Saturday, 09 October 2021 00:00

ፍሬው ከዛፉ ርቆ አይወድቅም

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

እነ አሌክስ ደዋል በሚመሩት ተቋም የታተመው ጥናት…
                                  
      ባለፉት ወራት “የተራበችው ትግራይ” በሚል ርዕስ 66 ገፅ ያለው ፅሁፍ በተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው የዓለም ሰላም ማዕከል ታትሞ በድረገፆች ተሰራጭቷል። ተፍትስ በ1852 ዓ.ም የተቋቋመ በአብዛኛው፣ በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ምርምር የሚያደርግ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ድረገፁ ያስረዳል።
ወደ ፅሁፉ ስንመለስ በመግቢያው ላይ ጎርበጥ የሚሉ ማሳሰቢያዎች ይገኛሉ።
“የጥናቱ ጸሐፊዎችን ማንነት በጥያቄአቸው መሠረት ከመግለፅ ተቆጥበናል።” ይላል፡፡ በእውነቱ አንቱታን ያተረፉ የትምህርት ተቋማት ከተሰበሰቡበት ሰፈር ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ፤ ይህንን አይነት ማሳሰቢያ መስጠት ያልተለመደ ነው። ተቋማቱ በሚያሳትሟቸው ጥናቶች እንኳንስ የፀሀፊዎቹን ማንነት ሊደብቁ ቀርቶ፣ በቡድን በተዘጋጁት ሥራዎች ሳይቀር ዋና አስተባባሪ ወይም መረጃ በማሰባሰብ ብቻ የተሳተፈ ሁሉ ስሙ የሚወጣበት አሰራር አለ። የትምህርት ማእረጎችም የሚገኙት በታተሙ ምርምሮች ጭምር ነው።

“የዓለም ሰላም ማዕከል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ካለው ፍሌቸር ትምህርት ክፍል በስተቀር ሌላ ግንኙነት እንደሌለው” ያሳስባል። የግንኙነትን ጉዳይ ማንሳት ለምን አስፈለገ?

