Sunday, 24 October 2021 00:00

የጦርነት ስጋት ያንዣበበበት የደቡብ ወሎ አካባቢ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   -  ያልተደራጀና ወጥነት የሌለው የድጋፍ አሰጣጥ ትርምስ ፈጥሯል
    - ዓለማቀፍ ተቋማት ለተፈናቃዮች ትኩረት እንዲሰጡ ሁሉም ድምጹን ያሰማ

           ከሰሞኑ ባገረሸው ጦርነት ሳቢያ የደቡብ ወሎ አካባቢ በተፈናቃዮች እየተጨናነቀ ነው፡፡ የጠላት ጦር ወደ አካባቢው ሊገባ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ማረበቡን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ምን ይመስላል? ተፈናቃዮች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? የዓለማቀፍ ሰብአዊ ድጋፍ ተቋማትስ? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአካባቢው የሰብአዊ ድጋፎችን በማድረግ ተግባር ላይ የተሰማራው የ”ወሎ ህብረት የልማትና በጎ አድራጎት ማህበር” አመራር አቶ ያሲን መሐመድ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል። እነሆ፡-

               እስካሁን በአካባቢው ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ምን ይመስላል?
የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ደረጃውን የጠበቀ የተደራጀና ወጥነት ያለው አይደለም። በአለማቀፍ ደረጃ በሚታወቁ የድጋፍ ስታንዳርዶች አይደለም የሚሰራው፤ ዝም ብሎ በጨበጣ፣ ግለሰቦች  በሚያመጡት ሃብት ላይ የተንጠለጠለ፣ ማዕከል  የሌለው  አይነት ነው። የተወሰኑ የማዘዣ ማዕከላት አሉ፤ ነገር ግን እርዳታውን እናስተባብራለን የሚሉ አካላት ፖለቲካው ላይ ተሳታፊ ስለሆኑ፣ ጦርነቱንም መምራት ይሻሉ። አጠቃላይ ፖለቲካውን መቆጣጠር ይፈልጋሉ። ከዚያው ጎን ለጎን እርዳታውንም እነሱ ብቻ ማስተባበር ይሻሉ፡፡ ስለዚህ የእርዳታ አሰጣጡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ አንዳንድ ወገኖች በአንድ እግራቸው ፖለቲካው ላይ በሌላ እግራቸው ሰብአዊ ድጋፉ ላይ መቆማቸው፣ በተለይ የሰብአዊ ድጋፍ በሚመለከታቸው የሰብአዊ ድጋፍ ተቋማት ትኩረት እንዳያገኝና ማህበረሰቡ ተገቢውን ድጋፍ እንዳያገኝ እያደረገው ነው። እኔ ለምሳሌ  ወደ 40 የሚጠጉ የቤተሰብ አባሎቼ ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ የኔ ዘመዶች እንኳ ተነስቼ ባስረዳ፣ 75 በመቶ የሚሆኑት እስካሁን አንድም ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም። በአንጻሩ ሌሎች የሚቀርበውን ድጋፍ ከሚገባቸው በላይ ደጋግመው የሚወስዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ ሁሉ የድጋፍ አሰጣጡን በትርምስ የተሞላና ወጥነት የሌለው አድርገውታል። ይሄም የድጋፍ አሰጣጡን ለተበላሸ አሠራር የተጋለጠ ያደርገዋል። አብዛኛዎቹ እርዳታ ወሳጆች ደግሞ ወጣቶች መሆናቸውን ስናይ፣ አቅመ ደካሞች በአግባቡ የማያገኙበት ዕድል እንደሚፈጠር መገመት አያዳግትም። ይሄን ሁሉ የፈጠረው ወጥነት ያለው የድጋፍ አሰጣጥ ስርዓት አለመዘርጋቱ ነው። የእያንዳንዱ ተፈናቃይ ትክክለኛ መረጃ ተመዝግቦ አለመያዙም በዚህ እርዳታ አሰጣጥ ላይ ችግር እንደፈጠረም  መረዳት ተችሏል። በዚያ ላይ የተረጂው ቁጥር በትክክል ሳይመዘገብ፣ ምን ያህል ተጠባባቂ ክምችት እንዳለ ሳይታወቅ፤ እጅግ በጣም በተምታታ ሁኔታ ነው ድጋፍ ሲሰጥ የቆየው- በተለይ ከሁለት ወራት ወዲህ።
ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ነገሩ መልኩን እየለወጠ መጥቶ ጦርነቱ ከወሎ ምድር ይወጣል ሲባል፣ ጭራሽ እየገፋ በመሄዱ ነጻ የነበሩ መሬቶች በጠላት ቁጥጥር ስር እየሆኑ መጡ። ይሄን ተከትሎም ተፈናቅለው በየቦታው የነበሩ ሰዎች ጠላት ሲጠጋ፣ እነሱም ከተፈናቀሉበት ቦታ በድጋሚ ወደ ኮምቦልቻ፣ ሃርቡ የመሳሰሉ ከተሞች  እየተፈናቀሉ ነው ያለው። በየትምህርት ቤቶቹ ያለው የተፈናቃይ ሁኔታ ደግሞ በእውነቱ ልብ የሚሰብርና እጅግ አሳዛኝ ነው። የሚገርመው ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም የመንግስት አካል ብቅ ብሎ አለማየቱና ተፈናቃዮችን ለማጽናናት አለመሞከሩ ነው።
በሌላ በኩል፤ ህዝቡ ተፈናቅሎ ወደ ትላልቅ ከተሞች ሲጎርፍ፣ የጠላት ሰላይ ከህዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ቢመጣ እንኳን የሚጣራበት መንገድ አለመኖሩ ያሳስባል። እኛ እንደውም እነዚህን ተፈናቃዮች ለአንድ ቀን የሚሆን ብስኩት ያቀመስናቸው ከመከላከያ ለምነን ነው። በተረፈ ህብረተሰቡ ነው ባለው አቅም እርስ በርሱ እየተረዳዳ ያለው።
የዓለማቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች በአካባቢው የሉም?
አሉ፤ ነገር ግን የተቀናጀ ስራ እየሰሩ አይደሉም። የመንግስት ድጋፍ አድራጊዎችም አሉ፤ ግን እንዳልኩት ድጋፉ የተቀናጀና መሰረታዊ የእርዳታ አሰጣጥ መስፈርቶችን  ያሟላ አለመሆኑ ነው ችግር የተፈጠረው። በየእርዳታ ማዕከሉ ሰዎች በጠዋት ይሰለፋሉ። ነገር  ግን ማታ ባዶ እጃቸውን ይበተናሉ። ይህ ነው እየሆነ ያለው። በነገራችን ላይ ሰዎች ሊረዱት የሚገባው ጠላት ከወረራቸው አካባቢዎች ወደ ደሴና ሌሎች ከተሞች የገቡ ተፈናቃዮች፣ በየሰው ቤት ተጠልለው ነው ያሉት፤ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አይደለም ያሉት።  በደሴ ከተማ እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ  ቢያንስ እስከ 15 የሚደርሱ ተፈናቃዮችን አስጠልሎ ከቤተሰቡ እየቀነሰ እየመገበ ነው። አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝተኛ የከተማው ህዝብ ምን ያህል የወገኖቹን ስቃይ እንደተሸከመ መረዳት አያዳግትም። ይሄን ማህበረሰቡ ውስጥ የገባውንና በየቤተሰቡ የተጠለለውን ተፈናቃይ፣ መንግስትም ሆነ ረድኤት ድርጅቶች አያስቡትም። ድጋፋቸውም ሪፖርታቸውም እኒህን ተፈናቃዮች ታሳቢ ያደረገ አይደለም። በየቦታው ተከራይተው የሚኖሩም ተፈናቃዮች አሉ። እነዚህ እንግዲህ የራሳቸው ገቢ የሌላቸው፣ በሰው ድጋፍ የሚኖሩ፣ የእርዳታ ማግኛ መንገዱን ያላገኙ ዜጎች ናቸው። መንግስት ይህን ሁኔታ ተረድቶ በጊዜ ማስተካከያ ካላደረገ፣ በቀጣይ ሊከሰት የሚችለው ሰብአዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ነው የሚሆነው፡፡ በአካባቢው ያሉ የመንግስት አካላትም ሆኑ የረድኤት ተቋማት፣ ችግሩን አሳንሰው በመመልከት፣ ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑ የከፋ ችግር እንዳይፈጥር ስጋት አለን።
በጦርነቱ ያጋጠመውን ሰብአዊ ቀውስ በተመለከተ ጥናት ስታካሂዱ ነበር፤  ምን ላይ ደረሰ?
