Saturday, 23 October 2021 14:04

አስተናጋጇ

Written by  ደራሲዋ.. ‘ምርት’
Rate this item
(10 votes)

  ቀጭን! ጠይም! መካከለኛ ቁመና እና አሳዛኝ የፊት ገፅታ ያላት አስተናጋጅ ገና ከመቀመጣችን መጥታ በትህትና “ምን ልታዘዝ” አለችን፤ ገና ፊቷን ሳየው የሆነ የሐዘን በትር በላዬ ላይ ያረፈብኝ ይመስል አመመኝ፤ ሴት አስተናጋጆች ለሴት መታዘዝ የማይመቻቸው እስኪመስለኝ ድረስ ጥሩ ፊት አሳይተውኝ አያውቁም፤ ካየሁት አሳዛኝ ገፆታዋ ላይ ለአፍታ ዓይኔን መንቀል አቃተኝ፤ እንዴት ሰው ፊቱ በዚህ ልክ ተነባቢ ምስል ሊሆን ይችላል?
እንዴትስ ሰው ብዙ አሳዛኝ ታሪኮችን ገፁ ላይ አትሞ ሊንቀሳቀስ ይችላል? ብዙ የልብ ስብራቶችን የሚያሳብቅ ፊት፣ “ምን ልታዘዝ?” ከሚለው ጥያቄዋ ቀጥላ በደስታ ያልተዋዛ አመዳም ፈገግታ አሳየችን፤ የተቀባችው ሜካፕ ገጿ ላይ የተጣበቀውን የሐዘን ጭጋግ ሊደብቀው አልቻለም፤ ያን ለገቢያቸው ሲሉ የግድ ያስታጠቋትን፣ ጭንና ባቷን የሚያጋልጠውን፣ ከእራፊ ጨርቅ የተሰራ ጉርድ አስሬ ወደ ታች ትስበዋለች።
“ምን ልታዘዝ?” አለች በድጋሚ፤ ተሰብስቦ እላይዋ ላይ ያረፈው ትኩረቴ ሳያስገርማት አልቀረም፤ ምን ታዘዢን ልበላት?! ለምን ነበር የመጣነው? ሐሳቤ አዕምሮዬ ውስጥ ሲተረማመስ ታወቀኝ፤ ቃል ከአንደበቴ ራቀ፤ ለአፍታ አፅናኝ ነብይ መሆን አማረኝ፤ “እህቴ ሆይ ብዙ የሚያስጨንቀሽ ነገር እንዳለ ከፊትሽ ላይ ማንበብ ችያለሁ እባክሽ አትጨነቂ ልላት ሁሉ ፈለኩ፤ ወይ ደግሞ “አዪ ሌላ ሰው ያስተናግደን አንቺ እዚህ ከኛ ጋር ተቀምጠሽ እየበላሽ የውስጥሽን ሁሉ ንገሪኝ እስኪ” ልላትም ፈለኩ፤ ግን እንዴት ብዬ። ከረዥም አመታት በፊት ገና በልጅነቴ ልቦለድ ሳነብ አሳዛኝ ፊቷ ውስጤ ተስሎ የቀረ የሆነች ገፀ ባህሪይ፣ አሁን ስጋ ለብሳ አጠገባችን የቆመች መሰለኝ፤ የኔ ያልሆነ አብዝቶ መርበትበትና ማዘን ውስጤን ተቆጣጠረው።
