሳ ብዙም አያስኬድም። ከሰኞ እስከ አርብስ መች ተሰራና ነው! አሁን ለጊዜው፣ ዋናው ነገር፤ የተለመደው መደበኛ ስራ እንደቀድሞው እንዲከናወን ማድረግ ነው (ኖርማላይዜሽን)። ቢሮክራሲው ከቀድሞው ብሶበት እንዳይንዛዛና እንግልት እንዳያበዛ፤ ከዚሁም ጋር ከቀድሞው በባሰ ሙስና እንዳይዝረከረክ መከላከል... ከመጀመሪያዎቹ የማረጋጊያ እርምጃዎች ተርታ መካተት አለበት።

ዋናዎቹ ፈተናዎች

የማረጋጊያ (የኖርማላይዜሽን) እርምጃዎቹ ራሳቸውን የቻሉ ስራዎች ቢሆኑም በቂ አይደሉም። ድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ ተረጋግቶ መቀመጥ አይቻልማ። ለጊዜው እርጋታ የሚያስፈልገው፤ በሰከነ አእምሮ ወደ ፊት ወደ ስልጣኔና ወደ ብልፅግና ለመራመድ ስለሚጠቅም ነው። በፅሁፌ መግቢያ ላይ ከጠቀስኳቸው አምስቱ ፈተናዎች መካከል ሁለቱን በማንሳት የውይይት አስተያየት ላቅርብ።

ከስራ አጥነትና ከሙስና ተገላግሎ ወደ ብልፅግና

ከእኛው ጋር የነበሩና ወደፊትም በቀላሉ የማይለቁን በርካታ ፈተናዎች አሉብን። ኢትዮጵያ እንደ ወትሮው ዛሬም እጅግ ድሃ አገር ነች። በእርግጥ፤ በጠ/ሚ መለስ ዘመን የግል ኢንቨስትመንት በተወሰነ ደረጃ ተፈቅዶ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ተፈጥረዋል፤ ንብረት የማፍራት እድሎች ታይተዋል። በዜጎች ኑሮ ላይ የመጣው ለውጥ አነስተኛ ቢሆንም፤ ለበርካታ አመታት ከ7 በመቶ የሚበልጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ፤ ዛሬም ጭምር፣ ኢትዮጵያ በአለማችን ከአስሩ የመጨረሻ ድሃ አገራት መካከል አንዷ ነች።

በገጠር፤ አመቱን መዝለቅ የማይችሉ የሴፍቲኔት ተረጂ ችግረኞች እንዲሁም ደራሽ እርዳታ የሚጠብቁ የረሃብ ተጠቂ ዜጎች ቁጥራቸው፤ ከ11 ሚ. በላይ ነው። በከተማም፤ የብዙ ዜጎች ኑሮ ከድህነት ወለል በታች እንደተቀበረ ነው። በተለይ ባለፉት አምስት አመታት የተከሰቱት ከፍተኛ የዋጋ ንረት ቀውሶች የከተሜዎችን ኑሮ አናግተዋል። ከድህነቱ ጋር፤ የወጣቶችና የተመራቂዎች ስራ አጥነትም ከባድ ፈተና ነው። የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ መዳከምም፤ እጅግ ያሳስባል። መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል።

እንደሚመስለኝ፤ እዚህ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የምንማረው ነገር ይኖራል። በእርግጥ፤ ጠ/ሚ መለስ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የኢኮኖሚ ሃሳቦችንና ፖሊሲዎችን አራምደዋል። በበረሃ የትጥቅ ዘመን፤ ለሶሻሊስታዊ ኢኮኖሚ ተከራክረዋል። ኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ በተቃረበበትና የአለም ሶሻሊስት አገሮች በቀውስ በፈራረሱበት ወቅት ደግሞ፤ ጠ/ሚ መለስ የቅይጥ ኢኮኖሚ ሃሳቦችን አስተጋብተዋል። በመጀመሪያዎቹ የኢህአዴግ የስልጣን አመታት፣ አገሪቱ በቅይጥ ኢኮኖሚ ብዙም ፈቅ ማለት ሲያቅታት፤ ጠ/ሚ መለስ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት አለበት ብለዋል። ባለፉት ሰባት አመታት ደግሞ፤ መንግስት ለተወሰነ ጊዜ ኢኮኖሚው ውስጥ ገናና መሆን እንዳለበት ሲያመለክቱ ነበር። ከእነዚህ የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ሃሳቦች መካከል የትኛው እንምረጥ የሚል አይደለም ጥያቄው።

ከጠ/ሚ መለስ የምናገኘው ትምህርት፤ ይሄኛውን ሃሳብ ወይም ያኛውን ፖሊሲ እንድንከተል የሚያደርግ አይደለም። የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመንጨት የመትጋት ትምህርት ነው ከአቶ መለስ የምናገኘው ትምህርት። ዋነኛው አላማ ድህነትን በማሸነፍ ወደ ብልፅግና መራመድ እንዲሁም አስተማማኝ መሰረት መገንባት መሆኑን ለአፍታ ባለመዘንጋት፣ መረጃዎችን በመመርመርና ችግሮችን በመፈተሽ አዳዲስ መፍትሄዎችን እያፈለቁ መተግበር ያስፈልጋል። ጠ/ሚ መለስ ይህንን ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክረዋል፤ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርም እንዲሁ መረጃዎችን በመመርመርና ችግሮችን በመፈተሽ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማበጀት መትጋት ይኖርበታል። ችግሮቹና መረጃዎቹ ምንን ይጠቁማሉ?

