Saturday, 23 October 2021 13:39

በኢትዮጵያ ላይ የማይሰበሰብ አገር ጠፋ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ሰላም ያገኘ አገር የለም

              የሶሻሊዝም አድናቂ ሆኜ አላውቅም፡፡ በትወራም በትግበራም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሶሻሊዝምን የምናውቀው በመፅሐፍ አንብበን ወይም በፊልም ተመልክተን አይደለም፡፡ በህይወት ኖረን ነው የምናውቀው። በደርግም በኢህአዴግም። በማርክሲዝም ሌኒኒዝም የተጠመቁ ፖለቲከኞች ያመጡብንን መዘዝ አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ የብሔረሰብ ፖለቲካ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስት፣ የፖለቲካ ሴራና መጠላለፍ፣ በመንጋ ማሰብ ወዘተ… የሶሻሊዝም  ውጤቶች ናቸው።
ሶሻሊዝም ኢትዮጵያን ከ40 ዓመት በላይ አድቋታል፡፡ ሁሌም ሶሻሊዝም ሲባል ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ድቅድቅ ጭለማ ነው፤ ጭቆና- ድህነት- አፈና- እስር- ግድያ -ስደት- ምዝበራ…ወዘተ፡፡ (የሶሻሊዝም ብርሃን የለውማ!) በዚህ የተነሳ እነ ራሺያ፣ ቻይና፣ ኩባ፣ ቬትናም፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ቬኔዝዌላ….በአጠቃላይ ሶሻሊስት አገራት ብዙም አይመቹኝም፡፡ (“ነበር” ብል ይሻላል!)  ለኔ ሃገር ማለት አሜሪካ ብቻ ነበረች፡፡ (እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ!) ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ያለ ገደብ የሚከበርባት፣ የሰው ልጅ ከየትም የዓለም ዳርቻ ሄዶ በትጋቱና በጥረቱ ብቻ የሚበለፅግባት፣ ያለመውንና የተመኘውን የሚያሳካበት፣ የሥልጣኔና የብልፅግና ተምሳሌት ናት- አሜሪካ ለእኔ፡፡
የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክራቸውን ሳይቀር በቴሌቪዥን እየኮመኮምኩ የማድርበት ወቅት ነበር፡፡ በፖለቲከኞቹ የንግግር ችሎታና የማሳመን ብቃት ያልተደመምኩበት ጊዜ አልነበረም። ለአገራቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅርና መሰጠት፣ በሥልጡን የፖለቲካ ባህላቸው፣ በዳበረ የዲሞክራሲ ሥርዓታቸው፣ በሰብአዊ መብት አጠባበቃቸው… ስደነቅ ነው የኖርኩት፡፡ መደነቅ ብቻም ሳይሆን አገሬ ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ የምትሆንበትን ጊዜ አበክሬ ናፍቄአለሁ፡፡ በአጭሩ አሜሪካ በብዙ ነገሯ የምመርጣትና የምጠቅሳት አገር ሆና ለዓመታት ዘልቃለች፡፡ (ከአገሬ ቀጥሎ ማለት ነው!)
በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ መጥተዋል፡፡ የድሮዋ አይደለችም- አሜሪካ። ዘረኝነትን ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ተከፋፍላለች። ዲሞክራሲና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት  አደጋ ተጋርጦባቸዋል። አሜሪካን ከእነ ስሟና ታሪኳ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማዋ ጭምር “አትወክለንም” የሚሉ ቡድኖች ተፈጥረዋል። አሜሪካውያን የሚኮሩበትንና የሚያከብሩትን ህገ መንግስት፤  “ዘመኑን የማይዋጅ ነው” እያሉ የሚያጥላሉ የኮሌጅ ወጣቶች እንደ አሸን እየፈሉ ነው፡፡ ነፃ ሃሳብን በነፃነት በማንሸራሸር የሚታወቁት እነ ፌስቡክና ትዊተር፣ ነፃ ሃሳብን በማፈን እየተወነጀሉ ነው። በፓርቲ ወገንተኝነትም እየተከሰሱ ነው። የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዲሞክራቲክ ፓርቲ፤ “ዲፈንድ ዘ ፖሊስ”፣ “ክሪቲካል ሬስ ቲዮሪ”፣ “ካንስል ካልቸር”፣ “ኦፕን ቦርደር”፣ #ክላይሜት ቼንጅ; ወዘተ… በሚሉ አወዛጋቢ አጀንዳዎች ግራ ዘመምነቱን እያጠናከረ መጥቷል፡፡   
በተለይ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ነጩ ቤተ መንግስት መግባታቸውን ተከትሎ፣ አሜሪካ በውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ጉዳዮች  እየተዳከመች መምጣቷን ራሳቸው ሪፐብሊካኖች ቀን ከሌት እየተናገሩ ነው፡፡ እኔ ግን ዛሬ በአሜሪካ ጉዳይ ልጽፍ የተነሳሁት በቀጥታ ከአገሬ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘ ባለፉት ወራት አሜሪካ ስታወጣ የቆየችውን መግለጫና የማዕቀብ ማስፈራሪያ በጥሞና ስከታተል ቆይቻለሁ - በትዕግስት፡፡ (ለመደምደም ሳልጣደፍ!) ነገር ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፍርደ ገምድል መሆኗን ነው የታዘብኩት፡፡ ፍትሃዊ አለመሆኗን ነው የተገነዘብኩት፡፡ በአገሬ ህልውና ላይ አደጋ መጋረጧን ነው የተረዳሁት፡፡ ግን ለምን? እያልኩ ደጋግሜ ራሴን  እጠይቃለሁ።
አዎ ለምንድን ነው አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሚዛናዊ መሆን ያቃታት? ለምንድን ነው ከአማጺው ቡድን ይልቅ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ውንጀላና ጫና ያበዛችው? ለምንድን ነው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ፍርደ ገምድል የሆነችው? ለምንድን ነው የጆ ባይደን አስተዳደር፣ የአማፂውን ቡድን የጅምላ ጭፍጨፋና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ በዝምታ ለማለፍ የመረጠው? አማፂው የህወሃት ቡድን  ከ8 ወር በኋላ ከምሽጉ ወጥቶ መቀሌ በገባ ማግስት፣ በአፋር-በአማራና-በኤርትራ ላይ ጦርነት ሲያውጅ አሜሪካ የት ነበረች? የህወሃት አማጺ ቡድን፣ በአፋር ለፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ላፈናቀለው ሰላማዊ ህዝብ፣ ላወደመው ንብረት አሜሪካ መቼ ትንፍሽ አለች ? (ጁንታው ራሱ ታዝቧታል!!)
የተባበሩት መንግስታት አባላት፣ አማፂው፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ለፈፀመው ጭፍጨፋና ውድመት መቼ ስብሰባ ጠርተው ያውቃሉ? በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማዕቀብ ለመጣል  ግን ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ባለፉት ሁለትና ሶስት ወራት ብቻ ለአስር ጊዜ ያህል ተሰብስቧል? (ባተሌ ሆኖ የከረመው በኢትዮጵያ ጉዳይ ነው!)  
በአሜሪካ መንግስት ላይ ቅሬታና ጥርጣሬ ያድርብኝ የጀመረው በኢ-ሚዛናዊነቱና በተዛባ ፍርዱ ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ ላይ ለመጣል በሚያስፈራራው የማዕቀብ እርምጃ ጭምር እንጂ። እውነቱን ለመናገር የአሜሪካ መንግስት ባለፉት 20 ዓመታት በተለያዩ ሰበቦች ጣልቃ በገባባቸው የዓለም አገራት ሁሉ ውድቀት እንጂ ውጤት አላመጣም፡፡ በኢራቅ-ሊቢያ-ሶሪያ- የመን- አፍጋኒስታን…ግቡን አላሳካም። እስቲ የአሜሪካ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሰላምና ዲሞክራሲ፣ ዕድገትና ብልጽግና ያሰፈነበትን አገር ንገሩኝ፡፡ (አትልፉ፤ አታገኙም!)  