Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 10 September 2012 13:52

2 0 0 4 ለተቃዋሚዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ዘንድሮ ፈታኝ ዓመት ነበር”  አቶ ሙሼ ሰሙ (የኢዴፓ ሊ/መንበር)

ደምረን ቀንሰን ስንመለከተው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተዳከመበት፣ በርካቶቹ እስር ቤት የገቡበትና ከሀገር የተሰደዱበት፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ፈተና የተጋረጠበት ነበር ብዬ ነው የማስታውሰው፡፡ያሳለፍነውን ዓመት በአብዛኛው ከፖለቲካ አኳያ ስናየው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ሚናቸውን በሚፈልጉት ደረጃና በሚገባቸው ልክ መጫወት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው ያለፈው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ታስረዋል፤ ጋዜጦች ተዘግተዋል፡፡ አሁን ጥቂት የግል ጋዜጦች ነው ያሉት፡፡ ጋዜጦች ቁጥራቸው ማደግና መጎልበት ሲገባቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያነሰ፤ ጋዜጠኞችም በፀረ ሽብርተኝነት ህግ እየታሰሩ ይገኛሉ፡፡ የነፃ ፕሬሱም ጉዳይ ቀጥታ ከፖለቲካው ጋር ግንኙነት ስላለው፣ ህትመትም ሽያጭም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግም አማራጭ ሃሳብ መስተናገድ የሚችልበትን እድል ችላ ያለበትና በዚህ ጉዳይ ላይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መስራት ያቆመበት ጊዜ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ከአምስት ዓመት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበትና የእቃ እጥረት የባሰበትና ሰው ኑሮውን መቋቋም ያቃተበት ዓመት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል አነስተኛው የህብረተሰብ ክፍል መሰረታዊ የምግብ እህሎች (እንደ ሽሮ ያሉትን) እንኳ ገዝቶ መብላት ያልቻለው፡፡ በኢኮኖሚው ረገድ የተሰሩ ነገሮች ቢኖሩም የዜጎችን ህይወት በተደላደለ መሠረት ላይ ከማስቀመጥ አኳያ ገና ብዙ እንደሚቀር የታየበት ዓመት ነበር፡፡

ደምረን ቀንሰን ስንመለከተው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተዳከመበት፣ በርካቶቹ እስር ቤት የገቡበትና ከሀገር የተሰደዱበት፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ፈተና የተጋረጠበት ነበር ብዬ ነው የማስታውሰው፡፡ በአጠቃላይ 2004 ዓ.ም ከጠቀስኳቸው ጉዳዮች አንፃር ሲቃኝ፣ በጥሩ ሁኔታ አልፏል ብዬ መናገር አልችልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግሉ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ በቅጡ ማበርከት የማይችሉበት ሁኔታ ስለነበር ፈታኝ ዓመት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የሚያራምዱት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትክክል ነው ብለን ባናምንም፣ ዜና እረፍታቸው በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ በመሪነት እንደመቆየታቸው፣ እንደ ቤተሰብ ሃላፊነታቸውና እንደ ዜግነታቸው ህልፈታቸው አሳዛኝ ነበር፡፡ የአስተሳሰብ፣ የአቅጣጫ፣ የአሰራርና የርዕዮት አለም ልዩነት ቢኖረንም አማራጭ ሃሳብ ሆነው በሃገሪቱ ውስጥ እንደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ከመቅረብ  አኳያ የሚያጎድሉት ነገር አለ ብዬ ነው የማምነው፡፡

