Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 September 2012 11:12

የግል ት/ቤቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከምዝገባ በኋላ በወርሃዊ ክፍያ ላይ ዋጋ መጨመር  ህገወጥ አሠራር ነው - ት/ቢሮ

ት/ቢሮ በመማሪያ መፃህፍት ዋጋ ላይ ጭማሪ  በሚያደርጉ ት/ቤቶች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ

በአዲስ አበባ የሚገኙ አብዛኞቹ የግል ት/ቤቶች በወርሃዊ ክፍያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪው ተከትሎም ወላጆች ቅሬታቸውን እያሰሙ ሲሆን የአዲስ አበባ ት/ቢሮ የትምህርት ቤቶችን የዋጋ ተመን ለመወሰን ስልጣን የለኝም ብሏል፡፡ ት/ቤቶቹ የማስተማሪያ ዋጋውን አሣውቀው ተማሪዎችን ከመዘገቡ በኋላ የሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ ሕገወጥ ነው ሲልም ገልጿል፡፡

በወርሃዊ ክፍያዎች ወይንም በየትምህርት ተርሙ በሚደረጉ ክፍያዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አደረጉ ከተባሉ ት/ቤቶች መካከል አንዳንዶቹ ጭማሪው የተደረገው ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ በመምህራን ደሞዝና በልዩ ልዩ ወጪዎች ላይ የሚደረገው ክፍያ በመጨመሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ቅሬታቸውን ካቀረቡ ወላጆች መካከል አብዛኛዎቹ የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግስት አንዳንድ ት/ቤቶች እያደረጉ ያሉትን አግባብነት የሌለው ጭማሪ ተቆጣጥሮ ት/ቤቶቹ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ማድረግ ያልቻለበት ምክንያት አልገባንም ብለዋል - ወላጆች፡፡ ልጆቻቸውን ባለፈው ሰኔ ወር እንዳስመዘገቡ የነገሩን አንድ ወላጅ፤ አሁን በመስከረም ወር ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት ሲልኩ 50 በመቶ ጭማሪ መደረጉ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃይለ ስላሴ ፍስሃ ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ ት/ቢሮ በግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣት እንደማይችልና በነፃ ገበያ ሥርዓት መሰረት ት/ቤቶች የራሳቸውን የዋጋ ተመን ማውጣት እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የዋጋ ተመናቸውን (ወርሃዊ ክፍያቸውን) አሣውቀው ምዝገባ ካካሄዱ በኋላ ቆይተው ጭማሪ አድርገናል ማለት እንደማይችሉና ይህ አሠራር ህገወጥ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዘንድሮው አመት ት/ቤቶች ለተማሪዎች የሚሸጡትን የመማሪያ መፃህፍት ት/ቢሮ በሚያወጣው የዋጋ ተመን ብቻ እንዲሸጡ መመሪያ ቢወጣም  አንዳንድ ት/ቤቶች መመሪያውን በመጣስ በመፃህፍት ሽያጭ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉባቸው እንደሆነ ወላጆች ገለፁ፡፡ የት/ቢሮው ምክትል ሃላፊ በበኩላቸው ቢሮው  ካወጣው የመማሪያ መፃህፍት መሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ በተገኙ ት/ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ እነዚህን ህገወጦች በመጠቆም ተሳትፎ እንዲያደርግም አቶ ኃይለስላሴ አሳስበዋል፡፡

 

 

 

 

 

Read 2756 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 11:34

Latest from