Tuesday, 19 October 2021 18:16

ምሽትና የመንፈስ ተጋቦት

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተረፈ ኤርሚያስ ምዕራፍ 9 ላይ አንድ የሚገርም ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ በእስራኤል ህዝቦች ላይ መከራ ከብዶ በመጣ ጊዜ ነብዩ ኤርሚያስ ከሞት ያዳነውን አቤሜሌክን የበለስ ፍሬ ቀጥፎ ያመጣ ዘንድ ወደ ማሳዎች ላከው። አቤሜሌክ እንደታዘዘው የበለሱን ፍሬዎች ቀጥፎ በሙዳዩ አጠራቀመ፡፡ ችፍርግ ያለች አንዲት የበለስ ዛፍ አግኝቶ ጥቂት ያንቀላፋ ዘንድ አሸለበ፡፡ እናም 66 ዘመናት እስቲፈራረቁ፣ ነብዩ ኤርሚያስና ባሮክ እንዲሁም እስራኤላውያን በባርነት ወደ ባቢሎን እስቲጋዙ፣ ኢየሩሳሌም እንዳልነበረች ሆና እስክትወድም ጥልቅ እንቅልፍን ተኛ፡፡
ከእንቅልፉ ሲነቃ የቀጠፋቸው የበለስ ፍሬዎች ትኩስ (fresh) ነበሩ፡፡ ወደ ከተማ ሲገባ ግን ብዙ ነገሮች ተቀያየሩበት። አንዳችም የሚያውቀው ነገር አጣ፡፡ ፍፁም ድንጋጤን ደነገጠ፡፡ በተራራማው መንገድ ሲጓዝ አንድ አዛውንት አግኝቶ፤ ‹‹እባክህ እንቅልፍ ውስጥ ነበርኩና ብዙ ነገሮች ተቀይሮብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ ነብዩ ኤርሚያስና ባሮክ ወዴት ናቸው?››  ጠየቃቸው፡፡
አዛውንቱም፤ ‹‹አንተ የዚህ አገር ሰው አይደለህምን? 66 ዓመታት ቆይተህ እንዴት ይህንን ጥያቄ ትጠይቃለህ? ኤርሚያስና እስራዔላውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ከተጓዙ እነሆ 66 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡›› አሉት፡፡
‹‹ይህ እንዴት ይሆናል? የያዘኳቸው የበለስ ፍሬዎች እንኳን ትኩስ ናቸው፡፡››
‹‹እግዚአብሔር የእስራኤልን ጥፋት እንዳታይ ጥልቅ እንቅልፍ ጣለብህ እንጂ ወደ ማሳዎች ተመልከት፤ ወቅቱ እንኳን የበለስ አይደለም፡፡›› ብለው አስረዱት፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉ ታሪካዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ አቤሜሌክ የተቀየሩ መገበያያ ሳንቲሞችን ሳይቀር ይዞ ተገኝቷል። ምናልባት የአቤሜሌክ ግር የመሰኘት ሂደት አውዱ መንፈሳዊነት ስለሚጫነው ሊለይ ይችላል፡፡ ሆኖም እኔም በእያንዳንዱ ዕለት የሚሰማኝ እንግዳነት ልክ እንደ አቤሜሌክ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ወይም ሌላ የመካከለኛው ዘመን ሰው በጎልማሳነት ዕድሜ እንደገና አሁን ቢጠራ የሚሰማው ዓይነት፡፡ በየዕለቱ ግር የሚሉኝ የማውቃቸው የነበሩና የሚቀየሩብኝ፣ የማይገቡኝ፣ የሚያደነጋግሩኝ ነገሮች እልፍ አዕላፋት ናቸው፡፡ ይሁና!
