Saturday, 16 October 2021 00:00

«ባዶ ቤት»

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(6 votes)

አይመስላትም ነበር። እዚያ ዳር ተቀምጣ የምትለምን ልጅ ውብ ከሆነ ፍቅር የወጣች... አይመስላትም ነበር። እነዚያ ጀግና ወንዳዶች ውብቷን ፍለጋ የሚዳክሩ...  በጠወለገ ውበቷም እንደሚቀልዱ፣ ያደነቁት ቅናታቸውን መሆኑን አይመስላትም ነበር።  ... ፍቅራቸው ከማስመሰል ጭቃ የተላቆጠ ... አይመስላትም ነበር።  ሰዎች ማታለልን  እንደ ዳዊት እንዲሚደግሙ፣ እምነትን ለገዛ ጨለማቸው መሸሻ እንዳደረጉ፣ ፍቅርም ብቸኝነትን ማሸነፊያ መንገዳቸው  እንደሆነ ... በማወቅ የሰሩትን ስህተት ባለማወቅ ይቅርታ የሚጠይቁ... አይመስላትም ነበር። ብዙ ነገር  አይመስላትም ነበር። ውበት እንደሚረግፍ፣ ጊዜም  ሄዶ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ባዷችንን እንደምንቀር አይመስላትም ነበር። ትላንት ከፍ  አድርጋ የሳቀችውን ሳቅ ዛሬ በእንባ እንደምትውጠው፣ ትላንት በሞቅታ ያታለለችው ብቸኝነት ዛሬ አብጦ እና ደልቦ  የሚመጣ አይመስላትም ነበር።
ዛሬ ዛሬ ህይወት ተቀይሯል። የትላንቱ ሳቅ አሁን የለም። የትላንቱ ደስታ ዛሬ አልተደገመም። ከሚቀርቧት ጥቂት ሰዎች ውጪ አጠገቧ ማንም የለም። ሁሉም ሰዎች አታላዮች ነበሩ።
“ወጥመድ ውስጥ እስስክንገባ የሰጡን ፍቅር አሁን እንደ ጉም  በኖ ጠፍቷል። እጃቸው መግባታችንን አረጋግጠው ሄደዋል። ሁሉም ተከታይ ይፈልጋል። ሃበሻ  ባይመፀውትም ለማኝ ማየት ይወዳል። እንደ ውሻ ጅራቱን እየቆላ የሚከተለው ሰው ይናፍቃል። አዎ! ዓለም ተለውጣለች።” አለች።
“ዓለም ተለውጣለች። አጠገባችን የነበሩ ሰዎችም ተለውጠዋል። ህይወት  እንዲህ ናት”
ስትወጣ ንፁህ ልቧን፣ ጉጉ ነፍሷን ተሸክማ ተንከራታለች። እዚያ ዳር በአድናቆት  ጣፋጭነቷን የነገራት ተባዕት ሀሞት መሆኗን ለመናገር ጊዜ አልፈጀበትም። እንደ ዛሬ ብቻዋን ሳትቀር፣ እንደ ዛሬ እንባ እንባ ሳይላት በፊት... ውብ ነበረች። ፊቷ ላይ ያረፈው ማድያት መውደቅያዋን እየጠበቀ እንደነበር ሁሉ  የዘመኗ ፀሃይ ስትጠልቅ ወጣ። የአንገቶቿ ቆዳዎች ተሸበሸቡ... ዓይኗ እንባ ማቅረር ጀመረ...