2005 ዓ.ም. ዋናውና መሰረታዊ አጀንዳችን ሆኖ በአብዛኛው ሊነሳ የሚችለው ለአዲስ አበባ መስተዳድር የምናደርገው ምርጫ ይሆናል፡፡ ለዚህም አቅማችን የፈቀደውን ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁን ወደ አፈፃፀም ሂደት በመውሰድ በተግባር ማዋል ነው የቀረን፡፡ ምርጫው በጠበቅነው ጊዜ የሚፈፀም ከሆነ፣ ሥራችን የሚሆነው የመለመልናቸውን እጩዎችና አባሎቻችንን ብቃት በተግባር እየፈተሽን ለምርጫ ውድድር ማዘጋጀት ነው፡፡ የዲሞክራሲ ስርዓት ዓይነተኛ መገለጫው የመድብለ ፓርቲ መኖር ነው፡፡ ይህም ሲባል ፓርቲዎች ለይስሙላ መኖራቸው ሳይሆን ማህበረሰቡ ውስጥ አስተሳሰባቸውን አስርፀው፣ ማህበረሰቡም አማራጭ ሀሳቦችን ተገንዝቦ (ተረድቶ) ከዛም የተሻለውን አወዳድሮ መምረጥ የሚችልበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ሆኖም በአለፈው ዓመት የአዳራሽ ስብሰባዎች እንኳን ለማድረግ በጣም ከባድ ችግርና ፈተናዎች ነበሩብን፡፡ እነዚህን ነገሮች ተወያይቶ እና ችግሮቹን ፈትቶ፣ እኛም ሃሳባችንን ለህዝቡ የምናደርስበት፣ ህዝቡም በነፃ አስተሳሰብ የሚፈልገውን መምረጥ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡ በዚህ በኩል የፖለቲካ ስራ መሰራት እንዳለበት አምናለሁ፡፡

ከኢዴፓ አኳያ በሚቀጥለው ዓመት ጠቅላላ ጉባኤያችንን እናካሂዳለን - ከአምስት ወር በኋላ፡፡ እኔ ለ14 ዓመታት በከፍተኛ አመራርነት ስሰራ ነው የቆየሁት፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ አመራርነት የምሰራበት የመጨረሻ ዓመት ይሆናል፡፡ በአመራርነት አልቆይም ማለት ነው፡፡ ነባር አባላት እየተጠናከሩ አዳዲስ አባላት አቅም እየገነቡ፣ ፓርቲው በጥሩ ሁኔታ ይዘልቃል ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባዔያችንም በየሁለት ዓመቱ ስለሚደረግ አዲስ አመራር መርጦ እንቅስቃሴውን ይቀጥላል፡፡

አዲሱ ዓመት ህብረተሰቡ በዓልን በዓል ማድረግ የሚችልበት የኢኮኖሚ መሰረት የሚጣልበት፣ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነትን ማሸነፍ የሚችልበት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን፡፡ እቺ አገር ያለው የሌለውን እየደገፈ የሚኖርባት ስለሆነች፣ 2005 ዓ.ም እንዲሁ ተረዳድተንና ተደጋግፈን የምንቀጥልበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

===============

“ገዥው ፓርቲ መንገዱን መዝጋት የለበትም”

አቶ ጥላሁን እንደሻው

(የመድረክ ሊ/መንበር)

በ2004 ዓ.ም በርካታ ችግሮችን አልፈናል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም ሆነ በሃገራችን ህዝብ ዘንድ አያሌ ውጣ ውረዶችን ያሳለፍንበት ዓመት ነበር፡፡ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው መኖር ባለመቻላቸው ወደተለያዩ አገሮች ለመሰደድ ሲሞክሩ በየመንገዱ፣ በየበረሃውና በየባህሩ አልቀዋል፡፡

ኮንቴነር ውስጥ ታጭቀው የሞቱም እንዳሉ እናስታውሳለን፡፡ እነዚህ ዜጎች የሚሰደዱት አገራቸውን ጠልተው ሳይሆን አገራቸውን እየወደዱ፣ በአገራቸው ሰርተው የመኖር እድል ስላልተመቻቸላቸው ብቻ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ መሪያችንን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በማጣታችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልፃለን፡ ሃገራችን ያለፈውን አመት በአንፃራዊነት በሰላም ስላሳለፈች እግዚአብሄርን እናመሰግናለን፡፡

በ2005 ዓ.ም. ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የሚበሉበት፣ በፓርቲ አመራርና አባልነት ምክንያት ስራ ማግኘትና ስራ ማጣት ሳይኖር፣ በጎጠኝነት ምክንያት ጫና ሳይፈጠር ሁሉም ባለው ብቃት ሰርቶ የሚኖርበትና የሚተማመንበት አገር ሆና እንድትቀጥል ነው የምንመኘው፡፡ በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰው ገደብ የለሽ ተፅዕኖ በአስቸኳይ ቆሞ፤ አገሪቱ በጠርናፊ ውስጥ ገብታለች የሚለው መጥፎ ስም ተወግዶ፤ ዜጐች በትምህርታቸውና በችሎታቸው ተመዝነው ሰርተው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እንድትሆን እንመኛለን፡፡