እንዳለመታደል ሆኖ፣ አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ማዕቀብም በሉት ሌላ እርምጃ የወሰደችበት አገር ሁሉ መቅኖ አጥቷል። ሊቢያ ከ10 ዓመታት በኋላም ከጦርነት አልወጣችም፤ የሽብርተኞች መፈልፈያ ሆናለች። በአፍጋኒስታን ከ20 ዓመታት በኋላም ሰላምና መረጋጋት አልሰፈነም፤ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ በእጅጉ ተሰግቷል፡፡ አገሪቱ ተመልሳ  በታሊባኖች ቁጥጥር ስር ውላለች፡፡ ሶሪያ ፍርስርሷ ወጥቶ ህዝቦቿ በመላው ዓለም እንደ አሸዋ ተበትነዋል (ዕድሜ ለአሜሪካ!)። እንዲያም ሆኖ አሜሪካ ዛሬም በስህተቷ የተፀፀተች አትመስልም፡፡ በ21ኛው ክ/ዘመን፣ ሌላ አዲስ አገር ለማፍረስ አቆብቁባለች። አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ለመጣል እያስፈራራች ያለችው ማዕቀብ፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስትን በማዳከም፣ የህወኃት አማጺ ቡድንን የመሰሉ ሌሎች በርካታ አሸባሪ ቡድኖችን የሚፈጥርና አገሪቷን ከእነ አካቴው የሚያፈራርስ እንደሚሆን፣ አንድ የአሜሪካ የፖለቲካ ልሂቅ አስጠንቅቀዋል። እነ አሜሪካ ግን ማስጠንቀቂያውን ከቁብ የቆጠሩት አይመስሉም፡፡ ለነገሩ በሌሎች ላይ  የሚጥሉት ማዕቀብ ስለሚያስከትለው ጥፋት፣ ከመቼ ወዲህ ነው እነ አሜሪካንን አስጨንቋቸው የሚያውቀው?  የሰው  አገር ጉዳት ቢያሳስባቸው ኖሮማ፣ የሊቢያውን መሪ ሙአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ከመገርሰሳቸው በፊት ሁለቴ ያስቡ ነበር፡፡  ቀድሞውኑ ያልነበረውን ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ፍለጋም  ኢራቅን ባላፈራረሱ ነበር፡፡ (ኢራቅ ዛሬም ከድቀቷ አላገገመችም!)  ለካስ አሜሪካ በገዛ እጇ ጠላቶቿን ስትፈለፍል ነው የኖረቸው። (አሁን ገና ገባኝ!)
በነገራችን ላይ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያችን ከየአቅጣጫው ተወጥራ ነው የሰነበተችው። (ጦቢያ እንደ ዘንድሮ የዓለምን ትኩረት ስባ አታውቅም!) እናም አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ ላለው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብን ጨምሮ በእጇ ያሉትን አማራጮች በሙሉ በመጠቀም፣ አስገዳጅ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች (ዝታለች ማለት ይቀላል!) በሌላ በኩል፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ህብረት፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመንና የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት በዚያው ሳምንት  በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተወያዩ ሲሆን የግጭቱ ተሳታፊ አካላት በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው፣ ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህ ጥሪ የቀረበው ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር በአማጺው ቡድን ላይ በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ጥቃት መክፈቱን አማጺያኑ መግለፃቸውን ተከትሎ እንደሆነ እነ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግበዋል። ህወኃት በኢትዮጵያ መንግስት ሃይል እየተሰነዘረበት ያለው ጥቃት በ“ከባድ  ጦር መሳሪያ፣ በታንክና በሮኬቶች እንዲሁም በድሮኖችና ተዋጊ ጀቶች የታገዘ መሆኑን” መግለፁንም ዘገባው አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት  ያለ ምንም ማጋነን፣ በኢትዮጵያ ላይ  ያልተሰበሰበ  አገርና መሪ  የለም ማለት ይቻላል። (ከራሷ ከኢትዮጵያ በስተቀር!)። በተቃውሞ የምትናጠው የሱዳን ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም የቡድን ሰባት አባል ሀገራትና ሌሎች  ለጋሽ ሀገራት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውም ታውቋል፡፡  የኬንያው ፕሬዚዳት በዋይት ሃውስ  ለመጀመሪያ ጊዜ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር የተወያዩትም ባለፈው ሳምንት ነበር። የኢትዮጵያ ጉዳይም ዋና አጀንዳ ነበር ተብሏል። (ባይሆን ነበር የሚገርመኝ!)