ሂጂ፣ ሂጂ ይላታል...ወደ እዚያ ወደ ማትነቃበት ዓለም፣ ወደ እዚያ ትላንት ይሉት የጠዋት ጤዛ ምድር ሂጂ - ሂጂ ይላታል። ሰዎች መጥፊያዋ፣ ህይወትም ምራሪ  ነበረች። በበሯ መቃን በኩል ሾልከው የሚገቡ የፀሃይ ጨረሮች  አሉ። የእትዬ ቀለሟ ድምፅ ጅሮዋ ውስጥ ይዋኛል። ይሄ ይሄ ታድያ ትላንትን አይተካም። ነገን  ጥሩ በሆነ የሰው እቅፍ አይሞላም። ዙሪያዋ ገደል እንደሆነ፣  ሊበላት የሚጠብቃት አንዳች አውሬ ነገር ይታያታል። እንዲህ መሆን ነበረበት፤ ትላለች። እንዲህም ሊደረግ አይገባም እያለች ከራሷ ጋር ሙግት ገጥማለች። ዓለም ግን ከዝምታ ውጪ የምትሰጣት አንዳችም ነገር የለም። ዓለም ሁሌም እንዲህ ናት። ከዝምታ ውጪ ሌላ ነገር አታውቅም። የበደል ደም ጠጥታ ነው የምትረካው። በሰዎቿ የችግር ዝናብ ነው የምትለመልመው። ዓለም ሁሌም እንዲህ ናት። ታድያ ይሄ ይሄ ነገር አይመስላትም ነበር።
ተነሳች እና የገዛችውን አረቄ በመለኪያ ቀዳች። ወደ ጉሮሮዋ ላከችው፤ እያቃጠላት ወረደ። እንዲህ ከመቃጠል የሚትርፍ ነገር እንዳለ ሁሉ፣ እንዲህ ከአደንዛዥ አረቄ የሚገኝ ትርፍ ያለ ይመስል...
ፍቅርን ያወቀችው በእናቷ በኩል ነው። እነዚያ ጡቶቿን እየጠባች፣ ያን ወተት ስትቀምስ አንዳች መለኮት ተላበሳት። ከዚያ  እድሜዋ ጀምሮ መለኮት አልተለያትም ነበር። አሁን ግን ሁሉም ጥለዋት ሸሽተዋል። ከጡት የሚገኝ ወተት የለም። የእናት እቅፍ ዘመኑ እርቆ ለመረሳት ደርሷል። አሁን እንዲያ አይደለም። አሁን ምንም ነገር የለም። አሁን ሁሉ ነገር ብርሃንን የተካ ጨለማ ነው። አሁን ባዶ ነው ምድሩ... የሚወዷት ሰዎች ከአጠገቧ እርቀዋል። እናቷ የእግዜር ሞት ዳብሷት ከዓለም መከራ ተገላግላለች። አባቷ አገሩን ሊጠብቅ እንደ ዘመት ሃገሩ ከጠላት እጅ ስታመልጥ እሱ ግን በጠላት ጥይት ወድቆ ቀርቷል። ትላንት ሃገሪቷን ወርራ አባቷን ለሞት የዳረገቻት ሃገር ዛሬ “ፍቅሬ ሆይ... ፍቅሬ ሆይ” የሚል ዘፈን ከ ሃገሯ ጋር ስትዘፍን ታያለች። አሁን እንዲያ አይደለም። ዓለም ተቀይራለች። የዘመተ አባቷ በሃገሩ መደፈር ተቃጥሎ ነበር። አሁን ግን ጠላት ወዳጅ ሆኗል።  ታላቋና ገናናዋ ኢትዮጵያ ከተፈጠረች ጥቂት ዓመት  ከሆናት ሃገር እርዳታን ትሻለች። አሁን ይህቺ ገናና ሃገር ለማኝ ሆናለች። አሁን እንደ ድሮ አይደለም። ማን ነው በድሮ በሬ ያረሰ፣ ማን ነው ትላንትን በዛሬ የተካ...ማን ነው?
የአባቷ ፎቶ ግርግዳ ላይ ተሰቅሏል። እናቷም በጎን አለች። የአንድ ዘመን ብርቀኞች... የማትዳሰሰውን  ፍቅር በእንባቸው አጥበው የኖሩ ሁለት ጥንዶች አሉ። ውብ ነበሩ። ሁሉም በዘሙኑ ውብ ነው። እዚያ ውስጥ የሚገኝ እሾህ ባይጠፋም ቅሉ...