በሚቀጥለው ዓመት እስካሁን ድረስ ጥረት አድርገን ያልተሳካልንን ከገዥው ፓርቲ ጋር የመደራደር ሥራ በማከናወን፣ አሁን ያለውን ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ማስፋትና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማስወገድ ተቀዳሚ አላማችን ነው፡፡ በአገራችን ህገ መንግስቱ በፈቀደልን መብት ተንቀሳቅሰንና አላማችንን አሳውቀን፣ የህዝቡን ውሳኔ እየተቀበልንና ለህዝብ ውሳኔ እየተገዛን መኖር እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠር ከገዥው ፓርቲ ጋር ሰላማዊ ድርድር ለማድረግ እንጥራለን፡፡ በሰላማዊ ትግል ለሚስማሙት ሁሉ ገዥው ፓርቲ መንገዱን መዝጋት የለበትም፡፡ አላስፈላጊ በሆነ ቅድመ ሁኔታ፣ የውይይት በር ዘግቶ ያስቀመጣቸው ነገሮች ከተከፈቱ ለሃገራችን የሰላማዊ ትግል ባህል መጠናከር የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናበረክታለን፡፡ አባሎቻችን ያለመሳቀቅ የሚሰሩበት ሁኔታ ከተመቻቸ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ፅ/ቤቶቻችንን የመክፈት አላማ አለን፡፡ በተለይ የፖለቲካ ምህዳሩ ከሰፋልን ለመስራት ያሰብናቸው በርካታ ጉዳዮች አሉን፡፡

======

“አዲሲቷን ኢትዮጵያን መገንባት እንደምንችል እናምናለን”

- አቶ ተሻለ ሰብሮ (የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት)

ሕዝባችን የመሪውን ህልፈተ - ሕይወት ከሰማበት ጊዜ አንስቶ በአስገራሚ ሁኔታ ዝናብ ሳይበግረው መሪር ሀዘኑን በገለፀባቸው ቀናት አንዳንድ ያልተጠበቁ አፍራሽ ክስተቶች ከውስጥም ከውጭም ተፈጥረው በሀገራችንና በህዝባችን እንዲሁም በመልካም ስማችንና ገጽታችን ላይ መጥፎ አሻራ ጥለውብን እንዳይሄዱ፣ የፀጥታና የደህንነት ሥጋቶቻችንን በመቆጣጠር ረገድ የሚመለከታቸው አካላትና ወገኖቻችን ላደረጉት አስተዋፅኦ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ ህዝባችን የኢትዮጵያዊነት ጨዋነትንና ህዝባዊ ታላቅነትን ለዓለም ሕዝብና መንግስታት በድጋሚ ለማረጋገጥ የቻለበት አጋጣሚ በመሆኑ እንኳን ደስ አለን እንላለን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

በመጨረሻም ራዕዮቻችንን በራዕዮቻችን እያበለፀግን፣ ሁለንተናዊ ዕድገቶቻችንን ማፋጠን የምንችለው ሕዝብ እንደ ህዝብ፣ ብሔረሰብ እንደ ብሔረሰብ፣ ዜጋም እንደ ዜጋ በብሔራዊ መግባባትና በወንድማማችነት/እህትማማችነት ተሳስረን፤ የልማት ጉዞአችንን በነፃነት፣ በህግ የበላይነትና በትክክለኛ ፍትህ፤ በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች መረጋገጥ አዛምደንና አቆራኝተን መጓዝ ስንችል ነው፡፡ ያኔ ሁላችንም የምንመኛትን የተሻለችና የተሻሻለች፣ የበለፀገችና የተፈራች አዲሲቷንና ታላቂቷን ኢትዮጵያ ነገ ሳይሆን ዛሬ መገንባት እንደምንችል እናምናለን፡፡ በመቻቻል፤ በዲሞክራሲያዊና ሠላማዊ መርሆዎቻችን ላይ ተመስርተን፣ ሁሉን አቀፍ ግንባታ ላይ በንቃት ለመሰማራት እንድንችል እንዲሁም፤ ለጤናማ ውይይቶች፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለዕርቀ ሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንድንንቀሳቀስ በትህትና እንጠይቃለን ብልዋል ራዕይ ፓርቲ፡፡

 

 

Read 3564 times Last modified on Monday, 10 September 2012 14:02