Saturday, 16 October 2021 00:00

“በአዲሱ መንግስት ጅማሮ ትልቅ ተስፋ አይቻለሁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 (የታላቁ ህዳሴ ግድብ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አረጋዊ በርሄ)

           የአዲሱ መንግስት አካታችነት በእጅጉ የሚመሰገን ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ተካትተዋል። ይሄ ደግሞ በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚሳይ ጥሩ ጅማሮ ነው። ከተለያዩ ፓርቲዎች የተሻሉ ናቸው የተባሉ  ተመርጠው ገብተዋል።  ቀደም ሲል አንድ ፓርቲ ካሸነፈ የራሱን ሰዎችና የፓርቲ አባላት ብቻ ነበር የሚሾመው። አሁን ግን አቃፊ በሆነ መልኩ የሌሎች ፓርቲዎች አባላትን ማሳተፉ መልካም ጅማሮ ነው።
የመንግስት አካታችነት  ለወደፊቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና እድገት ጥሩ መረማመጃና  በር ከፋች ሆኖ ነው የተሰማኝ።  የፓርላማ አባላቱም ጠንከር ጠንከር ያሉ  ጥያቄዎችን በእጩ ሚኒስትሮቹ ላይ ሲያነሱ ተደምጠዋል። ለምሳሌ አንድ የምክር ቤት አባል  በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ሾልከው የገቡ ሌቦች አሉ”  እስከ ማለት ደርሰዋል። ይሄ ደግሞ ለስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ይሁን በአጠቃላይ ለሚመለከተው አካል ጉዳዩን እንዲፈትሽ ጥሩ ማሳሰቢያ ነው የሚል እምነት አለኝ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌብነትን እንደሚጸየፉና ሁሉም ሌብነትን እንዲጸየፉ አስረግጠው መናገራቸው ተገቢ ነው፡ የሚኒስትሮቹን ሹመት በተመለከተ ለምሳሌ የኦነጉን ቀጀላ መርዳሳን በባህልና ስፖርት ሚኒስትርነት አልጠበቅኩትም፣ የአብኑ በለጠ ሞላም ትምህርቱ ከፍልስፍና ጋር የተያያዘ ከመሆኑ አንጻር፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትርነት አልጠበቅኩትም፤ በትምህርት አካባቢ ሊሆን ይችላል ብዬ ነበር ያሰብኩት። ፕሮፌሰር ብርሃኑንም ቢሆን በትምህርት ሚኒስትርነት አልጠበኩትም ነበር። ይሄ ማለት ግን የተመደቡበትን ተቋም አስተባብረው የመምራት አቅም ያንሳቸዋል ማለቴ አይደለም።
አዲስ መንግስት የመሰረትነው በብዙ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ጫናዎች ውስጥ ሆነን ነው፡፡ ነገር ግን ሀገረ መንግስት መመስረት ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሀገረ መንግስት ምስረታ በዓለም የምትታወቅ ሀገር ናት። ይሁን እንጂ ብዙ ተግዳሮቶች እየገጠሟት ወደ ኋላ መቅረቷ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር፣ ያሁኑ የሃገረ መንግስት ምስረታ ከቁጭት የመነጨ ነው።
የአሁኑ መንግስት ከወትሮው በተለየ የህዝብ ተሳትፎ ያለው ነው። በህዝብ ተሳትፎ የመጣ በመሆኑም የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሃይሎች አሳትፎ እንቅስቃሴውን መጀመሩ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነው። በእርግጥ አሁንም የዱሮውን አካሄድ የመረጡ እንደነ ህወኃት ያሉ ቡድኖች ጦርነት እስከ መክፈት ደርሰዋል። ይሄ ደግሞ ራሱን የቻለ አንድ ተግዳሮት ቢሆንም  ቡድኑን የኢትዮጵያ ህዝብ የማይፈልገው በመሆኑ ውሎ አድሮ  ተሸናፊ ነው። ከድሮም ጀምሮ ህወኃቶች የሚታወቁት በክህደት ነው። የራሳቸውን ህገ-መንግስት፣ የራሳቸውን መከላከያ ሃይልና የራሳቸውን ምርጫ ቦርድ ክደው በተናጥል ምርጫ አካሂደዋል።
በነገራችን ላይ ሁሉ ነገራቸው የሆነውን የትግራይንም ህዝብ ክደዋል። ህዝቡ ከድህነት አረንቋ አልወጣም። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ከለውጡ ጋር ሊሄዱ ያልቻሉ፤ ሀገረ መንግስትን ለማፍረስ የሚታገሉ ቡድኖች ናቸው። ነገር ግን አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን በቃኝ ብሎ ስለተነሳ ነው ለውድቀታቸው ቀን መቁጠር  የያዙት። ሌሎች እነሱን የሚረዱ ተጠቃሚ የነበሩ የውጪ ሃይሎችም አካሄድና አመለካከት ከህወሃት ጋር አብሮ የሚቀበር ነው የሚሆነው። ይህንን የተመለከቱ የአፍሪካ መሪዎችም በአዲሱ መንግስት ምስረታ ላይ  ተገኝተው ድምጻቸውን አሰምተዋል፤ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ተስፋም አንጸባርቀዋል።
ህዝቡም በነቂስ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉን ገልጿል። ስለሆነም ህዝቡ በቀጣይ በእውቀቱ፣ በገንዘቡና በጉልበቱ አገሩን ለማገዝ ቆርጦ መነሳቱን አይተናል። በአጠቃላይ የአዲሱ መንግስት ጅማሮ ኢትዮጵያን የሚያነሳሳ፣ ተገቢውን ቦታ የሚያጎናጽፍ ሆኖ ነው የሚታየኝ።
አዲስ የተመረጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሆኑ አዲስ የተሾሙት ሚኒስትሮች፤ በህዝብ ድምጽና ፍላጎት ነው የተመረጡት፡፡
የህዝቡን የልብ ትርታ እያደመጡ፣ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። በተረፈ  በጅማሮው ትልቅ ተስፋ አይቻለሁ፤ ጥሩም እንደሚሰሩ እጠብቃለሁ፡፡ ለሁሉም መልካም የሥራና የአገልግሎት ዘመን እመኝላቸዋለሁ።


Read 9672 times