በሯ  እየተንኳ ኳ ነው። እትዬ ቀለሟ ናቸው።
“ስምረት” ይጠሯታል።
ባትፈልግም እንደምንም “አቤት” አለች።
“ቡና ፈልቷል”
“እሺ”
ቡና ልትጠጣ ተነሳች። የእትዬ ቀለሟ ቤት ቅርቧ ነው። ነጠላዋን ደረበች። እንዲህ ስትለብስ ትልቅ ሰው ትመስላለች። ከእድሜዋ በላይ የገዘፈች።
“አሁን እንደዚያ አይደለም” አለች። “አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል።” ያ ወንድ ያጅበው የነበረው ገላዋ በነጠላ ተጀቡኗል። ወጣች። በሯን ዘግታ አዘገመች። ስትደርስ ቤቱ ጭር ብሏል። እትዬ ቀለሟ ትንሽ ወንበር ላይ ከረከቦቱ ዃላ ተቀምጠዋል።
“ግቢ ፣ ግቢ” አሏት።
ወንበር ላይ ቁጭ አለች።
“ምንድነው እንደዚህ መሆን”
“ምን ሆንኩ”
“እራስሽን ጠብቂ እንጂ...ባልወልድሽም  እናትሽ ነኝ። ወጣ ወጣ በይ እስቲ። እንደ አሮጊት በነጠላ ተሸፍነሽ መውጣት ጀመርሽ እንዴ?”
“ነው ብለው ነው”
“እንግዲህ አትቅለስለሺ”
“ምን ላድርግ ብለው ነው”
“እንዲህ መሆን አይገባሽም”
“አይ እትዬ ቀለሟ...እኔ እኮ ከዘመን ጋር ተኳርፌያለሁ። ያለሁ ይመስላል አይደል? የለሁም እኮ። የተሸከምኩትን መስቀል ማን አየ ብለው ነው። ዓለምን በትከሻዬ ተሸክሜ የምጓዝ ሴት ነኝ። ዓምላክ ብቻ ነው ተስፋዬ፣ እሱ መቼም አይረሳኝም አይደል? ሰው አምላኩን ይረሳል እንጂ አምላክ ሰውን አይረሳም አይደል? አዎ እንዲያ ነው እንግዲህ... “ እንባ ተናንቋት ዝም አለች።
“ኤዲያ የምን ብሶተኛ መሆን ነው”
“ብሶት አሉት... አይ ይሄ ብሶት አይደለም - እትዬ ቀለሟ...ሃቅ ነው። አንዳንዴ እውነትም ይመራል ...በሉ ቡናውን ቅዱት አስለፈለፉኝ እኮ”
“ይልቅ እዛ የምትሰሪበት ቦታ ወንዱ አያስቸግርሽም? ለምን አንዱን አታገቢም ስምረቴ...እድሜም  ይሄዳል። ሴት ልጅ ብዙ ነገር አለባት እኮ። ብቸኝነት ክፉ ነው፤ አውቀዋለሁ። ክፉ አውሬ ማለት ነው። የሚያስተርፈው ስጋ አይኖረውም። እናም ቶሎ ብለሽ አንዱን ያዢ”  ሳቅ አሉ...
“እስቲ እንደ እግዚያብሔር ፍቃድ።”
“ወንዱ ከእንደኔ አይነት ሴት ጋር ምን ያረጋል” አለች በልቧ...