የህወኃት አማጺ ቡድን  በኢትዮጵያ ሀይል ከየአቅጣጫው  የተቀናጀ ጥቃት እንደተከፈተበት መግለጹን የዘገቡ አንዳንድ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች፣ ጥቃቱ ትግራይን በደቡብ በሚያዋስናት የአማራ ክልል መከፈቱን ምዕራባውያን ባለስልጣናት ጭምር እንዳረጋገጡላቸው ጠቅሰዋል። (ጭራሽ የአማፂው ቃል አቀባይ ሆነው አረፉት!?) በሚገርም ሁኔታ አንዳንድ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች (ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ፌክ ሚዲያ” የሚሏቸው!) ኢትዮጵያና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንደተገለሉ ሲዘግቡ ነው የሰነበቱት፡፡ (ለእነሱ “ዓለማቀፍ ማህበረሰብ” ማለት አሜሪካ ብቻ ናት!) በእርግጥ 7 የተመድ ከፍተኛ ሃላፊዎች ከኢትዮጵያ መባረራቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ ከመንግስታቱ ድርጅት አመራር ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷንም ጠቅሰዋል። እናም ጠ/ሚኒስትሩን በመደገፍ እስካሁን የዘለቁት ጥቂት የአፍሪካ መሪዎች ብቻ ናቸው ሲሉ የተዛባ መረጃ አሰራጭተዋል። (ጦቢያ ከሳር ቅጠሉ ጋር የተጋጨች አስመሰሏት እኮ!) በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ከምዕራባውያን አገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመከባበር ላይ ብቻ የተመሰረተ ይሆናል በሚል አቋሙ መጽናቱ ይታወቃል። (አናጎበድድም ብሏል!)
በነገራችን ላይ “ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ዓለም ላይ ፊታቸውን ማዞራቸውን” እንዲሁም “ኢትዮጵያ ወዳጆቿንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን እያጣች” መሆኑን የሚያትት ዘገባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣው ታዋቂው  “ዘ ኢኮኖሚስት” መፅሔት ነው፡፡
የዛሬ ሁለት ሳምንት፡፡ እውነት ግን  ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ “ወዳጆቿንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን”  እያጣች ነውን? መቀመጫውን በሩሲያ ያደረገው አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ፤ “Analayizing The American Hybrid War on Ethiopian” በሚል ርዕስ በጦማሩ ላይ ባሰፈረው ትንተና፣ ቻይና ሩሲያና ህንድ ከአሜሪካና ከተባበሩት መንግስታት በተቃራኒ በመቆም ለኢትዮጵያ ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኙ በመጥቀስ፣ “ዘ ኢኮኖሚስት” መጽሄት “ኢትዮጵያ ወዳጆቿንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን  እያጣች ነው” በሚል ያቀረበውን ሃሰተኛ ዘገባ አጋልጧል፡፡
በተቃራኒው ኢትዮጵያ አዲስ ወዳጆችንና ተፅዕኖ ፈጣሪነትን እያገኘች መምጣቷን፣ የፖለቲካ ተንታኙ ይጠቁማል፤ በተለይ ከአዳዲስ ሀያላንና ከሶስተኛው ዓለም ሀገራት፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት የተባበሩት መንግስታት አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለ10 ጊዜ ያህል የተሰበሰቡ ሲሆን በአገሪቱ ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ ያገዳቸው የእነ ቻይና፣ ራሽያና ህንድ የተቃውሞ ድምጽ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ (ኢትዮጵያችንን ታድገውልናል!) ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ 7 ከፍተኛ ሀላፊዎች “በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል” በሚል ከሀገር መባረራቸውን ተከትሎ፣ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት  ሁለት ጊዜ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር። አሜሪካ፣ እንግሊዝና አየርላንድ የጠሩትን 9ኛውን ዙር ስብሰባ አስመልክቶ አንድ የፌስቡክ ከታቢ ካሰፈረው ጽሁፍ አንዲቷን አንቀፅ ብቻ እዩልኝ፡፡ እነሆ፡-
“…ጀግናው ልጃችን ታዬ አፀቀስላሴ በለሰለሰ አንደበት፣ በሃቅ ልምጭ፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተላላኪዎችን ስብሰባ በትኖታል፡፡ የራሺያን ውለታ በቃላት መግለፅ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያ አምላክ ደግሞ የኢትዮጵያን መሻገር፣ የኢትዮጵያን ማሸነፍና የኢትዮጵያን ከፍታ ያረጋግጣል! የወጉንም ያስወጉንም በአይናቸው ያዩታል፤ አይቀርም!! አባት ሃገር ራሺያ ምስጋናችን ብዙ ነው! ጀግናው ልጃችን አምባሳደር ታዬ ዘመንህ ይለምልም! ኢትዮጵያ የሃያላኑ መፋረጃ! የክፉዎች መቅጫ!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃት!!

Read 1665 times