አልበርት ካሙ the ‹stranger› በሚል ርዕስ ፍልስፍናዊ አመለካከቶቹን በልብወለድ መልክ ባቀረበበት መጽሐፉ ላይ በዋናው ገፀባህሪ አንደበት እንዲህ ይላል፡- ‹‹በአንድ ቦታና ጊዜ ያለው ሕይወት ምርጥ የመሆኑን ያህል በሌላ ቦታ ያለውም ሕይወት እንዲሁ ምርጥ ነው፡፡…እኔ በዘመኔ ይህንን አድርጌያለሁ፡፡ ያንን አላደረግኩም፡፡ ይህን ፈጽሜያለሁ፡፡ ያንን አልፈፀምኩም፡፡ ይህንን አሸንፌያለሁ፡፡ ያንን አላሸነፍኩም፡፡ እዚህ ቦታ ሄጃለሁ፡፡ እዚያ ግን አልሄድኩም፡፡ እና ምን ይጠበስ?››
እውነትስ ምን ይጠበስ? አስቡት እስቲ እኔ ገርጂ ጊዮርጊስ የመቃብር ቦታ ላይ ቆሜ ሞተው እንኳን እረፍት ያጡ ሰብዓዊያንን እያሰብኩ ስብሰለሰል፣ እዚያ አሜሪካ በውሃዋ ማማ ሚያሚ በጀልባ የሚፈነጥዘው የማላውቀው የማያውቀኝ ወዳጄ፣ ከእኔ የተለየ ስሜት እየተሰማው ስላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አልችልም። እንደኔ ሰው በመሆን የተጣለበትን ሃዘን እያባበለ ቢሆንስ? የእርሱ የቅብጠት፣ የመዘባነን፣ የቅንጦት የኑሮ ዘይቤ በሕይወት ለዛው ከእኔ የሽሽት፣ የመፍገምገም፣ የመሳከር ኑረት መብለጡን አላውቅም፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ የገበሬ ልጅ በብዙ ዓይነት እንግልትና ባህላዊ እውቀት ተሞርዶ እንደሚያድግ ሁሉ የህንዱም እንደዚያው ነው፡፡ በዚህ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ምንም… ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ተወለድክ ወይም ጃፓን አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ሕይወትን በንቃት መኖሩ ነው፡፡ ሆኖም ወዳጄ መንቃት እንዲሁ ስለፈለጉ ብቻ የሚገቡት ክፍት በር ከመሰለህ ተሳስተሃል፡፡ መንቃት ሂደት ነው፡፡ ብዙ ዋጋ የሚጠይቅ የፍለጋ ሂደት…አይገርምም አንዲት ዘለላ የሕይወት እውቀት ለመማር የዘመናት ጥበቃና ስቃይ ያስፈልግሃል፡፡ ለዚያውም ከዚያ ወዲያ ይኸው እውቀትህ ምንም ላይጠቅምህ ነገር መሆኑ ያበግናል፡፡ ሆኖም ሕይወትን በንቃት መኖር እንዲሁ ቀላል አይምሰልህ። ከመንፈሳዊነት፣ ከየዋህነት ሕይወትን መመልከቻ ጽንፍ አጥተህ ሕይወትን በሌጣው ስትመለከት ምን እንደሚገጥምህ ኦስካር ዋይልድ ይንገርህ፡፡ እኔን ላታምነኝ ስለምትችል…
‹‹after the first glass you see things as you wish they were. After the second you see them as they are not. finally you see things as they really are and that is the most horrible thing in the world.››
as they really are...እህ እውነት እንጂ ውሸትማ ምኑ ያስፈራል? ውሸት ሽልምልም ነው፡፡ ያጥበረብራል፡፡ ‹በአራጣ የተያዘ ጭን› የሚል መጽሐፍ ላይ ይመስለኛል፣ በደረሰበት የመኪና አደጋ ህሊናው ‹ተዛብቶ› ምንም ነገር መዋሸት የማይችል ገጸባህሪ ከሰዎች ጋር ለመኖር ሲቸገር አንብቤያለሁ፡፡ ውሸት ከእውነት ይልቅ ሰላማዊ ይመስላል። ውሸት እልፍ መንገዶች አሉት፡፡ እውነት ግን አንዲት ብቻ... እንደ ህዝብ አሁን ላለን ስነልቦና እውነት ከውሸት ይልቅ ቁጡ፣ ጨካኝ እና መራር ሆናለች፡፡