ቡናው ተቀዳ። ቀለማም ጥለትዋን እያፍተለተለች ዝም አለች።
“እንደው ድሮ ነው ...” ብለው ጀመሩ እትዬ ቀለሟ።
“እንደው ድሮ ነው። ያኔ ኮረዳ እያለን ሁሉም ነገር ውብ ይመስለን ነበር። ወንዶች በኛ ምክንያት ሲጣሉ፣ ሲፈናከቱ፣ ጠጅ ጠጥተው ሲጎነትሉን በጣም ተፈላጊነት ይሰማናል። አንዱ መጥቶ ያጫውተናል። እሱ ሲሄድ ሌላው ይመጣል። ሁሉም ፍቅርን የሚዘምሩ የእግዜር መላዕክት ይመስሉን ነበር። ዓለም እንደ ልጅነት ጊዜ መልካም ብትሆን እንዴት ጥሩ ነበር። እናልሽ አንድ ጠጅ ቤት ነው የምሰራው። እዛ የሚመላለስ አንድ ቄስ ነበር። ወጣት ነው። ሳያገባ ቄስ እንደማይሆን አስሪዬ ነግራኝ ነበር። እኔ ግን ያግባ አያግባ አላውቅም...ቄስ እከሌ ብለው ሲጠሩት ነው የማውቀው። ስም እዚህ ጋር ምን ያደርጋል። መልኩ እንዴት ግሩም መሰለሽ። ጥምጣሙን ሲያወልቅማ ሰማይ ላይ የተዘራ ኮኮብ ነው የሚመስለው። ዓይኖቹ ጥርት ያሉ ናቸው።  ሲስቅ ፀሃይም  አብራ ፈገግ ትላለች። እነዚያ ተስተካክለው የተቀመጡት ጥርሶቹ ልቤን ወከክ ያደርገዋል። ሳየው ልቤ መምታ ጀምሯል። ጠጅ እቀዳለታለሁ። አጠገቡ እቀመጥና የሚለውን እሰማለሁ። የሚያወራው ዝብርቅርቅ ነገር ነው።  እና ይሄ ድርጊቴ ታውቆ ኖሮ የጠጅ ቤቱ ባለቤት አውቃለች። አንድ ቀን እንዲሁ አጠገቡ ተቀምጬ ጠጋ ብሎ ከንፈሬን ሳመው። ደነገጥኩ...ቄስ መሆኑን አስቤ መሰለኝ። እንግዲህ ከዚያ ጊዜ ጀምሬ እልም ያለ ፍቅር ያዘኝ። ቡዝዝ ባሉት ዓይኖቼ አየውና የማደርገው ይጠፋኛል። በዚህ ጊዜ ነበር አባቴ ባል ያመጣልኝ። እምቢኝ አልኩ። እኔ ቀልቤ ከዚያ ቄስ ጋር ነው ያለው። ግን አልሆነም። አባቴ ለአንድ ገበሬ ዳረኝ። እዚያ መስራቴም ቆመና ያን ወጣት ቄስ ማየት ተውኩኝ። ይሄ ሁሉ ዘመን አልፎ እንኳን እያስታወስኩት አለቅሳለሁ። ምን አይነት እድል ነው ያለኝ። ትዳሩም አልሆነልኝም  ባሌ  እርጉዞ ሆኜ ትቶኝ ጠፋ። ላይወደኝ እድሌን አበላሸው። ከዚያ አጎቴ ጋር አዲስ አበባ መጣሁ። ይሄም ቤት አውርሶኝ የሄደ እሱ ነው ታድያ? እናልሽ አንድ ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስ  አስቀድሼ ልወጣ ስል ያን ቄስ አየሁት። በህልሜ መሰለኝ። በእውኔም መሰለኝ። ዝብርቅርቅ አለብኝ።  እሱ ግን መጀመሪያ አላየኝም ነበር። ጊዜ ሄዶ መልኩ ላይ ምንም ነገር አልፈጠረበትም። እንደ ድሮ ቆንጆ ነው። ላናግረው ፈልኩ። ተጠጋሁት። ሳወራው ለካ እረስቶኛል። አየሽ አይደል? ባፈቀሩት እንደመረሳት አስከፊ ህመም የለም። የወደዱት ሲርቅ ደስ አይልም። እና አለቀስኩና እንባዬን በነጠላዬ አብሼ ወጣሁ። ፍቅር እዚህም ድረስ መጥቶ ነበር። እናውቀዋለን። በእርግጥ የዘሙኑ መንፈስ ደስ አይልም። ሁሉም ነገር ጊዚያዊ ሆኗል። ፍቅርን እንደ ይሁዳ ጉንጩን ስሞ የሸጠው ሰው ነው። ባናውቀውም ሰው ነው ከሃዲው። ሰው ነው ያረከሰው። የስውን ልጅ ውስጡን ገልብጠሽ እንደ ጨርቅ ብታይው እንኳን ልታምኚው አይገባም። ምን አብቅሎ እንዳደረ እንዴት  ታውቅያለሽ? አለመፈለግ ደስ አይልም። አለመፈለግ ቅር ይላል። ያፈቀሩት፣ የእኔ ያሉት ሲሸሽ ፣ የቀረቡት ሲርቅ፣ ያመኑት ሲከዳ ቅር ይላል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ህይወቴን ያሳለፍኩት በብቸኝነት ነው። ፍቅርን ፈራሁ። ህይወትን ፈራሁ። ዓለምን ፈራሁ። መረሳቴ ብቸኛ አደረገኝ። ቢረሳ ቢረሳ ያኔ የቀመሰውን ከንፈር እንዴት ይረሳል? አየሽ አይደል ስምረቴ? ህይወት እንዲህ ናት። አንድ ጊዜ ነበርሽ ፣ አንድ ጊዜ ውበተሽ ተስተካካይ አልነበረውም...ስትረሺ ግን እንዲህ ነው። አንድ ነገር ልምከርሽ፤ ዓለምን አታፍቅሪ። ህይወትን አትወደጂ። ፍቅርን አትመኚ -ስምረቴ። ሁሉም እንደ ጠዋት ጤዛ ጠፊ ናቸው። ብቻ ጀግና ሁኚ። የሴት ጀግና። አለት ልብ እንደመያዝ አኩሪ ነገር የለም አየሽ። ለማንም ልብሽን አትስጪ። ማስመሰል ጥሩ ነው አየሽ። የሞኝ ሳይሆን የብልጥ ማስመሰል። ውስጣችን እያለቀሰ ነው የምንስቀው። እሱም ጥሩ ነው። የቀረቡሽ ሰዎች እንደሚርቁሽ እወቂ። ዛሬ የወደደሽ ነገ ጠላትሽ ነው። ዛሬ ያፈቀሩሽ ነገ ይሰለቹሻል። ሰዎች የሚጠጉሽ የብቸኝነት ብርድ መቻል አቅቷቸው ሙቀት ፍለጋ ነው። ሰዎች የሚጠጉሽ የዛሬ ዳገት የሆነ ቀናቸውን ለማለፍ ምርኩዝ ስለሚፈልጉ ነው። ለዚያ ነው የትኛውንም ፍቅር አትመኚ የምልሽ። ባል ብታገቢ እንኳን ባልሽን አታውቂውም። እንደ እኔ ልጁን ተሸክመሽ ጥሎሽ ሊሄድ ይችላል። አየሽ የሰው ሆድ ምን አብቅሎ እንዳደረ አናውቀውም። ሰው ማመን ልብ ይሰብራል። ብቻ መልካም ሁኚ። ሰው ሆን ብለሽ አትጉጂ። ባፈቀርሽው ሰው ብትረሺ እንኳን አልቅሶ ከመሄድ የዘለለ ነገር አታድርጊ። ልጄ ነሽ ብዬ ነው ይሄን ሁሉ ነገር መቀባጠሬ። እኔን ያደናቀፈኝ ድንጋይ እንዳይጥልሽ ነው ስጋቴ።  ልብ አድርጊ ያኔ እኔን እንኳን አልልሽም። ስትወድቂ ባይሽ እንኳን ምንም ነገር አላደርግም። እንደተረሳሁ እረሳሻለሁ። አንድ ቀን የኔም ሆድ ምን አብቅሎ እንዳደረ አላውቅምና።”
“አይ እትዬ ቀለሟ ...ትክክል ነዎት። አታገቢም እንዴ  እያሉ ፍቅርን አትመኚ ማለት ግን አይቃረንም”
“አዎ ይቃረናል።  ትዳር ውስጥ እውነተኛ ፍቅር አለ ብለሽ ነው ስምረቴ? እንዳልኩሽ ነው። ሁሉም ነገር ማስመሰል ነው። ትክክለኛ ፍቅር ዝንት ዓለም አይቀየርም። እውነተኛ ፍቅር ከሞት በዃላ እንኳን ይገናኛል። ሞት አይረታውም። ግን ያንን የምትጠብቂ ከሆነ አፍንጫሽን ላሽ ብሎሽ ነው የሚሄደው። አንቺም እውነተኛ ፍቅር ለመስጠት እንዳትሞክሪ። ክርስቶስ ብቻ ነው ከእኛ ምንም ሳይፈልግ እውነተኛ ፍቅር የሰጠን። የተጋነነ ነገር ስትሰጪ አንቺ ያንኑ ትጠብቅያለሽ። ያ ደግሞ ቅዠት ነው። እራስሽን ቆጥቢ ነው የምልሽ። እንደሰጡሽ አትቀበይ። ስትሰጪም መጥነሽ ነው ስምረቴ። እኔ ፈላስፋ አይደለሁም። ህይወት ግን አስተምራኛለች። ፊደል የቆጠርኩ እንዳልመስልሽ፤ ስሜን መፃፍ እንኳን አልችልም። ሁሉን ነገር ያስተማረኝ መረሳት ነው። ከዚያ ውስጥ ነው እውነትን የፈለቀቅኩት።”
“መረሳት አስከፊ ነገር ነው። ግን እንዴት ቄሱ ሊረሳዎት ቻለ?”
