Monday, 25 October 2021 00:00

የትሕነግ ክፍል ሁለት ሴራ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 በጠቅላይ ግዛቱ የሚገኙ ታሪክ አዋቂዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን፣  ፊውዳልና የደርግ አገልጋይ የሚል ስም በመስጠት ተራ በተራ እየነጠለ ቢገድልም፤ #ነፃ ላወጣህ ተነስቻለሁ; ከሚለው የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን ድጋፍ  ትሕነግ ማግኘት ሳይችል ቀረ፡፡ እንዲያውም ሕዝብ እንደ  ዘንዶ ያሉ የራሱን ታጣቂ ኃይሎች ከገባበት ጉድጓድ እየገባ፣ ቁም ስቅሉን ያሳየው ጀመር። ማጣፊያው ያጣረው  የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት (ትህነግ)፤ የትግራይን ሕዝብ ከመንግስት ለመነጠል የሚያስችለውን ሴራ አውጠነጠነ፡፡ !በተቀነባበረና ይሁነኝ ተብሎ ለደርግ በተሰጠ መረጃ፣ ሐውዜን በአይሮፕላን እንድትደበደብ ተደረገ። ድብደባውን ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ የተደረጉት የትሕነግ ሰዎች፣ ፎቶግራፍና ቪዲዮ እንዲያነሱት ተደረገ፡፡ ይህን መረጃ ይዞ ትህነግ፣ የትግራይን  ሕዝብና ወጣት “ምን እስክትሆን ነው የምትጠብቀው?!” በማለት ቀሰቀሰው፤በሰበካው እየተገፋፋና ወደ በርሃ እየወረደ፣ ከቡድኑ ጋር የሚቀላቀለው  እየበዛ ሄደ፡፡ ደርግ መቀሌን በለቀቀ ጊዜ ደግሞ ሁኔታው የበለጠ ለትሕነግ የተመቸ ሆነ፡፡
እንደ ህፃን የሚቆነጥጣቸው እንደ ፈረስ የሚጋልባቸው እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ  ንቅናቄ እና ኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ያሉ ድርጅቶችን  ፈጥሮ ፊት መሪ በማድረግ፣ እስከ አዲስ አበባ መጣ፡፡ የመንግስት ሥልጣን ለመጨበጥና አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን በቃ፡፡
  ጣሊያናዊ ጆሴስ ሰፓቶ ወደ ኢትዮጵያ  የመጣው እ.ኤ.አ በ1840 አካባቢ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከእነ ሱልጣን ኢብራሂም አሰብ ላይ ሰባት ኪሎ ሜትር ከገዛ በኋላ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ መሬት ላይ መቆናጠጫ አገኘች። ከዚያ ቀስ በቀስ ወደ አስመራ አቀናች፡፡ አስመራ ላይ ተቀምጣ በልዩ ልዩ የሙያ ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ ባስገባቻቸው ሰላዮች አማካይነት መልክአ ምድራዊ  ብቻ ሳይሆን የሕዝቡንም  ሥነ ልቦና አጠናች። አንደኛውን አገረ ገዢ በሌላው ላይ እያነሳሳችና እያስታጠቀች ስታዋጋም ቆየች፡፡ ተመቸኝ ባለች ጊዜ ጦርነት ገጥማ አድዋ ላይ ተሸነፈች፡፡ አርባ ዓመት ተዘጋጅታ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ ወረራ ከፈተች፡፡ በዚህ ጊዜ ኢጣሊያ ከያዘችው የጦር መሳሪያ በላይ ያዋጣኛል ብላ ያሰበችው አገሪቱን በዘርና በሃይማኖት ከፋፍላ፣ ለቅኝ ተገዢነት ማዘጋጀት ነበር። ይህ መሳሪያ የታሰበውን ያህል ውጤት አላመጣም። በዘር የተከፋፈለው ሕዝብ ወደ አንድነቱ ተመልሶ በኢጣሊያ ላይ ክንዱን አነሳ፡፡ የወረራ ዘመኗም በአምስት ዓመት ተገድቦ ለፍጻሜ በቃ፡፡  ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የሴራ ክንዷን ሰንዝራ እስከ ወደቀችበት ጊዜ ድረስም አንድ መቶ ዓመት ያህል  ጊዜ ማለፉን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ትሕነግ የኢጣሊያ መንገድን ተከትሎ ኢትዮጵያውያንን በብሔረሰብ ከፋፍሎ፣ የብሔረሰብ ክልል በመፍጠር፣ አንደኛው ብሔረሰብ በሌላው ዘንድ መጤ ተብሎ እንዲቆጠር፣ እርስ በእርስ የጎሪጥ እንዲተያይም ከዚያም አልፎ እንዲጋጭ በትጋት ሰርቷል፡፡ በእነሱ እጣ ፈንታ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ ታንኩንም ባንኩንም ይዞ የፈለገውን ሁሉ አድርጓል፡፡
ይህ ግን ፍላጎቴ ተሳካ ብሎ እፎይ እንዲል አላደረገውም፡፡ የመንግስት ሥልጣኑን ተጠቅሞ ለጦርነት ሲሰናዳ ነው የኖረው። አሁን እየተዋጋበት ያለው የጦር መሳሪያ፣ በሥልጣን ዘመኑ ወደ ክልሉ አግዞ ያስገባውና በትግራይ ብቻ ሳይሆንም በሌሎችም አካባቢዎች ቀብሮ ያስቀመጠው መሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡ እያወጡ ያሉ መረጃዎች ደግሞ የሚያመለክቱት፣ የራሱን የጦር መሳሪያ ማምረቻና መጠገኛ ማቋቋሙን ነው፡፡
ደርግ የለቀቀለትን ትግራይ ለማስተዳደር ዝግጁ ያልነበረው ትሕነግ፤ ራሱ ባረቀቀውና ባጸደቀው ሕገ መንግስት መሰረት በሕዝበ ውሳኔ  ትግራይን አገር ማድረግ ሲችል፣ ለምን እንዲህ ያለው ጦርነት ውስጥ  ለመግባት መረጠ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለእኔ መልሱ ቀላል ነው፡፡ አገር የማፍረስ ተልዕኮውንና ህልሙን ሊያሳካ የሚችለው፣ የትግራይን ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲያጋጭ ብቻ እንደሆነ ስለገባው ነው፡፡
የሴራው ሁለተኛ ምዕራፍ፣ የትግራይን ሕዝብ በመራር ጦርነት ውስጥ በመክተት፣ “ኢትዮጵያ ለምኔ” የሚል ጥላቻና ምሬት በትግራይ ምድር ላይ ለመፍጠር ነው፡፡ እንዲህ ማሰብ ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

Read 12345 times