Monday, 11 October 2021 09:31

….እኔን ያያችሁ ተቀጡ…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የካንሰር ሕመምን በተመለከተ የተለያዩ ጽሁፎችን ባለፉት እትሞቻችን ማሰነበባችን ይታወ ሳል፡፡ ይህንኑ መሰረት በማድረግ አንዳንድ እናቶች ገጠመኛቸውን አካፍውናል፡፡ እናቶች ብቻም ሳይሆኑ ከአባቶችም እንዲሁ በፕሮስቴት ካንሰር ዙሪያ አንድ ገጠመኛቸውን ያካፈሉን አሉ፡፡ ገጠመኞቹ በስተመጨረሻው እኔን ያየህ ተቀጣ የሚል ምክር ስለአለው እና ምክሩም እውነት በመሆኑ ለአንባቢ ብለነዋል፡፡ ለአስተያየቶቹ የተጠቀሱት ስሞች ትክክለኛ ስሞች አይደሉም፡፡      
የመጀመሪያው ገጠመኝ የደረሰን ከኮተቤ አካባቢ ከወ/ሮ ሀና ነው፡፡ መልእክቱን ያደረሱን እናት በእድሜያቸው የአርባ ስምንት አመት ሴት ናቸው። ሀሳባቸው እንደሚከተለው ነው፡፡  
‹‹….በጤንነቴ ጥሩ የሆነ ስሜት ካጣሁ ቆይቻለሁ። ነገር ግን ምንሆኜ ነው የሚለውን ሀሳብ እንኩዋንስ ለሰው ለእራሴም መልስ ሳልሰጥበት ደብቄው ኖርኩ፡፡ ከእለት ወደእለት፤ ከጊዜ ወደጊዜ መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ ከብልቴ ይወርድ ጀመር። የውስጥ ሱሪ ከመቀያየር ወጥቼ ሞዴስ መጠቀም ጀመርኩ፡፡ ባለቤቴ ከእኔ ምንም ስላልሰማ በትዝብት ይመለከተኛል፡፡ ውሎ አድሮም የወሲብ ጥያቄውን አቋረጠ፡፡ በስተመጨረሻ ሞዴስ በድንገት አልቆብኝ የመጀመሪያ ልጄ ሴት በመሆንዋ አንድ ብቻ እንድትሰጠኝ ጠየቅሁዋት፡፡ እሱዋም ለምንሽ ነው……የወር አበባ የለኝም ስትይ አልነበር እንዴ ….አለችኝ፡፡ እኔም …ይህንን.. በቃ….ለእስዋ ብነግር ይሻለኛል ብዬ አማከርኩዋት፡፡ ይህች ሴት ልጄ እድሜዋ ሀያ ሁለት አመት ነው፡፡ በዲፕሎም ተመርቃ ስራ ተቀጥራለች። ነገሩን ሳዋያት በጣም ደነገጠች፡፡ እማ…..ምን እያደረግሽ ነው ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ይሻለኛል ብዬ ነበር ነገር ግን አልሆነልኝም… …እየባሰብኝ ሄደ….አልኩዋት፡፡ አባስ…ይህንን እያየ ዝም አለሽ እንዴ…አለችኝ፡፡ ከእኔ ምንም ስላልሰማ መሰለኝ…ዝም ብሎ በትዝብት ይመለከተኛል… አልኩዋት፡፡ አንቺ ግን ለምን አልነገርሽውም…ስትለኝ ….አፍሬ ነው…አሁን ግን ከአቅሜ በላይ ሆኖአል…. ስራ መዋልም…በትራንስ ፖርት መጠቀምም አልቻልኩም…አልኩአት…፡፡ ልጄም የጠየቅሁትን ሞዴስ ሰጥታኝ ፊትዋን አዙራ ሄደች፡፡ በማግስቱም ለአባትዋ ነግራ ይዘውኝ ወደሐኪም ቤት ሔድን፡፡ በጣም ያሳዝናል። ለካስ የማህጸን በር ካንሰር ይዞኛል፡፡ ከዚያ በሁዋላ የህክምናው አይነት ሁሉ ተደረገ፡፡ ግን እነሆ ዛሬ አልጋዬን ይዤ….