ረሃቡ፣ ድህነቱና ስራ አጥነቱ፤ በ”መንግስት ኢንቨስትመንት” እንደማይፈታ የአገራችንና የሌሎች በርካታ አገራት የቅርብና የሩቅ ታሪኮች በግልፅ ይመሰክራሉ። እንዲያውም ኢኮኖሚው ውስጥ መንግስት ገናና እየሆነ በመጣ ቁጥር፤ በዚያው መጠን የሃብት ብክነትና ሙስና ነው የሚስፋፋው።

እስካሁን፤ መንግስት ገናና ከመሆን አልፎ ኢኮኖሚውን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ስራ አለማዋሉና መጠነኛ የነፃ ገበያ እድል መፍጠሩ፤ ለተወሰነ ጊዜ ኢህአዴግን ጠቅሞታል። አንደኛ፤ ኢኮኖሚውን በተወሰነ ደረጃ ለማነቃቃት ችሏል። ሁለተኛ፤ በአለማቀፍ ደረጃ፤ ከውግዘትና ከመገለል እንዲተርፍ አግዞታል።። በአገር ውስጥም ከብርቱ ተቃውሞ ለመዳን ረድቶታል። ነገር ግን፤ በዚሁ የመንግስት ገናናነት ብዙ መንገድ መጓዝ አይቻልም። ከመንግስት ገናናነት ጋር፣ የግል ኢንቨስትመንት እየተዳከመ ስራ አጥነት ይስፋፋል። በተለይ በተማሩ ወጣቶች ዘንድ የሚስፋፋ የስራ አጥነት ችግር እጅግ አደገኛ ነው። ከመንግስት ገናናነት ጋር የሃብት ብክነትና ሙስና ይበራከታል። በተለይ በኢትዮጵያ መዘዙ የከፋ ነው። ኢትዮጵያ ከቻይናና ከደቡብ ኮሪያ በእጅጉ ትለያለች። እነሱ እንደኛ ብዙም ከብሄረሰብና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጣጣዎች የሉባቸውም። እንደ ኢትዮጵያ፣ በብሄር ብሄረሰብና በሃይማኖት የመቧደን ስር የሰደደ ኋላቀር ባህል ባለበት አገር ግን፤ ስራ አጥነትና ሙስና የመሳሰሉ የኑሮና የኢኮኖሚ ችግሮች በሙሉ በሰበብ አስባቡ ከብሄር ተወላጅነትና ከሃይማኖት ተከታይነት ጋር እየተያያዙ መዘዝ ያመጣሉ፤ ለዘረኝነትና ለቡድንተኝነት ቀውስ የሚያጋልጡ አደጋዎች ይሆናሉ። ስለዚህ፤ የወደ ፊት የመንግስት ስራ፣ የነፃ ገበያ ስርዓትን ማስፋፋትና አስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባት ሊሆን ይገባል።

ከኋላቀር ፖለቲካ ወደ ስልጡን የነፃነት ፖለቲካ

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መስክ ብቻ ሳይሆን፤ በፖለቲካውም በኩል በጣም ድሃ አገር ነች። በእርግጥ፤ በጠ/ሚ መለስ ዘመን፤ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ፈርሶ ብዙ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ስርዓት በህገመንግስት ተደንግጓል። አገሪቱ ውስጥ፣ በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሰረቱና ሲንቀሳቀሱ ለማየት ችለናል። ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የፖለቲካ ምርጫም በተደጋጋሚ ተካሂዷል።

ነገር ግን፤ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ብቻ ሳይሆን የሚፎካከሩበት ምርጫ፣ እንዲሁም ፓርቲዎች ስልጣን ላይ የሚፈራረቁበት ሰላማዊ ስርዓት ላይ አልተደረሰም። በሌላ አነጋገር፤ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግርና ፍርርቆሽ አስተማማኝ ስርዓት ገና አልተገነባም። ገና ከፖለቲካ ድህነት አልወጣንም። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ ዲሞክራሲ ሰፍኗል የሚባለው፤ ፓርቲዎች ስልጣን ላይ በሰላም የሚፈራረቁበትን ስርዓት ስንገነባ ነው በማለት የተናገሩትም በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል።

በእርግጥ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውና በየወቅቱ የፖለቲካ ምርጫ የሚካሄድ መሆኑ፤ ለመነሻ ያህል ጥሩ ነው። በዚያ ላይ፤ በተወሰነ ደረጃ አለማቀፍ ውግዘትንና መገለልን ለመከላከል ይረዳል። በአገር ውስጥም፤ ተቃውሞዎችን ለማለዘብ ያግዛል። ነገር ግን፤ አንድ ፓርቲ ሁሌም ከ99 በመቶ በላይ በሆነ ድምፅ ምርጫዎችን የሚያሸንፍ ከሆነ፤ ምርጫዎች መካሄዳቸውና ፖርቲዎች መሳተፋቸው ትርጉም የለሽ እየሆነ ይሄዳል። ከመነሻ ቦታ ሳይንቀሳቀስ፤ ከግቡ ሳይደርስ የመቅረት ያህል ነው።

ኢህአዴግ፤ “መነሻ ነገር ፈጥሬያለሁ” በሚል መከራከሪያ ብቻ የሞራል ተቀባይነቱን (legitimacy) ይዞ መቀጠል አይችልም። ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ቀድሞ የተፈጠረውን መነሻ በመያዝ፤ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ብቻ ሳይሆን ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ምርጫ በሰላም ለማካሄድ የሚያስችል ስርዓት ለመገንባት መጣር ይኖርበታል።

 

 

Read 3521 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 11:48

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.