አሁን ያሰባሰብናቸውን መረጃዎች በመተንተን ላይ ነው ያለነው። መረጃዎችን ወደ ሪፖርት ለውጠን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን። ጥናታችን በጣም ሰፊ ነው። በቀጣይ ሪፖርቱ ለሁሉም እንዲደርስ እንጥራለን።
“ወሎ ህብረት” በአሁኑ ወቅት ምን አይነት ድጋፎችን እያደረገ ነው? ተፈናቃዮችስ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
በዚህ ቀውስ የሚያሳዝነው ነገር፣ ሴቶችና እናቶች ሶስትና አራት ህጻናት ይዘው ላለፉት 3 ወራት ጫካ ውስጥ ነው ተሸሽገው  የቆዩት።  በተለይ በሶዶማ፣ በድሬ ሮቃ ጦርነት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጫካ ውስጥ ነው ተደብቀው የኖሩት። በጠቅላላው አካላቸው በእጅጉ የተጎዳ፣ ለመንቀሳቀስ እንኳ አቅም ያነሳቸው ተፈናቃዮች ናቸው። እውነት ለመናገር እነዚህን ወገኖች እየደገፈ ያለው የአካባቢው ማህበረሰብና በግላቸው እርዳታ ያሰባሰቡ ሰዎች ናቸው። አለማቀፍ ተቋማት ለአካባቢው የሰጡት ትኩረት በጣም አናሳ ነው። የእኛ ተቋም “ወሎ ህብረት” ቀደም ሲል ሲሰራ የነበረውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አሁን ሊሰራ አይችልም። ምክንያቱም እኛ  ከበጎ አድራጎት ስራዎች ጎን ለጎን  የወሎ ማህበረሰብን አደጋ ውስጥ የጣለ ሁሉ ወራሪ ነው ብለን ነው የምናምነው። ስለዚህ በዚህ አቋም በአካባቢው በነጻነት እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት መንቀሳቀስ አንችልም።  እኛ ስናደርገው የነበረው የድጋፍ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎብናል ማለት ነው። የኛ ተቋም በነጻ ህክምና መስጠትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ያደርግ ነበር። ይሄን ሁሉ አሁን ላይ ማከናወን አልቻልንም፤  ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ማለት ነው።
በአካባቢው ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? የጦርነቱ ስጋትስ ምን ያህል ነው?
አንደኛ፤ አሁን ጦርነቱ ገፍቶ ደቡብ ወሎ በአመዛኙ ከተያዘ፣ ብዙ ነገር ተበላሸ ፈረሰ ማለት ነው። በነገራችን ላይ  አለማቀፉ ተቋማት ወሎ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በሚገባ ያውቁታል። ግን ለምን ዝምታ  እንደመረጡ አይታወቅም። በነገራችን ላይ የጦርነቱ ስጋት ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ነው። ነገርዬው አፋጣኝ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል፡፡ አለማቀፍ ተቋማትም ነገሩን በቸልታ እንዳይመለከቱ፣ ሁሉም ድምፁን ሊያሰማ ይገባል።
ህወኃት ከሰሞኑ እንደ አዲስ የቀሰቀሰው ጦርነት በነዋሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል ማለት ይቻላል?
እንግዲህ  አሁን በከተሞች አቅራቢያ የከባድ መሳሪያ ድምጾች በየሰአቱ እየተሰማ ነው፡፡ ደሴ አካባቢ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ይሰማል። (ቃለ ምልልሱ የተደረገው ረቡዕ ነው) በዚህ ሁኔታ ውስጥ ህፃናትና ሴቶች ይረበሻሉ። በተለይ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ በደሴ አካባቢ ይሰማ የነበረው የከባድ መሳሪያ ድምጽ በጣም  ነበር የሚረብሸው። የጠላትን ወረራ በተመለከተ ግን ብዙ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። እንዴት ጠላት በዚያ መጠን እስኪጠጋ ድረስ ዝም ተባለ? ሳይጠጋ መከላከል ወይም መመከት የሚቻልበት መንገድም አልነበረም?  አሁን የጠላት ሃይል ወደ ከተሞች የመጠጋት ሁኔታ እያሳየ ነው፡፡ ይሄ ማህበረሰቡ ላይ ስጋት ቢደቅን የሚገርም አይሆንም። ባዶ እጁን ያለ ህዝብ ነው። ህፃነትና ሴቶች ቢሸበሩ የሚደንቅ አይደለም። መንግስት ለዚህ በቂ ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑ ደግሞ በእጅጉ አጠያያቂ ነው።

Read 1293 times