“ግማሽ ሸክላ” አልኳት፤ በልምምጥ መልሳችንን እየጠበቁ ያሉት አሳዛኝ አይኖቿ፣ የግድ አንደበቴን ፈልቅቀውት፤ ከሰው ጋር መቀመጤን ሁሉ ዘንግቻለሁ፤ ስትሄድ በአይኖቼ ተከተልኳት፤ ውስጤን አንዳች የጠለቀ ሐዘን አገለባበጠው፤ ለሰዎች ግድ ይሰጠኛል፤ ነገሮችን ሳልፈልግ በጥልቀት የማየው ነገር አለኝ፤ ይህኛው ግን ከፍ አለብኝ፤ ሰው እርምጃው ሳይቀር እንዴት አሳዛኝ ሊሆን ይችላል?! መሬቱን ስትረግጠው እራሱ እንደ ገል እንዳይሸረፍባት የምትጠነቀቅ ነው የሚመስለው፤ ህይወት አስገድዳ ከህልሟ ያፋታቻት አይነት፤ ወይ ደግሞ የሆነች ሚጢጢዬ፣ የምታሳዝን፣ እየታመመች ለህክምናዋ ብር እንዲሞላላት ብላ ጎረቤት ጋ ጥላት የመጣችው ህፃን ልጅ ያላት አይነት፤ ወይ ደግሞ እሷንና እህቶቿን ለማሳደግ በቀን ስራ ስትደክም ኖራ በሽታ አሸንፏት፣ መታከሚያ አጥታ፣ አልጋ ላይ የቀረች እናት ያለቻት አይነት፤ ወይ ደግሞ በዚህ የኑሮ ውድነት እናትና አባት የሌላቸው፣ የምታሳድጋቸው፣ የምታስተምራቸው ትንንሽ እህቶችና ወንድሞች ያላት አይነት ነገር መሰለችኝ።
አዕምሮዬ አሳዛኝ ታሪኮችን በፍጥነት ያዥጎደጉድልኝ ጀመር፤ እራሴ በፈጠርኳቸው ታሪኮች ሳላስበው አይኖቼ በእንባ ተሞሉ፤ አብረውኝ ያሉት ጓደኞቼ አላስተዋሉኝም፤ ሞቅ ያለ ጨዋታ ይዘው ይሳሳቃሉ፤ የሚያወሩትን አንዱንም አልሰማኋቸውም፤ እንባዬ ከአይኖቼ ቋት እንዳይዘረገፍ ትግል ጀመርኩ፤ በዚህ ሁሉ በሳቅ! ፈንጠዚያ ተሞልቶ እየተመገበ ባለ ህዝብ መሐል እንባዬ ቢዘረገፍ ምን ሆንኩኝ ብዬ እላለሁ? አሳዝናኝ ነው ያቺ ልጅ፣ እንዴት ልል እችላለሁ? አንቺ የአባባ ታምራት እህት ነሽ ወይንስ አጥንትንና ጅማትን የሚመረምር የአምላክ አይን የተቸረሽ ነሽ ሲሉኝ ታየኝ፤ እብደት! ተመጋቢዎቹ ጨዋታቸውና ሳቃቸው ሲታይ አንድ ኪሎ ቁርጥ ስጋ 800 ብር ገዝተው እየበሉ ያሉ አይመስሉም፤ እራሴን መምከር ጀመርኩ፤ “ተሳስተሽ እኮ ይሆናል፤ እውነታው ከዛ ተቃራኒ ሊሆን ይችላል” ብልም እራሴን ማድመጥ አልቻልኩም፤ በአይኖቼ በር ላይ የተኮለኮሉትን የእንባ ኳሶች ጎንበስ ብዬ በሶፍት አነሳኋቸው፤ ማንም ሰው ምን ሆንሽ እንዲለኝ አልፈለኩም።
“የሚጠጣስ ምን ላምጣ?” አለች ወዲያው ተመልሳ፤ ከመሄዷ መመለሷ የቀደመ መሰለኝ፡፡ “ለሁላችንም አንዳንድ ሊትር #ሰላም ውሃ” አልኳት፤ ስብር ብለው ውስጠቷ ላይ፣ ቁስለቷ ላይ ያተኮሩ የሚመስሉትን አይኖቿን እያየሁ፤ ሄደች፤ አጫጭርና የተጣበቀ ጉርድ ለብሰው ውር ውር ከሚሉ አስተናጋጆች መካከል እሷ ብቻዋን የሆነ ከፍ ያለ የሐዘን ኮረብታ ላይ ተቀምጣ የምትታይ መሰለኝ።