“እኔንጃ ስምረቴ። ማን ነሽ አለኝ? ዘመኑ ብዙም አልራቀም። ማን ነሽ ለመባል ያብቃሽ እንጂ ስሜቴን ትረጂዋለሽ! አይ ዘመን ሄዶ ዘመን ይተካል። የተፈቀረም ይረሳል። ፍቅር መላመድ ይመስለኛል። የዓይን ፍቅር የሚሉት ነገር አይገባኝም። ፍቅር አብረው ሲውሉ ፣ አብረው ሲኖሩ ነው የሚዳብረው። አለዚያ ትረሳሻለሽ። ፍቅርን በመላመድ እንዳገኘሽው፣ መለያየቱንም ትለምጂዋለሽ ...አየሽ አይደል? እኔ ከዛ በዃላ አላገባሁም። ልጄም ሞት ነጥቆኛል። አሁን ብቻዬን ነኝ። ቡና እንኳን የምጠራው አንድ አንቺን ነው። እርጅናም መጣ። እርጅናን የመሰለ ቆሻሻ ነገር አይቼ አላውቅም። ያለ ልጅ ማርጀት፣ ያለ ልጅ አንቱ መባል...ባል እንኳን የሌለበት ጭር ያለ ቤት...ያለ ሰው፣ ያለ ፍቅር ...ያለ ወዳጅነት...አየሽ ...ሰው እድሜ የሚለምነው ለማርጀት ነው፤ ግን ደስ አይልም። የተጣልሽ ይመስልሻል። በእግዜር፣ በሰው የተረሳሽ ይመስልሻል። ማንኛውም ነገር ሲንዘላዘል ደስ አይልም። ቶሎ መሰብሰብ ይሻላል ስምረቴ.... ለዛ ነው ያንቺ ነገር እንደ እናት ሆዴን የሚበላኝ። ብቻሽን ሳይሽ...ብቻሽን ስትሆኝ ልቤ ይፈራል። አንዳች ሰይጣን እንዳያሳስትሽ እሰጋለሁ... ለዛ ነው አንዱን ያዢ የምልሽ። የዘመኑ ፍቅር እውነት ባይሆንም ግን ከብቸኝነት ይሻላል። ከብቸኝነት የማይሻል ነገር የለም። አይዞሽ ስምረቴ...”