ከቤት መውጣቴን ትቼ….የካንሰር ሕመሙም ቢታገሉት …ቢታገሉት… እየተሰራጭ ሞቴን እየጠበቅሁ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ለምን ሆነ ብትሉኝ የእኔ አጉል አስተሳሰብ… የማይረባ እፍረት….ችላ ባይነት…. ድብቅነት… ሁሉም ነገር ነው፡፡ ብቻ ያሳዝናል፡፡ እባካችሁ ሴቶች…. የካንሰር ሕመም ለሴት ልጅ ህይወት ጠንቅ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም፡፡ እኔን ያያችሁ ተቀጡ….››
በቀጣይነት አስተያየታቸውን የተቀበልናቸው እናት ገጠመኛቸው የጡት ካንሰር ነው፡፡ የሚኖሩት በቃሊቲ አካባቢ ሲሆን በእድሜአቸው በአሁኑ ወቅት ሀምሳ ሶስት አመት ነው፡፡ ችግሩ በገጠማቸው ጊዜ ግን አርባ አራት አመት እንደነበራቸው ገልጸዋል።፡
‹‹….እድሜዬ ወደ አርባ አራት አመት ገደማ ሲሆን የማይመች ነገር ይሰማኝ ጀመር፡፡ ምግብ አይበላልኝም፡፡ የበላሁትም አይረጋልኝም።  በተለይም ጠዋት ጠዋት ልክ እንደ እርጉዝ ሴት ያደርገኛል፡፡ ቀደም ሲል ሁለት ልጆች ስለወለድኩ አውቀዋለሁ፡፡ ይሄ ነገር ምን አይነት በሽታ ነው ብዬ ወደሆስፒታል ሄድኩ፡፡ ሐኪሙ ምርመራዎች አዘዘልኝ፡፡ በውጤ ቱም እርግዝና ያሳያል ተባልኩ። እኔም አሻፈረኛ አልኩ፡፡ እኔ በዚህ እድሜዬ እንዴት አረግዛለሁ…. ምን ማለት ነው…. አይሆንም …ተሳስታችሁዋል… አልኩ፡፡ ሐኪሙም… አንቺን ደስ እንዲልሽ ሌላ ላቦራቶሪ አሰርተሸ ነይ ብሎ ወረቀት ሰጠኝ፡፡ ከባለቤቴ ጋር እየተዝናናን… ያሾፋሉ እንዴ… የምን እርግዝና ነው እያልን… ሄድን፡፡ የላቦራቶሪ ውጤቱም እርግዝና ሆነ፡፡ ይሁን በቃ…. በስተርጅና ብቻችንን እንዳንሆን እግዚአብሔር የሰጠን ነው ብለን ወደ ሐኪሜ ተመለስኩ፡፡ እርግዝናው ካለምንም ችግር ተጠናቀቀ፡፡ እንዲያውም ካአሁን ቀደም ያላገኘሁትን ሴት ልጅ አገኘሁ፡፡ ደስታ…ፈንጠዚያ…ሆነ፡፡ ፈንጠዚያው ከክርስትና ቡዋላ አልቀጠለም። አንደኛውን ጡቴን ማጥባት አልቻኩም፡፡ ሰዎች ሳማክራቸው…አንዳንድ ሰዎች እኮ ሁለቱንም ጡት አያጠቡም ይሉኛል፡፡ እኔ ደግሞ አለማጥባት ብቻ ሳይሆን ሕመም አለኝ፡፡ ለመጣ ሁሉ ሳማክር ቆየሁ፡፡ አንዴ ምች ነው ሲሉኝ… አንዴ ግርፋት ነው ሲሉኝ….. በስተመጨረሻ እንደ ሽፍታ እና ቁስለት አየሁበት፡፡ ልጄን በአስቸኩዋይ ለእህቴ ሰጥቼ እኔ ወደሕክምናው ፊቴን አዞርኩ፡፡ በአስቸኩዋይ ቀዶ ሕክምና አድርገውልኝ.. ክትትሉንም ጨርሼ አሁን ደህና ነኝ፡፡
እኔ ለማለት የምፈልገው …የማይመለከታቸውን ሰዎች ማማከር አይገባም፡፡ በጤንነት ላይ አንድ ጥርጣሬ ሲኖር ወደሚመለከተው ቦታ መሄድ ተገቢ ነው…››
