Sunday, 03 October 2021 18:13

የዓለም ማራቶን ሪከርድ በ3 የኢትዮጵያ አትሌቶች ለ19 ዓመታት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በዓለም የማራቶን ሪከርድ ታሪክ በወንዶች ምድብ የኢትዮጵያ 3 አትሌቶች  ጉልህ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት ግን በወንዶች ምድቡ የዓለም ሪከርዱ በኬንያውያን ቁጥጥር ስር  እየተፈራረቀ ቆይቷል፡፡
በማራቶን ታሪክ በወንዶች የመጀመርያው የዓለም  ሪከርድ የተመዘገበው እኤአ በ1908 በለንደን ማራቶን በአሜሪካዊው ጆን ሄይስ በ2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ከ18 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያ ሪከርድ ከተመዘገበ ከ32 ዓመታት በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያዊ አትሌት የተመዘገበው በ1960 እኤአ ላይ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባሸነፈው አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ በወቅቱ አበበ ያስመዘገበው የማራቶን ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃዎች ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡
ከ4 ዓመታት በኋላ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ሪከርድን   በ1964 እኤአ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ያስመዘገበ ሲሆን ጊዜውም 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃዎች ከ11 ሰኮንዶች ነበር፡፡ አበበ በቂላ  በኦሎምፒክ መድረክ ባስመዘገበባቸው  ሁለት የዓለም የማራቶን ሪከርዶች  ለአምስት አመታት ነግሶ ቆይቷል፡፡ ከአበበ ቢቂላ ሁለት የዓለም  ሪከርዶች 24 ዓመታት  በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊያዝ የበቃው  ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ ነበር፡፡ በላይነህ እኤአ በ1988 በተካሄደው ሮተርዳም ማራቶን ሲያሸንፍ ርቀቱን የሸፈነበት 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃዎች ከ50 ሴኮንዶች የሆነ ጊዜ አዲስ የዓለም ሪከርድ ነበር፡፡ በላይነህ ዴንሳሞ በዚህ ሪከርዱ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 7 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያው አትሌት ከመሆኑም በላይ ክብረወሰኑን ለ10 ዓመታት ይዞ ቆይቷል። ከበላይነህ ዴንሳሞ በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ክብረወሰን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከ19 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሰኮንዶች   በሆነ ጊዜ ባሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት ነበር፡፡
 በ2008 እኤአ ላይ ኃይሌ ይህን ክብረወሰኑን በድጋሚ ሲያሻሽል 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ነበር።  በዚሁ ሁለተኛ የማራቶን  ሪከርዱ ኃይሌ ገብረስላሴ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያ አትሌት ሲሆን በክብረወሰኑ ባለቤትነት ለ5 ዓመታት ቆይቷል። በአጠቃላይ በወንዶች የዓለም ማራቶን  ታሪክ ሶስት የኢትዮጵያ አትሌቶች 5 ጊዜ ሪከርዶችን አሻሽለዋል። 3 ደቂቃዎች 49 ሰኮንዶች ከማራቶን የሪከርድ ሰዓት ላይ በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡
ኢትዮጵያ በሪከርዱ ባለቤትነት ለ19 ዓመታት የበላይ ሆና እንድትቆይም አድርገዋል፡፡


Read 1828 times