“እሱስ ልክ ነዎት...በፊት ሰዎች ሲከቡኝ፣ ወንዶች ሲጠጉኝ ባዶ ቤት የምውል አይመስለኝም ነበር። ዛሬ ተቀይሯል። ሁሉም ነገር ተለውጧል። ወንዶች ተንጠባጥበው ቀርተዋል። ሰዎም እንደጊዜው አይፈልገኝም”
“እኔን ልከፋ ስምረቴ...ለዛሬ ሰው እንኳን እንዲህ መሆንሽ ልክ አይደለም። ምን የዛሬ ሰው ቢመጣ ባይመጣ ምን ይጠቅማል ብለሽ ነው። ዋናው ሰው አለመጉዳት ነው። ይሄ ሻጋታ ህዝብ መጣና ደግሞ ምን ይቀራል? እከኩን ይዞ ነው የሚመጣው! ችጋርና ችግር የከበበው ህዝብ ደግሞ ምን ይረባል ? ሲኖርሽ ነው ሁሉም ሰው የሚከብሽ! ሲኖርሽ ፊት የነሳችሽ እናትሽ እንኳን ፈገግ ብላ ትቀበልሻለች። ጨረቃ እንኳን ፊትሽ ላይ መድመቅ ትጀምራለች። ተፈጥሮም በእግዜር እጅ እንዳልተፈጠረ ሳይኖርሽ  ይሸሻል። ሃገርሽ ላይ ሆነሽ በዓድነት ይሰማሻል። በፊት እጅ ነስቶ ስላም የሚልሽ ሰው ዛሬ ሲያይሽ መንገድ ይቀይራል። ገንዘብ ዓለም ይገዛል ቢሉ ተሳስተዋል አልልም። ገንዘብ የማይገዛው ምን ነገር አለ። ብቻ ይሄን ህይወት የምትችይበት መሸሻ ያስፈልግሻል። ለዛ ነው ወንዶችን ቅረቢ የምልሽ። የሽሽትሽ በኣት ይሆናል። መከፋትሽ በእሱ የውሸት ሳቅ ትጋርጂያለሽ። እቅፉ የውሸት ቢሆንም ከብቸኝነት ብርድ ይከልልሻል። እየሳቁ አስመስሎ መኖር ነው። እንደነገርኩሽ ነው። ስትረሺም ስቀሽ መሄዱን አትርሺ። ሳቅ መልካም ነገር ነው። “
ሳቀች። በደንብ ሳቀች።
“አዎ እንደ እሱ ስምረቴ... ቢከፋንም ሳቅ መልካም ነገር ነው።”
ተነስታ ስትወጣ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዋ እየመጣ ነበር። በብዙ የበሰሉ አሮጊት መሆናቸው ገባት። እኚህ ሴትዮ ቀላል ሰው አይደሉም አለች።
ከቀረቧት ወንዶች መሃል አንዱ ዳዊት ነው። ትንንሽ አይኖቹን አጨንቁሮ እንደሚያፈቅራት ሲነግረት ተደስታ የምትጨብጠውን አጥታ ነበር። አቅፏት አስፋልታ መሃል ሲሄድ ዛሬ ጥሏት የሄደው መለኮት ይላበሳታል። አንዳች ተዓምር መስራት የምትችል የእግዜር ሰራዊት አድርጋ እራሷን ትቆጥራለች። ሁሉም ነገር ውብ ነው ትላለች። እንዲሁ እንደዛሬ ሳትወድቅ በፊት ያኔ እንዴት ውብ ነበረች? እንደዛሬ ሰው ሳይረሳት በፊት እንዴት ልበ ሙሉ ነበረች? የእትዬ ቀለሟ መረሳት አስገርሟታል። ሰው እንዴት አብሮ አሳልፎ ይረሳሳል? አብሮ በልቶ ይጠላላል? ሰው እንዴት እንዲህ ይሆናል? አውሬት አዋጪ ንግድ መሆን አልገባትም ነበር። መጨካከን ሰው በህቡዕ የከተበው ህግ እንደሆነ አታውቅም ነበር። ታድያ ዳዊት ከሁሉም ወንዶች የሚለየው በሄደበት ሁሉ ይዟት የመሄዱ ጉዳይ ነው።  ይኮራባት ነበር።  