እንደተለጎምኩ ምግቡን በልተን ጨረስን፤ ጓደኞቼ እየሆንኩ ያለሁትን ነገር ባለማየታቸው ደስ አለኝ፤ ሁሌም ሰው ልብ የማይላቸውን ነገሮች ትኩር ብዬ በማየት አሰልችቻቸዋለሁ፤ መንገድ ላይ እየሄድን “እስኪ እዩአቸው እነዚህን ጉንዳኖች፣ ለአንድ አላማ እንዴት በህብረትና_በሰልፍ እንደሚጓዙ” ብያቸው አላግጠውብኝ ያውቃሉ፤ የተሰማኝን ነገር ልነግራቸው አልፈለኩም፤ ሂሳብ ስንከፍል ቲፕ ብዙ ብር ላስቀምጥላት ፈለኩ፤ ግን ጓደኞቼ እያዩኝ ስለነበር “ደግሞ ምን ይሁን ብለሽ ነው ይሄ ሁሉ ብር? ጉረኛ ነገር እኮ ነሽ” ቢሉኝ የተሰማኝን ነገር ለነሱ በማስረዳት መድከም አልፈለኩም፡፡ እራሷኑ ስልክ ስጪኝ ልላትም ፈለግኩ፤ ግን ምን ልታስብ ትችላለች?! ሁሉንም ተውኳቸውና የተለመደውን ያህል ቲፕ አስቀምጬ፣ ሌላ ጊዜ ብቻዬን መጥቼ ላገኛት ወስኜ ተከትያቸው ወጣሁ።
ሳምንቱን ሙሉ ውስጤ ሳመላልሳት ከረምኩ፤ የፈጠርኳቸውን ታሪኮች ተራ በተራ እያገላበጥኩ፦ #እናቷ እንዴት ሆነው ይሆን? ልጇስ ድናላት ይሆን? ለእህት ወንድሞቿ የትምህርት ቤት ክፍያ አግኝታ ከፈለች ይሆን?” እያልኩ መጨነቁ ሲደክመኝ፣ በሳምንቴ ብቻዬን ተመልሼ ሄድኩ፤ ግን ያቺን አሳዛኝ ልጅ ላገኛት አልቻልኩም፤ ስሟን አላውቅም፤ ማን ብዬስ ልጠይቅ? አሳዛኟ ልጅ የት ሄደች ልበላቸው? ለኔ እንጂ ያሳዘነችኝ ማንም እኮ ልብ ብሎ አይቷት ላያውቅ ይችላል፤ ወይስ ብዙ ቀጫጭን ጠያይም አስተናጋጆች በሞሉበት ግዙፍ ሆቴል ውስጥ “ያቺ ባለፈው ሳምንት እኛን ያስተናገደችን ቀጭኗ ጠይሟ ልጅ የት ሄደች” ብዬ ልጠይቃቸው?
ለሰአታት ከተቀመጥኩበት ሳልንቀሳቀስ ስጠብቃት ብቆይም ብቅ ልትል አልቻለችም፤ ተስፋ ቆርጬ ሊመሻሽ ሲል የተጠቀምኩበትን ሂሳብ ከፍዬ ወጣሁ፡፡ #ምን_ይሉኛል;ን ይሉኝታ አብዝቼ ጠላሁ፤ የዛን ቀን ሁሉንም ነገር ማድረግ ስችል፣ ስልኳን መቀበል ስችል፣ ላወራት ስችል “ጓደኞቼ፣ ሌላውም ሰው፣ እሷም ጭምር ምን ሊሉኝ ይችላሉ?” ብዬ ትቼ ሄጄ፣ እድሜ ልኬን የምጨነቅበትን ነገር ታቅፌ ቤቴ ገባሁ፤ ሰው እራሱን ሆኖ፤ ስሜቱንና ፍላጎቱን እንዲኖር የማይፈቅድ ብሽቅ ማህበረሰብ ስልም አጉረመረምኩ።.........

Read 1917 times