በቀጣይ ገጠመኛቸውን ያካፈሉን አቶ ወንድሙ ምህረቴ ከለቡ አካባቢ ናቸው፡፡ አቶ ወንድሙ የፕሮስቴት ካንሰር ታማሚ ናቸው፡፡ ገጠመኛቸውን እንደሚከተለው አውግተውናል፡፡
‹‹….ሕመም ሊሰማኝ ከጀመረ ወደ አራት አመት ይሆነዋል፡፡ በተለይም ጠዋት ጠዋት መታጠቢያ ቤት ገብቼ ሽንቴን በምሸናበት ወቅት ኡኡ ያሰኘኛል። ሽንቴን ብዙ ሰአት ይዤ መቆየትም አልችልም፡፡ እንደ እብጠት ያለ ነገር ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ ባለቤቴ ሁል ጊዜ አንተ ሰው ምን ሆነሀል ….ስትለኝ…ምን ሆንኩ ….ምን አየሽ… እላታለሁ፡፡ እኔ ግን ስቃዬ እየጨመረ መጣ፡፡ ለሰው አላወራም፡፡ ወይንም ሐኪም ቤት አልሄድኩም፡፡ እንዲሁ እየሆንኩ ስራዬን ሳላቋርጥ እሰራለሁ፡፡ የሁዋላ ሁዋላ ግን አልቻኩም። በጣም አመመኝ፡፡ ከቤተሰብ ጭቅጭቁም በዛብኝ። እንግዲህ አይቀር….. ብዬ ተነስቼ ወደሐኪም ቤት ሔድኩ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ የካንሰር ሕመሙ ወደ 3ኛ ደረጃ ደርሶአል፡፡ ሐኪሙም ጭምር በጣም አዘነ፡፡ እኔም ደነገጥኩ፡፡ ቤተሰቤ በሙሉ ተረበሸ፡፡ በአስቸኩዋይ ወደ ኦፕራሲዮን ተመራሁ፡፡ ኦፕራሲዮን ተደርጌ የካንሰር ሕመሙ የጎዳው ክፍል ወጣልኝ፡፡ ከዚያም ደስታ ሆነ፡፡  እግዚ አብሔር ይመስገን …በቃ ተገላገልክ… እንዲሁ ስትሰቃይ ኖርክ ተባልኩ። የሐኪም እረፍቴን ስጨርስ በተወሰነ የጊዜ ርቀት እንደ ገና ወደሐኪም ቤቱ መመለስ እንዳለብኝና ያለሁበት ሁኔታ ክትትል እንደሚያስፈልገው ተነገረኝ፡፡ እኔም ፈቃዴን ስጨርስ ወደ ሐኪም ሳይሆን በቀጥታ ወደስራዬ ተመለስኩ፡፡ ለምን ሐኪም ቤት አትሄድም የሚል ጥያቄ ሲቀርብልኝ….አአ….አይ…አሁንማ ምን ሆንኩ ብዬ እሔዳለሁ…ዳንኩ እኮ…እያልኩ መልስ እሰጣለሁ፡፡ ዘመድ አዝማድ…ጉዋደኞቼ… ልጆቼ…. ቢነግሩኝ አልሰማሁም… ወደ ሐኪም ቤት ለመሄድ እሺ አላልኩም፡፡ ነገር ግን ጊዜውን ቆጥሮ ሕመሙ እንደገና ተመለሰ፡፡ ምክንያቱም ክትትል አላደረግሁም፡፡ ችላ ባይነት ያመጣብኝን ጣጣ ልናገረው አልችልም፡፡ አሁን በጣም ታማሚ ሆኛለሁ፡፡ የወደፊቱን አላውቅም፡፡ ሰዎች……እባካችሁ …..እንደእኔ እንዳት ሆኑ… ተጠንቀቁ፡፡ እኔን ያየህ ተቀጣ የሚለው አባባል በኔ ላይ ሰርቶአል፡፡
ከመራረጥናቸው መልእክቶች የመጨረሻው የደረሰን ከቦሌ ሀራምሳ ነወ፡፡ ወ/ሮ ተናኘ በእድሜያቸው ወደ ስድሳ አመት ይጠጋሉ። ሕመም ከገጠማቸው ወደ አራት አመት ገደማ እንደሚሆናቸው ነው የገለጹት፡፡ ገጠመኛቸው እንደሚከተለው ነው፡፡