ለሰዎች ሲያስተዋውቃት ፍቅረኛው እንደሆነች አድምቆ ይናገራል። እናም አንድ ቀን ውጪ እንደሚሄድ ነገራት። ሙቅ ፍሳሿ ከዓይኗ ወደ ጉንጯ መውረድ ጀመረ። መለየት እንደ ጦር ወጋት። መለየት የሞት ታናሽ ወንድም ሆነባት። ቅር ይላል። እንደዚያም ሆኖ ተለየችው። እንደ ቀልድ ሄደ። እንደ ቀልድ ጥልዋት ነጎደ። ከሄደ አንድ ሁለት ቀን ደወለላት። ሰላም መድረሱን ነገራት። ከዚያ በዃላ እሱም እንደሌሎቹ ጠፋ። መጥፋት የብዙ ወንዶች ባህሪ ይመስላታል። ምን እንደፈልጉ ሳታውቅ የሚፈልጉት አግኝተው ይጠፋሉ። ወንዶች በመጥፋት ታሪክ የሰከሩ፣ በጥቅም ጭንብል የታወሩ የዘመን እንስሶች እንደሆኑ ታስባለች። ወንዶች አንዳንዴ ከእግዜር የተላለፈ አስፋሪ እርግማን አለባቸው ትላለች። ሙሴ ቸል ያለው ወይ አውቆ የዘነጋው አንዳች መጥፎ እርግማ አለ ባይ ናት። ከማትፈልጋቸው ሴት ስር እንደ ውሻ ላጫቸውን አዝረብርበው መከተል ልማዳቸው ይመስላታል። ዛሬ ዛሬ ግን ሁሉም ተቀይሯል። የውበቷን ማዕድን ቆፍረው ካወጡ በዃላ ጠፍተዋል። አሁን የሚፈልጉት ነገር የለም።  የወደቀን ውብት የሚያይ ከወንድ ወገን ብቻውን የበቀለ የለም። የተረሳን ነፍስ የሚያድስ ጠቢቢ ወንድ ዓለም ላይ  ቢፈለግ አይገኝም። ይሄን ያለችው እሷ ናት። በእሷ ዓለም፣ በእሷ እውነት ውስጥ ቢያንስ ጠቢብ ወንድ የለም።ወንድ ልጅ ደደብ እንደሆነ ታውቃለች። ዓይኑ በጭን አምሮት የተጋረደ እውር መሆኑን ትረዳለች።
“ወንድ ልጅ” እያለች ቤቷ ገባች...ሳታስበው እንባዋ መጥቷል። ቅድም የቀዳችውን አረቄ መጠጣት ጀመረች።
ማስታወሻ ደንተሯን አወጣች። ብዕሯን ያዘች። መፃፍ ጀመረች።
“ዛሬ አስገራሚ ነገር ሰማሁ። እትዬ ቀለሟ ከንፈራቸውን በቀመሰ፣ ባፈቀሩት ሰው መረሳታቸው አስገረመኝ። እንዴት ሰው የአንድ ዘመን ወዳጁን ማን ነሽ ይላል? ምናልባት የመርሳት በሽታ ከሌለበት በቀር። እንደዚያ ነው። መረሳት የብዙ ሰው ህመም ነው። እኔንስ የረሱኝ እነማናቸው? ላውቃቸው እየፈለኩ የሸሹኝ እነ ማን ናቸው? የትላንቱ ዳዊት ዛሬ ማንነሽ እንደማይለኝ በምን እርግጠኛ ነኝ? ዛሬ ሁሉም ነገር ተቀይሯል.. ክርስቶስ ለኛ ብሎ ተሰቅሎ ዛሬ ማን ናችሁ ቢለን ጥሩ ነው? ለእኛ ብለው ስንት መስቀል የተሸከሙ ሰዎች ዛሬ ማንነታችንን እረስተዋል። ለእኛ ብለው በሁለት ወንበዴ መሃል የተሰቀሉ ወዳጆች ዛሬ መኖራችንም ትዝ አይላቸውም።”
“መሳቅ መልካም ነገር ነው”
ድምጿን ከፍ አድርጋ ሳቀች። ባዶ ቤቱ ውስጥ ሳቀች። ሳቋ ወደ ጆሮዋ ሲያስተጋባ ደጋግማ ሳቀች።
“መረሳትን ማሸነፊያ መንገድ አንዱ ሳቅ ነው”
“አዎ፤ መሳቅ መልካም ነገር ነው”

Read 1465 times