ይህንን ይዘን የፅሁፉ ጭብጥ ባ’ጭሩ በሚገለፅበት የአሳታሚው ማስታወሻ ስንጀምር፤ “‘ትግራይን ሙሉ በሙሉ አውደመዋታል’፤ ሙሉጌታ ገብረሂወት፤ ጥር 2, 2013 በስልክ እንደገለፀው።”  የሚል ጎላ ያለ ጥቅስ ተቀምጧል።
ከዚህ ጀምረን ብዙ ስለ ፅሁፉ ይዘት ሳንጨነቅ “ስማቸው እንዳይገለፅ” የጠየቁት ፀሐፊዎች፤ ራሳቸውን መደበቅ የፈለጉበትን ምክንያት ማየት እንችላለን።
ተጠቃሹ ሙሉጌታ ገብረሂወት ቀድሞ የሕወሃት አመራር ውስጥ የነበሩ ሲሆን እንደ ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይና አበበ ተክለሃይማኖት፣ ወደ ፀጥታ አማካሪነትና ተመራማሪነት ፊታቸውን ያዞሩ ናቸው። የሳቸውን ለየት የሚያደርገው አሁንም የዚሁ የዓለም ሰላም ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር መሆናቸው ነው።
የዓለም ሰላም ማዕከል ሥራ አስፈፃሚ አሌክስ ደዋል፣ ባለፈው የካቲት ወር፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ሙሉጌታ ባቋቋሙት የሰላምና ደህንነት ኢንስቲቱት ውስጥ ተቀጥሮ መስራቱን ተናግሯል። ስለዚህ ሁለቱ ግለሰቦች የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ያላቸው ወዳጆች ናቸው። በዚህም መሰረት፣ሙሉጌታ ገብረሂወት፣ ትግራይ ሆነው ለወዳጃቸው አሌክስ ደውለው የነገሩት፣ በዩኒቨርሲቲው ስም ለወጣው ጥናት የመግቢያ ጥቅስ ሆኗል፡፡
ፀሀፊዎቹ በጠየቁት መሰረት ማንነታቸው ያልተገለፀው ዋነኛው ደራሲ የተቋሙ ሃላፊ የሆነና በግሉ ባለው ተሳትፎ ገለልተኛ የማይባል ምሁር በመሆኑ ነው። በፅሁፉ ሕዳግ ላይ ያሉት ምንጮች ራሳቸው አሌክስ በተለያየ ጊዜ የፃፋቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ በድርጅቱ ስም አደረግኳቸው በሚለው ቃለ ምልልስ የተሞሉ ናቸው። እርግጥ አንዳንዴ ስምን ላለመግለፅ አሳማኝ ምክንያት ቢኖርም፣ እዚህ ፅሁፍ ላይ ግን ከደህነነት ስጋት ባለፈ ሌሎች ፍላጎቶች እንዳሉ ይታያል። የምስጢራዊነቱ ምክንያት በአብዛኛው በራሱ የተፃፉ ሊሆኑ ስለሚችሉና ሌሎች ቢኖሩ እንኳ በአንድም ሆነ በሌላ በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች ስለሚሆኑ ጥናቱን ተዓማኒነት ያሳጡታል ከሚል ፍራቻ የመነጨ ይመስላል።
የማዕከሉ ድረገፅ መግቢያን ላስተዋለ፣ የአንድ ትምህርት ተቋም ክፍል ሳይሆን፣ ትግራይ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ላይ ብቻ የሚሰራ ድርጅት ነው የሚመስለው። ድረገፁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ግጭቱና በዛም ስለተፈጠረው ሰቆቃ የዘገቡትን ይዟል። ታዲያ እዛ ላይ ለመለጠፍ ወግ የደረሳቸው አሌክስን እየጠቀሱ ከፃፉት መካከል፡- አልጀዚራ፤ ዘ ቴሌግራፍ ፤ ኤን ፒ አር የተሰኘው የአሜሪካ ሬዲዮ፤ እንዲሁም አሌክስን “የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ” የሚል ማዕረግ የሚሰጠው ቢቢሲ ይገኙባቸዋል።
በ1980ዎቹ መጀመሪያ የእጅ ሳተላይት ስልኮች ሥራ ላይ ሲውሉ፣ በውድ ዋጋ እየገዙ ሲጠቀሙ የነበሩት የአፍሪካ አማፂያን መሪዎች ነበሩ። በተለይም የአንጎላው ጆናስ ሳቪምቢ፥ የላይቤሪያው ቻርልስ ቴይለር እንዲሁም የጎረቤታችን ኤርትራ ኢሣያስ አፈወርቂ በዚህ ይታወቃሉ። ታዲያ የስልኩ ዋነኛ ዓላማ እንደምንም ብሎ ቢቢሲን ማግኘትና “አለሁ” ማለት ነበር። ያንን በሚያስታውስ መልኩ በቅርቡ አሌክስ በዚሁ በሳተላይት ስልክ የተገናኙትን የጄኔራል ፃድቃንን ‘የጦር ሜዳ ጀብድ’ ቢቢሲ ላይ አስነብቧል፡፡
በእውነቱ የአሌክስ ደዋል ምሁርነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ችግር የሚሆነው አቋም በያዘበት ጉዳይ ዩኒቨርሲቲውን ተገን አድርጎ፣ ገለልተኛ መስሎ መቅረቡ ነው። ራሱ በተናገረው እንኳን ከሕወሓት ጋር ለ34 ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ያለው ሰው ነው። ቢቢሲም ቢሆን አሌክስ ገለልተኛ ወይም የዳር ተመልካች ሳይሆን የህወሃት ቡድን ዋነኛ ተቆርቋሪ መሆኑን ለተከታዮቹ ግልፅ ማድረግ ይኖርበታል።
ጥናቱ፤ ወደፊት የጦር ወንጀልና የዘር ፍጅት ክስ ለማቅረብ፣ ከዛም ሲያልፍ ካሣ ለመጠየቅ በመንደርደሪያነት እንደተዘጋጀ የሚጠቁሙ ፍንጮች አልጠፉም፡፡ ይህንን ጉዳይ ቀደም ሲል ራሱ አሌክስ በግንቦት ወር ላይ “የዕልቂትና ረሃብ ስጋት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ዘገባ፣ “የዘር ፍጅት መዝገብ” ለመክፈት የሚያስችል መሠረት አለ ብሎ ፅፎ ነበር። እርግጥ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ሰቆቃ እንዳስከተለ የሚካድ አይደለም።
አሌክስ በተለያዩ ድረገፆች በሚያወጣቸው ፅሁፎች ሃሳቡን ለማጠናከር ያልተረጋገጡ ዘገባዎችን ሳይጨነቅ ነው የሚጠቅሰው። እንደውም ባለፈው ጊዜ ጭልጥ ብሎ፣ "ዐቢይ አህመድ ማምጣት የሚፈልገው “ጥንታዊውን የአቢሲኒያ አፄአዊ አገዛዝ ነው” ሲል በእርግጠኝነት ሞግቶ ነበር፡፡ ለበርካታ አስርት አመታት፣ እንዲህ አይነት ቅላፄ ያለው ፕሮፓጋንዳ እስኪታክተን ድረስ ሰምተናል። ፍሬው ከዛፉ ርቆ አይወድቅም።


Read 768 times