‹‹…..ሕመም የገጠመኝ በብልቴ ላይ ነው። እንደማሳከክ… እንደማቃጠል… ያለ ነገር ሲሰማኝ እንዲያው በደማከሴው… በቅጠላቅጠሉ…እያሻሸሁ…ትንሽ ሻል ሲለኝ እተወዋለሁ፡፡ በልማድ እንደሚነገረው ግርፋት ነው እንዳልል ሽንቴን ከሜዳ ላይ አልሸናሁ…. ከየት መጣብኝ እያልኩ ለራሴ አብሰለስላለሁ፡፡ ባለቤቴ በሕይወት ስለሌለ በቅርብ የማወራውም ሰው የለኝ፡፡ ልጆቼም ወንዶች ስለሆኑ ይሄ ምን ተብሎ ይነገራል ስል….. እፍን አድርጌ ቁጭ አልኩ፡፡ ሲብስብኝ …ከጎረቤት ለምግባባት ሴት አዋየሁዋት፡፡ እሱዋም እርግጠኛ ሆና የነገረችኝ ነገር ልክ እንደእኔ የታመመች ሴት ሄዳ የዳነችበትን የባህል ሐኪም አድራሻ ነበር፡፡ እኔም …ጎሽ እስከዛሬ ደብቄ …ተሰቃየሁ… እስቲ ልሂድና ሁኔታውን ላዋያቸው ብዬ ሄድኩኝ፡፡ ለሁለት አመት ከስድስት ወር ያህል እየተመላለስኩ የሚቀባ እና የሚጠጣ ነገር እየሰጡኝ ቆየሁ፡፡ ሕመሙም እየባሰ ሲሄድ… ሁኔታውን ስነግራቸው….አ…አ…አይ… ሊድን ሲል እኮ እንደዚህ ነው የሚያረገው…ገና ይፈነዳል አሉኝ። እሳቸውን አምኜ ስመላለስ… አንድ ቀን ትልቁ ልጄ…እማዬ… ለመሆኑ የት ነው የምትሄጂው አለና ጠየቀኝ። እኔም አስረዳሁት፡፡ አይሆንም ….በይ እንደዚህ ያለ ነገር እንዴት ታደርጊያለሽ…. ሐኪም ቤት መሄድ አለብሽ አለኝ፡፡ እኔም… አረ ከሐኪም በላይ ናቸው ….ሰምቻለሁ… ግድ የለም …እዛው ልጨርስ… አልኩ። አይሆንም ብሎ ይዞኝ ወደ አንድ የግል ክሊኒክ ሄድን፡፡ የህኪሙ ጥያቄ… የት ነው የምትኖሪው…የሚል ነበር፡፡ እኔም እዚሁ አዲስ አበባ…አልኩት፡፡ እሺ…አለና…እኔ ከወጣሁ በሁዋላ ከልጄ ጋር ትንሽ ቆዩ፡፡ ለካስ ልጄ ከሐኪሙ ጋር ይተዋወቃል፡፡ ልጄ ሲመጣ … አይኑ ሁሉ በርበሬ መስሎ መጣ፡፡ ምን ሆነህ ነው አንተ…..ምንሆንክ ስለው…አ..አ..ይ… አንድ ጉዋደኛችን ሞተ ብሎ ነግሮኝ ነው…አለኝ፡፡ አይሄይሄ… በቃ… ነፍሱን ይማር እንግዲህ ምን ይደረጋል አልኩና ዝም አልኩ። በሶስተኛው ቀን ወደባህል ሐኪሙ ልሄድ ስነሳ አብሬሽ እሄዳለሁ አለና አብሮኝ ሄደ፡፡ እሱንም እንዲሁ ከእኔ ተለይቶ አናገረው፡፡ ግን የጸብ ንግግር ነበር፡፡ እናቴ እንዲህ እስክትሆን ምንድነበር ያንተ ህክምና….ሲለው ተሰማኝ፡፡ በቃ ተስፋ ቆረጥኩ። ሕመሜ እየተሻለኝ ሳይሆን እየባሰብኝ መሆኑን አወቅሁ፡፡ ከዚያ በሁዋላ አንዴ ኬሞ… እሱ ሲያልቅ ጨረር… ታዘዘ፡፡ ግን ህመሙ ተስፋ ከሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ መድረሱን አውቄ እየተጠባበቅሁ ነው፡፡ አያድርስ ነው፡፡ ሌላ ምን ይባላል፡፡ ሰው ሁሉ ይህን ይስማ፡፡ እራሱን ያድን፡፡  


Read 9543 times