‹‹ሞት ገና ስታስበው የሚያብረከርክ ነው፡፡ ሲይዝህ ግን በደስታ የሚያፍነከንክ›› የሚለው የአረቦቹ አባባል፣ ለእውነትም ድብን አድርጎ ይሰራል፡፡ እውነት መራር ቢሆንም ምንጊዜም ነጻ የሚያወጣ ነገር ነው፡፡
ለማንኛውም አሁን እየመሸ ነው። ቢያንስ ይህን መጣጥፍ በምጽፍበት ቅፅበት እየመሸ ነበር... ሲመሽ ነፍስ ስክነትን፣ ጽሞናን ትራባለች፡፡ ሰዓሊ ዳንኤል ታዬ ‹ቅዠት› በተሰኘ መፅሀፉ፤ ‹‹ዝንብ ምግቧን ስትፈጭ በጨጓራዋ ውስጥ የምትፈጥረው ድምፅ ሳይቀር ይረብሸኛል›› ይላል፡፡ ፅሞናን አጥብቆ ለሚመኝ ሰው የትንኝ ድምፅ እንኳን ስሜትን ያናጥባል። እኛ ግን የምንኖረው ለ24 ሰዓታት በሙሉ አቅሟ በምታባርቅ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ይጮሃል። ስልኩ፣ ስፒከሩ፣ ክላክሱ፣ ሰው ራሱ ይጮሃል፡፡ ብዙ አትቸገር ሰው ሳትነካው ገና ይገነፍላል፡፡ ሁሉም ሰው ሴቱ ወንዱ ከቤት ሲወጣ ለጠብ ተዘጋጅቶ ነው፡፡ ወያላው፣ ሾፌሩ፣ ተሳፋሪው፣ ትራፊክ ፖሊሱ፣ እግረኛው፣ ጥግ የተቀመጠው... ሁሉም፡፡ አንተ ደግሞ ሲመሽ ራስህን የምታደምጥበት ጥቂት ፋታ ትፈልጋለህ፡፡ ግን መሸሻ የለህም። አንተ ማለት ከስለት እና ከጩኸት ከበባ መካከል አጣብቂኝ የገባህ ምስኪን ፍጥረት ነህ፡፡ ልውጣ ካልክ ስለት፣ ልግባ ካልክ ጩኸት ይቀበልሃል፡፡ መደማመጥ የሌለው ድብልቅልቁ የወጣ ጨካኝ ስነልቦናችን የተገነባው ከዚህ መተዛዘል ይሆን?
ቢሆንም ሲመሽ ዘወትር ግር ይለኛል። በአዲስ አበባ አንድ የከፍታ ጥግ አድፍጬ ጀንበሯን ለመሰናበት፣ ከሰከረ ድንግዝግዝ ብርሃን ጋር ለመደነስ እቅበጠበጣለሁ። የደስታ የሚመስል ግን ደግሞ የሚያባባ ስሜት አቅሌን እስክስት ይቆጣጠረኛል፡፡ ጸጋዬ በብዕሩ ስሜቴን እንዲህ ተጋርቶታል፡፡ ምሽቱን እስከ ውድቅት ቢለጥጠውም ቅሉ...
‹‹…መሽቶ ረፍዶ ጀምበር ጠልቆ
በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ፣ በዝምታ ሲዋጥ አገር
ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ ብቸኝነት ብቻ ሲቀር…
የኋላ ኋላ ማታ
ምድር አገሩ በእፎይታ
ዓይኑን በእንቅልፍ ሲያስፈታ
ሁሉ በእረፍት ዓለም ርቆ ብቸኝነት ብቻ ሲቀርብ
ያኔ ነው ወንድ ዓይኑ የሚረጥብ
የብቻ እምባ ወዙ እሚነጥብ፡፡…››
በበኩሌ ሕይወት የምልዑነት ከፍታ የምታገኝበት ነጥብ፣ እሱ ምሽትና ምርጥ ሙዚቃ የተገናኙበት ነጥብ ይመስለኛል። ምሽት ልብ ብለው ሲያስተውሉት የሆነ ከጥልቅ ሃዘን ጋር እየታገለ ፈገግ ያለን ሠው ፊት ይመስላል። የሁለትዮሽ መስመር ጠርዝ ስለሆነ ይሆን? የብርሃንና የጨለማ... ምርጥ ሙዚቃ ይህን የፅሞና አፍታ ልክ የለሽ የመንፈስ ከፍታ ይሠጠዋል።
ምሽት... የጊዜ ግንጥል ጌጥ... የድብልቅልቅ ስሜቶች ነፀብራቅ... እጅ ላይ የሚሟሟ የቅፅበት ውበት... ከዘለዓለም የተቀነጨበ የጊዜ ሽርፍራፊ አፍታ...ፍዝ የሕይወት ሰሌዳ፣ ዓይን ላይ የሚቀልጥ የቅጽበት የውበት ድግምት…
ምሽት!.




Read 1053 times